አዲስ አበባ፡- ለጠረፍ አካባቢ ነዋሪዎች ከማዕከል መሰረታዊ ሸቀጦች በአግባቡ የማይደርሳቸው መሆኑ ኮንትሮባንድን እያስፋፋ እንደሚገኝ የጉምሩክ ኮሚሽን ጠቁሟል፡፡
የህግ ተገዢነት ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሸናፊ ባሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ ኮንትሮባንድ ላይ እየተካሄደ ያለውን ቁጥጥር በማጠናከር ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መከላከልያልተቻለባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ሲሆኑ፤ የንግድ ሥርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት ዋነኛው ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ መሰረታዊ ሸቀጦች ከማዕከላዊ ገበያ ወደ ጠረፍ በአግባቡ አለመድረሳቸው የአካባቢው ህዝብ ሸቀጦችን ከኮንትሮባንዲስቶች እንዲገዙ ማስገደዱ ተጠቃሽ ነው፡፡
የቀድሞ ንግድ ሚኒስቴር የአሁኑ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እየተጠቀመ ያለው ከ10 ዓመት በፊት ባስጠናው የኮታ ጥናት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ አሁን የነዋሪው ቁጥር እጅግ በመጨመሩና የመግዛት አቅም በማደጉ ቀድሞ የተገመተው የኮታ መጠን ለአካባቢው ነዋሪዎች እንደማይበቃ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ነዋሪዎች አማራጭ ገቢያ ወደሚገኙበት ኮንትሮባንድ ላይ መሰማራታቸው የመቆጣጠር ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው አመላክተዋል፡፡
እንደ አቶ አሸናፊ ገለፃ፤ የንግድ ሥርዓቱ መዛባት እና ሌሎችም በተቋማት መሰራት ያለባቸው መሰረታዊ ሥራዎች አለመከናወን የኮንትሮባንድ ንግዱን በማስፋፋት በኩል ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
ለአብነት የግብርና ሚኒስቴር ከቁም እንስሳት ጋር በተለይ ከቀንድ ከብት ጋር ተያይዞ የህክምና አገልግሎትም ሆነ የማቆያና የመሸጫ ማዕከላትን አለማዘጋጀቱ ከብቶቹ በኮንትሮባንድ እንዲወጡ እያስገደደ ይገኛል። ከዚህ አንፃር ኮንትሮባንድን ለማስቆም ጉምሩክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቋማትና ህብረተሰቡ ተገቢውን ሚና ካልተጫወቱ ቁጥጥሩ ብቻውን ኮንትሮባንድን ሊያስቆመው አይችልም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ምህረት ሞገስ