አዲስ አበባ፡- ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች መስራች አባል ከመሆን የዘለለ ሚና የሌላቸው እና ወደ አመራር ደረጃ መምጣት አለመቻላቸውን የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ባቀረበው ጥናት ጠቆመ።
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ረድኤት ያስቻለው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶች ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ የሆነና ከአባልነት ያልዘለለ ነው።
ከምርጫ ቦርድ በተገኘው መረጃ መሰረት በ73 የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ በተደረገ ጥናት የፖለቲካ ፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንቦቻቸው ላይ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ወንድና ሴት ብለው ለይተው አያስቀምጡም። ፓርቲዎቹ ሲመሰረቱ መስራች አባላት ላይ ሴቶች ቢኖሩም በቁጥር ወንዶቹ ይበልጣሉ። ከእዚህም በላይ መስራች አባላት የሆኑ ሴቶች ወደ አመራር ሲመጡ አይታይም።
እንደ መምህርት ረድኤት ገለፃ፤ ‹‹50 በመቶ የሆኑ ሴቶችን እንደመራጭም፤ እንደ ተመራጭም፤ እንደ አስመራጭም በፖለቲካው ማሳተፍ አስፈላጊ የሚሆነው፤ የሰብዓዊ መብት ግዴታ እና የዴሞክራሲ አመልካች በመሆኑ ነው። የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ፤ ሴቶች ይዘው የሚመጡት የተለያዩ አመለካከቶች፤ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ወንዶችም እንደዚያው መስተጋብሩ ወደ አንድ ያጋደለ እንዳይሆን ለማድረግ ያስችላል። ›› በማለት ይገልፃሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸው፣ ፕሮግራሞቻቸውና መተዳደሪያ ደንቦቻቸው ላይ ማሻሻያ በማድረግ ወደ ሪፎርም ገብተው ሴቶችን የሚያበረታቱና የሚጋብዙ ስራዎችን ቢሰሩ ምናልባት አሁን የሚመጡ ፓርቲዎች ይህንን አሻሽለው ሊመጡ ይችላሉ።
ፓርቲዎች ሴቶችን በትምህርትና በኢኮኖሚ ማብቃት ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህንን በማድረግ በአባልነት ያሉ ሴቶችን ወደ መሪነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ብሎም ወደ እጩ ተመራጭነት እንዲያድጉ በማድረግ አሰልጥኖ ወደ አመራር እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቃል። መምህርቷ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሴቶችም አቅማቸውን ማብቃት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ወርቅነሽ ደምሰው