አዲስ አበባ፡- የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና የመረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመን እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ። ኢንስቲትዩቱ የተቋማትን አሰራር ማዘመን ስራ እየተገበረ መሆኑ አሳውቋል።
የኢንስቲትዩቱ የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሚኒሊክ ሳሙዔል፤ የመንግስት ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥና መረጃ አያያዛቸውን ማዘመን ተገቢ መሆኑን ገልፀው፤ አገልግሎትን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።
የተቋማትን አሰራር ዘመናዊ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ተግባር መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል። አብዛኞቹ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን ዘመናዊ በሆነ መልኩ መስጠት የማይችሉና በመረጃ አያያዛቸው ላይ ችግር እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል። የተጀመረው የማዘመን ተግባር ይህንን አሰራር የሚያሻሽል መሆኑን አመልክተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የኢንፎርሜሽን ሲስተምና መሰረተ ልማት ዳሬክተር አቶ ሰልማን ሙሀመድ በበኩላቸው፤ ተቋማትን የማዘመን ተግባር ለማከናወን ኢንስቲትዩቱ ከመንግስትም ሀላፊነት የተሰጠው ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ የመንግስት ተቋማት የደንበኞች እርካታን ከፍ ለማድረግና አስራራቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም የመንግስት ተቋማት በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ውጤቶች የተደገፉና አገልግሎትን በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የተቋማቱን የውስጥ አሰራር፣ የደንበኞችን ጥያቄና መልስ ማስተናገጃና የመረጃ አያያዝ ማዘመን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የተሰሩ ስራዎች አመላካች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን ለኢንስቲትዩቱ ጥያቄ ካቀረቡ ተቋማት ውስጥ ከስድስት ያላነሱ ተቋማት አገልግሎት ያገኙ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ተቋማቱ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል። በተቋማቱ ውስጥ አገልግሎት ለማሳለጥና መረጃዎችን በወጉ ለመሰደር የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በኢንስቲትዩቱ የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ፣ የብሄራዊ ስነ ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣንና የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በተቋማት ማዘመኑ ስራ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ተገኝ ብሩ