አዲስ አበባ፡- የአገሪቱን የትራንስፖርት ሥርዓት ለማሻሻል ሦስት ቢሊዮን ብር ብድር የተገኘለት ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ በየሮ በተለይም ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለፁት፤ ከዓለም ባንክ ሦስት ቢሊዮን ብር ብድር የተገኘለትና የትራንስፖርት ሥርዓት ለማሻሻል የተወጠነው ፕሮጀክት በአገሪቱ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል፤ ዘመናዊ አሠራሮችን ለመተግበርና አገሪቱ እንደ ሌሎች ዓለማት እንድትዘምን የታቀደ ነው፡፡
በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠሙ የጂ ፒ ኤስ (GPS)፣ የአሽከርካሪ ብቃት፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን፣ የማሰልጠኛ ተቋማትን ለማዘመንና ከማንዋል አሰራር በመላቀቅ የትራንስፖርት ሥምሪቶችና እንቅስቃሴዎችን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ በተበጣጠሰ መልኩ እየተከናወነ የሚገኘውን የትራንስፖርት ስምሪት ወጥ ወደሆነ አገራዊ አሠራር ለመዘርጋት እና ብሎም መንጃ ፈቃድን ጨምሮ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመለየትና ለመቆጣጠር ዓላማ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያም ይሆን ዘንድም ከዓለም ባንክ ሦስት ቢሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን፤ ሥራው መጀመሩን አብራርተዋል፡፡ ይሁንና አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ስራው በታሰበው ፍጥነት እንዳይሄድ ምክንያት ናቸው ብለው ወይዘሮ አልማዝ ከሚያነሷቸው ውስጥ ሥራው መጠን ሰፊ፣ ውስብስና ትልቅ ከመሆኑ የተነሳም መስፈርቱን የሚያሟሉ ተጫራቾች ባለመገኘታቸው በተደጋጋሚ ጨረታዎች ይወጡ እንደነበር አስታውሰዋል። የውጭ አማካሪ ያስፈልግ የነበረ ሲሆን ይህንን ለማግኘትም ጊዜ ወስዷል። በአሁኑ ወቅት ግን ጨረታውን ያሸነፉ አካላት ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የትራንስፖርት ሥርዓቱን ከማዘመን በተጨማሪም የቃሊቲ መናኸሪያን በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት መንግስት 445 ሚሊዮን 554ሺ ብር በጅቷል። ይህም ለዓመታት ሕብረተሰቡ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያስችላል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው የተጀመረ ሲሆን ለተቋራጩ 80 ሚሊዮን 925ሺ ብር ቅድሚያ ክፍያ ተፈፅሟል። ይሁንና የዚህም ግንባታ አፈፃፀም ‹‹በጣም ዝቅተኛ ነው›› ብለዋል።
ቀድሞ ለነበረው መናኸሪያ ተለዋጭ ቦታ አለመሰጠቱ ሥራው ላይ ጫና መፍጠሩን ገልፀዋል። ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሥርዓትን ለማዘመንና በእውቀት የታገዘ እንዲሆንም የቃሊቲ ትራፊክ ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ግንባታ የተጀመረ መሆኑን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ 381 ሚሊዮን 206ሺ ብር ተበጅቶለታል። የኢንስቲትዩት ግንባታ የዲዛይን ማስተካከያ ተደርጎ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት 69 ሚሊዮን ብር ለተቋራጩ ቅድሚያ ክፍያ ተፈፅሞ ሥራው ተጀምሯል።
የቃሊቲ ትራፊክ ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅም በምስራቅ አፍሪካ በትራፊክ ማኔጅመንት ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለማድረግም ታስቧል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር