አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ በ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ 515 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶችን በመጠገን ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጡዑማይ ወልደገብርኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ እድሳት የሚያስፈልጋቸው ከ515 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶችን እየጠገነ ይገኛል። ባለስልጣኑ እሰከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ ከ 47 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና አከናውኗል።
ጥገናቸው ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቁ መንገዶች ውስጥ እህል በረንዳ- መሳለሚያ፣ ሰሜን ማዘጋጃ- ቀጨኔ፣ ቁስቋም -እንጦጦ እና አፍሪካ ህብረት- ሜክሲኮ እንደሚገኙ አመልክተዋል። በተያዘው ወር አፍንጮ በር- መነን፣ ሃያ አራት- መገናኛ፣ሰዓሊተ ምህረት- ጉርድ ሾላ እና ግሎባል ሆቴል አካባቢ የአስፋልት ማልበስ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ጡዑማይ ገለፃ፤ የምኒልክ -ስድስት ኪሎ አስፋልት መንገድ ረጅም አገልግሎት በመስጠቱ እና ከፍተኛ የትራፊክ ጫና ያለበት በመሆኑ ለብልሽት ተዳርጓል። በተጨማሪ መንገዱ ለተሽከርካሪ ማቆሚያነት እና ለሰንበት ገበያነት እያገለገለ በመሆኑ፤ ለጉዳቱ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ጥገናውም በመጀመሪያ ህዳር ወር የተጀመረ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት የአስፋልት ማልበስ ስራው በመሰራት ላይ ነው። ጥገና እየተደረገለት ያለው የመንገዱ ክፍል አጠቃላይ ርዝመት አንድ ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 700 ሜትር የሚሆነው የአስፋልት ማንጠፍ ስራው ተጠናቋል።
በመልሶ ግንባታ ደረጃ ከፍተኛ ጥገና እየተከናወነለት የሚገኘው ከሰዓሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን – ጃክሮስ መስቀለኛ መንገድ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር ስፋት ያለው አቋራጭ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ መንገድ በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳቱ የመልሶ ግንባታ ስራ ማስፈለጉን አስረድተዋል።
የመንገዱ እድሳት ስራ በያዝነው ሳምንት የተጀመረ ሲሆን፤ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታሳቢ ተደርጐ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን በመጥቀስ፤ መንገዱ በዚህ ደረጃ መጠገኑ ከመገናኛ ወደ ሃያት የሚወስደው ዋናው መንገድ
ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅን ከመቀነሱም በተጨማሪ ከጐሮ ወደ መገናኛ፣ ከሰሚት በሳፋሪ አደባባይ አድርጎ ወደ ቦሌ፣ ከሰዓሊተ ምህረት ወደ ቦሌ አራብሳ፣ ከኮተቤ ካራ እንዲሁም ከሃያት አካባቢ የሚመጡ አሽከርካሪዎች እንደ አቋራጭ መንገድ በመሆን እንደሚያገለግል ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
መርድ ክፍሉ