በምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኘው የጋምቤላ አውራጃ ከቆላማ የአየር ንብረቷና የተፈጥሮ ሃብቷ ባሻገር፤ በባህላዊ እሴቶቿም ትታወቃለች። በአካባቢው ኑዌርና አኝዋክ አሃዛዊ ከፍታ ካላቸው ብሄረሰቦች መካከል ዋንኞቹ ናቸው። ሁለቱም የየራሳቸው ባህልና ትውፊት ባለቤቶች ቢሆኑም፤ መጠነኛ ተመሳስሎ በመካከላቸው አለ። አብሮ ሲኖር መዋዋስና መበዳደር ያለ በመሆኑ ባህላዊ መስተጋብር አላቸው።
በተለይ በቦታው ተግኝቶ ስለማህበረሰቡ ያጠናው ደራሲ እና ጋዜጠኛ አበራ ለማ እንደሚለው በኑዌርና አኝዋክ ብሄረሰቦች ዘንድ ሴት ልጅ ከፍተኛውን የክብር ስፍራ ትይዛለች። አንድ ቤተሰብ ወንድ ልጅ ሲወለድለት፤ “ደኸየ” ሲባል፤ በአንጻሩ ደሞ ሴት ልጅ ስትወለድ ፤ “ከበረ” ይባላል። በእነዚህ ብሄረሰቦች ዘንድ አባባሉ እውነትነት አለው። ሴት ልጅ ስትዳር ቤተሰቡ የሚቀበለው ጥሎሽ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፤ ሀብትና ጸጋ ወደ ቤታቸው ሰተት ብሎ ይገባል ተብሎ ይታሰባል። በአጸፋው ደግሞ ወንድ ልጅ ትዳር ሲመሰርት ከፍተኛ የጥሎሽ ወጪ በማስወጣት፤ ቤተሰቡን በማራቆቱ፤ ግምኛ(መጥፎ) ነው ይሉታል። እስቲ በየጎራቸው እንቃኛቸው።
እንደ አበራ ለማ ገለጻ ኑዌሮች ጋብቻን በዘር ቆጠራ ልማድ ላይ መስርተው የኖሩ ናቸው። አስቀድሞ በሚደረገው የዘር ቆጠራ እርካታ ከተገኘ፤ የልጁ ቤተሰቦች ሽማግሌዎችን ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ልከው፤ ጋብቻውን ያስፈቅዳሉ። ይሁንታው ከመጣ የልጁ ወላጆች ለልጅቷ ወላጆች ሰባት የቀንድ ከብት በጥሎሽ ይልካሉ። ለጥሎሽ የሚሰጡት ከብቶች ውፍረታቸውና ጥራታቸው በሽማግሌዎች መረጋገጡ የግድ ይሆናል።
የልጅትዋ ወላጆች ሰባቱን ከብቶች ከተቀበሉ በኋላ፤ የጋብቻው ውል እንደጸና ተቆጥሮ፤ ሌሎች ተጨማሪ አሥራ ስምንት ከብቶች ይላክላቸዋል። በአጠቃላይ ሃያ አምስቱን የቀንድ ከብቶች የተቀበለው የልጅቷ ቤተሰብ ጥሎሹን ይከፋፈለዋል። የልጅቷ አባት፣ እናት፣ አጎት፣ አክስት፣ ወንድምና እህት ወዘተ… እንደ እድሜያቸው ቅደም ተከተል (ከትልቅ እስከ ትንሽ) ከሰንጋ እስከ ጊደርና ወይፈን ያሉትን ይከፋፈላሉ።
በኑዌር ብሄረሰብ ባህል አንዲት ልጃገረድ ከማግባትዋ አስቀድሞ፤ የግድ አንድ እውቅ የከንፈር ወዳጅ መያዝ እንደሚኖርባት የሚናገረው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ከንፈር ወዳጅዋ በቤተሰቦችዋና በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ በሙሉ መታወቅም ይኖርበታል። የሦስት ጉልቻ መሥሪያዋ ጊዜ ደርሶ፤ በብሄረሰቡ ልማድና ወግ መሠረት የሠርጉ ሥነ ሥርዓት በሚካሄድበት እለት የልጅትዋ የከንፈር ወዳጅ የራሱን እድምተኞች ይዞ ወደ ሰርግ ቤቱ ይሄዳል። የልጅትዋ የወደፊት የትዳር ጓደኛና የእለቱ ሙሽራም በበኩሉ የራሱን እድምተኞች ይዞ ይመጣል። የሁለቶቹም ወገኖች እድምተኞች ጎራ ጎራቸውን ይዘው ይቀመጣሉ። ይበላሉ፤ ይጠጣሉ። እጅግ በሚያስገርም ሥነ ሥርዓት ያለ አንዳች ጸብና ረብሻ በየተራቸው እየተነሱ ይጨፍራሉ።
በመቀጠል የሁለቱም ወገኖች እድምተኞች ሙሽራውንና የከንፈር ወዳጅዬውን በየጎራቸው አጅበው ወደ ደጅ ይወጣሉ። እደጅ ሲደርሱ፤ በቅድሚያ የልጅቷ የከንፈር ወዳጅ በጠመንጃው ተኩሶ የቤቱን ጉልላት ይመታዋል። የሸክላ ወይም የቅል ጉልላት ከሆነ ይፈረካከሳል። ከዚያም የጥይት እራት የሆነውን ጉልላት በተራው ተኩሶ መፎከር የሙሽራው ፋንታ ይሆናል። ይህ በሁለቱ መካከል የሚካሄደው የተኩስ ሥነ ሥርዓት ለልጅቷ መቀነት መፍታት አለመፍታት ጉዳይ ተምሳሌትነት አለው።
ከንፈር ወዳጅዬው የግድ ክብረ ንጽህናዋን የገሠሠ መሆን አለበት። ያንን መፈጸሙን ለማረጋገጥ ሲልም በቅድሚያ ጉልላቱን ተኩሶ ይሰብራል። በብሄረሰቡ ልማድ መሰረት ልጃገረድ ከነሙሉ ክብሯ ካገባች የተረሳች እንደነበረች ተደርጎ ስለሚቆጠር፤ የግድ ሁነኛ የከንፈር ወዳጅ ይዛ ክብረ ንጽህናዋን አስረክባ መገኘት ይጠበቅባታል። ልጅቷ ባጋጣሚ ከከንፈር ወዳጅዋ ወልዳ ቢሆንና ከንፈር ወዳጅዋም በጋብቻ ሊጠቀልላት ካልተስማማ፤ የተወለደውን ህጻን ተረክቦ፤ ልጅቷን በልጃገረድ ወግ እንድታገባ ነጻ አድርጎ ይለቃታል።
ጫጉላው ካለፈ በኋላ መሽራው ሙሽሪትን ከወላጆቹ ቤት ወደ ቤቱ ወስዶ፤ ይደበድባታል። የድብደባው ዋና ዓላማም የወንድ የበላይነቱን በጡንቻው ለማሳየት ነው። በዚህም እሱ የበላይ እሷ የበታች ሆነው ለመኖር የሚያስችላቸውን ያኗኗር ሥርአት ለመዘርጋት ነው ተብሎ ይታመናል። ይሄ የቆየ ልማድ በመሆኑ ወንዱን ተቃውሞ አይገጥመውም።
አዲሶቹ ጎጆ መሥራቾች የመጀመሪያ ልጅ መወለድ ያለበት በልጅቷ ወላጆች ቤት ነው። ሙሽሪት የመጀመሪያ ልጅዋን እንደወለደችም መታረሻና የልጅ ማሳደጊያ ትሆናት ዘንድ አንዲት ጥገት ትሰጣታለች። ልጇ ሁለት ዓመት እስኪሞላት ድረስ ከቤተሰቦችዋ ጋር እንድትቆይ ትደረጋለች። በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ባልና ሚስቱ ምንም ዓይነት የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም። ባልዬው የልጅቷን እናት አስፈቅዶ፤ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርገው ከተጠቀሰው ሁለት ዓመት በኋላ ነው። በሁለት ዓመታቱ የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለ ልጅትዋ ወላጆች ፈቃድ ባልዬው ከሚስቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርጎ ቢገኝ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል።
በብሄረሰቡ ትውፊት መሠረት ከእለታት በአን ደኛው ቀን ሁለት ጎሳዎች ተጣልተው ከአንደኛው ወገን አንድ ሰው የሞት ጽዋን ቀምሶ ቢሆን፤ የሟች ወገን ከገዳይ ወገን ጋር በጋብቻ ላለመቆራኘት ተቆራርጦ ይቀራል። ድርጊቱ የተፈጸመው ከዘ መናት በፊት ቢሆንም ፋይዳ አይኖረውም። ደም ተቃብተናል የሚለው እምነት በጋብቻ ክልክልነቱ ጸንቶ ይኖራል።
በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ የጋብቻ ፍቺ መጥፎ ዳፋን የሚያስከትል በመሆኑ በጣም ይፈራል። ትዳር ሲፈርስ ከፍተኛ የሕይወትና የንብረት መስዋእትነት ያስከፍላል። ሃብት መዘራረፍና ሕይወት መጠፋፋት በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል ይካሄዷል።
ይህን ፅሁፍ ወደናንተ ለማድረስ አንጋፋው ደራሲ አበራ ለማን እና ዊኪፒዲያን ዋቢ አደረግን። ሳምንት በጋምቤላ ከሚገኙ ሌሎች ብሔረሰቦች ባህላዊ ሁነቶች ጋር እስክንገናኝ ሰላም!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2012
አብርሃም ተወልደ