ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ውበቷ፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በበርካታ ብሔር ብሄረሰቦች መገኛነቷ እንዲሁም በቱሪዝም ሀብቶቿ የምትታወቅ አገር ነች። ከእነዚህ መካካል ደግሞ ዋነኛው ባህል ነው። ባህል ሲባል በመሰረቱ እጅግ ክቡር ነው፤ የአንድ ህብረተሰብ ባህል በራሱ የህብረተሰቡ እንክብካቤ መጠበቅ፣ መዳበር፣ መሻሻልና የላቀ ዕድገት ማሳየት እንዳለበት ይታመናል። ባህልን የመንከባከብ ኃላፊነት የሚወድቀው ደግሞ በአዲሱ ትውልድ ላይ ነው።
ባህልን ለውስጣዊ እና ውጫዊ ሰላም ከመጠቀም ባለፈ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት ለአገሪቱ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል የኢትዮ ኤርትራን ጉዳይ እናንሳ። እንደሚታወቀው ባሳለፍነው ረጅም ዓመታት ነበር አትዮጵያ እና ኤርትራ ለዘመናት ከቆዩበት ሰላምም ጦርነትም ከሌለበት ጦርነት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሰላም የመጡት። ታዲያ ይህ የአገራቱ አንድነትና የሰላም ስምምነት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ የሰላም አየር እንዲነፍስ አስችሏል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በባህል፣ በቋንቋ፣ በሀይማናት እንዲሁም በተለያዩ ዕሴቶች የሚመሳሰሉ ሲሆን ለሁለት አስርት ዓመታት “ሞት አልባው ጦርነት” እየተባለ የሚጠራውን የወንድማማች አገራት የጥላቻን ግንብ በፍቅር ድልድይ እንዲናድ ባለፈው አንድ ዓመት ከፍተኛ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚሁ መሰረት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም መሰረት በማድረግ የተከወኑ ሁነቶች ነበሩ። የኤርትራ የባህል ቡድን ባለፈው የካቲት ወር 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ በመገኘት የባህል እና የህዝብ ለህዝብ አንድነትን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶችን በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህርዳር እና በሃዋሳ ከተሞች አቅርቦ ነበር። በተመሳሳይ ደግሞ ከስልሳ በላይ አባላትን የያዘው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ ሦስት ከተሞች ባህላዊ የሙዚቃ ትርዒቱን ለማቅረብ ታህሣሥ 6 ቀን 2012 ዓ.ም አስመራ ከተማ ገብቶ ነበር። ይህም ማለት በአሳለፍናቸው ጊዜያት አገራቱ ይህን መሰል ግንኙነት ሲያደርጉ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
ለአንድ ሳምንት በኤርትራ የቆየው የባህል ቡድን በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የተመራው ነበር። የኢትዮጵያ የባህል ቡድን አስመራ ኤርፖርት ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ይህ ሁነት ባህል የማህበረሰብ እሴት ከመሆን አልፎ የሰላምና የእርቅ ድልድይ እንደሚሆን በግልፅ ያሳየ ነው። ጉዳዩን ይበልጥ ለመዳሰስ እንዲመቸን ከቡድኑ አባላት ጋር የተጓዙ የልዑካን ቡድን ሀሳብ ለማየት እንሞክር።
አቶ ወሰንየለህ መብረቁ የባህል ቡድኑ የኦርኬስትራ ኃላፊ ሆነው ወደ ኤርትራ ተጉዘዋል። አቀባበሉን ምን ይዘት እንደነበረው ሲያስረዱ፤ አስመራ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኤርትራው የባህል እና ስፖርት ኮሚሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክሌ፣ በኤርትራ የኢፌዴሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር አርዓያ ደስታ፣ በታዋቂ አርቲስቶች፣ የሴቶች ማህበር አባላት እንዲሁም በሌሎች የስራ ኃላፊዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች ደማቅ የወንድማማችነት አቀባበል ተደርጎልናል።
‹‹በኤርትራ ለአንድ ሳምንት ቆይተናል›› የሚሉት ኃላፊው፤ ከ60 በላይ ሰዎችን የያዘው የባህል ቡድን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቴአትር፣ ከታዋቂ ድምጻውያን እና ከጃኖ ባንድ የተውጣጣ እንደነበር ያስረዳሉ። የባህል ቡድኑ ዓላማ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ይናገራሉ። በቆይታቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች በሚያቀራርብና የባህል ልውውጥ ላይ መሰረት ያደረገ የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በአስመራ፣ ከረን እና ምጽዋ ከተሞች ማቅረባቸውን ይገልፃሉ።
የባህል ቡድኑ የመጀመሪያ የሙዚቃ ዝግጅቱን ያቀረበው በከረን ከተማ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ወሰንየለህ፤ በከተማው በሚገኘው ስታዲየም በተካሄደው ልዩ ዝግጅት የብሄራዊ ቴአትር የሙዚቃ ክፍልና ታዋቂ ድምጻዊያን የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃ ጨዋታዎችን ለከተማዋ ነዋሪዎች አቅርበዋል። በተለይ አመልማል ሙዚቃዋን በምታቀርብበት ወቅት ለቅሶ፣ ደስታ፣ ናፍቆት ብቻ የተደበላለቀ ስሜት ነበር። ይህ ህዝብ ላይለያይ የተገመደ፤ ግማዱ ላይበጠስ የጠነከረ መሆኑን በዝግጅቱ ታይቷል።
የባህል ቡድኑ የሙዚቃ ዝግጅቱን በቀጣይ በአስመራ የማጠቃለያ ዝግጅቱን ደግሞ በ‹‹ሲኒማ ሮማ›› አቅርቧል። በፕሮግራሙ ላይ የኤርትራ የባህል እና ስፖርት ኮሚሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክለ እንዲሁም የኢፌዴሪ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ንግግር አድርገዋል። ኮሚሽነሩ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ከረጅም ዓመታት በኃላ ሰላም እንዲሰፍን የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት ማከናወናቸውን አንስተው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል። ይህን መሰል የባህል ትስስር የሚፈጥር ዝግጅት እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን እንዲሁም የኤርትራ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ያደረጉት አስተዋጽኦ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነም አንስተው ነበር።
የኢፌዲሪ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ ባለፈው ዓመት የኤርትራ የባህል ቡድን በኢትዮጵያ አራት ከተሞች የሙዚቃ ዝግጅቱን ያቀረበ መሆኑን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ የባህል ቡድንም ተመሳሳይ ዝግጅት በኤርትራ ለማቅረብ እዚህ መገኘቱን ተናግረዋል። የአስመራ ነዋሪ ዝግጅቱን ለመታደም በመምጣቱም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ በነበረው ቆይታ በከረን እና ምፅዋ ደማቅ ዝግጅት ከማቅረቡም በተጨማሪ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘቱን ጠቅሰዋል። ይህም ሁለቱ አገራት በተለያዩ ዘርፎች ለመተባበር ያላቸውን እድል መገንዘብ መቻሉን አቶ ወሰንየለህ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2012
አብርሃም ተወልደ