ላይለያይ ሆኖ የተጋመደው ፤ ላይበጠስ ሆኖ የተሰራው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ከ20 ዓመታት በላይ በነበረው ‹‹ሞት አልባው ጦርነት›› ተራርቆ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ሁለቱ ሃገሮችና ህዝቦች ማግኘት የነበረባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞች አጥተዋል።
መድረስ ከሚገባው የዕድገት ደረጃ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይሄንን ሂደት አሁን ላይ ቆም ብሎ ላሰበው በጣም ያስቆጫል። ሆኖም ዛሬ ይሄን አስከፊ ታሪክ የመቀየር ስራ በመሰራቱ የሁለቱ ሃገራት መንግስታትና ህዝቦች ወደ ሰላም መንገድ ገብተዋል።
የሃገራቱ ወደ ሰላም መምጣት ትርፉ ለሁለቱ ሀገራት ብቻም ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በኩል ለሚታሰበው የኢኮኖሚ ትስስር እና ሰላም ያለው ዋጋም ትልቅ ነው።
ሁለቱ ሃገራት ያሳለፏቸው የባከኑ ዓመታት ኢኮኖሚያቸውን ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ብሎም ዕድገታቸውን የሚያጎለብቱበት ዘመን ነበር። ሆኖም ግን ይህ ሳይሆን ቆይቷል።
ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም እንዳይጎለብት ሆኗል። ይሄ በጣም ያስቆጫል። መቆጨት ብቻም ሳይሆን አቅምን፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አጠናክሮና ፈር አስይዞ ፈጣን በሆነ መልኩ የባከነውን ጊዜ የማካካስ ስራ ለመስራት ከውስጥ መነሳሳትን ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን እና ከሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ሰላማዊ እና የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚው መስክ የጎለበተ ትብብር እና ግንኙነት ፈጥራለች። በተለይም በአየር መንገድ፣ በኤሌክትሪክ፣ በወደብ፣ በቴሌኮም እና በሌሎችም የመሰረተ ልማት እንቅሰቃሴዎች ጠንካራ ግንኙነት መስርታለች።
ከኤርትራ ጋርም ባለፉት የባከኑ ዓመታት ሁለት ሀገራት ሆነው እንደ አንድ በማሰብ ቢሰሩ ኖሮ የኢኮኖሚ ዕድገታቸው የት ሊደርስ ይችል እንደነበር መገመት አይከብድም። በእግርጥ በከንቱ ያለፉትን ጊዜያት ማንሳትና መቆጨት አስፈላጊ ባይሆንም ወደፊት ለምናስበው የኢኮኖሚ ግንኙነት ሀይልና ጉልበት ሊሆን ይችላል። አሁንም አልረፈደምና በቁጭት መነሳቱ ውጤታማ እንደሚያደርገን አንጠራጠርም።
አሁን የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ግንኙነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በተሰሩት ስራዎች የተገኙት ውጤቶች በቁጭትና በቆራጥነት ከተነሳሳን ብዙ ስራዎችን መስራትና ሀገርና ህዝባችንን መለወጥ እንደምንችል ማሳያ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በቴሌኮም ዘርፍ ብቻ የአራት ነጥብ አምስት ሚሊየን ዶላር የንግድ ልውውጥ ማድረግ ተችሏል። በአየር መንገድ ዘርፍም ከዚህ በሚልቅ ደረጃ የንግድ ልውውጥ ተደርጓል።
በአገራቱ መካከል ሰላም፣ ልማት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጠር በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ለኤርትራ የኤምባሲ መስሪያ ቦታ መሰጠቱ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር የባህል ቡድኖች ወደ ሁለቱም ሀገራት እንዲሄዱ መደረጉ እና ተደጋጋሚ የመሪዎች ይፋዊ ጉብኝት አንዱ የግንኙነት ማጠናከሪያ መስመሮች ናቸው። ይሄ የሚያመለክተው ሁለት ሆኖ እንደ አንድ ማሰብ፤ ግንኙነቱን ማጠናከር እና በሙሉ አቅም መስራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ኪሳራውም ማካካስ እንደሚቻል ነው። ስለዚህ የተጀመሩ ስራዎችን በቁርጠኝነት ለማስቀጠል በሁለቱ ሀገሮች በኩል መትጋት ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ ኢኮኖሚያችንን ከልመና ወደ ብልጽግና እንድናሸጋግር አብረን ለመስራት በኢትዮጵያ በኩል ልባችን፣ አእምሯችን፣ እጃችን ክፍት ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል። ስለዚህ ሁለት ሆኖ እንደ አንድ በማሰብና በመስራት ወደ ብልጽግና ጎዳና ለሚደረገው ጉዞ ዳግም ቃል የተገባበት ነው።
ስለዚህ ወደ ስራ መመንዘር አለበት። አሁን በመሪዎች መካከል የሚሰሩ ስራዎች፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አበረታች ቢሆኑም በተጠናከረ መልኩ ወደ ህዝብ መውረድና መሰረት መያዝ አለባቸው። እያንዳንዱ ግንኙነትና የንግድ ልውውጥ በህግ፣ ስርዓት ባለው መንገድ መመራት አለበት።
ህግና ስርዓት የያዘ ማንኛውም ግንኙነት ለሀገሮችም ሆነ ለህዝቦች ዘለቄታዊ ግንኙነት ዋስትና ነው። በመሆኑም በህግ የተመራ ግንኙነትን በማጠናከር በ‹‹ሞት አልባ ጦርነት›› የባከነውን ጊዜ ማካካስ ይገባል!።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2012