ይህ የበጋ ወቅት ነው። በበጋ ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የእረፍት ወቅት ነው። በእንዲህ አይነቱ የእረፍት ወቅት ደግሞ ጥምቀት፣ ሰርግና ሌሎች ጉዳዮች ይበዛሉ። እነዚህ ወቅቶች የጨዋታና የደስታ ናቸው። ወጣቶችና ልጅ አገረዶች የደስታ ጊዜያቸው ነው። አዋቂዎችም ቢሆን ከሌሎች ወቅቶች በተለየ የሚጫወቱት በዚህ በበጋ ወቅት ነው። በበልግ እና በክረምት ወራት ሰርግ ወይም ሌላ ጉዳይ ቢኖር እንኳን ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ዘና የሚባልበት አይደለም። ቢያንጎራጉሩም በሥራ ቦታ ላይ ሆነው ነው። በዚህ በገና ሰሞን የበጋ ወቅት ግን ጎረቤት ከጎረቤት እየተጠራሩ ጨዋታው ይደምቃል፣ ሃሴቱ ይበዛል።
‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የተባለው ደግሞ ለልጆች ነው። የገና ወቅት የበጋ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ልጆች የሥራ ጫና የለባቸውም። የግብርና ሥራ አይታዘዙም፤ ከብትም አይጠብቁም። በዚህ ወቅት ሰብል ስለሚሰበሰብ ከብቶች ከቤት ይመገባሉ
ልጆችም ከብቶችን ጠብቁ ተብለው አይገደዱም።
ስለዚህ ልጆቹ ገና ሲጫወቱ ቤተሰብ ተቆጣኝ አልተቆጣኝ ብለው ሳይሆን በሙሉ ነፃነት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለአሸንዳ ለልጅ አገረዶች እንደሚሰጠው ነፃነት በገና ጨዋታም ለልጆች ነፃነት ይሰጣል።
በነገራችን ላይ የገና ጨዋታ በበጋ ወቅት መሆኑ ወሩን ሙሉ ነፃነት ስለሚሰጣቸው እንጂ ለበዓሉ ዕለት ብቻ ከሆነ በክረምት ወራትም የተወሰነ ነጻነት አለ። ለምሳሌ ለፍልሰታ (ነሐሴ 16) እና ለእንቁጣጣሽ ልጆች እንዲጫወቱ ተብሎ ለእዚያን ቀን አባቶች ናቸው ከብት የሚጠብቁት። አባቶች እንኳን ባይመቻቸው ሌላ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ያለ (ወደ ጨዋታው የማይሄድ) ሰው ከብት ይጠብቃል እንጂ ልጆች ከብት እንዲጠብቁ አይገደዱም።ወደ ገናችን እንመለስ። የገና ጨዋታ ብዙ የተባለለት ነው። አሁን ላይ ከገጠር ይልቅ ወደ ከተማ ያዘነበለም ይመስላል (በእርግጥ ብዙ ባህሎች ከገጠር ይልቅ ወደ ከተማ እየገቡ ነው)። የገና ጨዋታ ከባህል ስፖርቶች አንዱ ሆኖም እውቅና ተሰጥቶታል። የገና ጨዋታ ራሱን ችሎ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን ለመሆን በቅቷል። ጨዋታውም የራሱ የሆነ ህግና ደንብ ያለው ነው። የራሱ የሆነ ጥበብ አለው።
ሌላው የገና ጨዋታ ጥበብ አዳጊዎች (ልጆች) ሲጫወቱ እርስ በርስ የሚለዋወጡት የቃል ግጥም ነው። ይወዳደሳሉ ይተራረባሉ። በተለይም በጨዋታው የተሸነፈው ቡድን በአሸናፊዎች ይተረባል፤ አሸናፊዎች ደግሞ የድል መልዕክት ባላቸው ስንኞች ይጫወታሉ። መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ስለገና ጨዋታ አንዳንድ እንበል። የገና ጨዋታ ሁለት ቡድኖች ጎራ ለይተው የሚጋጠሙበት ልዩ ባህላዊ ትዕይንት ነው። ለሁለቱ ቡድኖች እኩል እኩል ቁጥር ያላቸው ተጋጣሚዎች ላይኖራቸው ይችላል። ያንደኛው ቡድን በርከት ብሎ፣ የሌላኛው ቡድን አነስ ያሉ ተጋጣሚዎች ሊይዝ ይችላል።
አንደኛው ቡድን ከቀኝ ወደ ግራ ከያዘ፣ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ ያለውን ስፍራ ይይዛል። አቅጣጫውን ያልለየ ተጫዋች ካለ፣ ‹‹ሚናህን ለይ›› ተብሎ፣ ካስፈለገም በዱላ ቸብ ተደርጎ፣ ቦታውን ይይዛል። በጨዋታ መሃል ሚናውን ስቶ በሌሎች ሚና በኩል ከተገኘ ‹‹ከሚናህ!›› የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። በሰሜኑ በተለይም በአማራ አካባቢዎች ‹‹ጥንጓን›› ወይም ‹‹ሩሯን›› የመቱበት የዱላው ራስ ‹‹ገና›› ይባላል። ከወደ ራሱ እንደ ከዘራ ቆልመም ያለ ዱላ ነው።
የገና ጨዋታ አሁን በዘመናዊ መልኩ በከተሞች ከምናየው ይለያል። በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በገባው ዘመናዊ የገና ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ዱላውን (ገናውን) ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም። በጥንታዊው ወይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚደረገው የገና ጨዋታ ላይ ግን እንደተፈለገው በማንሳት፣ ሩሯን (ጥንጓን) አክርሮ መለጋት ይቻላል።ሌላው ደግሞ በዘመናዊው የገና ጨዋታ ስፖርት፣ ሩሯ የምትገባበት (የምትለማበት) ሥፍራ እንደ እግር ኳስ የግብ ሥፍራ ያለው ነው። በጥንታዊው ጨዋታ ግን የገና ጨዋታው የሚካሄድበት ሜዳ ወይም የእርሻ ማሣ፣ ሁለቱም ጫፎች የግብ ወይም የመልሚያ ቦታዎች ናቸው። ከሜዳው ወይም ከማሳው ስፋት የተነሳም ተጫዋቾቹ እንደ ልባቸው እየሮጡ ይጫወታሉ። ጨዋታው በውጤት አሊያም በሽንፈት እየታጀበ ይቀጥላል።አንዱ ቡድን ሩሯን (ጥንጓን) እንዳለማ ወይም እንዳገባ በተቃራኒው ቡድን ላይ የተረብ መዓት ይዥጎደጎዳል። በገና ጨዋታ ላይ የሚሰነዘሩ ተረቦች ታዲያ እንደ መዝናኛና እንደ ማድመቂያ ነው የሚቆጠሩት። የሚተርበው ቡድን እንኳን በተረቡ ይዝናናል ይስቃል እንጂ ቂም መያዝ ብሎ ነገር በገና ጨዋታ አይታሰብም። ተሸናፊውም በእልህ ለማሸነፍ ይነሳሳል እንጂ በጨዋታ አድማቂው ተረብ አይቆጣም።
በጨዋታው ላይ የሚሰነዘሩ ወይም የሚወረወሩ ተረቦች በአብዛኛው በአካላዊ ገፅታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለምሳሌ ቁመት፣ እርዝመትና እጥረት፣ ውፍረትና ቅጥነት ወዘተ…
‹‹አሲና በል አሲና ገናዬ
እያሃ … አሲና ገናዬ››… እያሉ ተጋጣሚዎች ጨዋታውን ያደሩታል።
ለምሳሌ አጫጭሮቹን የቡድን አባላት ለመተረብ አሸናፊዎቹ እንዲህ ይላሉ።
ይህን ወዳጅ ብላ ታስከትለዋለች
አንድ ቀን ጩልሌ ታስወስደዋለች
አጭሮቹ በተራቸው ደግሞ፡-
እረጅም ነህና ሞኝነት አታጣም
እቆርጥልሃለሁ አሳጥሬ በጣም
ይኸን ረጅሙን ጎምዶ ጎማምዶ
ግማሹን በርጩማ ግማሹን ማገዶ
እያሉ የአፀፋ ምላሹን ያዥጎደጉዱታል። አሁንም ወፍራሞች ደግሞ ቀጭኖችን እንዲህ ይሏቸዋል፤
ሲሄድ ቅትር ቅትር ሲበላ እንዳንበጣ
ወዘና የሌለው የጨጓራ ቋንጣ
የተረብ በትር ያረፈባቸው ቀጭኖችም ከአፀፋ ምላሽ አይቦዝኑም፤
እ የው አካሄዱን አረማመዱን
እን ደ ቃሪያ ሎሚ ወጥሮ ሆዱን
በጥንቱ የገና ጨዋታና አሁንም በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ሴቶች ባይጫወቱም በሜዳው፣ ዙሪያ ሆነው የሚደግፉትን ቡድን ያበረታታሉ፤ የሚነቅፉትን ደግሞ በተረብ ይሸነቁጡታል።
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጋሻ
ለእናቱ ሰጣት ለአመድ ማፈሻ
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጦር
ለአባቱ ሰጠው ለቤት ማገር
እያሉ የገናን ጨዋታ ያደምቁታል።
ገና ጨዋታ በትክክል በአገራችን መቼ እንደተጀመረ በጽሁፍ የተደገፈ መረጃ ባይገኝለትም ከክርስቶስ ልደት በፊት ይዘወተር እንደነበር ይነገርለታል። በዚህም የክርስቶስ ልደት (ገና) ይከበራል። እረኞች የገና ጨዋታን ከታህሳስ ጀምሮ እስከ ጥር እና ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ ይጫወቱት እንደነበር አባቶች ይናገራሉ። በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የገና ባህላዊ ስፖርት በስፋት ይተገበር እንደነበርም ይነገራል።
በገና ጨዋታ ልጆች ልክ እንደ ሆያ ሆዬ በየቤቱ እየዞሩም ይጫወታሉ።
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
ባለቦቃ ነው ባለምልክት
ልጆች ደግሞ ‹‹ፍየሌን ነብር በላት፤ ለገና ብዬ ሳደላድላት…›› እያሉ ይጫወታሉ። ‹‹ማታ ነው ድሌ ይሄ ነው አመሌ›› በማለት ሌሎች የፍቅር ዘፈኖችም ይዘፍናሉ።
ታህሳስ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና።
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታህሳስ።
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ።
የገና ጨዋታ ወጥ የሆነ ህግ የለውም፤ ከአካባቢ አካባቢ እንዲሁም በከተማና በገጠር የተለያየ ህግ ሊኖረው ይችላል። የሚያስፈልገው የተጫዋች ቁጥር ሲሞላ ወገን ወገናቸውን ይዘው በዱላ ቀልጣፋ የሆኑ ተጫዋቾች ጥንጓን (መጫወቻ ኳሷ) ወደፊት እንድትቀጥል ይመቷታል ወይም ይመልሷታል። ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ በጨዋታው ስለሚሰጡ ጥንጓን ከእግር መካከል በገባች ጊዜ ከሰው እግር ጋር ደርበው ስለሚመቱ የእግር መሰበር በዚህም ሳቢያ ወገን ለይተው እስከመፈናከት ይደርሳሉ። በንጉሳውያን ዘመን የመኳንንቱም አሽከሮች፣ የንጉሡና የንግሥቲቷ አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም በጉብዝና የሚያስጠሩት በባህላዊው የገና ጨዋታ ነው።አንዳንድ ጊዜ ጨዋታው በመጨረሻ ፀብ ስለሚያነሳ ጉዳት ያጋጥማል። ጥንጓም ኃይለኛ ለጊ በመታት ጊዜ ዓይን እስከ ማጥፋት ትደርሳለች። ተጫዋቾች ‹‹ሚና›› ብለው በሚጫወቱበት በቆልማማ ዱላ ቢደባደቡም የሚገላግል ዳኛ አልነበረም፤ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ ከመሳቅ በስተቀር ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አልተለመደም። ‹‹እግር ይብሳል፣ ያንከላውሳል›› እያሉ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት በገና ጨዋታ የተለመደ ነበር።በገና ጨዋታ አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፊሪዳና ጠጅ ተሰጥቷቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ሜዳውን የጦርነት ድል ያገኙበት ያስመስሉት ነበር። ከሚዘፍኑት ግጥሞች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
ማታ ነው ድሌ
ይሄ ነው አመሌ
አሲና በል አሲና ገናዬ
ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ
ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው
የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው።
የብብቱ ሽታ
የመንፈቅ በሽታ።የጀርባው መረሬ፣ ያውላል ጥንድ በሬ።ከአሥር ጋን አተላ
አይተርፈው በአንኮላ።እግርህ የሸረሪት ሆድህ የእንቁራሪት
ቀን እንደጠላሁህ እንዳትመጣ ሌሊት።ስድብ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመኳንንቱና በነገሥታቱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል። በሚደርስባቸው ስድብ ግን ምንም ዓይነት ቁጣና ቅጣት አያደርጉም። ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፤ በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ›› የተባለላቸውም ለዚህ ነው።
የገና በዓል መነሻውና የስነ ቃል ምንጩ ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ቢሆንም አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ የሚከበረው ከተማ ቦታ በተለይም አዲስ አበባ ነው። ለዚህም ምክንያቱ በገጠር አካባቢ ተገቢ የግንዛቤ ማስጨበጫ አለመሰጠቱ ነው። እንዲያውም በተቃራኒው ኋላቀርነት ነው እየተባሉ ስለሚነገሩ ለአገር ባህል እንዳይቆረቆሩና እንዳይጠብቁት ተደርጓል። ከተማ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በማንበብም ሆነ መገናኛ ብዙኃንን በመከታተል ባህል አኩሪ መሆኑን ግንዛቤ ስለሚኖረው ይመስላል ባህል ሁሉ ወደ ከተማ እየገባ ነው። በውጭው ዓለም እንኳን ለራሳቸው ሌላውም ባህል ክብር ሲሰጡ እናያለን። ዳሩ ግን የአገሪቱ አኩሪ ባህል ባለቤት የሆነውን የገጠሩ ማህበረሰብ ላይ አልተሰራም። ይህ ጉዳይ የሁላችንም ነውና ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማሳወቅም ይጠበቅብናል!
ባህላዊ የገና ጨዋታ አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ዋለልኝ አየለ