ሰዓቱ 7፡15 ሆኗል። የሕክምና ባለሙያዎች ምሳቸውን በልተው መመለስ ጀምረዋል። የእነሱን መምጣት በአግዳሚ ወንበር ተኮልኩለው የሚጠብቁት ታካሚዎች እናቱ ገበያ የሄደችበት ሕጻን ያህል ጓጉተዋል። እኔም ከአጠገባቸው ቁጭ ብዬ በጉጉት የሚጠብቁት አካል በመሆን ጨዋታየን ቀጠልኩ።
‹‹ወሬን ወሬ ያነሳዋል›› ነውና ብሂሉ የመጣንበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕመም ስሜት ጭምር እየተነሳ ወጉ ቀጠለ። ‹‹እኔማ በ‹ሪፈር› ተልኬ ነው የመጣሁት›› አለችና ቀና ስትል ምልከታዬ ከአግራሞት መሆኑን ለመረዳት ሰከንድ አልወሰደባትም። ትክክል ነበረች። ለሆስፒታል የተጻፈላትን በስህተት ጤና ጣቢያ ይዛ የመጣች አድርጌ እያሰብኩኝ ነበር። በእጇ የያዘችውን ወረቀት ዘረጋችልኝ። ተቀብዬ አየሁት፤ መላልሼ አነበብኩት።ልጂቱ አልተሳሳተችም።ወርቅነሽ ዳርሰማ ትባላለች።ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተገቢው የነፍሰጡር ክትትሏን በግንቦት 20 ጤና ጣቢያ ማድረግ እንድትችል እና አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግላት የተጻፈላት የ‹‹ሪፈር›› ወረቀት ነበር።
ከዚህ በፊት ‹‹ሪፈር››ን የምናውቀው ከታች ወደ ላይ (ከጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታል ) ነበር። አሁን ደግሞ ከላይ ወደ ታች (ከሆስፒታል ወደ ጤና ጣቢያ) መላክ መጀመሩን እየተመለከትን ነው። ለመሆኑ ምን ተገኝቶ ይሆን? ስንል የጥያቄያችን መነሻ አደረግን።
አቶ ተስፋዬ ፉጃጋ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የግንቦት 20 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ጤና ጣቢው በሕክምና ደረጃ የተቀመጡትን አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ይሰጣል። የእናቶችና የሕጻናት፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የተመላላሽ ታካሚዎች ሕክምና እና የአስተኝቶ ማከም (እስከ ሶስት ቀን) የሚደርሱ አገልግሎቶች በመስጠት ላይ ነው።
ከዚህ በፊት በሆስፒታሎች ብቻ ይሰጥ የነበረው የአስተኝቶ ሕክምና አሁን ላይ በጤና ጣቢዎች ደረጃም ጠቅላላ ሐኪም ተመድቦ ካሉት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት አገልግሎት እየተሰጠ ነው። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንም ከተመላላሽ ሕክምናዎች ጋር በማጣመር ሙሉ አገልግሎቶች በግንቦት 20 ጤና ጣቢያ እየተሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቶቹ በዚህ ደረጃ በጤና ጣቢያው የጀመሩ መሆናቸውን የሚገልጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ ከባለሙያ ቁጥር ማነስ እና ከሕክምና ግብዓቶች እጥረት አኳያ አስተኝቶ ማከምን በስፋት መስራት እየተቻለ አይደለም።ይሄን ማድረግ ቢቻል ኖሮ የሆስፒታሎችን ጫና ማቃለል ይቻል እንደነበረ ተናግረዋል።
በጤና ጣቢያዎች ደረጃ መሰጠት የሚችሉት አገልግሎቶች በሆስፒታሎች ደረጃ መሰጠት አይገባቸውም። ምክንያቱም ሆስፒታሎች አገር አቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው አላስፈላጊ መጨናነቅ ይፈጠራል። ብዙ አገርና ረዥም መንገድ አቋርጠው የሚመጡ ታካሚዎች ይጉላላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሕይወት ሊያልፍ ይችላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ደረጃ የትኞቹ ጤና ጣቢያዎች ለየትኞቹ ሆስፒታሎች ‹‹ሪፈር›› መጻፍ እንዳለባቸው በግልጽ ይታወቃል፤ ትስስር አላቸው። በዚህ መሰረት ከጤና ጣቢያዎች አቅም በላይ የሆኑ ሕክምናዎችን ለሆስፒታሎች ‹‹ሪፈር›› እንደሚላክ ሁሉ ሆስፒታሎችም በጤና ጣቢያዎች ደረጃ አገልግሎቱ በሚገባ እየተሰጠ መሆኑን እያረጋገጡ ‹‹ሪፈር›› የሚልኩበት አሰራር መኖሩን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል።
ይሄ ብቻ ሳይሆን አሁን ጤና ጣቢያው የአልትራ ሳውንድ እና የመለስተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው። ሥለዚህ የአዲስ ከተማ ወረዳ አንድ ነዋሪዎች እና ለዚህ ጤና ጣቢያ ቅርበት ካላቸው አካባቢዎች ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚሄዱ ታካሚዎች በቀጥታ ወደዚህ ይላካሉ። ምክንያቱም በቅርበት ትስስር ፈጥረን እየሰራን በመሆኑ በሶስት ቀን ቢበዛ በሳምንት እየተገናኘን ስለምንነጋገር አገልግሎታችን እስከምን ድረስ እንደሆነ ሆስፒታሉ ያውቀዋል ብሏል።አልፎ አልፎም በጤና ባለሙያዎች እና በጤና መሳሪያዎች ጭምር መተጋገዞች እንዳሉም ተናግሯል።
የጤና ጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር እንደገለጹት፤ በጤና ጣቢያው በቀን በአማካኝ እስከ መቶ ሃምሳ ሰው ይስተናገዳል። የጤና ጣቢያው ባለሙያዎች ከሚፈተኑባቸው ችግሮች መካከልም አካባቢው በመልሶ ማልማት የተነሳ አብዛኛው ነዋሪ ለቅቋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ከነበረው ሕዝብ የማይተናነስ ምንአልባትም የሚበልጥ ቁጥር ያለው ሕዝብ በአካባቢው ሸራ ወጥሮ ይውላል፤ ያድራል።
በዚህ የተነሳ ለበሽታ የመጋለጥ እድሉ በጣም እየጨመረ መጥቷል። በብዛት ደግሞ ድንገተኛ ታካሚዎች የሚበዙ ሲሆን የቆሰለም ሆነ የደከመ ታማሚ እንደምንም ብለው የአካባቢው ሰዎች፣ፖሊሶች ወይም የጎዳና ተዳዳሪዎች አምጥተው ጤና ጣቢያ ካደረሷቸው በኋላ ጥለዋቸው ይሄዳሉ። ይህ ሁኔታ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የራሱ የሆነ ጫና አሳድሯል።ቤተሰብ የሌላቸው፣አስታማሚ የሌላቸው ነገር ግን ለከፍተኛ ሕመም የተጋለጡ ሰዎች በተደጋጋሚ ያጋጥማሉ።እነዚህን ይዘን እስከ ሆስፒታሎች ድረስ በመሄድ ለከፍተኛ እንግልት እንዳረጋለን።በሽተኛውም ይጎዳል።ባለፈው ክረምት የተከሰተው የኮሌራ ወረርሺኝም መነሻ እዚሁ አሜሪካን ግቢ እንደነበረ አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል።
በድንገተኛ ክፍል የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ያገኘናቸው የቢ ኤስሲ ነርስ ባለሙያው ጌታቸው ከበደ በበኩላቸው፤ የጤና ጣቢያው ከፍተኛ አገልግሎት ድንገተኛ ታካሚዎች ሲሆኑ በሽታዎቹም ተመሳሳይና ተደጋጋሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።በድንገተኛ ክፍል በብዛት ለሕክምና የሚመጡትም በዋናነት በከፊል በፈረሱ ቤቶች ውስጥ ሲያድሩ የቀረው የቤት ፍርስራሽ ተንዶ አደጋ የደረሰባቸው (የሞቱም ይገኛሉ )፣በእብድ ውሻ በሽታ የተለከፈ እና በሸራ ተጠልለው የሚውሉና የሚያድሩ እንዲሁም ብር እያስከፈሉም በሸራ የሚያሳድሩ ብዙ ሰዎች በመኖራቸው እነዚህ ለተላላፊ በሽታ እየተጋለጡ ነው። በአንድ የሸራ ቤት ውስጥ ከ20 እስከ 30 ሰዎች ታጭቀው ያድራሉ። በዚህ የተነሳም ለተባይና መሰል ችግሮች ከመጋለጥ ባለፈ በሌሎች አካባቢዎች የማይከሰትና እዚህ አካባቢ ደግሞ በስፋት የሚታይ የግርሻት ትኩሳት የሚባል በሽታ የተለመደ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ተናግረዋ።
በግንቦት 20 ጤና ጣቢያ ሲታከሙ ካገኘናቸው ሰዎች መካከል አቶ አቶ ተስፋዬ አብዝሃ አንዱ ናቸው።ተገልጋዩ እንደሚሉት፤ በዚህ ጤና ጣቢያ የሚታከመው አብዛኛው ምስኪን ሕዝብ ነው።የቀን ሰራተኛ ነው።በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።ማንም አይቶ መፍረድ የሚችለው ደሃና አሁን ደግሞ በሸራ ድንኳን ውስጥ ከነሙሉ ቤተሰቡ የሚኖር ሰው ነው።ሥለዚህ ይሄን ያገናዘበ የመድሃኒት አቅርቦት የለውም።በልቶ የማደር አቅም የሌለው ሕዝብ ከውጪ መድሃኒት እንዲገዛ ይታዘዝለታል።ስለሌለው ሳይገዛ ይቀራል።በዚህ የተነሳ ሕብረተሰቡ ለችግር ተጋልጧል።መንግስት ጥናት በማድረግ የዚህን አካባቢ ማህበረሰብ በተለየ መንገድ ማገዝ ቢችል ጥሩ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሲጠቃለል ለበሽታ ተጋላጭነታቸውን በሚጨምሩ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት አለበት።የጤና ተቋማት በቅንጅት በሚሰሩበት ወቅት ውጤታማነታቸው ይጨምራል።ተግባርና ሃለፊነታቸውን በተገቢው መዋጣት ያስችላቸዋል።ተደራሽነታቸው ብቻ ሳይሆን ጥራታቸውም ይጨምራል።ባለሙያውም በተገቢውና በአስፈላጊ ሥራው ላይ ተሰማርቶ ውጤት እንዲያመጣ እድል ይኖረዋል።የዘርፉ አገልግሎትና የማህበረሰቡ ጤናማነት ይጎለብታል። ዜጋውም አምራችነቱ በዚያው ልክ ያድጋል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 17/2012
ሙሐመድ ሁሴን