ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 50 የመንግስት እና 201 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ።ከእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በአመት አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ተማሪዎች ይመረቃሉ።ያም ሆኖ ግን በትምህርት ጥራት ላይ በርካታ ችግሮች ይነሳሉ።በዚህም የተነሳ ለአመታት ዘርፉ ሮሮዎችን ሲያስተናግድ ኖሯል።
በዚህ ምክንያት የአገሪቱ ትምህርት ጥራት ችግሮች በአገሪቱ ምሁራን መፍትሔ ያገኙ ዘንድ ምክክር ከተደረገ በኋላ ለዚህ ችግር መፍትሄነት የተቀመረው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተካርታ በተግባር ላይ መዋል ጀምሯል።
በዚህ መነሻነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሰራራቸውን በአዲስ መልክ ቃኝተው የመማር ማስተማሩን ሥራ መጀመራቸው ይታወቃል። በመሆኑም ለጀማሪ ተማሪዎች የተዘጋጀው የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት የተማሪዎችን የማገናዘብ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ማስገኘቱን ተግባሩን በባለቤትነት የሚመሩ አመራሮችና ተማሪዎች ይናገራሉ።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቱ የተማሪዎች ፕሬዚደንት የሆነው ተማሪ አደባባይ ጋሻው እንደሚለው፤ በዚህ ዓመት የተጀመሩትና አዲስ ገቢ ተማሪዎች የሚወስዷቸው የትምህርት አይነቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።
ተማሪ አደባባይ እንደሚለው አዲስ ገቢ ተማሪዎች የሚወስዷቸው የፍሬሽ ማን ኮርሶች ተማሪዎች ነገሮችን በሰፊው ማየት እንዲችሉ ረድቷቸዋል።ዙሪያ ገባውን መቃኘትና ማየት አስችሏቸዋል።
እነዚህ ኮርሶች ነገሮችን በጥልቀት መረዳትና መመርመር እንዲችሉ የሚያደርጉ ናቸው የሚለው ፕሬዚደንቱ፤ የአገራቸውን መልክዓም ምድር፣የሥራ ፈጠራ እና ሌሎች እውቀቶችን የሚያስጨብጡ በመሆናቸው ወደየት መሄድ እንደሚችሉ እና የት መድረስ እንዳለባቸው ራሳቸውን ዝግጁ ለማድረግ በእጅጉ እንደጠቀማቸው አስረድቷል።
ተማሪዎቹ ትምህርቱን ከመጀመራቸው በፊት የመመረቂያ ዓመት መራዘሙን ብቻ በማየት ጥርጣሬ አድሮባቸው እንደነበረ የሚናገረው የተማሪዎች ፕሬዚደንት፤ አሁን ላይ ሆነው ሲረዱት በምርጫቸው ወቅት ያጡትን እድል ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ እንዳሳደረባቸውም ጠቁሟል።የሚሰጡትን ትምህርቶች ከተማሩ በኋላ ባሉት መመዘኛዎች ተጠቅመው የእድሉ ተጠቃሚዎች መሆን እንደሚችሉ ግንዛቤያቸው መስፋቱን ተናግሯል።
መምረጥ የሚፈልጉትን መስክ ለማግኘት አስልተው እንዲራመዱ ያግዛል። አገራቸውን በተገቢው እንዲያውቁ፣ባህላቸውን እንዲረዱ፣ታሪካቸውን እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ነው።በመሆኑም በምን መልኩ ራሳቸውን እና አገራቸውን መጥቀም እንዳለባቸው መለየት አስችሏቸዋል።በመሆኑም ተማሪዎች ወደውት እየተማሩ እንደሆነ አስረድቷል።ከዚህ በፊት ከዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ይለያይ የነበረውን የነጥብ አሰጣጥ (ግሬዲንግ) ወደ አንድ አይነት በማምጣት ፍትሃዊነትን የሚያሰፍን እንደሆነም አክሎ ገልጿል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ግዛቴ ጌጤ እንደሚሉት፤ የአገራቸውን ሁኔታ የሚያሳውቁ እና መሰረታዊ እውቀትን የሚያስጨብጡ ትምህርቶች በመሆናቸው ለተማሪዎች ግንዛቤ መዳበር አግዘዋል።የቋንቋ፣የቁጥር እና በአስተውሎት ማጤን የሚያስችሉ ትምህርቶች በመሆናቸው ብስለታቸውን ማሳደግ አስችሏቸዋል ይላሉ።
በመጀመሪያው መንፈቅ በመማር ላይ የሚገኙት ሰባት የትምህርት አይነቶች እንደሆኑ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ አቶ ግዛቴ፣ ነገሮችን በጥልቀት ማጤን (critical thinking)፣ ጂኦግራፊ፣ ሲቪክስ፣ ሒሳብ ለማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች፣ሒሳብ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች፣ ስነልቡና፣ እንግሊዝኛ ተግባቦት ክፍል አንድ፣ኢኮኖሚክስና ፊዚክስ፣ እንደሆኑም ዘርዝረዋል።
ተማሪዎቹ እንደገቡ በጋራ እነዚህን ትምህርቶች እንዲወስዱ ይደረጋል።በመሆኑም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ በመሆናቸው መግባባት እንዲፈጠር፣ አንድነትና መተዋወቅ በመካከላቸው እንዲኖር አድርጓል ይላሉ አቶ ግዛቴ።
በዘንድሮው አመት ከመጀመሪያውም ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡት 3300 ተማሪዎች እንደሆኑ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ የጀማሪነት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው ብለዋል።የሕግ ተማሪዎች የመጀመሪያው መንፈቅ ትምህርት እንደተጠናቀቀ እንዲመርጡ በማድረግ በውጤታቸው መሰረት ወደ ሕግ ኮሌጅ የሚገቡ ይኖራሉ፤ ሜዲስን፣ቬትርነሪና ፋርማሲም በውጤታቸው መሰረት እንዲገቡ ይደረጋል።ነርሲንግ ፣አንስቴዥያን እና የመሳሰሉት ደግሞ አንድ አመት ሲያጠናቅቁ ወደ መረጡት የሚገቡ ናቸው ያሉት አቶ ግዛቴ፤ ለምሳሌ ሲቪል፣መካኒካል እና የመሳሰሉት የኢንጂነሪንግ ትምህርቶች የመጀመሪያውን መንፈቅ እንዳጠናቀቁ በውጤታቸው መሰረት ወደ ቅድመ ኢንጂነሪንግ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ዶክተር ነጋ ጣሴ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ዲን ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት፤ የትምህርቶቹ መሰጠት የተማሪዎቹን የአስተሳሰብ አድማስ በማሳደግ በኩል ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።
በትምህርቶቹ ዙሪያ በየጊዜው ከተማሪዎቹ የሚገኘው ግብዓት የሚያበረታታና አዎንታዊ ነው የሚሉት ዶክተር ነጋ 6278 ተማሪዎች የዚህ ፕሮግራም ተካፋዮች መሆናቸውን አንስተው፣ የመማሪያ ቁሳቁሶች እና የማጣቀሻ መጽሐፍት እግር በእግር እንዲሟሉ በማድረግ በጥሩ ሁኔታ መማር ማስተማሩ እንደቀጠለ አስረድተዋል።
አንትሮፖሎጂ፣ እንግሊዝኛ፣ጂኦግራፊ ሒሳብ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ሳይኮሎጂ፣ ሲቪክስ የትምህርት አይነቶችን ለማህበራዊ ሳይንስም ሆነ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሁም ለተፈጥሮና ለማህበራዊ ሳይንስ መምህርነት ለሚሰለጥኑ ተማሪዎች እያስተማሩ እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር ነጋ፤ በተማሪዎች በኩል እስከ አሁን የተነሱ አሉታዊ አስተያየቶች የሉም ብለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቀደም ሲል በበጀት ዓመቱ መግቢያ በገለጸው መሰረት የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ዝቅተኛ የቆይታ ጊዜ አራት አመት እንደሚሆን አሳውቆ ነበር።በተጨማሪም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ ሴሚስተር ቅበላ በአራት የቅበላ ዓይነቶች እንደሚሆንም ገልጿል።እነዚህም በየተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በመምህርነት፣በማህበራዊ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በመምህርነት ናቸው።
በሁለተኛው ሴሚስተር ደግሞ የተማሪዎችን የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤትን መሠረት በማድረግ በአምስት የሙያ መስኮች ምደባ ይደረጋል።እነርሱም ህግ፣ህክምና እና የጥርስ ህክምና፣ የእንስሳት ህክምና፣ ፋርማሲ እና ኢንጂነሪንግ ናቸው።የሌሎቹ የሙያ መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ የተማሪዎችን ዓመታዊ ውጤት መሠረት በማድረግ እንደሚሆን ነው የተገለጸው።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ የሚኖራቸው ቆይታ ጊዜ በጣም ውስን ቢሆንም የወደፊት ሕይወታቸውን በመወሰን ረገድ ደግሞ ትልቅ ሚና ያለው ነው።ስለሆነም ተማሪዎች ጊዜ ካለፈ ተመልሶ የማይገኝ ትልቅ ሀብት መሆኑን በማስተዋል በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሙሉ ትኩረታቸውን የላቀ እውቀትና ክህሎት በመሸመት እንዲሁም ራስን በመልካም ስብዕና በማበልጸግ ላይ ቅድሚያ መስጠት ከተገቡት ስምምነቶች ተቀዳሚው ነው።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለእውቀት ፍለጋ የሚተጉ፣ በሀሳብ ሌላውን የሚሞግቱ፤ በመተባበር፣ በመመካከር እና በመደጋገፍ ለውጤት የሚጥሩ እንዲሆኑ፤ ለሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች በሥነ ምግባራቸው፣ በመልካም ስብዕናቸውና በአለባበሳቸው አርዓያ እንዲሆኑ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የግልና የጋራ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ የዩኒቨርሲቲውን ህግ አክብረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
በአጠቃላይ የተማሪዎች ውጤታማነት እንዲረጋገጥ ብዙ ተስፋዎች ተሰንቀዋል።የመጀመሪያው መንፈቅ እስከ አንድ አመት ድረስ ተማሪዎች በጋራ የሚማሯቸው የአስተሳሰብ አድማሳቸውን የሚያሰፉ ናቸው።
በመሆኑም የአገር መውደድ ስሜት በውስጣቸው እንዲጠነሰስ ያደርጋሉ።የሚፈልጉትን ለመሆንም እድሎች ይዘዋል።በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ትውልድ የመቅረጽ አደራን የተቀበለ ነው።ለዚህ ደግሞ የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 17/2012
ሙሐመድ ሁሴን