ብዙዎቻችን ለአንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ ስንባል የቻይናን ፖሊሲ ልናስታውስ እንችላላን። የኔ ጉዳይ ግን ወዲህ ነው። የራሳችንን ሀገራዊ ችግር በራሳችን ለመቅረፍ ስለተነሳ ሀሳብ። በከተማችን አዲስ አበባ በጎዳና ላይ የምናያቸው ህጻናት ቁጥር ስንት ይሆናል? ያጠናውስ ይኖር ይሆን ? ለነገሩ በየቀኑ ጎዳናን የሚቀላቀሉ ልጆች በሚኖሩባት ሀገር ምንስ አይነት ጥናት ተጠንቶ በድፍረት ቁጥሩን መናገር ይቻላል? ነገር ግን ራሳችንን እንደ አንድ አጥኚ ሳይሆን እንደ ተራ ተመልካች አስበን ቢያንስ በየትኛውም አቅጣጫ የአንድ ታክሲ ጉዞ ብንጓዝ እንደየሰፈሩ ሁኔታ በጣት ከሚቆጠሩ በአስርታት የሚገመቱ ህጻናት ልጆችን በጎዳና ማየታችን የማይታበል ሀቅ ነው። ይህም ሆኖ ብዙዎቻችን የእነዚህን ልጆች ችግር የደቂቃ የወሬ ርእስ ከማድረግ ያለፈ ችግሩን ለመፍታት የተሳታፊነት ሚና ሲኖረን አይታይም። ለምን ጎዳና ወጡ? የነሱ በጎዳና መኖር እነሱን ለችግር ከማጋለጥ ባለፈ እንደ ህዝብ እኛ ላይ እንደ ሀገርስ ምን ጉዳት ያመጣል? ብለን ስንጠይቅም አንታይም። የዛሬ እንግዳዬም እነዚህን ልጆች ተመልክተው አላስችል ስላላቸውና የራሳቸውን ቢያንስ «ለአንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ» ሀሳብ ያፈለቁና ተግባራዊ ያደረጉ እናት ናቸው።
ወይዘሮ መስቀሌ አለሙ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ጌቶ ወረዳ ቆንትር በሚባል አካባቢ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሚኖሩት ደግሞ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ነው። ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት ገና በልጅነታቸው ነበር። አዲስ አበባ ደግሞ ተቀብሎ አብልቶ አጠጥቶ የሚያሳድር የቅርብ ቤተሰብ አልነበራቸውም። በመሆኑም ኑሮን ለማሸነፍ በሰው ቤት ተቀጥሮ ከመስራት ጀምሮ አቅማቸው በፈቀደ ከትንሽ እስከ ትልቅ በንግዱ አለም ሲሰሩ ቆይተዋል።
አዲስ አበባ ከመጡ ጀምሮ ሁሌም የሚረብሻቸው ነገር አለ፤ ሰዎች ጎዳና ላይ ተኝተው በብርድም በዝናብም በጸሀይም እየተንገላቱ ሲውሉ ያያሉ። እሳቸው በተወለዱበት አካባቢ የሚቸግረው ሰው ይኖራል፤ እንደ አዲስ አበባ ግን በየቦታው መንገድ ላይ ተኝተው ውለው የሚያድሩ ህጻናት የሉም። በመሆኑም በተለይ ህጻናቱ በጣም ያሳዝኗቸዋል። ከብርድ የሚከላከል ደህና ልብስ እንኳን አይለብሱም፤ እናም ለምን ይሆን ለዚህ ህይወት የተዳረጉት? ምንስ ሀጢያት ሰርተው ነው? እያሉ ራሳቸውን ሲጠይቁ ኖረዋል። አምላክ ጥሩ ሀብት ቢሰጣቸው ደግሞ ልጆቹን ሰብስበው አንድ ቦታ ለማሳደግ እያሰቡ ለራሳቸው ቃል ሲገቡ ኖረዋል። ግና ቀን ቀንን እየወለደ አዲስ አበባም ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እድሉን እያገኙ የልጆቹን ብዛት ብቻ ሳይሆን በየቀኑ አንድም ሁለትም ልጆች ጎዳናውን እየተቀላቀሉ እንደሆነ ሲገነዘቡ ችግሩ እንኳን በሳቸው ሀሳብና አቅም በሌላውም የማይደፈር መሆኑን ይረዳሉ። ሀዘናቸውና ሀሳባቸው ግን ከሳቸው ጋር ይቀጥላል።
አዲስ አበባን ከተቀላቀሉ ከአመታት በኋላም ወይዘሮ መስቀሌ በ1992 ዓ.ም ትዳር መስርተው የራሳቸውን ጎጆ አቁመው አዲስ የህይወት ምእራፍ ይጀምራሉ። የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅ እናት ለመሆንም ይበቃሉ። ትዳራቸውን ከመሰረቱ ከስምንት አመት በኋላ ግን ከባላቸው ጋር ስላልተስማሙ ፍቺ ፈጽመው የአራትና የሁለት አመት እድሜ ያላቸውን ልጆቻቸውን የማሳደጉን ሃላፊነትና ሸክም ብቻቸውን ለመወጣት ይገደዳሉ። በዚህ ወቅት ሁለቱንም ልጆቻቸውን የወለዱት በኦፕራሲዮን ስለነበር የጤናቸውም ጉዳይ መጣ ሄድ እያለ ይረብሻቸው ነበር ። ነገር ግን በዚህ ህይወት ውስጥም ሆነው ቢሆን ስለእነዛ አቤት ባይ ያጡ የጎዳና ላይ ህጻናት ማሰቡ የዘወትር ስራቸው ነበር።
በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ አንድ ቀን የዘወትር ህልማቸውን ለማሳካት የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጠራል። በቀራንዮ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት በተገኙበት ሰባኪው ከመድረክ ላይ ሆነው «ህጻናት በወላጆቻቸው እቅፍ ፍቅርና ክብካቤ እያገኙ ማደግ አለባቸው። እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ በተለያቱ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ወስደን አቅማችን በፈቀደ እንደ ልጆቻችን ባህሪያቸውንም በጥሩ እየቀረጸን ማሳደግ ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ ምንም ጊዜ መውሰድ፣ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አይጠበቅብንም፤ ከልባችን ከወሰንን ያለንን ተካፍለን እየበላን ይህን አምላክ የሚወደውን መልካም ስራ ማድረግ እንችላለን። ልጆችን ለመርዳት እቤታችን ለመውሰድ ባንችል እንኳ ባሉበት መታደግ እንችላለን» ሲሉ ይናገራሉ።
ይሄኔ ነበር ወይዘሮ መስቀሌ እውነትም አንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ ቢወስድ ችግሩ መቀረፍ እንደሚችል የገባቸው። እናም በምድርም የህሊና እረፍት በሰማይም የዘላለም መዳንን እንዳገኝ ብለው ቢያንስ አንድ ልጅ ማንሳት እንዳለባቸው ይወስኑና እዚያው ሲያስተምሩ የነበሩትን ሰባኪ ሀሳባቸውን ነግረው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይጠይቋቸዋል። መምህሩም “ይህን የተቀደሰ ሀሳብ ለመተግበር ጊዜ መውሰድ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የችኮላ ነገር እንዳይሆን ቤተሰብ ማነጋገር ከራስዎትም ጋር በርጋታ መምከር ይጠበቅብዎታል። ለሁሉም መቼም ቢሆን በሀሳብዎ ከወሰኑና ከጸኑ ሌላው ቀላል ነው” ብለው በዚህ ጉዳይ ከተሰማሩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ቤተኒ የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት አድራሻ ሰጥተው ይልኳቸዋል።
ወይዘሮ መስቀሌ በተነገራቸው መሰረት ወደ ቤት ይመለሱና በቅድሚያ ልጆቻቸውን ያማከራሉ። ልጆቻቸውም ሀሳባቸውን ከመቀበል አልፈው ወንዱ ልጃቸው ወንድ ልጅ እንዲመጣ ሲጠይቅ ሴቷ እህት እንደምትፈልግ ትናገራለች። በተነገራቸው መሰረት ነገሩን ለጎረቤትም ለዘመድ አዝማድም ያማክራሉ፤ ሁሉም ሀሳባቸውን ተቀብሎ ያበረታታቸዋል። በተለይ ጎረቤቶች ለማንኛውም ልጅ ወሳጅ ቤተሰብ የሚደረገው ማጣራት ለማከናወን በሚመለከታቸው አካላት በኩል ምስክርነታቸውን በተጠየቁበት ወቅት “የሁል ጊዜ ሀሳቧ ነው፤ ጥሩ ጸባይም አላት፤ እንኳን ለአንድ ልጅ ለሁለት ሶስትም ትበቃለች” ብለው መስክረውላቸዋል።
ወይዘሮ መስቀሌ ይህንን ከጨረሱ በኋላ የተቀበሉትን የቤተኒ የክርስቲያን አገልግሎት ድርጅት አድራሻ ተቀብለው ወደ ድርጅቱ ያቀናሉ። ቤተኒ ሲደርሱም ስለመልካም ሀሳባቸው ምስጋናና አድናቆት ከተቸራቸው በኋላ አኗኗራቸውን በተመለከተ ጥያቄ ይቀርላቸዋል። ገቢያቸውን በተመለከተ የደመወዝ መጠን ይጠይቋቸዋል። ከሰባት ሺህ ብር በላይ የቤት ኪራይ ገቢና የልብስ ስፌት መኪናም እንዳላቸው፤ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው የሚነግዱበትም ሱቅ እንዳለ፣ በጥቅሉ በወር ከአስር ሺ በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ይናገራሉ። ለቀሪዎቹም ጥያቄዎች የቤት ባለቤት መሆናቸውን በመግለጽ ሙሉ የህክምና የምርመራ ወረቀት ጨምረው ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ በማስረጃ አስደግፈው ያቀርባሉ። ስነ ምግባራቸውንም በተመለከተ በአቅራቢያቸው ካለ ቤተክርስቲያን የድጋፍ ደብዳቤ ያስልካሉ። ጥያቄው አላበቃም፤ ሴት ወይንስ ወንድ ልጅ ነው የሚፈልጉት? የስንት አመት? እድሜስ? ተብለው ይጠየቃሉ። የሁለቱን ልጆቻቸውን የጾታ ምርጫ ወደ ጎን በመተው “ሴትም ትሁን ወንድ ችግር የለም፤ እድሜውም አያሳስበኝም፤ እናንተ የፈቀዳችሁትን ስጡኝ” ሲሉ ይመልሳሉ። ወዲያውም በየተራ እንዲመለከቱ በርከት ያሉ ፎቶዎችን ደርድረው ያቀርቡላቸውና ከዛ መሀል በመጀመሪያ የአንዲት ህጻን ፎቶ ያሳዩዋቸዋል፤ ወይዘሮ መስቀሌ ምንም ግዜ ሳይወስዱ የመጀመሪያዋን ምርጫ የመጨረሻዋምን አድርገው ይቀበላሉ። ህጻኗን ባለችበት ሄደው በአካል እንዲመለከቷትም ይደረጋል። በጣም ደስ ትላቸዋለች እናም አዎ ይቺው ህጻን ልጄ ትሁን ሲሉ ያረጋግጣሉ። ልክ አንድ ልጅ አርግዞ እስኪወልድ የሚወስደውን ጊዜ ዘጠኝ ወር ይቆዩና በረከት የምትባለውን የአራት አመት ህጻን ተቀብለው ሶስተኛ ልጃቸው ለማድረግ ይበቃሉ።
በረከትን ከክበበ ጸሀይ የህጻናት ማቆያ ይዘው ከመውጣታቸው በፊት በተለያዩ ቀናት እየሄዱ ሲያጫውቷት ቆይተዋል። እዛ እያለች ብዙም ሰው ለመቅረብ አትደፍርም ነበር። አፏን በደንብ የፈታችና መናገር የምትችል ልጅ ብትሆንም አብዛኛውን ጊዜ ሲያናግሯት መልስ የምትሰጠው ጭንቅላቷን በማወዛወዝ በምልክት ነበር። አዲሱ ቤቷ ከመጣች በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተቀይሮ በቀናት ውስጥ ሁሉንም በትክክል ማናገር ጀመረች። ለመጀመሪያ ግዜ ወደ አዲሱ ቤተሰብ ስትመጣም በጣም ደንግጣ አስቸግራ ነበር። ከመኪና አልወርድም ብላም በትግል ነበር ወደቤት ውስጥ እንድትገባ የተደረገችው። በረከት ብዙ ትፈራቸው ያስደነግጧት የነበሩ ነገሮችንም መላመድ ጀመረች በመጀመሪያዎቹ ቀናት ድመት ስታይ ታለቅስ ስለነበር ድመቷ እቤት እንዳትገባ ይደረግ ነበር፤ ዛሬ ግን በረከት ያቺኑ ድመት የገባችበት ገብታ ለማቀፍ ጭራዋን ስትከታተላት ትውላለች። እዛ ፓምፐርስ ትጠቀም ነበር፤ ከመጣች ሁለት ሳምንት በማይሞላት ግዜ ሙሉ ለሙሉ ፖፖ መጠቀም ጀምራለች። ውላ ስታድር ደግሞ ቀስ በቀስ እየተላመደች ትመጣለች በተለይ ከሴት ልጃቸው ጋር ያላት ግንኙነት ከሁሉም የበለጠ እየተጠናከረ በመምጣቱ ሁሉም ነገር ተቀይሮ የቤቱ ድምቀት ለመሆን ትበቃለች። ወይዘሮ መስቀሌ «ከአለፍ አገደም የአስረኛ ክፍል ተማሪ የሆነችውን ልጄን ስቆጣት ታኮርፈኝ ነበር፤ በረከት ከመጣች በኋላ ግን ይሄ ጠፍቷል፤ ከቤት ውስጥም ሳቅ ጠፍቶ አያውቅም» ይላሉ።
ወይዘሮ መስቀሌ የሳቸውን ጅምር መነሻ አድርገው እኔን ያየ ይቀጣ ሳይሆን “እኔን ያየ ይዳን” እላለሁ ሲሉ ለህዝቡም የሚያስተላለፉት መልእክት አላቸው። አንዳንድ ሰዎች ልጅ ብታሳድጉ ሲባሉ ልጅ አለኝ ልጅ አልቸገረኝም፣ ልጅ ምን ያድርግልኛል ሲሉ ስሰማ እናደዳለሁ። የሁላችን ሀይማኖት የሁላችንም ባህል መረዳዳትን ይደግፋል። ውስጣችን የቀናነት ሀሳብ ስለሌለ እንጂ ለእነሱ ብለን ምጣድ አናሰማም፤ ድስትም አንጥድም። በተዘጋጀው በበሰለው ባለው ነገር ልናሳድጋቸው እንችላለን። ይህን ለሀገርም ለህዝብ ፋይዳ ያለው ስራ ለመስራት ካሰብን ሞልቶ እስኪተርፈን መጠበቅ የለብንም። ስለዚህም አቅሙ የቻለ እያንዳንዱ ቤተሰብ አንዳንድ ልጅ ወስዶ ቢያሳድግ በምድርም በሰማይም ያተርፋል።
ከልባችን አስበን ካደረግነው ልጅ ስላመጣን የተለየ የሚገጥመን ችግር አይኖረም፤ የማንም ቤት ሁሌ አይሞላም፤ ሳይደርስ ቢርበን አብረን ነው የምንራበው። ቢያጠፉም ቢናገሩም ቢጠይቁም የወለድናቸው ልጆች የሚያጠፉት የሚናገሩት የሚጠይቁትን ነው፤ የተለየ የሚያስቸግሩት ነገር የለም። ትምህርትም ቢባል ዛሬ መንግስት በየትኛውም ቦታ በነጻ እያስተማረ ነው። አሁን ደግሞ ዩኒፎርም ድብተር እስክርቢቶም ከዛው ከትምህርት ቤት እየተሰጠ ነው። ልጆቹ ለኛም ለሀገርም ጥቅም የሚሰጡ ናቸው። ብዙዎቻችን ግን ይህን የማናደርገው አቅሙ ሳይኖረን ወይንም ሳናስብ ቀርተን ሳይሆን እየፈራን ነው።
አንዳንድ ቤተሰብ ጉድፈቻ ሲባል ይፈራል። የሚፈራው ደግሞ ከማህበረሰቡ አመለካከት ያልተስተካከለ የሚረብሽ ነገር በመኖሩ ነው። አንዳንድ ሰው የራሱን ልጅ ሲቆጣ ምንም የማይመስላቸው ሰዎች ሌላ የሚያሳድገውን ልጅ ቢቆጣ ግን ስላልወለደው ብለው ብዙ ያወሩበታል። ይህንን አሉባልታ እየፈሩ ልጅ ሲወስዱ መኖሪያቸውን እስከ መቀየር የሚደርሱ እያንዳንዱን ነገር ለማድረግም የሚጨነቁ አሉ፤ ይሄ ተገቢ አይደለም። ማንም የፈለገውን ይበል ዋናው ነገር ራሳችን ፈቀድን በንጹ ልብ ፍቅር እየሰጠን የቻልነውን እያደረግን ማሳደጋችን ብቻ ነው። ዞር ብለን ካየነው አይነቱ ቢለያይም ያልወለዱትን ማሳደግ በሀገራችን የኖረ ባህል ነው። የክርስትና ልጅ የአይን ልጅ እየተባለ ብዙ ልጅ ካልወለደው ጋር እየኖረ ለወግ ለማዕረግ ሲበቃ ካሳደገው ቤተሰብም ጋር በፍቅር ሲጠያየቅ አይተናል። እኔ በበኩሌ ፈጣሪ ከፈቀደ ወደፊት ቢያንስ አንድ ልጅ ለመጨመር ሀሳብ አለኝ ሲሉ ተናግረዋል።
የቤተኒ ክርስቲያን አገልግሎት የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ዳዊት ፈቃዱ በበኩላቸው ችግሩ ከኛው የተፈጠረ እስከሆነ ድረስ እኛው መፍትሄ መሆን አለብን፤ ለዚህ ደግሞ አቅሙ አለን ይላሉ። ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት ሀላፊነት ወስዶ መስራት አለበት ህዝቡ ለእምነቱ ትልቅ ቦታ ስላለው በተለይ ከሀይማኖት አባቶች ብዙ ይጠበቃል። ዛሬም በርካታ ህጻናት በየማሳደጊያው ይገኛሉ። የክበበ ጸሀይ የህጻናት ማቆያን ብቻ እንኳን ብንወስድ ከ250 በላይ ህጻናት አሉ። በአንጻሩ ብዙ ቤተሰብ ልጅ ወስዶ ለማሳደግ በልቡ ቢያስብም “ያልወለድኩትን ልጅ ባሳድግ ሰው ምን ይለኛል” በማለት የተቀመጡ አሉ። በመሆኑም ብዙ ቤተሰብን አሳምኖ ለመመልመል ከሀይማኖት አባቶች ከምሁራን እንዲሁም ከሚድያው ብዙ ይጠበቃል ። በሌላ በኩል ፈቃደኛ ቤተሰቦች ሲገኙም ጉድፈቻ በህግ የታወቀና የህግ ከለላ ያለው ሲሆን የአደራ ቤተሰብ ግን በህግ ያልተካተተ በመሆኑ ለረጅም አመታት መሰናክል ሆኖ ቆይቷል። ይህንን ማስተካከል ይጠበቃል። አንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎችም ቤተሰብ ተፈልጎ ያለመገኘቱን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥተው የማይሰሩ በመሆኑ ልጆች ከማሳደጊያ ወጥተው በቤተሰብ የሚቀላቀሉበትን ጊዜ ሲያረዝመው ይታያል ይላሉ።
አቶ ዳዊት ስለተቋሙ ሲናገሩም ቤተኒ ክርስቲያን አገልግሎት በጎ አድራጎት ድርጅት ከተቋቋመ ከ70 አመት በላይ የሆነው ሲሆን በኢትዮጵያ ከጀመረ 12 አመታት አስቆጥሯል። ተቋሙ ህጻናትና ቤተሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ በሶስት ፕሮግራሞች ላይ አንደኛ ቤተሰብ እንዳይፈርስና ህጻናት ለችግርና ለጎዳና ህይወት እንዳይዳረጉ ብሎም በፍቅርና በቤተሰብ ውስጥ እንዲያድጉ ለማስቻል የምግብ፣ የትምህርት፣ የህክምናና የድንገተኛ ድጋፍ ያደርጋል። በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቻቸው ጋር ማደግ ያልቻሉና በተለያዩ ማቆያዎች ውስጥ ያሉ ህጻናትን ከሴቶችና ህጻናትና ቢሮ ጋር በመተባበር ምትክ ቤተሰብ እንዲያገኙ ያርጋል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በሙከራ ደረጃ ያለውና በቅርቡ ወደስራ የሚገባበት ጊዜያዊ የአደራ ቤተሰብ ማገናኘት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ይህም በማቆያ ያሉትን ልጆች እስከመጨረሻውም ባይሆን ወደቤተሰብ እስኪመለሱ ድርስ በቤተሰብ ውስጥ እንዲቆዩ ማስቻል ነው።
ተቋሙ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰባቸው የተለያዩትን በተለይ ከአረብ ሀገራት የመጡትን ጨምሮ ከቤተሳበ ጋር የማቀላቀልና የቤተሰቡንና አቅም የማሳደግ ስራም እየሰራ ይገኛል። ከደቡብ ሱዳን ተፈናቅለው የመጡና በጋምቤላ ክልል ለተጠለሉ እንዲሁም ለተለያዩ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ችግር የተጋለጡ ቤተሰብ አልባ ህጻናት ስድተኞችም ድጋፍ ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት ለ32 ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን እስካሁንም ከ450 ባላይ ህጻናት ከማሳደጊያ ወጥተው ቤተሰብ እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል። ባጠቃለይ ከ7 ሺህ አምስት መቶ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 17/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ