የሽፋን ሥዕል እራሱን ችሎ እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሚሰጥባቸው የተለያዩ አገራት አሉ። በነዚያ አገራት ራሱን የቻለ የጥናትና ምርምር ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ይመረመራል፤ ይፈተሻል፤ ይተቻል፤ ይወደሳል። በአገራችን ግን ከዚህ የተለየ ነው። የሥነጽሑፍ መማሪያ መጻሕፍትም ገና ከዛው “ጭብጥ፣ ገፀባህሪይ፣ ግጭት . . .” ከሚሉት ከፍ ሲሉ ለማየት አልበቃንም። መጻሕፋዊ ሂሶችም እዛው መሸነጋገል ላይና ውስጥ ነው ያሉት። ዘርዝረን አንዘልቀውም።
አንድ የተዋጣለት የሽፋን ሥዕልን ለመንደፍ ተግባራት መካከል የመፅሀፉን አጠቃላይ ጭ ብጥ ወካይ መሆኑ፤
ሚስጢራዊነቱ፤ አሰልቺ አለመሆኑ፤ ቁልፍ የሆኑ የመጽሃፉ ይዘቶች ላይ ማተኮሩ፤ አንባቢ አእምሮ ውስጥ አንዳች ስሜት መፍጠሩ እንዲሁም የተለየ የማንበብ ጉጉት መፍጠር መቻሉ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ለዚህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናት ማድረግ፤ ባለሙ ያን ማማከር (ከተቻለም መጠቀም)፤ በተቻለ መጠን የሽፋን ሥዕሉን፣ ጽሑፉን/መልእክቱንና አጠቃላይ መጽሐፉ ከሚያቀብለው መረጃ ጋር የተጣጣመና ሚ ዛኑን የጠበቀ፤ የታሪኩ ወካይና ጠቋሚ እንዲሆን፤ ግልፅ ማድረግ፤ “ኢ-ልቦለድ ለአእምሮ፤ ልቦለድ ለልቦና” የሚ ለውን አለመርሳት፤ ማንበብ የማይችል ከሽፋን ሥዕሉ አንዳች መልእክትን እንዲረዳ ማድረግና የመሳሰሉት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡
ይህን መንገድ በተከተለ ባለሙ ያ የተሰራ ምስል/ሥዕል ለአይን አይጎረብጥም፣ አያጭ በረብርም። ፋታ ሰጪ፣ የንባብ ፍላጎትን ቀስቃሽና አመራማሪ ነው። ወይም ባለሙ ያዎቹ እንደሚ ሉት በሰዎች ላይ ያልተፈለጉ ስነልቦናዊ ችግሮችን አይፈጥርም።
የድርሰቱን መልእክት ወደ ንድፍ ለመቀየር ሲታሰብ በቅድሚ ያ ታሪኩን ተጨባጭ ማድረግ ተገቢ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ገፆች በተለያየ መንገድ የተገለፁ ሀሳቦችን በአንድ ገላጭ በሆነ ነገር መወከል ይገባል። ያ ይወክላል የተባለውን ጉዳይ እያሻሻሉ እያሳመሩና ይበልጥ ወካይ እንዲሆን እያደረጉ በመሄድ ወደ ትክክለኛው የሽፋን ሥዕል ማ ምጣት ይቻላል። የወካይ ሥዕሉ ቁጥር እያነሰ ወይም ወደ አንድ እየመጣ ሲሄድ የምንጠቀማቸው የቀለም አይነቶችና መጠኖችም ያንኑ ያህል ይቀንሱልናል፤ አሰራሩ አዋጭ ነው።
የመጻሕፍት ሽፋንንም ሆነ የጀርባ አስተያየት ለተለያዩ አላማዎች የሚጠቀሙ መኖራቸው አይካድም። የመጽሐፉን አጠቃላይ መልእክት ለማስተላለፍና የአንባቢን ፍላጎት ለማንቃት፤ ለመቀስቀስ፣ ገበያ ለመሳብ፣ የደራሲውን ወይም የሰአሊውን የግል ስሜት ለማንፀባረቅ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው። በበሳል ደራሲያን ዘንድ ግን የገበያው ጉዳይ ቀዳሚ ተተኳሪ አይደለም።
የመጽሐፍን የፊት ሽፋን ልክ እንደ ገበያ ተኮሮቹ ሁሉ ከመጻሕፍት መደርደሪያ አኳያ የሚመለከቱም አሉ። እንደ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች አተያይ መደርደሪያ ላይ ያሉ መጻሕፍት ቶሎ ብለው ስሜ ታችንን ሊስቡ፣ አይናችን ሊገቡ ይገባል፤ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው በሽፋን ሥዕሎቻቸው/ ምስሎቻቸው አማካኝነት ነው።
ይህ የሽፋን ሥዕልን ከፈጠራ ስራው እኩል የማየትና ለስራው መጨነቅና መጠበብ የቀረ ይመስላል የሚሉ አሉ። በተለይ አደጉ በሚባሉት አገራት የግል ህትመት ስራዎች፤ ማለትም የራሳቸውን ስራ ያለማንም እና ምንም ጣልቃ ገብነት እራሳቸው ጽፈው በራሳቸው ማተሚያ ቤት የሚ ያሳትሙ ና ለገበያ የሚ ለቁ ደራሲያን (self-published authors) በብዛት እየተፈለፈሉ መምጣት ሲሆን የፀሀፊዎቹ አላማ ም ለጥበብ መጨ ነቅ ሳይሆን ደራሲ መባል ላይ የተጣበቀ መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል። እንደውም ለአሁኑ ዘመን ምርጥ ስራ መታጣትና የሽፋን ሥዕል ጥበብ (brilliant book cover design) መዝቀጥ ምንጮች ናቸው የሚሏቸው እየበዙ ነው።
ማተሚያ ቤቶች አንድን ስራ ለማተም ከውስጥ ይዘቱ ባልተናነሰ ደረጃ ለውጭ ገፅታውም ዋጋ ይሰጣሉ። ካላማራቸው፣ ስራው ጥበብና ሀላፊነት ከጎደለው “እኛን አይመጥንም” በማለት ይመልሳሉ እንጂ ስለተከፈላቸው አይሰሩትም። ባለፈው ሳምንት እንዳየነው፤ እኛ አገር ያለው እውነታ ደራሲው በማተሚያ ቤቶችና አዟሪዎች ትእዛዝ ከመጽሐፉ ይዘት ውጪ መቀየሩን ነው። የሜ ጋ የፍቅር እስከ መቃብርን የፊት ገፅ ለማስታወቂያ ሰሌዳነት መጠቀሙ ም ሌላው የማተሚያቤቶች አጉራ ዘለልነት አንዱ መገለጫና ፀረ ጥበብ አቋም ነው።
“አንድን መጽሐፍ በሽፋኑ አትመዝነው” የሚለው በ“No matter how the saying goes, we all judge books by their covers” /”ምንም እንኳን መፅሃፍን በሽፋኑ አትመዝነው የሚል አባባል ቢኖርም መጽሃፎችን በሽፋናቸው መዝነው” በሚል የተተካ መሆኑን መ ገንዘብ ጠቃሚ ነው። ጥንቱንም ቢሆን የዚህ አባባል ኣላማ ንባብን ማበረታታት እንጂ የሽፋን ሥዕልን ማጣጣል አይደለምና አረዳዳችን ስህተት ነበረበት ማለት ይቻላል።
የሽፋን ሥዕል ሲሰራ ምን አይነት ቀለም መጠቀም ጥሩ ነው? የሚል ብዙ ጊዜ የሚ ነሳ የፀሀፊዎች ጥያቄ/ክርክር አለ። እዚህ ላይ የቀለም አይነቶችን በመጥቀስ “የተሻለው ይሄ ነው፤ ያን ሳይሆን ይህን ምረጥ።” ማለቱ ተፅእኖ የመፍጠር ያህል ሆኖ ስለሚቆጠር ዝምታው ይመረጣል።
ለመሆኑ የፊት ሽፋን ለምን አስፈለገ? ለምንስ ይህንን ያህል እንድንጨነቅበት ይፈለጋል? ለሚለው “Book covers matter” ከሚሉት ወገኖች ፓንቶስ እንዲህ ይላሉ። ለሽፋን ሥዕል ትኩረት አለመስጠት ሞኝነት ነው። በተለይ ፀሀፊው አዲስ ከሆነ የተዋጣለት የሽፋን ሥዕልን ይዞ ብቅ ይል ዘንድ ይገደዳል (ይህ የአዳም ረታን “ማህሌት” ያስታውሰናል)። ይህን ካላደረገ ወደ ሰው ልብ ውስጥ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት ሁሉ ዋጋ ቢስ ሆኖ መቅረቱን ሊያውቅ ይገባል። እንደ ፓንቶስ አባባል ነባር ፀሀፊዎችም ባህልን፣ እይታዊ ጥበብን፣ ምስላዊ ገለፃን፤ አካባቢያዊ ሁኔታን፣ የአንባቢን ስነልቦናዊ ባህርይን ወዘተ ግምት ውስጥ አስገብተው የማይሰሩ ከሆነ የእነሱም ነገር አበቃለት ማለት ነው።
አጥኝዎቹ እንደሚሉት የሽፋን ሥዕል የመፍጠሩ ስራ (Cover creation) የመምጫው ሰአት ከሁሉም መጨረሻ፤ በኋላ ነው። “መጨረሻ” ስንል ከመጨረሻው እርማት በኋላና ስራው ወደ ህትመት ከመሄዱ በፊት ማለታችን ነው። ከዚህ ደረጃ በፊት ስለፊትም ኋላ ሽፋን ሥዕል ማሰብ ተገቢ ነው የሚል አንድም ምክንያት የለም። ገና እየፃፉት ያለው ጉዳይ መሀል ላይ ሳይደርስ ስለ ሽፋን ሥዕል የሚጨነቁ ሰዎች መኖራቸው እርግጥ ሲሆን ትርፋቸው ኪሳራ መሆኑን ከወዲሁ ሊያውቁት ይገባል።
የሽፋን ሥዕል ሲታሰብ፣ የጀርባ-ፊት ሽፋን፣ አጠቃላይ ገፅ ቅምጠት፣ ስእሎች (ካሉ)፣ የተፃፈበት የፊደል መጠን እና ሌሎች ሁሉ ታሳቢ መደረግ ያለባቸው መሆኑ ሁሌም ይነገራል። እነዚህን ልብ ማለት ከእነዚህ በተፃራሪነት የቆመ የፊት-ኋላ ሽፋን ስእል እንዳይከሰት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በጉዳዩ ላይ በርካታ ምርምሮችን ያደረጉትና ግንዛቤን የሚያስጨብጡ መጻሕፍትን ያሳተሙት ካርላ ላንት እንደሚሉት ከሆነ ወደ ሽፋን ሥዕል ተግባር ዝም ተብሎ አይሮጥም። አንድ የመጽሐፍ ሽፋን ሥዕል ሊሰራ ያሰበ ሰው ከመስራቱ በፊት ከ50 ያላነሱ የሌሎች ከሱ ርእሰ ጉዳይ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ስራዎችን የሽፋን ሥዕሎች መመልከት አለበት፡፡
“ልክ መጽሐፍዎትን ጽፈውና አስፈላጊውን የአርትኦት ተግባርዎን እንዳከናወኑ ወደ የሽፋን ሥዕል ምርምር ስራዎ ይሂዱ። የምርምር ስራዎትን በሚገባ ማከናወኖትን ካረጋገጡና የሚፈልጉትን ውጤት ካገኙ ተሳካ ማለት ነው። አሁን የመጽሐፍዎትን የሽፋን ሥዕል ዲዛይን ስራዎን መጀመር ይችላሉ።” የሚለውም በብዙዎች የሚጠቀስላቸው የተመራማሪዋ ካተሊን መልእክት ነው።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 17/2012
ግርማ መንግሥቴ