ለአካባቢው እንግዳ ብሆንም ከተማዋን ለማየት አስጎብኝ አላስፈለገኝም፡፡በከተማዋ ስዘዋወር አይኔ አስፓልት ዳር ላይ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተከለለ ቤት ላይ አረፈ፡፡ቤቱን የሞሉት ወጣቶች ነበሩ፡፡ምን እየሰሩ እንደሆነ ቀድሞ የሚታየው የፑል መጫወቻ ያሳብቃል። ወደ ውስጥ ዘልቄ ገባሁ፡፡ ፑል ከሚጫወቱትና መጫወቻውን ከበው በተመልካችነት ከታደሙት ሌላ ካርታ የሚጫወቱ ወጣቶች ጥግ ይዘዋል። ተማሪዎችም የደንብ ልብሳቸውን እንደለበሱ ጎራ ይላሉ፡፡ ጨዋታውን ከምትቆጣጠረው ወጣት በስተቀር ሴቶች አልነበሩም፡፡
የወጣቶቹን ጨዋታ እያየሁ በአዕምሮዬ አንዳንድ ነገሮች ይመላለሱ ነበር፡፡የፑልና ካርታ ጨዋታ አንዱ ጊዜ ማሳለፊያ ወይም መዝናኛ ቢሆንም ከዚህ ሌላ ወጣቱ ጊዜውን የሚያሳልፍበት መዝናኛ ይኖር ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ ወጣቶቹ በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ምንስ ያስደስታቸዋል? በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ ቆይታዬ የታዘብኩትና ያነጋገርኳቸው ወጣቶችም ሀሳብ እነሆ፡፡
በከተማው ፑል ስታጫውት ያገኘኋት ወጣት ትርንጎ አበራ እንዳጫወተችኝ በ2007ዓም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ ዩኒቨርስቲ ብትገባም በተለያዩ ምክንያቶች አቋርጣለች፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስበው ያለትምህርትና ያለሥራ የባከነው ጊዜ ይቆጫታል፡፡ ቁጭቱን ለመመለስ በማታው ክፍለጊዜ እየተማረች ነው፡፡በመሆኑም ቀን ፑል በማጫወት ማታ በትምህርት ጊዜዋን ታሳልፋለች፡፡
ወጣት ትርንጎ እንደምትለው በሥራ ሳይደክሙ ለመዝናኛ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ አይደለም። ‹አዕምሮዬ በሥራ አልደከመም ስለዚህ ለመዝናኛ ትኩረት አልሰጠሁም› በማለት ሥራን ለማሸነፍ ቅድሚያ መስጠቷን ትገልጻለች፡፡ በግላቸው ፊልም እና የአውሮፓ እግርኳስ የሚያሳዩ ፊልም ቤቶች በከተማዋ ቢኖሩም ተጠቅማ አታውቅም፡፡ ኳስ ሜዳ መኖሩን እንጂ የጨዋታ መርሃግብር ተከታትላ ለማየት አልሞከረችም። ፑልም ታጫውታለች እንጂ አትጫወትም፡፡ በዞኑ ዙሪያ እንደ ላልይበላ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም ወደ መዳረሻዎቹ የመሄድ ልምድም የላትም፡፡እዚህ ላይ ፍላጎት በማጣት ሳይሆን፣ለጉዞ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት የገንዝብ አቅም ባለመኖሩ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡
አልባሌ በሆነ ቦታ የሚውል፣በደባል ሱስ ላይ የተጠመደና የአካባቢ ሰላምን በማወክ ችግር የሚፈጥር ወጣት በከተማው ይስተዋል እንደሆነም ለወጣት ትርንጎ አንስቼላት በአካባቢው እንደጫትና ሲጋራ በማዘወተር ጎልቶ የወጣ ነገር እንደሌለ ነው ምላሽ የሰጠችው፡፡ወጥቶ ለመግባት ስጋት የሆነ ወጣት በአካባቢው አለመኖሩንም ተናግራለች።
የተዘጋጁ የልብስ መሸጫ ውስጥ ከታላቅ ወንድሙ ጋር ሲሰራ ያገኘሁት በቀበሌ ዜሮ አንድ ውስጥ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሀየሎም ደባሽ በፍሳሽ አወጋገድ(ሳኒተሪ)በ2010ዓም በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡በተማረው ሙያ ሥራ እስኪያገኝ ወንድሙን ለማገዝ በልብስ መሸጫው ውስጥ በመስራት ላይ እንደሆነ ነው የነገረኝ፡፡
ላለፈው አንድ አመት በልብስ መሸጫ ሱቁ ውስጥ ሲሰራ የተለያዩ ደንበኞችን ባህሪ ችሎ እንደሚፈልጉት ማስተናገድ፣ሳምንቱን በሙሉ ከጠዋት እስከ ምሽት በሱቁ ውስጥ መቆየትም ትዕግሥት እንደሚጠይቅ ከሥራው ተምሯል፡፡በዚህ ሥራ ላይ መሆኑ መጽሐፍ እንዲያነብ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለታል፡፡አንዱ መዝናኛውም ሆኗል፡፡ ፊልሞችንም ያያል፡፡
ወጣት ሀየሎም ወንድሙ ሲቀይረው ነው እረፍት የሚኖረው፡፡በዚህ ጊዜም በይነመረብ (ኢንተርኔት)አገልግሎት ባለበት አካባቢ በመሆን ሻይ እየጠጣ የውጭ መረጃዎችን በማየት ለሰአታት ያሳልፋል፡፡ አንዳንዴም ‹የስምኃይላ› ወጣቶች ማዕከል ውስጥ መጽሐፍ በማንበብ ንጹህ አየር ይወስዳል፡፡በተማረው ሙያ ሥራ እስከሚያገኝም በንግድ ውስጥ እንደሚቆይ ገልጾልኛል፡፡
ለመንፈሳዊ ጉዞ ዝግጅት ሲያደርግ ያገኘሁት ወጣት ደረጀ በላይ የገዳማት ጉዞ ዝግጅት ሲኖር የተለየ ነገር ካልገጠመው በስተቀር እንደማይቀርና በጣም እንደሚያስደስተው አጫውቶኛል፡፡የእረፍት ጊዜውን በቤተእምነት ማሳለፍ ይመርጣል፡፡አንዳንዴ ደግሞ ‹የስምኃይላ› ወጣቶች ማዕከል ውስጥ ከረንቦላ እና የጠረጴዛ ቴኒስ በመጫወት ያሳልፋል፡፡
በተለየ ሁኔታ የሚገለጽ መዝናኛ በአካባቢው አለመኖሩን የሚናገረው ወጣት ደረጀ የአካባቢው ወጣቶች በአብዛኛው ጠላ ቤት ውስጥ እንደሚታዩ ይገልጻል፡፡ ጠላ ቤት መታየት እንደመልካም ነገር የሚጠቀስ ባይሆንም እንደጫትና ሲጋራ ባሉ ደባል ሱስና በመጥፎ ባህሪ የሚገለጽ ወጣት በአካባቢው አለመኖሩ ግን ትልቅ ዋጋ ለሚሰጠው ሰላም ጠንቅ ነው የሚባል ወጣት በአካባቢው አለመኖሩ ያስደስተዋል፡፡
ወጣት ደረጀ እንደነገረኝ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በተማረው ዘርፍ በ2009 ዓ.ም አምስት ሆነው ተደራጅተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡በሥራው ደስተኛ ነው፡፡በሙያው ትልቅ ደረጃ መድረስም ይፈልጋል፡፡ፍላጎቱን ለማሳካት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ያምናል፡፡
በከተማው በቅርብ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ‹ስምኃይላ› የወጣቶች የመዝናኛ ማዕከልም ጎራ ብያለሁ። በውስጡ የሚገኙት ሀገር በቀል ዛፎች ነፋሻ አየር እና ፀጥታ ለሚፈልግ ሰው ምቹ ናቸው፡፡ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ለሚፈልግ ጂም፣የከረንቡላ መጫወቻ፣የተደራጀ ባይሆንም የንባብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
‹የስምኃይላ› ወጣቶች ማዕከል ሰብሳቢ ወጣት ዓለማየሁ ታደሰ እንደነገረኝ 10 ሆነው ተደራጅተው ነው ማዕከሉን ማስተዳደር የጀመሩት፡፡ የማዕከሉን ተፈጥሮአዊ ይዘት ለመጠበቅ ችግኞችን በመትከል አባላቱ እንክብካቤ አድርገዋል፡፡ አባላቱ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚ ለመሆን እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ለወጣቱ የጊዜ ማሳለፊያ በማመቻቸት የአካባቢ ጥበቃ ሥራም በማከናወን ሁሉን አቀፍ ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በላይ ውብ ማድረግ ቢቻል አባላቱም የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ለከተማው ወጣቶች ጥሩ የጊዜ ማሳለፊያም ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ለመታዘብ ችያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 / 2012
ለምለም መንግሥቱ