የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር ሀብት አሰባስቦ ለስድስት መቶ ሺ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ አሟልቷል። ሶስት መቶ ሺ ተማሪዎችን ደግሞ ቁርስና ምሳ እየመገበ ነው።እገዛው ዘለቄታ እንዲኖረው ለማድረግም ከሰሞኑ ኤጀንሲ ለማቋቋም በካቢኒ ደረጃ ውሳኔ አስተላልፏል።
የኛ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬም አይደል … ኤጀንሲ ይቋቋማል መባሉን ተከትሎ ምገባ ፕሮግራሙ ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅ እየገለጹ “የበጀት ብክነት ነው” እያሉ የሚደሰኩሩ ተቺዎች ብቅ ብለዋል።እኔ የምለው … ከዚህ ጉዳይ በላይ ትኩረት የሚሻ ምን ነገር አለ ? እነዚህን ሰዎች ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ጋር ሆኜ “ቀጠሮ ይሰጣል ረሃብ?” ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ።
አንደበት ተርፏችሁ እንደሁ፣ ሳትነግሩን ከምትቀሩ
ካስቻላችሁ ተናገሩ።
ቆሽት-ሲቃው ሲያጣጥር ፣ ሰቀቀኑን ሳያጋግል
እስትንፋስ ስልምልም ሳትል
ቀጠሮ ይሰጣል ረሃብ? ለስንት ቀን ለስንት ያህል?
ስንት ሰዓት ነው የራቡ አቅም?
በትችቱ ከማዘንና ከመቆጣት በፊት ተቺው ማን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።በተደራራቢ ምሳ እቃ ሶስት አይነት ምግብ ተቋጥሮለት ፣ ውሃ በልዩ ኮዳ ተሞልቶለት ትምህርት ቤት የሚላክ ልጅ፣ እህት ወይም ወንድም ያላቸው ሰዎች ከሆኑ ልክ ናቸው።የትምህርት ዘመኑን አራት ቦታ በሸነሸኑ ቅንጡ የግል ትምህርት ቤቶች በተርም አራት ሺ ብር እየከፈሉ፤ በሰዓት 250 ብር የሚከፈለው አስጠኚ ቀጥረው ልጆቻቸውን የሚያስጠኑ ወላጆች ከሆኑ ትክክል ናቸው።ምክንያቱም ረሃብን አያቁትማ ! እንኳን እነርሱ የወገኖቹ ረሃብ አስጨንቆት መንፈሱ የታወከበት ሎሬት ስሜቱን ለተደራሲው ባጋባበት ግጥሙ እንዲህ ሲል ረሃብን እንደማያውቀው ገልጿል።
…ለኔ ብጤማ ትርጉሙ
የሁለት ፊደል ድምፅ ነው ፣ ‘ራብ’ የሚሉት ከነስሙ
እንጂ የኔ ብጤውማ
የት አውቆት ጠባዩንማ፣
ብቻ ሲነገር ይሰማል
ይህንን ሁለት ፊደል ቃል፡…
ቃሉማ ያው በዘልማድ፣ ይነገራል ይለፈፋል
ይተረካል ይዘከራል
ይደጋገማል ይተቻል
እንጂ እንኳን ጠባዩንና ፣ የራብ ዕድሜውን የት ያውቃል?…
ተቺዎቹ አልተራቡም።የመንግስት ትምህርት ቤቶችን የዛሬ መልክ አልተመለከቱም።መምህራን ከክፍል ወደክፍል መሸጋገር ሳይችሉ ቀርተው ከሚወድቁት ይልቅ ቁርስና ምሳ ባለመብላታቸው መቆም ተስኗቸው በሚወድቁ ተማሪዎች እንደሚብሰለሰሉ አያውቁም።የቋጠሩትን ምሳ ለተማሪዎቻቸው እንደሚያካፍሉ ፣ ባስ ሲልም ምሳ እቃቸውን ሰጥተው በተማሪዎቻቸው ፋንታ ጦማቸውን እንደሚውሉ አላዩም።ክፍል ውስጥ ካለ ጫጫታ በላይ የሆዳቸው ውስጥ ጩኸት ሰላም የሚነሳቸውን ህጻናትን ስቃይ አልተረዱም።በእረፍትና ምሳ ሰዓት በመጫወት ፈንታ ጥግ ይዘው ሆዳቸውን የሚያሹ ህጻናትን አይተው አይናቸውን አላሹም።አሊያም የህጻናቱን ሰቆቃ ተረድታ ከዓመታት በፊት የምገባ መርሃ ግብርን ሀ ብላ የጀመረችው ፍሬያለም ሽባባው ከጓደኞቹ እንዳያንስ ባዶ ምሳ እቃ ስለሚቋጠርለት ልጅ የጻፈችውን ታሪክ አላነበቡም።ስለዚህ ሎሬቱ
… ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ . . . .
የጣር ቀጠሮው ስንት ነው
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው
ስንት ሰዓት ነው ሰቆቃው ፣ ስንት ደቂቃ ነው ጭንቁ
እስቲ እናንተ ተናገሩ ፣ ተርባችሁ የምታውቁ … እያለ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መልስ መስጠት አይችሉም።
የዛሬ ልጆች በሁለት ሀዲዶች ላይ ነው የሚጓዙት።በፌስ ቡክ መንደር ታሪካቸውን ለመተረክ እንደበቁት “የዘጠናዎቹ ልጆች” አንድ ላይ በመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ አይማሩም።በዘጠናዎቹ ጥቂቶች ሊሴ ገብረማሪያምና ሚሽነሪ ትምህርት ቤቶች ከመማረቸው በቀር አብዛኛው ተማሪ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነበር የሚማረው።አሁን ግን ክሬዚ ደይ ፣ ከለር ደይ ፣ ቤቢ ደይ ፣ ከረቫት ደይና ኦልዲስ ደይን ለማክበር ከፍተኛ በጀት በሚመደብባቸው የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር በመንግስት ትምህርት ቤት ከሚማሩት ጋር ይስተካከላል።
በምሳ ሰዓት በኪሳቸው የያዟትን ቆሎ የሚቀምሱና ተደራራቢ ምሳ እቃዎቻቸውን የሚያርሱ ልጆችን አንድ የሚያደርጋቸው “ተማሪዎች” የሚለው ስም ብቻ ነው።የተቋጠረላቸውን ምግብ ጨርሰው ባለመብላታቸው በወላጆቻቸው በሚቀጡና የሚበሉት አጥተው ረሃብ በሚቀጣቸው ተማሪዎች መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ።
ተቺዎቹ “በመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩት እነማን ናቸው?” ተብለው ቢጠየቁ በጥቅሉ የድሃ ልጆች የሚሉ ይመስለኛል።አነስተኛ ገቢ የሚያገኙ ወላጆች ያሏቸው ደሀ አደጎች ፣ ጸሐይና ዝናብ የሚያጫውታቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ከወላጆቻቸው ጋር የሚለምኑ ታዳጊዎች ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ጥገኞች ፣ ከገጠር በገዛ ዘመዶቻቸው ለግርድና የተመለመሉ ተበዝባዦች ፣ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት ሊስትሮ ሲሰሩ ቆይተው የሚያረፍዱ ተሯሯጮች ፣ ምሽቱን እንጀራና ሽልጦ ከሚሸጡ እናቶቻቸው ጋር በየጉሊቱ ብርድ የሚጠብሳቸው ኮርማታዎች እና እኩለ ሌሊት ድረስ በየመጠጥ ቤቱ እየዞሩ ቆሎ ፣ እንቁላልና ማስቲካ የሚሸጡ ከዕድሜቸው በላይ ኃላፊነት የተሸከሙ ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ልብ አይሉም።
ጥቂት ደጋግ ኢትዮጵያውያን ለእነዚህ ልጆች ለዓመታት አቅማቸው በፈቀደ መጠን ቁርስና ምሳ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።ተቺዎቹ ደጋጎቹን የማናገር ዕድል ቢገጥማቸው ከሚመገቡት ተማሪዎች ቁጥር ይልቅ የእነርሱን ትራፊ ለመመገብ ተሰልፈው የሚጠባበቁ ተማሪዎች እንደሚበረክቱ ፤ ተመጋቢዎቹም ለተሰለፉት ጓደኞቻቸው ብለው ሳይጠግቡ እንደሚያስተርፉ ተገንዝበው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክቱ ነበር።
እግር ጥሏቸው በመንግስት ትምህርት ቤቶች ቢገኙ ተማሪዎች ከሚካሰሱባቸው ጉዳዮች አንዱ ምሳ እቃ መቀማት መሆኑን ያስተውሉ ነበር።ወላጆቻቸው ምሳ የቋጠሩላቸው ተማሪዎች ምሳ እቃቸውን እስኪያጋምስ ጠብቀው ፣ ቀምተዋቸው ረሃባቸውን ካስታገሱ በኋላ የሚቀጡትን የትኛውንም አይነት ቅጣት አሜን ብለው የሚቀበሉ ፤ ለራሳቸውና ለምሳ እቃው ባለቤቶች ሆድ ዕኩል የሚጨነቁ ታዳጊዎችን ይመለከቱ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከወላጆቻቸው እንኳን ተገቢውን ትኩረት የማያገኙ ተማሪዎች ለሚበዙባቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ መመስገን እንጂ መወቀስ የለበትም።የምናወራው በየዕለቱ በኮሙዩኒኬሽን ደብተር ከመምህራን ጋር ስለልጆቹ ሀሳብ ስለሚለዋወጥ ወላጅ ስለሞላባቸው የግል ትምህርት ቤቶች ሳይሆን፤ በዓመት አንድ ጊዜ (ከሞላላቸው) ልጆቻቸው ማለፋቸውንና መውደቃቸውን የሚገልጸውን ካርድ ለመቀበል ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ወላጆች ስለሚበዙባቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች ነው።
ተቺዎች ድጋፉ የሚደረገው ‹‹የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው ››ሲሉ ይከሳሉ።የህዝብን ችግር በመፍታት የሚገኝ የትኛውም አይነት ትርፍ ቅዱስ ነው።ህዝብን ጠቅመው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደክሙ ፖለቲከኞችን ያብዛልን ! ህዝብን ከህዝብ በማናከስ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ደፋ ቀና የሚሉ ፖለቲከኞች በበረከቱበት አገር ልከኛ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ መንገድ የቱ እንደሆነ ቢያምታታ አያስገርምም።
መርሃግብሩ ለምን በአዲስ አበባ ብቻ ይወሰናል ብለው የሚጠይቁም አሉ።ጥያቄው የሚቀርበው የችግሩን ስፋት ከግምት በማስገባት ከሆነ መልካም ነው።ነገር ግን በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስም የሚመለመል ልምጭ ከሆነ ደግ አይደለም።አንድ መልካም ነገር ሳይጀመር ከሚቀር በየትኛውም የዓለም ጥግ ቢጀመር ይሻላል።በመጀመሩ ሌሎች ተመልክተውት አቅማቸው በፈቀደ መጠን እንደ ነባራዊ ሁኔታቸው እያሻሻሉ ያስፋፉታል።
በበኩሌ የምገባ ፕሮግራሙ ከትምህርት ቀናት ውጭ ቅዳሜና እሁድንና የክረምት ወራትንም እንዲጨምር እጠይቃለሁ።ወላጆች ይህ ጉዳይ ያስጨንቃቸዋል።መሀል ጨርቆስ በሚገኝ አንድ የመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ አርቲስት ቻቺ ታደሰ በምትመራው የምገባ ፕሮግራም ተሳትፌ አውቃለሁ።ዩኒፎርም ፣ የትምህርት ቁሳቁስና አልባሳት ተሟልቶላቸው በምገባ ፕሮግራሙ የሚካተቱ 39 ተማሪዎች ከአጸደ ህጻናት ከተመረጡ በኋላ የመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የተማሪዎቹ ወላጆችና አሳዳጊዎች ተጠሩ።ሁሉም በሆነው ነገር እጅግ መደሰታቸውን እየገለጹ አመሰገኑ።በመጨረሻ ልጇ በምገባ ፕሮግራሙ የታቀፈላት እናት አንድ ጥያቄ ጠየቀች።“ልጄ ቅዳሜና እሁድም እየመጣ ይመገባል ?” አርቲስቷ ለጊዜው በትምህርት ቀናት ብቻ እንደሚመገቡ ገለጸች።በዚህ ጊዜ እናቲቱ “እንግዲያውስ በቃ ለልጄ ብዙ ምግብ አትስጡት ፤ በሰፊው ከለመደ ቅዳሜና እሁድ ከየት አምጥቼ እመግበዋለሁ ? ረሃቡን አይችለውም” አለች።የቻቺ አይኖች ተከፈቱ ፣ እንቧ።
በተጨማሪም ተማሪዎቹ ከዩኒፎርምና የትምህ ርት ቁሳቁስ ባለፈ ጫማ እንዲያገኙ ቢደረግ መልካም ነው።በበጋ ወራት እጅግ በሚሞቅ ኮንጎ ጫማ የሚቀቀሉና ዓመቱን ሙሉ ኤርጌንዶ በማድረጋቸው ተረከዛቸው የሚሰነጣጠቅባቸውን ተማሪዎች ችግር መቅረፍ ይቻላል።
ከንቲባውንም ሆነ ከተማዋን እየመራ ያለውን ገዢ ፓርቲ መቃወም መብት ነው።ነገር ግን መቃወም መልካም ነገርን ጭምር ላለማየት ጨርሶ አይንን መጨፈን መሆን የለበትም።ቋሚ ተቃዋሚና ቋሚ ደጋፊ መሆንን የጽናት ምልክት አድርጎ የማየት ልማዳችንን መጣል አለብን።እየደገፉ መንቀፍ፤ እየተቃወሙ ማድነቅ ወላዋይነት አይደለም።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 15/2012
የትናየት ፈሩ