ከሲዳማ ቡና ጋር ያለፉትን አራት ዓመታት የቆየው እና ዘንድሮ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃን በስድስት ግቦች እየመራ የሚገኘው አዲስ ግደይ ስለ እግር ኳስ ህይወቱ ፣ ስለዘንድሮው የውድድር ዓመት የሲዳማ ቡና ጉዞ እና አጠቃላይ በሊጉ ስላለው ዕቅድ ጋር በተያያዘ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የእግር ኳስ ህይወቱን እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሰፈር ውስጥ እንደጀመረ የሚናገረው አዲስ ግደይ ተወልዶ ያደገው በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ ነው። በአጋሮ በፕሮጀክት ውድድር ላይ ተሳትፎ የነበረው አዲስ በመቀጠል የክለብ ህይወቱን ለስልጤ ወራቤ በመጫወት ጀምሯል። ከስልጤ ወራቤ ጋር በብሔራዊ ሊጉ የሦስት ዓመት ቆይታን በማድረግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲዳማ ቡና አምርቷል። በሲዳማ ቀስ በቀስ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት አሁን ላይ የቡድኑ አምበል እና ወሳኝ ተጫዋች እስከመሆንም ደርሷል። ዘንድሮም እስከስምንተኛው ሳምንት ቡድኑ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በእያንዳንዱ ላይ ጎል በማስቆጠር በስድስት ግቦች ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል።
ከብሔራዊ ሊግ እንደመጣህ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ችለካል፤ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰልፈህ ስትጫወት አልከበደህም?
ልክ ነው በእርግጥ ከታችኛው ሊግ ከፍ ባልክ ቁጥር ጫናውም እንደዛው ነው። እኔም ስመጣ የተወሰነ ፍራቻ ነበረኝ ፤ ነገር ግን ማድረግ እንደምችል በራሴ አምን ነበር። ግን ዕምነቱ እንዳለ ሆኖ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ መኖሩ አይቀርም። ፈርቼ ነበር። ግን ያ ፍራቻዬ መጥቼ ሊጉን ከተቀላቀልኩ በኋላ ብዙም ከእኔ ጋር አልቆየም። በአጋጣሚም በወቅቱ ዕድለኛ ነበርኩ። እኔ ሲዳማ ቡና ስመጣ ብዙ ጥሩ እና ነባር ተጫዋቾች ስለነበሩ የእነርሱ እገዛ ለኔ እጅግ የተለየ ነበር። የሚነግሩኝን ነገር እሰማለሁ፤ ከኔ በጣም የተሻለ ልምድም ስላላቸው። እኔም ለመቀበል ራሴን ክፍት አድርጌ ስለነበር ራሴ ላይ በደንብ የሚታይ ለውጥ ነበር።
ከአራት ዓመት በፊት በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አማካይኝነት ሲዳማን ሰትቀላቀል አከራካሪ ጉዳዮች ነበሩ ይባላል። በተለይ የውል ዓመቱ መርዘም አጨቃጫቂ ነጥቦች ነበሩት ይባላል። ስለጉዳዩ ብትነግረን…
እንዳልከው ብዙ አጨቃጫቂ ሊመስል ይችላል። ከታች ስትመጣ ላይኛው ሊግ ላይ ዕድሉን ማግኘት ነው የምትፈልገው። አራት ዓመት፤ ሦስት ዓመት የሚሉት ነገሮች ጥያቄ አይሆኑብህም። አንተ ራስህን በዛ በምታልመው ውድድር ላይ ማየት ብቻ ነው የምትፈልገው እና በጊዜውም የኔ ፍላጎት ያ ነበር። ራሴን በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ማብቃት፤ ከዛ ባለፈ አራት እና ሦስት ዓመት የሚለው ነገር ለኔ ጉዳዬ አልነበረም ፤ እንጂ ያንን ነገር ሳላውቅ ወይንም ተጭበርብሬ የፈረምኩበት ሁኔታ አልነበረም። በፍላጎቴ እና በፈቃዴ የሆነ ነገር ነው። በርግጥ ሲባል እሰማለሁ፤ ሆኖም ሁሉም ሰው በዚህ ቢረዳው ጥሩ ይመስለኛል።
ያንተ ወሳኝ ተጫዋችነት እንዳለ ሆኖ፤ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ቡድናችሁ ውጤታማነቱ ተቀዛቅዞ ነበር። ላለመውረድም ሲጫወት አስተውለናል እነዚያን ጊዜያት እንዴት ታስታውሳቸዋለህ ?
ሲዳማ ቡና ከመጣው ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው በኳሱ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ አይቻለሁ፤ ከሻምፒዮንነት ውጪ። ሊጉን መምራት ችለናል፣ የመውረድ አደጋ ውስጥ ገብተናል ፣ መሃል ላይ ውጤታችን ወደዛ ወደዚህ የሚልበት ወቅትም ላይ ደርሰናል። ይህ ደግሞ የእግር ኳስ አንዱ ገፅታ ነው። በእርግጥ ግን ሁሉም ሰው ሥራውን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት። የኔ ሥራ ለቡድኔ ጎል ማስቆጠር ከሆነ ለኔ ማስቆጠር ሥራዬ ነው። በግል እኔ ውጤታማ ነኝ። እንደ ቡድን ግን ውጤታማ ልንሆን አንችልም። እንደተባለው አንዳንድ ችግሮች ገጥመውናል። ለምሳሌ አምና ነጥብ እስከመቀነስ ደርሶ ነበር። ያም የሆነው በእኔ ምክንያት ነው። አምስት ቢጫ በወቅቱ የተመለከትኩት እኔ ነበርኩ። እኔ ሲዳማ ቡና ከመጣው ከፍተኛ ጫና ውስጥ የገባንበት ጊዜ ነበር። ያን ሁሉ ችግርም አልፈን አሁን ላለንበት ደርሰናል። አሁን እንግዲህ ያለፉት ሦስት እና ሁለት ዓመታት ብዙ ነገር አስተምረውን አልፈዋል። አሁን ጅማሬያችን ጥሩ ነው፤ ያለፉትን ዓመታት ስህተቶች ላለመድገም የተሻለ ነገር አድርገን ሲዳማ ቡናም ወደተሻለ ውጤት ገብቶ እንዲጨርስ አሁንም ከጎደኞቼ ጋር የምችለውን ለማድረግ ወደ ኋላ አልልም።
ሲዳማ ዘንድሮ ጥሩ አጀማመር አድርጓል። ያንተን ያህል ደግሞ በዚህ ዓመት ቡድኑን የሚታደግ ተጫዋች አልታየም። እስከአሁንም በፕሪምየር ሊጉ ስድስት በጥሎ ማለፉ ደግሞ ሁለት ግቦች አሉህ። ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ስለመጨረስ ምን ታስባለህ?
እንደቡድንም በግሌም የዘንድሮውን ፕሪምየር ሊግ በጥሩ ሁኔታ ጀምረናል። በስድስት ጨዋታ ስድስት ጎል አስቆጥሬያለሁ፤ አሁንም እቀጥላለሁ። እኔ ወደ ሜዳ የምገባው ሥራዬን ለመስራት ነው ፤ ሥራዬ ደግሞ ጎል ማስቆጠር ነው። ዋነኛው ሥራዬን ስሰራ ጎን ለጎን ደግሞ ሌሎች የምሰራቸው ነገሮች ይኖራሉ። መጀመሪያ የማስቀድመው ቡድኔን ነው። ቡድኔ የሚሰጠኝን ኃላፊነት በአግባቡ ስወጣ የቡድኑ ድል ማለት የኔ ነው። የኔም ስኬት ከቡድኔ ጋር የተያያዘ ነው። ቡድኔ አስደሳች ነገር ካልገጠመው እኔም ልደሰት አልችልም። ከኔ ውጪም ጎል ማስቆጠር የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ። ብዙ ጊዜ ሲዳማ ቡና የአዲስ ግደይ ጥገኛ ነው የሚባለው ነገር እኔን አያስማማኝም። በእርግጥ በነዚህ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ጎል እኔ ልሆን እችላለሁ እያስቆጠርኩኝ ያለሁት። ነገር ግን ሌሎችም ማስቆጠር የሚችሉ ታዳጊዎች እና ነባር ተጫዋቾች አሉ። ከአሁን በኋላ በሚኖሩን ጨዋታዎችም የቡድን ጓደኞቼ ጎል አስቆጥረው ሲዳማ ቡና የኔ ጥገኛ እንዳልሆነ እንደሚያሳዩ አስባለሁ።
ካንተ ግብ አስቆጣሪነት ውጪ የክለባችሁን የዘንድሮው ጉዞ እንዴት አየኸው ?
ቡድናችን በዝውውሩ ብዙም እንቅስቃሴ አልነበረውም፤ ደካማ ነበር። ዝውውሩ ላይ በነበረን ተሳትፎ የመጡት አብዛኛዎቹ ታዳጊ ተጫዋቾች ናቸው። በዝግጅት ወቅት ደግሞ እኔ አብሬያቸው አልነበርኩም፤ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ነበርኩ። ረጅም ጊዜም እነሱ ሲሰሩ አብሬያቸው ለመስራት አልታደልኩኝም። ሆኖም መረጃ ስንለዋወጥ ያለው ነገር ጥሩ እንደሆነ ነበር የሚነግሩኝ፤ መጥቼ ከተቀላቀልኩም በኋላ ያየሁት ያንን ነው። በውስጤ ፍራቻ ነበር። ብዙ ክለቦች ቡድናቸውን እያጠናከሩ ነው ተጫዋቾችን እያስመጡ ነው የኛ ቡድንስ ? የሚለውን ጥያቄ ሳስበው ፍራቻ ነበረኝ። አብሬያቸው መስራት ከጀመርኩ በኋላ ግን ፍላጎታችንን እና አቅማችንን ሳየው የኛ ቡድን ከማንም ያላነሰ መሆኑን ተረድቻለው። አሁን ላይ ያለውም ውጤት ይገባዋል ብዬ ነው የማስበው፤ እንደውም ያንሰዋል። ከሜዳው ውጪ ሁለት ጨዋታዎችን አቻ መውጣት ችለናል። ከሜዳህ ውጪ ተጫውተህ ነጥብ ይዘህ መመለስ በዚህ ሰዓት ከባድ ነው። በአጠቃላይ ግን ውጤታችን እስከ አሁን ጥሩ ነው። አሰልጣኛችንም ወጣት እና በእግር ኳሱም ውስጥ ያሳለፈ ስለሆነ ለኛ ቅርብ ነው። ያም ነገር የቡድኑን ውጤት የተሻለ እንዲሆን አግዟል ብዬ አስባለው።
አምበልነት እንዴት ነው ? አምበልነቱ ስሜታዊም አድርጎታል ይባላል…
(ሳቅ) አምበልነት ከባድ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አምበል ስሆን፤ ለብዙ ክለብ እንዳለመጫወቴም። አንበል ስትሆን ብዙ ጫናዎች ይመጡብሀል። እንደአምበልነትህ ከእግር ኳስ ተጫዋችነትህ ውጪ ሰው የሚረዳው በተለየ መንገድ ነው። አምበል አይሳሳትም ብሎ የሚያስብ ተመልካችም አለ። ግን አምበልነት ከባድ ቢሆንም ሲዳማ ቡና ውስጥ ያለን ተጫዋቾች ተመሳሳይ ዕድሜ ላይ ስለሆንን እንግባባለን፤ እንረዳዳለን። እኔም ሁሉም ሰው አምበል እንደሆነ ነው የምነግራቸው። ሜዳም ስንሄድ ሆነ በማንኛውም ስብሰባዎቻችን ሁላችንም አምበል ነን ነው የምላቸው። እኔ የማስረው አንድ ሰው ማሰር ስላለበት ነው እንጂ ሁላችንም አምበሎች ነን የሚለውን ነገር ሁሌም እነግራቸዋለሁ። ያንን ነገር ስለሚረዱት ሁሉም ይቀበሉኛል፡፡ ይመስለኛል በእርግጥ ስሜታዊነቴ አምበል ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን ሽንፈት ራሱ የሆነ የሚያመጣብህ ነገር ስላለም ነው። ቅድምም አንበል ስትሆን ይጎላብሃል ያልኩህ ለዚህ ነው። ምናልባት በፊት እበሳጨ ነበር፤ አምበል ስላልነበርኩኝ ሰው ትኩረት አላደረገብኝም። አሁን ግን አንተ ልዩ ነህ። ከዛ ውስጥ ስሜታዊ ነገሮችን ትከላከላለህ እንጂ አንተ ተደርበህ ስሜታዊ አትሆንም። በመሆኑም አምበልነቴ በፊት ያልታዩብኝን ነገሮች አሁን እንዲታዩ አድርጓል።
ሜዳ ከሚገባውም ሰው አንዳንዱ ኳስን ይመለከታል፤ የሁሉንም እንቅስቃሴ እና ድርጊቶቹንም በደንብ የሚመለከትም አለና የኔ እንዲህ መሆን በአስተያየት መልክ ሲመጣ በጣም ነው ደስ ያለኝ። በነገራችን ላይ እኔ ድክመቴን የሚነግረኝን ሰው በጣም ነው የምወደው፤ ምክንያቱም ያ ሰው የኔን መለወጥ ስለሚፈልግ ነው። ይህም ነገር በተደጋጋሚ ተነግሮኛል። ይመስለኛል በመጀመሪያው የሊግ ጨዋታ ከፋሲል ጋር ስንጫወት ትንሽ ስሜታዊ ሆኛለው። ከዛ በኋላ ግን አንዳንድ ምክሮችን ተቀብያለሁ። ተቀብዬም ራሴን አስተካክዬ ከዚያን በኋላ በነበሩት ጨዋታዎች ላይ ያ ነገሬ አልተደገመም። በዚህ ጉዳይ ያስከፋሁት ሰው ካለም ይቅርታ እጠይቃለሁ።
በመሃል እና በመስመር አጥቂነት ትሰለፋለህ። የአንተ ተመራጭ የመጫወቻ ቦታ የቱ ነው ?
አሰልጣኞች የራሳቸው የሆነ የአሰላለፍ ምርጫ አላቸው። እንደአሰልጣኙ አጨዋወት ነው እኛም የምንመራው። ብዙ ጊዜ የፊት አጥቂም ሊያደርገኝ ይችላል፤ ተደራቢ አጥቂም ሊያደርገኝ ይችላል፤ የመስመር አጥቂም ሊያደርገኝ ይችላል። አሁን ግን አዲስ ግደይ ቦታው የቱ ጋር ነው ካልከኝ እኔ የመስመር ተጫዋች ነኝ። በብዛት ቡድናችን የሚጠቀመው 4-3-3 ስለሆነ ሦስቱ ከፊት ያሉት አስቆጣሪዎች ናቸው ተብሎ ነው የሚታሰበው። በዚህ አሰላለፍም ብዙ ጊዜ ከግራ በኩል እየተነሳሁ ነው የምጫወተው፤ እኔ ግን የመስመር አጥቂ ነኝ፡፡
በሲዳማ ቡና ያለህን ስኬት በብሔራዊ ቡድን መድገም አልቻልክም። ይህንን ችግርህን ለመቅረፍ ያሰብከው ነገር አለ?
ልክ ነህ ትክክለኛ ነገር ነው። በክለቤ ላይ ያለኝን ስኬት በብሔራዊ ቡድን መድገም አልቻልኩም። ያ ግን የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስጫወት በቦታዬ የመጫወት ዕድል አልተሰጠኝም። ለምሳሌ በአሰልጣኝ አሸናፊ ጊዜ ስጠራ የቀኝ መስመር ተከላካይ ነበር የሆንኩት። ያ ደግሞ ለኔ አዲስ ነው፤ ከባድም ነበር። በተደጋጋሚ የሚሰጠኝ ሚና ያ ስለነበር ሲዳማ ውስጥ ያለውን አዲስ እዛ ማግኘት አልተቻለም። አሁን ላይ ያለው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጎበዝ እና የማደንቀው አሰልጣኝ ነው። ያለው ነገር ጥሩ ነው፤ ይረዳሃል፣ ይጠይቅሃል ቅርብህም ነው። እሱ ከመጣ በኋላ ወደ ቦታዬ መልሶኝ ለማጫወት ሞክሯል። ግን ጊዜ አልነበረውም እና በቦታዬ በሥነ ሥርዓት ለመጫወት አልቻልኩም። በቀጣይ ግን በቦታዬ የመጫወት ዕድል ካገኘሁ በሲዳማ የሚታየውን አዲስ በብሔራዊ ቡድን የማትመለከቱበት ምንም ምክንያት የለም።
ከሀገር ውጭ ወጥቶ የመጫወት ህልምህ ?
ኳስ ስትጫወት ሁሌ ባለህበት መቆምን አትፈልግም፤ ማደግ ትፈልጋለህ። ከፍ ስትል ይበልጥ ከፍ የሚለውን ማየት ትፈልጋለህ። እኔም እንደማንኛውም ተጫዋች በሌሎች ሀገሮች የመጫወት ህልም አለኝ። አምና ውድድሩ ሲያልቅ አንዳንድ ዕድሎች መጥተውልኝ ነበር። ሰዎችን ሳማክር ግን ትንሽ ቆይ ብለውኝ አሳለፍኩት። ዕድሉ የመጣልኝም ቦታ የኳሱ ደረጃ ያን ያህልም ስላልነበር አልሄድኩም። በዚህም ዓመት መጨረሻ ግን የሚመጡልኝ ዕድሎች አሉ። እነሱን ለመጠቀምም ሊጉም ላይ ጠንክሬ መስራት አለብኝ። ስለዚህም ላሁኑ ሊጉ ላይ ጥሩ ለመሆን ነው እየጣርኩኝ ያለሁት።
እዚህ ለመድረሴ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል፤ እሱ ባይኖር እኔ እዚህ አልደርስም የምትለው ሰው አለ?
እግር ኳስ ተጫዋች ስትሆን በተለይ ከነበርክበት አንድ ደረጃ ከፍ ስትል ብዙ ሰው ከኋላህ ይኖራል። በራስህ ብቻህን ብዙ ነገሮችን ማድረግ ከባድ ነውና በዚህ ሰዓት ሁሉንም ለመጥራት ሊያስቸግር ይችላል። ግን እኔ ሁሌም ቢሆን ሳልጠራው የማላልፈው ከታች ከመሰረቱ እኔን ሲያንፀኝ የነበረ አንድ ሰው አለ። ካሳሁን አይሳ ይባላል። ከሰፈር ፕሮጀክት ጀምሮ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደምደርስ ይነግረኝ እና ሁሌም ይመክረኝ ነበር። ለኔ የኳስ አባቴ ነው። ለኔ እንደተለየ ሰው ነው እሱን የማስበው፤ ለኔ ካሳሁን የተለየ ስፍራ አለው።
በመጨረሻም…
በመጨረሻ ከሁሉም በፊት የሁሉም ነገር ባለቤት የሆነው ፈጣሪን አመሰግናለሁ። ከዛ ውጭ በኳስ ህይወት ውስጥ ብዙ ሰዎች ከጎንም ነበሩ። ከካሳሁን በተጨማሪ ለዚህ ህይወቴ መሳካት ቤተሰቦቼም ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው። ጎደኞቼም እጅግ ይረዱኛል። በግል ብጠራልህ መላኩ እና ተገኔ። በኳስ ያለፉ በመሆናቸው የሚያውቁትን እየረዱኝ ከጎኔ ናቸው። ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ከዛ ባለፈ አሁን ያለሁበት ክለብ ሲዳማ ቡና ደጋፊዎችን እጅግ እጅግ ማመስገን እፈልጋለሁ። እንደቡድንም እንደግልም አመሰግናለሁ፡፡
ምንጭ- ሶከር ኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011