3ኛው የአማራ ክልል የሴቶች ስፖርት ጨዋታ ከታህሳስ 17 ቀን 2011ዓ.ም በአዊ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር በእንጅባራ ከተማ እየተካሄደ እንደሚገኝ ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ታህሳስ 16 ቀን 2011ዓ.ም የሁሉም ተሳታፊ ዞኖች የተወዳዳሪ ስፖርተኞች ወኪሎች፣ አሠልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አጋር አካላት በተገኙበት የቅድመ ውድድር ስብሰባ በማካሄድ የውድድሩ ደንብ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሙሉ ድምፅ ፀድቆ ጨዋታው በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ መግባባት ተደርሶ ነበር ወደ ውድድሩ የተገባው፡፡
በውድድሩ ላይ ሦስቱን የሜትሮፖሊታንት ከተሞችን ጨምሮ ከ12 ዞኖች የተውጣጡ ከ1ሺ 500 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።
በውድድሩ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ በርካታ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ በሦስተኛው የአማራ ክልል የሴቶች ጨዋታ ላይ ሶስት ዞኖች ምንም ተሳትፎ የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እነርሱም የምዕራብ ጎጃምና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን በዝግጅት ማነስ፣ እንዲሁም የምዕራብ ጎንደር ዞን በፀጥታ ችግር ምክንያት በውድድሩ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።
የመክፈቻው እለት በተካሄዱ ወድድሮች በእግር ኳስ አዊ ብሔረሰብ ዞን የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንን 6 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በቮሊ ቦል ጨዋታ ሁለት ውድድሮች ተካሂደዋል። በዚህም መሰረት ኦሮሞ ብሔረሰብ ጎንደር ከተማን 3 ለ 1፣ ደቡብ ጎንደር ሰሜን ጎንደርን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ታህሳስ 18 ቀን 2011ዓ.ም በተካሄዱ የፍፃሜ ውድድሮች በከባድ እግር ጉዳት አሎሎ ውርወራ ጎንደር ከተማ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ተሸላሚ ሲሆን፤ መስማት በተሳናቸው የአሎሎ ውርወራ የፍፃሜ ውድድር ሰሜን ሸዋ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በዳርት ስፖርት የነጠላ ፍፃሜ ውድድር፣ ሰሜን ሽዋ ወርቅ አግኝቷል።
እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2011ዓ.ም ውድድር በ800 ሜትር ሩጫ የፍፃሜ ውድድር፣ አዊ ብሄረሰብ ዞን ወርቅ፤ በ100 ሜትር ሩጫ የፍፃሜ ውድድር፣ሰሜን ሸዋ ወርቅ፤ በእጅ ጉዳት ጦር ውርወራ ፍፃሜ፣ማዕከላዊ ጎንደር ወርቅ፤ በእጅ ጉዳት ጦር ውርወራ ፍፃሜ ማዕከላዊ ጎንደር ወርቅ ፤ እንዲሁም በቡድን የቼስ ጨዋታ አንደኛ ደቡብ ወሎ በ3 ወርቅ ፤ሁለተኛ ማዕከላዊ ጎንደር በ2 ወርቅ ሦስተኛ ባህርዳር በ1ወርቅ ውድድሩን እየመሩ ነው፡፡ በ 23/04/2010 ዓ.ም ፍፃሜውን ባገኘው የባህል ስፖርቶች የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የአጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል፡፡ 3ኛው የአማራ ክልል የሴቶች ጨዋታ እስከ ታህሳስ 26 ቀን 2011ዓ.ም ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
መላኩ ኤሮሴ