የኢፌዴሪ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ሥራና ሥራ ዕድል ፈጠራን አስመልክቶ የአምስት ወራት አፈጻጸምን ከ19 እስከ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ገምግሟል፡፡ ግምገማው በዋናነት ለተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ በ2009 ዓ.ም የተበጀተውን አስር ቢሊዮን ብር መነሻ በማድረግ ባሳለፍናቸው አምስት ወራት ውስጥ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር በተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በውይይቱም የክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊዎች፣ የከተማና የገጠር የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የአበዳሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ ተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ እንደክልል ብሎም እንደ ሀገር እንዴት እየተፈጸመ ነው? እስከ አሁን የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ምን ምን ናቸው? ወጣቶች ምን ምን ለውጦችን እያስመዘገቡ ነው? የሚሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች ለመፈተሽ መድረኩ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡ ጥንካሬዎችና ድክመቶች የሚለዩበት፣ መልካም ልምዶችና ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ የሚደረግበትና ለቀጣይ ሥራዎችም አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህዝባችን ሃምሳ ከመቶ በላይ ወጣት መሆኑንና የመጪዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋም በእርሱ ላይ የተጣለ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ስለ ወጣት ማውራት ማለት ስለሀገር ማውራት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ መድረኩ ሀገራችን አሁን ካለችበት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንጻር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በመጥቀስም የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ማስወገድ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡
በግምገማ መድረኩም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልና የሐረሪ ክልል ሪፖረቶችን ያቀረቡ ሲሆን የፌዴራል የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሱፐር ቪዢን ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በሪፖርቶቹ መነሻነት በተደረገው ውይይትም ከቅንጅት እስከ አፈጻጸም ያሉ የተለያዩ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፤ ጥንካሬዎችና ድክመቶችም ተነስተዋል፡፡
መንግሥት በወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ቀጣይነትና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማስፈን በማለም በ2009 ዓ.ም የበጀተው አስር ቢሊዮን ብር በአግባቡ ለክልሎችና ለፌዴራል ከተሞች መሰራጨቱ ተነስቷል፤ እስከ አሁን ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ክልሎች የተሰራጨ መሆኑ የተገለጸ፤ ሲሆን ለወጣቱ ያለው ተደራሽነትም ተገቢ እንደነበር ተገምግሟል፡፡ በተያያዥም ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ከማድረግ አንጻር መልካም የሚባሉ ጅምሮች እንደነበሩ ተወስቷል፡፡
በጀቱ ሲበጀትም አጠቃላይ የወጣቶችን ችግር ይፈታል ተብሎ ባይታሰብም ወጣቱ የሥራ ባህልን ከማሳደግ፣ የሥራ አማራጮችን ከመለየትና ከጠባቂነት መንፈስ በመላቀቅ እራሱ በፈጠረው ሥራ ተሠማርቶ ውጤት በማስመዝገብ ሌሎችም ዱካውን እንዲከተሉ ከማድረግ አንጻር ያለው ሚና ትልቅ እንደነበር ጉባኤው ገምግሟል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ሆነው የተበደሩትን ብር በመክፈል የታለመው ግብ እንዲሳካ ማድረጋቸውን ተሰብሳቢዎቹ በልምድ ልውውጣቸው አንስተዋል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድርና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተመደበላቸውን የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ አሰራጭተው በመጨረስ የራሳቸውን አዲስ በጀት በመያዝ ፕሮግራሙን እያስቀጠሉ መሆኑ እንደጥሩ ተሞክሮ ተወስቷል፡፡
በተለይም የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎችና የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው በማኒፋክቸሪነግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በንግድ፣ በማዕድን ሀብት ልማትና በግብርና ዘርፎች … ወዘተ በመሰማራት ተቀጣሪነትን ብቻ የመጠበቅ መንፈስን መስበር እንደቻሉም ተወስቷል፡፡
ተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ በሀገሪቱ ልማት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና እንደነበረው ተመልክቷል፡፡ የወጣቶች ቁጥርና ፍላጎት በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ፕሮግራሙን አጠናክሮ በማስቀጠል ወጣቶች በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስተያት ተሰጥቷል፡፡
የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ አፈጻጸም ጠንካራ ጎኖች ሚዛን ቢደፉም አንዳንድ ችግሮች እንዳሉበት የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ወጣቱም ሆነ ባለድርሻ አካላት ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የነበራቸው ጠንካራ ቅንጅት እስከ መጨረሻው ያልቀጠለ መሆኑ አሁን ለታዩት መጠነኛ ችግሮች እንደ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡ ክልሎች ባቀረቡት ሪፖርትና የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ሱፐር ቪዢን ውጤት እንዳመላክተው አልፎ አልፎ አንዳንድ ኢንተርፕራይዞች ብር ተበድረው በመሥራት ላይ እያሉ በድንገት ከሥራ የሚወጡበት ሁኔታም እንዳለ ተገምግሟል፡፡ አንዳንዶችም የተሰጠው ብድር እንደማይመለስ አድርገው በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸው ጠለቅ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዳልተሰጣቸው አመላካች ነው ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ የክትትልና ድጋፍ ማነስ በተለይም ጉዳዩን ከቤተሰብ ጋር ያለማስተሳሰር፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የገበያ ጥናት ሳይደረግ ወደ ሥራ መግባት፣ የማምረቻና የመሸጫ አቅርቦት ችግር፣ የገበያ ትሥሥር አለመፈጠር እንዲሁም የወጣቶች የሥነ ምግባር ችግር ለታዩት ድክመቶች እንደምክንያት ቀርበዋል፡፡ የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና በግብርና ሚኒስትር ከሚመራው የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ቅንጅታዊ አሠራር የሌለው መሆኑም እንደድክመት ተመላክቷል፡፡
በመድረኩ በተለይም ወጣቶች ብድር ወስደው ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ከተለያዩ ሱሶች የጸዱ እንዲሆኑ በሰብዕናቸው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን መፍጠር እንደሚገባ ተመክሯል፡፡
በሌላ በኩል አናሳ ውጤት አስመዝግባችኋል የተባሉ አንዳንድ ክልሎች ለውጤታቸው ማሽቆልቆል ቢሮክራሲን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ወጣቶች የኢንተርፕራይዞችን ስያሜ ለማስጸደቅ ከዞንና ከወረዳ ወደ ክልል በሚያደርጉት ምልልስ ስለሚጉላሉና የገንዘብ አቅማቸውንም ስለሚጨርሱ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶች በሁሉም ወረዳዎች ያለመኖራቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶቹ ከሚከተሉት ሃይማኖታዊ አስተምሮት አንጻር ወለድ ያለው ብድር መበደር ባለመፈለጋቸው ምክንያት በፕሮግራሙ የመሳተፍ ፍላጎት ስለማይኖራቸው አፈጸጸሙ አናሳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ወጣቱ የመድረስና ግንዛቤም የመስጠት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገምግሟል፡፡
በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ ወጣቶች ያልተወከሉ መሆናቸውም እንደ ጉድለት ታይቷል፡፡ በቀጣይ ወጣቶችን ያሳተፈ መድረክ ተዘጋጅቶ እያንዳንዱ ክልልና ከተማ መስተዳድር በተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ ላይ ስፋትና ጥልቀት ያለው ሪፖርት ማቅረብ እንደሚኖርበት ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ምን ያህል በጀት ተበጀተ፣ ምን ያህሉ ተሠራጨ፣ ምን ያህል ወጣቶች ተጠቃሚ ሆኑ፣ ምን ለውጥ ተመዘገበ፣ ምን ያህል በድር ተመለሰ የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል መድረክ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ አምስት ወር ውስጥ የታየው የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ እንቅስቃሴ ጥሩ በሚባል ደረጃ እንዳለ የተገመገመ ሲሆን፤ የታዩ ክፍተቶችን ማረም ያስችል ዘንድ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
በተቀመጠው አቅጣጫም ቢሮክራሲዎችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማስወገድ የብድር አሰጣጦችን ለወጣቱ ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈ ልግ ተነግሯል፡፡ አካባቢያዊና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን በመፈተሸ ምቹ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ ተመክሯል፡፡ የትኛው አካባቢ ለዓሳ ምርት ፣ ለመሥኖ ልማት፣ ለኮንስትራክሽን፤ ለማኒፋክቸሪንግ … ወዘተ ተገቢ እንደሆነ ማጥናት ቀዳሚ ተግባር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጀምሮ አስከ ወላጆች ድረስ መዋቅር በመዘርጋት ቅንጅታዊ አሠራር መፍጠር፣ ድጋፍና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ወጣቶች ከሱስና ከመሰል መጥፎ ባህሪዎች እንዲታቀቡ በሰብዕናቸው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትም ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
እያንዳንዱ አስፈጻሚና ባለድርሻ አካል ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ፣ የሲቭክ ማህበራት የመንግሥትን ፕሮግራሞች በማገዝ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ የመገናኛ ብዙኃንም ተሞክሮዎችንና ለውጦችን በማስፋፋትና አቅጣጫዎችን በማሳየት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በማለት ግምገማው ተጠናቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
ኢያሱ መሰለ