ያሳለፍነው ወር በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ሁነቶች የተካሄደበት ነው። በተለይ ኢትዮጵያ በልጆቿ በዓለም አቀፍ መድረኮች የደመቀችበት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት እስከ ፍሬወይኒ የሲ ኤን ኤን የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን፤ ከአብርሃም (እቴ አባይ) አፍሪካ የሙዚቃ ውድድር መሸለም እስከ ዶክተር አታላይ ዓለም የሳይንስ ሽልማት ድረስ እፁብ ድንቅ የሚያስብሉ ጆሮ ገብ ወሬዎችን የሰማንበት ነበር። መች ይሄ ብቻ የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በሽልማት ተንበሽብሸው አኩርተውናል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው በመሆን ከአፍሪካ ብቸኛዋ ሴት በሚል የኦርቢስ መጽሄት አስነብቧል። ሌሎችም እንዲሁ ኢትዮጵያን በከፍታ ላይ የሚያኖሩ የሰማናቸው ዜናዎች ነበሩ። እንዲሁም የደቡብ የባህል ቡድን ‹‹የዓመቱ የአፍሪካ የባህል ቡድን አሸናፊ›› የሆነበት ነበር። ምን አለፋችሁ ያሳለፍነው ወር የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ሆኖ አልፏል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ውበቷ፣ በታሪክ ቅርሶቿ፣ በብሔር ብሄረሰቦች መገኛነት እና በቱሪዝም ሀብቶቿ እንደምትታወቅ እሙን ነው። ከእነዚህ መካከል ‹‹ባህል›› አንዱና ዋነኛው ነው። ይህ ታላቅ እሴት እጅግ ክቡር በመሆኑ ማህበረሰቡ በራሱ ጥረትና እንክብካቤ ሊጠብቀውና ሊያሻሽለው ይገባል። ይህ ሲሆን ከላይ በመግቢያችን ላይ ለመግለፅ እንደቻልነው ባህልን በራሳችን እሴቶች እና በምናፈራቸው ጠንካራ ጀግኖች የዓለምን ትኩረት መሳብና ማንነታችንን በጉልህ ማሳየት ያስችለናል።
ልንጠብቀው ልናዳብረው ብሎም ልናስተዋውቀው ከሚገቡን ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ደግሞ ለዛሬ ርእሰ ጉዳያችን አድርገን በስፋት የምናነሳው የሙዚቃውን ዘርፍ ነው። በእዚህ ረቂቅ የጥበብ ዘርፍ ላይ ትኩረታችንን አድርገን ጥቂት ሀሳቦችን ለመሰንዘር እንሞክር። ይህን ስንል ግን ጉዳያችን ፈር ለቆ ደርዙን እንዳያጣ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘልቀን ሙዚቃና ባህላዊ እሴቶችን ለማቆራኘት ጥረት እናድርግ።
አሁን አሁን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሆኑ የሙዚቃ መሳሪያዎች ታጅበው የሚደመጡት ዜማዎች እና እንቅስቃሴያቸው ቱባነታቸውን ሳይለቁ ባህላዊ እሴቶችን በሚያንፀባርቅ መንገድ ሊቀርቡ ቢገባም በዚያው መጠን ባሉበት መዳከርና ተፈጥሯዊ እድገታቸው መገደብ እንደሌለበት አጠያያቂ አይሆንም። ታዲያ እነዚህን ሁለት አስፈላጊ ጉዳዮች ማቆራኘት የቻሉ ባለሙያዎች አሁን ላይ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ከዚህ ቀጥሎ የምናገኛቸው የባህል ቡድን አባላት የዛሬው ፅሁፋችን ማሳያ ሆነው ይቀጥላሉ።
ከዓመታት በፊት ለሚወክሉት ብሔረሰብና ለባህሉ የቆረቡ፤ ቆራጥ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተውጣጡ ወጣቶች ተሰብስበው ነበር የደቡብ የባህል ቡድንን የመሰረቱት። ከመነሻው በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ያለፈው ይህ ማህበር አንድ ቀን የብርሃን ወጋገን እንደሚያገኘው በማሰብ በተሰፋ ያለአንዳች ድጋፍ እሴቶቹን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። በስተመጨረሻም ለድል እና ለስኬት ሊበቃ ችሏል።
ከማህበሩ መስራች አባላት መካከል ወንድዬ አበበ (ኮንታ) አንዱ ነው። ወንድዬ ለረጅም ዓመታት ያደገበትን ባህል በማስተዋወቅ ቱባውን ማንነቱን ሳይለቅ መዝለቅ ችሏል። እርሱ ስለ አመሰራረቱ ይናገራል።
‹‹ቡድኑ ሲዋቀር ያደረግነው በደቡብ ክልል ከሁሉም ብሔረሰብ ፊተኛ የሆኑ እና ባህላቸውን በማስተዋወቅ ላይ የሚገኙትን እንዲሁም ሙዚቃን ለበጎ ተግባር የሚጠቀሙትን አርቲስቶች በመጋበዝ ነበር›› የሚለው ወንድዬ በዋናነት ባህል ነክ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የሚሰሩ አርቲስቶችን ለማካተት እንደተሞከረ ይገልፃል። በደቡብ ከሚገኙ 14 ዞኖች 4 ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሌሎች የብሔር ብሔረሰብ አባላትንም እንዳካተተ ይገልጻል።
ከስልጤ መሀመድ ሲርጋጋ፣ ከጉራጌ ይታገሱ መለስ (የቃቂ ውርድዎት)፣ከዳውሮ ወንድሙ ዳውሮ ባና፣ ወንድየዬ አበበ ከኮንታ ፣ ከደቡብ ኦሞ ቦና ቡንዴ፣ ከወላይታ ካሙዙ ካሳ ፣ አበራሽ ጋጋ ፣ ጊልዶ ካሳ እንዲሁም አቀናባሪው ስማገኘውን ጨምሮ የተለያዩ በአገሪቱ ሙዚቃ ፊት መሪ የሆኑ የባህል አምባሳደር አርቲስቶች አባላቶቹ ናቸው። ከመስራች አባላት በተጨማሪ ባህልን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንንም ያቀፈ መሆኑን ወንድዬ ይናገራል።
ማህበሩ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሆነ አባል መልምሎ ያስገባ እንጂ የስብስቡን ዓላማ፣ ራዕይ እንዲሁም ተልዕኮ ተረድተው የመከወን ግዴታም እንዳለባቸው የሚናገረው ድምፃዊ ወንድዬ፣ ባህላችን ማህበረሰብን የምንወክልበት በመሆኑ ጥንቃቄ መሰረታዊ ጉዳይ ነው የሚል አመለካከት ያንፀባርቃል።
‹‹ስማችን ደቡብ ይባል እንጂ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ያካተተ ነው››፤ የሚለው ወንድዬ ለምሳሌ የሙዚቃ ባንዱን ተጫዋቾች ሲመለምሉ ተሰጦና የባህል አምባሳደርነትን መሰረት ያደረገ ብቻ እንደነበር ይገልፃል። የከበሮ (ድራም) ተጫዋቹ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ ነው፣ የቤዝ ክራር ተጫዋቹ ከጅማ የመጣ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ነው፣ የክራር ተጫዋቹ ከትግራይ ነው ፣ማሲንቆ ከጎጃም ነው ፣ቶም ቶም መሳሪያ የሚጫወቱት ደግሞ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች የተገኙ ናቸው በማለት ኢትዮጵያዊ ቃና የተላበሰ ስብስብ እንደሆነ ያስረዳል።
አርቲስት ወንድዬ ‹‹ማህበሩ ትንሹ ኢትዮጵያ ነው›› በማለት ከተቋቋመ አራት ዓመታት ያስቆጠረ እንደሆነ ይገልፃል። በአሁኑ ወቅት በመስራቾች እና በባላገሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ የደቡብ ኮከቦች የሚል ዝግጅት የሚያቀርቡትን ጋዜጠኛ አባላቱን ጨምሮ ከሁለት መቶ በላይ ናቸው። ተሰጦ ያላቸው ታዳጊዎችም ላይም እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጿል።
እንደ አርቲስት ወንድዬ ሀሳብ ፤በኢትዮጵያ በስፋት ማኅበረሰባዊና ባህላዊ ሀብቶች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የደቡብ ክልል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። በክልሉ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ያሏቸው ቱባ ባህላዊ ዜማዎችና ውዝዋዜዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከክልሉ አልፎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጭምር ተወዳጅነታቸው እየጨመረ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶች በባህላዊ ሙዚቃ፣ ድምጻዊነትና ተወዛዋዥነት እየተሳተፉ ቢገኙም፤ አሁንም በዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ለመግባት በርካታ እንቅፋቶች እንዳሉበት ይናገራል። ልምምድ ማድረጊያ ስፍራ ማጣት፣ የአልባሳት እጥረት፣ የሙዚቃ መሳሪያች እና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው።
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የባህል አምባሳደር በመሆን የተለያዩ ስራዎች ሰርቷል። በስራውም የተለያዩ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል። ከዚህ ቀደም ከሰራቸው ባህልን የማስተዋወቅ ስራ መካከል አንዱ ‹‹አስራ አንደኛው የኢህአዴግ ጉባኤ›› ሀዋሳ ላይ ሲዘጋጅ የኢትዮጵያን ቱባ ባህል የማስተዋወቅ ስራ ሰርቷል። ለዚህም ሽልማት እንደተበረከተለት ሙዚቀኛ ወንድዬ ይናገራል።
ከዚህም ባሻገር አስረኛውን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስብሰባ ላይም ባህልን የማስተዋወቅ እንዲሁም አንድነትን በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ የጥበብ ስራ አቅርቧል። የባህል ቡድኑ የተነሳበት ዓላማ ሌሎች ያበላሹትን ባህል በጥበብ መስፋትና ማስተካከል እንዲሁም ያሳደፉትን የማንጻት ስራ ነው።
ኢትዮጵያ የብዙ ባህላዊ ዕውቀት ባለቤት ናት የሚለው ወንድዬ፤ በዚህ እውቀት አንድነታችንን ለማስጠበቅ፣ የጠፋውን ፍቅር ለመመለስ የባህል ቡድኑ ወሳኙን ሚና ይጫወታል። ዋና አላማው ዓለምን በመዞር ሸልማቶችንና ገንዘብ መሰብሰብ ሳይሆን ባህልን በመጠቀም ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ማዳን እንደሆነ አበክሮ ይናገራል።
‹‹ከዚህ ቀደም የዜግነት ክብራችንን ተነጥቀን በመደበቅ እና በመሸማቀቅ ነበር የምንኖረው›› የሚለው ሙዚቀኛው፤ አሁን በአንድነት መቆምና ባህላዊ ዕውቀቶችን መጠቀም ከተቻለ ኢትዮጵያን በማንሳት ቀና የምንልበት ነው ይላል።
“የአፍሪካ ሙዚክ አዋርድ”
ወደ ናጄሪያው “የአፍሪካ ሙዚክ አዋርድ” ውድድር የሄዱበትን ሁኔታ አርቲስት ወንድዬ ሲያስታውስ ‹‹ከተገኘው ዕድል ባሻገር ለዚህ ሁሉ ያነሳሳን በአገር ውስጥ የምዕራባውያን ተጽዕኖ ያደረባቸውን ሙዚቃዎች በተሻለ በቱባ ባህላዊ ስራ ውጤት ለማምጣት ነው›› ይላል። ኢትዮጵያዊ ልክ የሌላቸው የምእራባውያን ተፅዕኖ ያረፈባቸው ስራዎች ብቻ እስከዛሬ አገሪቷን መወከላቸው ቁጭት አሳድሮባቸው እንደነበርም ያነሳል።
በዚህ መካከል ነበር ከወራት በፊት በኢትዮጵያ የባህላዊ ልብስ የፋሽን ዲዛይኗን ስታቀርብ የነበረችው በዘርፉ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶክተር ሰናይት ማሪዮ በናይጄሪያ ሊደረግ ለታቀደው ውድድር የደቡብ የባህል ቡድንን እንዲታጭ ጥቆማ ያቀረበችው።
እንደ አርቲስት ወንድዬ ገለጻ ዲዛይነሯ ኢትዮጵያ መጥታ የስራ ውጤቶቿን በአቀረበችበት ወቅት ከቡድኑ ጋር በመሆን ስትሰራ ነበር። ባህልንና የባህል ልብስን ለዓለም ለማስተዋወቅ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የባህል ቡድኑ አብሯት በመሆን ብዙ ስራዎች ሰርቷል። የውድድሩ አዘጋጆች አሁን ባለችው አፍሪካ ትክክለኛ ባህል እና የባህል ሙዚቃዎች ይገኛል ብለው የሚያስቡት ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ነው። ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ እንደሆነች ሲናገሩ መስማቱን አርቲስት ወንድዬ ይገልፃል። በዚህም ትልቅ ኩራት እና ደስታ እንደተሰማው ያነሳል።
ጥቂት ስለ ውድድሩ
ውድድሩ የሚዘጋጀው በናጄሪያ ሌጎስ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በተከበበው ትሮፒካል ሎጅ ውስጥ ሲሆን ለሶስተኛ ጊዜ እንደተዘጋጀም አርቲስቱ ይናገራል።
‹‹ናይጄሪያ ሌጎስ ስንሄድ የወከልነው 56ቱን የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችን አይደለም። የወከልነው ኢትዮጵያን ነበር። ኢትዮጵያን ደግሞ ወክሎ ማሸነፍ የሚገርም ደስታን የሚፈጥር ነው›› በማለትም፤ በውድድሩ ሁሉም የአፍሪካ አገራት የባህል አምባሳደራቸውን ይዘው መቅረባቸውን ይናገራል። ከዚያ ነጥሮ ወጥቶ ለዚህ ክብር መብቃት አገሪቱንም ማስጠራት እጅግ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ይገልፃል።
እንደ አርቲስት ወንድዬ ሃሳብ በውድድሩ የአገራችንን ስም ከፍ ከማድረግ ባሻገር እንደ ቡድንም የተለያዩ እድሎች ተገኝተዋል። በውድድሩ ከአገኙት የገንዘብ ሽልማት ባሻገር በክልሉ መስተዳድር ትኩረት ማግኘት ችለዋል። በተለይ ከለውጡ ጋር ተያይዞ የመጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው ለባህል ቡድኑ የደርሶ መልስ የአየር ቲኬት ሙሉ ወጪ እና የባህል አልባሳት ወጪን ከመሸፈን ባሻገር ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሷል። ለዚህም ከልብ ማመሰገን እንደሚያስፈልግ ይናገራል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ቡድኑ ልምምድ በሚያደርግበት ቦታ በአካል ተገኝተው በማበረታታት የጥበብ አጋርነታቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግሯል። እንደ አርቲስት ወንድዬ ገለጻ ኢትዮጵያ የበለጸገ ባህል፣ የደረጀ ባህላዊ እውቀት ያላት አገር ናት። እነዚህን እውቀቶች በመጠቀም የአገር አንድነት ማስጠበቅ ተገቢ መሆኑን ያነሳል። በእያንዳንዱ ክልል ብሔረሰቦች የራሳቸው የሆነ በባህላዊ ዕወቀት፣ የደረጀና ድንቅ የመቻቻል፣ የሰላም ብሎም የፍቅር እሴቶች እንዳሉም ይገልጻል። እኩይ ሃሳብ ባላቸው ሰዎች አሁን አሁን እንዲመጣ የሚፈለገው ሰይጣናዊ የጥፋት ውሃ ለመግታት የሚረዱ መሆኑን ሳያነሳ አላለፈም።
የባህል ቡድኑ በብዙ መልኩ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። ከዚህ ባሻገር እንደ ደቡብ ክልል የሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ድንቅ ባህላዊ ዕውቀት ከአገር አልፎ ለዓለም ምሳሌ እንዲሆን ማበልጸግ እና ለአገራዊ መግባባት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ይህ ከተደረገ ኢትዮጵያ የፍቅር፣ የመቻቻል አገርነቷ ይቀጥላል። እያልን ለዛሬው መልካም ሳምንት ብለን ተሰናበትን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2012
አብርሃም ተወልደ