“ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል፣
በማለት ሰለሞን ቀድሞ ተናግሮታል።
ሳትደፈር ኖራ ጨረቃም እርቃ፣
በሰው ተደፈረች ጊዜዋን ጠብቃ። ”
ወደ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊጠጋ ከተቃረበ ዓመት በፊት ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ያንጎራጎረው የዜማ ግጥም ነበር። ድምፃዊው የቅዱስ መጽሐፉን መጽሐፈ መክብብ መነሻ በማድረግ ባዜመበት በዚያ ዘመን የሰው ልጅ ጭንቅላት እጅግ አስደናቂ ውጤቶችን በስፋትና በብዛት እያስመዘገበ አጃኢብ ያሰኘበት ዓመታት ነበሩ። ድምፃዊው እውነቱን ነበር። ለሁሉም ዘመን እንዳለው መጽሐፈ መክብብ በምዕራፍ 3 ላይ የምሥጢሩን ዝርዝር በሚገባ አሳይቶናል። እንዲህ በማለት፤
“ለሁሉ ዘመን አለው። ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው። ለመትከል ጊዜ አለው። የተተከለውን ለመንቀልም ጊዜ አለው። ለማፍረስ ጊዜ አለው። ለመሥራትም ጊዜ አለው። ለማልቀስ ጊዜ አለው። ዋይ ለማለትም ጊዜ አለው። ለመዝፈንም ጊዜ አለው። . . . “
ቀጥለን ለምንጠቃቅሳቸው ጉዳዮች መሐሙድ አህመድ የዘፈነበት ጊዜ ትክክለኛው ወቅት ነበር። እርግጥ ክስተቱ የተፈፀመው ከጠፈር በታች ብቻ ሳይሆን ከሰማይ በላይም ሃሰሳው የተጧጧፈበት ወቅት ነበር፤ ዘመኑ ደግሞ 1965 ዓ.ም። አፖሎ 17 በመባል የምትታወቀው የአሜሪካዋ ጠፈር አሳሽ መንኮራኩር እ.ኤ.አ ዲሴምበር 7 ቀን 1972 ዓ.ም ከጆን ኤፍ ኬኔዲ የጠፈር ምርምር ማዕከል ተተኩሳ ወደ ጨረቃ የመጠቀችበት ያቺ ታሪካዊ ዕለት ለጠፈር ምርምር ማዕከል ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለኢትዮጵያዊያንም ጭምር ተጠቃሽ ዕለት ነበረች። መንኮራኩሯ ከሦስት ቀናት ጉዞ በኋላ ተልዕኮዋን አሳክታና በጨረቃ ዙሪያ የምታደርገውን የቅኝት ሽክርክሪት አጠናቃ የያዘቻቸውን ጠፈርተኞች በሰላም ጨረቃ ላይ ስታሳርፍ ዓለም በአድናቆት ከምድር ሆኖ አጨብጭቦላት ነበር።
በመንኮራኩሯ ውስጥ የነበሩት ጠፈርተኞች ብዛት ሦስት ሲሆን ለምርምር ሥራ አብረው ሽርሽሩን የተጎዳኙት አይጦች ደግሞ ብዛታቸው አምስት ነበር። አፖሎ 17 መንኮራኩር በአፖሎ ስም ከተሰየሙትና ሰዎችን ይዘው ወደ ጨረቃ ከመጠቁ መሰል መንኮራኩሮች መካከል የመጨረሻዋ መንኮራኩር ነበረች።
ባለፈው ረቡዕ ታሪኩን አዳምጨ የጻፍኩለት ይህ የስምንት አስርት ዕድሜ ባለጠጋ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሐምሌ 9 ቀን 1965 ዓ.ም ዕትሙ ሀገሬ በብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማዋ ውክልና ከአፖሎ 17 ጋር የነበራትን ቁርኝት አስመልክቶ የሚከተለውን አስደናቂ ዜና አስነብቦን ነበር።
“የአፖሎ 17 ጠፈርተኞች ጨረቃ ላይ አድርሰው የመለሱትን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትናንት ተቀበሉ። በታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተደረገው ሥነ ሥርዓት ጨረቃ ላይ ደርሶ የተመለሰውን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማና ከጨረቃ ላይ የመጣውን ደንጊያ በክቡር ፕሬዚዳንት ኒክሰን ስም ለግርማዊነታቸው ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ክቡር ሚስተር ሮስ አዴር ናቸው። ” ይለናል፤ አይገርምም!!!
ዛሬ ዛሬ “የእነ እከሌ እንጂ ለእኔ ጉዳዬም አይደለ!” እየተባለ መዘበቻ በመሆን በፖለቲካ ጥፊ ግራና ቀኝ እየተጣፋ አሳሩን የሚበላው ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማችን ይህንን የመሰለ ክብር መጎናጸፉን ስናስብ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ብዙ ማይሎችን ወደኋላ መጓዛችንን በሚገባ ይመሰክራል። ይህንን ታሪክ ምን ያህሎቻችን እንደምናውቀው እርግጠኛ አይደለሁም። ለነገሩ በቂ የጽሑፍ ማስረጃ ባላገኝለትም ሠንደቅ ዓላማችን ብቻ ሳይሆን የወቅቱ ቅንስናሽ ሣንቲሞቻችንና የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የጥበብ ገድል የተሰነደበት ጽሑፍም አብሮ ተጓጉዞ እንደነበር በተደጋጋሚ የቃል ምስክርነት ሰምቻለሁ። አፈወርቅ ተክሌም የቃል ምስክርነት ሰጥተዋል የሚል ሐሳብ “ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር” ከሚል የቅርብ ወዳጄ አንደበት አድምጫለሁ። ይህ ጉዳይ እውነታነት ካለው የሚያውቁ ቢያሳውቁን እንማማርበታለን፤ ጥርት ያለ መረጃም ይኖረናል። ጨረቃን ለመርገጥ የሠንደቅ ዓላማችን የአምባሳደርነት ውክልና ግን እርግጥና በማስረጃ ጭምር አሜንታ ያተረፈ ጉዳይ ስለሆነ በክርክሩ መካከል ጣልቃ አይገባም።
ሀገራችን ያን ለመሰለ ክብር የተመረጠችው በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃና በመንግሥታት መካከል በነበራት ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷና ብቃቷ መሆኑን ልብ ማለት ይገባ ይመስለኛል። የሉዓላዊ ሀገራችን ውኪልና ተምሳሌት የሆነው ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማችን የጨረቃን አፈር ረግጦ ተመለሰ ማለት ኢትዮጵያን ወከለ ማለት ስለሆነ “ሀገሬ ጨረቃ ላይ አርፋ ነበር” ቢባል ምንም ስህተት፣ ምንም ማጋነን ሊሆን አይችልም።
መቼም ሊያማክሉን በሚችሉ ሀገራዊ ታሪኮቻችን ላይ ከመግባባት ይልቅ መጨቃ ጨቁና መናቆሩ ሥር የሰደደ እኩይ “ባህላችን” ስለሆነ እንጂ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ደማቅ ብሔራዊ ታሪኮቻችንን ለበጎ ህሊናችንና ለትውልዱ ብናስተምር መናቆራችንን መቀነስ ብቻ ሳይሆን በጋራ እሴቶቻችን ዙሪያ “ብሔራዊ ስሜትን” ከፍ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረው ነበር። “ያልተደልሽ እንዴት አደርሽ!” አሉ ነገር አዋቂ የሀገሬ ጎምቱዎች። ይህንን ጉዳይ ከነካካን አይቀር ግን ጨረቃ ላይ ደርሶ የመጣው ያ ባለታሪክ ብሔራዊ ሠንደቅ ዓለማችን ለመሆኑ ዛሬ መገኛው የት ነው? እንደ በርካታ ቅርሶቻችን ሰብሳቢ አጥቶ ስርቻ ሥር ተወርውሮ ይሆን? ብዬ ይመለከተኛል ባዩን እሞግታለሁ። በአሜሪካ መንግሥት የተበረከተ ሌላም ፕላክ (በአነስተኛ ሰሌዳ ላይ የተቀረፀ ምስልና ጽሑፍ) ስለነበር የእርሱም አድራሻ ቢታወቅ መልካም ይሆናል።
ከ47 ዓመታት በኋላ . . .
47 ዓመት የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ ነው። አፖሎ 17 የእኛንና የተወሰኑ አገራትን ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ በክብር ይዛ ወደ ጨረቃ የተወነጨፈችበት፣ ያረፈችበትና በሰላም የተመለሰችበት ወር ከዘንድሮ የታህሣስ ወር ጋር ተገጣጥሟል። ትናንት ወደ ጠፈር የመጠቀችው የእኛዋ ሳተላይት ET-RSS 1 (Ethiopian Remote sensus Satellite One) በተመሳሳይ ቀናት በዚሁ በታህሣስ ወር ከህዋ ላይ ሆና ቁልቁል መረጃ ለማጉረፍ መላኳን የግጥምጥሞሹን ታሪካዊነት ይመሰክራል። ይህ ጸሐፊ የተወለደውም በዚሁ ብራማ በታህሣስ ወር በሰባተኛው ቀን ስለሆነ እኒህን መሰል ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ሲያስታውስ ስሜቱ ሞቅ፤ መንፈሱም ደመቅ ይላል።
ሀገሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ዳቦ ቆርሳላትና ፌሽታው ደምቆላት ወደ ህዋ የሸኘቻት ሳተላይት ከምድራችን በላይ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተሽከረከረችና እየተብነሸነሸች ተልዕኮዋን በሰላም እንደምታጠናቅቅ አደራም ተስፋም ጥለንባታል። ረጂም ዕድሜ ለሀገሬ ጠቢባን፣ ምሥጋና ለቻይና አጋሮቻችን ይሁንና ወግ አይተናል። ሳተላይታችን ምጥቀቷ ቻይና፤ የምታቀብለው መረጃ የሚተነተነው ሀገር ቤት ቢሆንም የታቀደላትን ግብ እንደምታሳካ ግን ሙሉ እምነት ጥለንባታል። ማን ያውቃል ዛሬ ወደ ህዋ የተደረገው ጉዞ ነግ ተነገወዲያ ኢትዮጵያዊት መንኮራኩር ወደ ጨረቃ የማናመጥቅበት ምክንያት አይኖርም። ብቻ ፈጣሪ ዕድሜና ሰላሙን አይንሳን። “ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል” በማለት የመሐሙድን የዘፈን አዝማች ደግመን በጋራ እያንጎራጎርን “ለጊዜ ጊዜ መስጠቱ” መልካም ነው።
ታህሣስ 7 ቀን ቀጠሮ ተይዞላት የነበረችው ሳተላይታችን የሦስት ቀናት መዘግየት ቢያጋጥማትም ጉዞዋ ግን አልተስተጓጎልም። በህዋ ፈታኝ ጉዞ ወቅት አልፎ አልፎ ቀጠሮ የማፋለስ አጋጣሚዎች ተደጋግመው ስለሚስተዋሉ ቃል አባይ አሰኝቶ አያስተችም።
ከመወለዷና ከተወለደችም በኋላ የተመራማሪዎቹ ሕጋዊ ስም እንደተጠበቀ ሆኖ “አሉ” ለማለት ይሁን አይሁን ጉዳዩ ባይገባንም “የዳቦ ስም” አውጡላት የሚል የጅምላ ጥሪ ቀርቦልን ነበር። ለማንኛውም ኢትዮጵያዊቱ ሳተላይት በህዋ ውስጥ በምትሰነብትባቸው ዓመታት ውስጥ ለዓየር ንብረት ትንበያ፣ ለግብርናና ለተፈጥሮ ሀብታቸን ዕቅድ፣ አተገባበርና አጠባበቅ፣ ለደን ሀብታችን አያያዝና መረጃ አሰባሰብ፣ የማዕድን ሀብታችንን ለማበልፀግ የሚረዱ ዝርዝር መረጃዎችን ቁልቁል እንደምታዥጎደጉድልን ይጠበቃል። ሌላም እኛን ተራ ዜጎች የማይጠቅስ ሀገራዊ ተግባር ትከውን አትከውን ምንም ነገር አልተገለፀልንም። ለማንኛውም ግን ተልዕኮዋ በስኬት ሲጠናቀቅ ጉሮ ወሸባዬ እያልን እንደምናሞግሳት ከወዲሁ የማረጋገጫ ቀብድ እንሰጣለን።
ለማንኛውም ጉዞዋ እንዲሰምርላት “በሆት ግቢ” ብለን በመመረቅ ሸኝተናታል። ሳተላይቷ በህዋ ውስጥ እየተሽከረከረች ሥራዋን በምታቀላጥፍባቸው ዓመታት ውስጥ ወደ ጨረቃ ለሚደረገው ጉዞ ጠበብቶቻችን ዝግጅቱን እንደሚያጧጡፉም እምነት አለን። ምኞታችን እውን ሆኖ ቢሳካማ “ጨረቃ ድንቡል ዕቃ፤ አጤ ቤት ገባች አውቃ!” የሚለው የሕፃናት ልጆቻችንን የጨዋታ መዝሙር በተግባር ስለሚተረጎም ከታዳጊ ልጆቻችን ጋር በጎርናና የወላጆች ድምጽ አፖሎ 17ን እያስታወስን አብረን መዘመራችን አይቀርም። “አፖሎ!” የሚል የፀጉር ሥራ ፋሽን በሀገራችን እንዳለ እህቶችን እንኳ ባልጠራጠር ወንዶች እናውቅ ይሆን?
እግረ መንገዴን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲን ከመሰረቱት አንዱና በዓለም አቀፍ የህዋ ጥናትና ምርምር በርካታ ዘርፎች አክብሮትንና አንቱታን ያተረፈውን የፊዚክስ ሊቅ ሳልጠቅስ አላልፍም። ይህንን ሰው በሬዲዮ ያቀርባቸው በነበሩት ህዋ ነክ ዝግጅቶቹም እናውቀዋለን፣ ሀገሩን ያኮራውና ትናንት በመጠቀችው በኢትዮጵያዊቷ ሳተላይት ዘፍጥረት ላይ ቀዳሚ የአዋላጅነት የምርምር ድርሻ ከነበራቸው የሀገራችን ሳይንቲስቶች መካከል ዛሬ በሕይወት የሌለው ነፍሰ ኄሩ ሳይንቲሰት ወንድማችን ዶ/ር ለገሠ ወትሮ የስፔስ ሳይንሱ ጉዳይ በቀዳሚነት ያገባናል በሚሉ ሹማምንትና ተመራማሪዎች አማካይነት ጋዜጣዊ መግለጫ ወይንም ማብራሪያ ሲሰጥ ለምን ስሙን እንደማይጠቅሱት ግር ብሎናል። “ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ . . .” ብለን ለማንጎራጎር የቃጣንም በዚሁ ምክንያት ነው። በእንጦጦው የህዋ ሳይንስ ምርምር ጣቢያ ውስጥ አንድ መታሰቢያ ቢቆምለት፣ ተንጠራራችሁ ካልተባለ በስተቀር መንግሥትስ ቢሆን አስተዋጽኦውን መዝኖ ዛሬ በሕይወት ባይኖርም ቢዘክረው ብዙ ትርጉም አይኖረውም ትላላችሁ።
ህዋና ጨረቃ ከሰው ልጆች ጋር እንዴት ተደፋፈሩ!?
የሰው ልጅ ለአዳዲስ የዕውቀትና የፈጠራ ሐሳብ በቃኝ ብሎ አያውቅም። ይህም አይጠገቤ ፍላጎቱ በውኑም ሆነ በቅዠቱ ጤናና እረፍት ስለሚነሳው ሁልጊዜም ጉጉቱ አይበርድም። ጨረቃ በሰው ልጆች ስትሞገስ የኖረችው በዋነኛነት በኪነ ጥበባት ውጤቶች ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶችም ቢሆኑ ከኪነ ጠቢባኑ ባልተናነሰ ሙገሳ ገበናዋን ለመበርበር ቀን ከሌት መጣራቸው አልቀረም። ለታሪክ ትውስታ እንዲያግዝ የማስታወሻ ቅኝት እናድርግ።
ሳተላይቶች በዋነኛነት በሁለት ምድብ ይከፈላሉ። በመጀመሪያው ምድብ ውስጥ የሚጠቃለሉት ተፈጥሯዊ ሳተላይቶች በመባል ሲታወቁ እነርሱም ጨረቃን የመሳሰሉ አካላትን የሚያጠቃልሉ ናቸው። ሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚካተቱት ሰው ሠራሽ አርቲፊሻል ሳተላይቶች ይባላሉ። ኢትዮጵያችን ያመጠቀችው ሳተላይቶች ዓይነት መሆኑ ነው።
በታሪክ ተጠቃሽ የሆነችውንና ስፑትኒክ አንድ በመባል በታሪክ የተመዘገበችውን የመጀመሪያዋን ሳተላይት እ.ኤ.አ ኦክቶበር 4 ቀን 1957 ዓ.ም ያመጠቀችው የዛሬዋ ሩሲያ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ነበረች። ከዚያን ጊዜ ወዲህ አርባ ያህል አገራት ወደ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ ሳተላይቶችን አምጥቀዋል። በ2018 ዓ.ም የወጣ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው አገራት ወደ ህዋ ከላኳቸው ሳተላይቶች ውስጥ ህዋው ላይ እየተንሳፈፉ የሚገኙት አምስት ሺህ ያህሎቹ ብቻ ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል ቢሆን ተግባራቸውን እየከወኑ የሚገኙ 1900 ያህሉ ብቻ ናቸው። መረጃው የቅርብ ጊዜ አይደለም።
የሳተላይቶች አገልግሎት ዘርፉ ብዙ ነው። በጥቅሉ እንበይን ከተባለ ግን የአጥናፈ ዓለማትን ጓዳ ጎድጓዳ ማሰስ ነው ብሎ መጠቅለል ይቀላል። ያም ቢሆን ግን አገራት ሳተላይቶቹን የሚጠቀሙባቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አፅንኦት በመስጠት ነው። አንዳንድ አገራት ከዋክብትንና ፕላኔቶችን ለመመርመር ሲጠቀሙበት አንዳንዶች የፕላኔታችንን ከርሰ ምድር ለመበርበር ይጠቀሙበታል። አንዳንዶችም እንዲሁ ከኮሚዩኒኬሽን፣ ከወታደራዊና ከፀጥታ ሥራ ጋር ተያያዥ የሆኑ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ይገለገሉባቸዋል። እኛን መሰል ከድህነት ጋር ግብ ግብ ላይ ላሉ አገራት ደግሞ ተቀዳሚ ፍላጎቱ ለልማት አጋዥ የሆነ ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ ነው።
ባለፉት ስልሳ ዓመታት ውስጥ የሰው ልጅ ጠፈርን የማሰስ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ወቅት ነበር። በተለይም ወደ ጨረቃ የሚደረገው ጉዞ በወቅቱ የቀዝቃዛው ጦርነት ሁለት ተፎካካሪ ኃያላን መንግሥታት (ሶቪዬት ኅብረትና አሜሪካ) መካከል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተካረረበት ወቅት ነበር። ሴፕቴምበር 13 ቀን 1959 ዓ.ም ጨረቃ ላይ ያረፈችው የመጀመሪያዋ ሰው አልባ መንኮራኩር የሶቪዬት ኅብረቷ ሉና 2 በመባል የምትታወቀው መንኮራኩር ስትሆን የሰው እግር ጨረቃ ላይ የረገጠውን መንኮራኩር ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጠቀችው ደግሞ አሜሪካ ነበረች። ዘመኑም ጁላይ 16 ቀን 1969 ዓ.ም ነበር። የሦስቱ ጠፈርተኞች አስተባባሪና መሪው ኒል አርምስትሮንግ ነበር። ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጅ ወደ ጠፈር ያደረገውን ጉዞ ፈር የቀደደው የሶቪዬት ኅብረቱ ዩሪ ጋጋሪ ሲሆን ጊዜው ኤፕሪል 12 ቀን 1961 ዓ.ም ነበር።
በሶቪዬቶችና በአሜሪካኖች መካከል የነበረው የጠፈር እሽቅድምድምና እኔ እበልጣለሁ ባይነት በብዙ መልኩ የተገለጠ ነበር። የሳይንሳዊ ምርምሩ እሰጥ አገባ እንዳለ ሆኖ በሃይማኖታዊ ጉዳዮችም ሳይቀር በተላኩት ጠፈርተኞች መካከል ትልቅ ፉክክር ይስተዋል እንደነበር ሰነዶች ዝርዝሩን ይተነትኑልናል። በሶሻሊስት ፍልስፍና የተጠመቁት አምላክ የለም ባዮቹ ሶቪዬቶችና “አምላክማ አለ እንጂ!” እስከሚሉት አሜሪካዊያን እንኪያ ሰላንትያው እጅግ የከረረ ነበር። በተግባርም በወሬም።
ያም ሆነ ይህ ፉክክሩ አሁንም ቀዝቅዟል ለማለት ያዳግታል። ዛሬም ቢሆን ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማቸውን ጨረቃ ላይ ደጋግመው የተከሉ ኃያላን አገራትም ሆኑ እንደ የኔዋ ሀገር ኢትዮጵያ ያሉ የጠፈርን ምሥጢር ለመመርመር የሚጓጉ አገራት ወደ ጨረቃ ማማተራቸው አልቀረም። ትናንት ወደ ጠፈር የላክናት ሳተላይት ውሎ አድሮ ወደ ጨረቃ የምትምዘገዘግ መንኮራኩር ሳታስከትል ስለማትቀር ለጊዜ ጊዜ ሰጥተን በትዕግስት እንጠብቅ። ቦን ቮዬጅ ET-RSS 1። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)