ይህ ዓመት ኢትዮጵያውያን ወደ ከፍታ መውጣት እንደጀመሩ ያሳዩበት ታሪካዊ ወቅት ነው። ወትሮ በአትሌቶቻችን ብቻ ይነሳ የነበረው ስማችን ዛሬ በመሪዎቻችንና በተመራማሪዎቻችንም እየተደገመ በኩራት ሰንደቅ ዓላማችንን ለማውለብለብ አስችሎናል።
ተከብረው ካስከበሩን ጀግኖቻችን መካከል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ አንዱ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በበዓለ ሲመታቸው በፓርላማ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንደሚመጣ በገቡት ቃል መሰረት ሰላም አምጥተዋል።
በሀገር ውስጥ ለዘመናት ተዘግቶ የቆየው የዴሞክራሲ በር እንዲከፈት፣ እስረኞች እንዲፈቱ፣ በውጭ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ተቃዋሚዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲያንሸራሽሩ እና የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ስራዎችን በዚች አጭር ጊዜ ውስጥ አከናውነዋል። ከሀገር ውስጥ ባሻገርም በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። ተሳክቶላቸዋልም።
ኢትዮጵያን ካኮሩና የዘመኑ ፈርጥ ከሆኑት መሪዎቻችን መሃል ደግሞ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ፎርብስ መጽሔት ከ100 የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አንዷ አድርጎ መርጧቸዋል። ፕሬዚዳንቷ ከመቶ የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል የተመረጡ ብቸኛ አፍሪካዊት ናቸው። አምና ጥቅምት ወር ላይ በሀገራችን የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ አገራቸውን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ናቸው። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም በልዩ ልዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሰሩና ሀገራቸውንም በዓለም መድረክ ያኮሩ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ፣ አትሌት ደራርቱ ፣ የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን፤ ‹‹ማሪያም ሳባ›› የተሰኘ የፅዳት መጠበቂያ ምርት የሚያመርት ፋብሪካ በመቐለ ያቋቋመቸው ፍሬወይኒ መብርሃቱ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ የኬሚስትሪ ጀግና ተብለው ለሽልማት የበቁት ዶክተር ሐረገወይን አሰፋና ሌሎችም በየስራ መስካቸው በዓለም መድረክ ደምቀዋል። በአጠቃላይ በፈረንጆቹ 2019 ከሃያ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሸላሚ ሆነዋል። ኢትዮጵያ በከፍታ ጎዳና ላይ እንደሆነችም አሳይተዋል።
ትናንትና ደግሞ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳተላይት በማምጠቅ የከፍታ ዘመን ላይ መሆኗን አስመስክራለች። ስራውን ለመጀመር ከቻይና መንግስት ጋር ስምምነቱ ከተፈረመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሳተላይቷ ለማምጠቅ አራት ዓመታትት በወሰደ ዝግጅት የሳተላይቷን መምጠቅ ማሳካት ተችሏል። ለታዳጊ ሀገራት የቅንጦት ያህል የሚቆጠረው የሳተላይት ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያውያን በይቻላል መንፈስ ዕውን አድርገውታል።
ይህ የከፍታ ጉዞ ቀጥሎ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ሳተላይትን ማምጠቅ ችለናል። በትናትናው ዕለት ኢትዮጵያ ያመጠቀችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወይንም ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት የምትሰበስበው እና የምታቀብለው መረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታን የሚሰጥ እና ከመረጃ ጥገኝነት የሚያወጣ ከመሆኑም በሻገር የዘመናት ምኞት ሆኖ የቆየውን ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎታችንን ዕውን ያደረገ ነው።
በቀጣዮቹ ዓመታትም ኢትዮጵያ ተጨማሪ የመሬት ምልክታ ሳተላይትን የምትልክ ሲሆን ሌሎች የኮሙዩኒኬሽን እና የብሮድካስት ሳተላይቶችን የማምጠቅ እቅድም ይዛለች። ይህ ደግሞ ለዘመናት በሀገራችን ተንሰራፍቶ የቆየው የአይቻልም መንፈስ እየተሰበረ መምጣቱንና ሀገራችንም በከፍታ ማማ ላይ መቆናጠጥ መጀመሯን የሚያሳይ በመሆኑ አገራዊ ሰላማችንን በማረጋገጥ በሁሉም ዘርፎች መሰል ጥረቶችን በማድረግ ሀገራችንን ወደ ከፍታው ማማ የማውጣቱ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2012