“ኢትዮጵያ የሠመረ ነገ እንዲኖራት የተጀመሩ ሥራዎችን ማብዛትና ማጽናት ያስፈልጋል”› – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የሠመረ ነገ እንዲኖራት የተጀመሩ ሥራዎችን ማብዛትና ማጽናት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመለከቱ። የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት በንግግር እልባት ማግኘት እንዳለበት አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ክፍል ቃለ መጠይቅ፤ የኢትዮጵያ የሚያጓጓና ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር እንደሆነች በጽኑ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የምንተጋው ኢትዮጵያ የሠመረ ነገ ኖሯት ልጆቻችን ዛሬ ላይ የሚስተዋሉ ችግርና ስብራቶች ተወግደው በታሪክ የሚያወሱት እንዲሆን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የሠመረ ነገ እንዲኖራት ዛሬ ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን ማብዛትና ማጽናት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ሕልማችን እውን እንዲሆን መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ከተሞችን መገንባት፣ የዘመኑ የገጠር አካባቢዎችን መፍጠር፣ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ አምርቶ ለአርሶ አደሩ ማቅረብን ጨምሮ በየዘርፉ ያለውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ መሥራት ነው ብለዋል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል፣ በሁሉም ዘርፍ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዚህም ሰዎች ሳይቸገሩ የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሀገሪቱ ስፔስ ላይ ያላት ተሳትፎም ማደግ እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ከፍታዋን የሚመጥኑና የሚገጥማቸውን ፈተና መሸከም የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትም መገንባት እንዳለባቸው ያብራሩት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በየዘርፉ በሚገኙ ውጤቶች አስፍተን ማስቀጠልን ከቻልን፤ ከልመና የተላቀቀችና ተሰሚነቷ ከፍ ያለ ሀገር እውን ማድረግ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ያለ እረፍት እየሠራን ያለነው የነገዋን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ የነገዋ ኢትዮጵያ ስንልም ሕልም ብቻ ሳትሆን እውን መሆን የምትችል መሆኗን ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶች አመላካች መሆናቸውን አንስተዋል።

ወደኃላፊነት የመጡት ለሀገራቸው የሆነ ነገር ለማበርከት አስበው እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። በየትኛውም መልኩ የሚገኘውን ሀብት፣ ጊዜ እና ጉልበት ኢትዮጵያን ለማበልፀግ እየዋለ እንደሆነም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ወደብ አልባ ሆና የቆየችበት መንገድ በጣም የሚቆጩበት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቁጭታቸው አሁን ኃላፊነት ላይ ሆነው የተጀመረ ሳይሆን ዓመታትን የተሻገረ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ወደብ በማጣቷ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ሌላውን ሳትጎዳ መጠቀም እና ጉዳቷን መቀነስ የምትችልባቸው ዕድሎች እንደነበሩ አንስተዋል።

የተዘጋች ሀገር ዜጋም፤ መሪም መሆን በእጅጉ የሚያስቆጭና እንደሌሎቹ ሀገራዊ ስብራቶቻችን ሁሉ መፍትሔ ማግኘት ያለበት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የተጎዳ እና የተሰበረ ሀገር በዘላቂነት የሰከነ ሰላም ያመጣል ብዬ አላስብም ፤ በወደብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ በታሪክ የሌለ ግፍ ተሠርቶባት፤ ችግሩ በንግግር መፈታት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ነገር የምናራክስበት ሁኔታ በጣም ያሳዝነኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ብዙ ሀገራትን የማየት ዕድል አጋጥሞኛል፤ ኢትዮጵያ የምትራከስ ሀገር አይደለችም፤ ኢትዮጵያውያን የሚራከሱ ሰዎች አይደሉም፤ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን አርክሰን የሌላውን አግዝፈን የምናይበት ልክ ያሳዝነኛል ብለዋል።

ለራሱ ክብር የሌለውና እውቅና የማይሰጥ ትውልድ ሀገር ይለውጣል ብዬ አላምንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሀገሩ ታሪክ የሚኮራ፣ ተነጋግሮ የሚግባባ እና የራሱን የማያራክስ ትውልድ እንዲፈጠር አብዝተው እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You