
ዜና ሐተታ
ታኅሣሥ 14 ቀን 1895 ዓ.ም ምሽት ሁለት ሰዓት የመጀመሪያው ባቡር ከጅቡቲ በመነሳት በርካታ በረሃማና ሞቃታማ አካባቢዎችን አቋርጦ ድሬዳዋ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ይህ አጋጣሚም ለድሬዳዋ ከተማ መወለድ ምክንያት ሆኗል።
በስምጥ ሸለቆ ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ የምትገኘው የድሬዳዋ ከተማ ምሥረታዋ በ19ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን መደምደሚያ ላይ ከተዘረጋውና መዲናይቱ አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋር ከሚያገናኘው የባቡር መስመር ጋር ይያያዛል።
የባቡር መስመሩ እና ከእርሱም ጋር ተያይዞ በከተማዋ እምብርት የተቋቋመው ጣቢያ ለንግድ መቀላጠፍ ትልቅ በር ከመክፈቱም ባሻገር፤ በሺህዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ነበር።
ከጥቂት ዓመታት አንስቶ ግን መስመሩ ለዕድሜ ጫና እጅ ሰጥቶ የወትሮ አገልግሎቱን መስጠት ተስኖት ቆይቷል። ይህም ቀድሞ ይታወቅበት የነበረው ግርግር እና ሞቅታ ርቆት ድብታ ተጭኖት በመታየቱ ብዙዎች ሲቆጩበት ነበር።
የአዲሱ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር እውን መሆን ከጀመረ ወዲህ የከተማዋን የንግድ ማዕከልነት ተስፋ ዳግም እንዲወለድ አድርጎታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንቀላፍታ ከቆየችበት እየነቃች የምትገኘው ድሬዳዋ አሁን ላይ በበርካታ የልማት ሥራዎች ተጠምዳለች። በዚህም ከባቡርና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ባሻገር ተጨማሪ በረከቶች ማግኘቷን ቀጥላለች።
የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የነበረችው ድሬዳዋ የቀድሞ ስሟን የሚያድስ አጠቃላይ ስፋቱ 4 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍንና ከከተማዋ ሦስት እጥፍ ስፋት ያለው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ደረቅ ወደብን አጠቃሎ የያዘው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲሁም ከጅምሩ ውብ ገፅታን እያላበሳት የሚገኘው የኮሪዶር ልማት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ያገኘቻቸው በረከቶች ናቸው።
የምሥራቋ ጮራ በቀጣይ ደግሞ ሌላ ገጽታ የሚያላብሳት የልማት በረከት ይጠብቃታል። ይህም ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የኮንቬክንሽን ማዕከል ነው፣ በንግድ እንቅስቃሴ የምትታወቀውን ከተማ የኮንፍረንስ ማዕከል ሌላ ዕድል ይዞ እንደመጣ ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል።
የከተማዋ አስተዳደር የድሬዳዋን ኮንቬንሽን ማዕከል የግንባታ ፕሮጀክትን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩና ባጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በርብርብ እየሠራ ይገኛል። የማዕከሉ ግንባታ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ካሉ ፕሮጀክቶች ትልቁ፤ በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ የተደረገበት ሜጋ ፕሮጀክት ነው።
በድሬዳዋ አስተዳደር በባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የባህል ጥናትና ጥበቃ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ገበየሁ ወጋየሁ እንደሚናገሩት፣ ፕሮጀክቱ ድሬዳዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ፣ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት፣ የድሬዳዋን ዕሴቶች አጉልቶ ለማውጣትና የፈጠራ ጥበብን ማስተዋወቅና ማጎልበትን ዓላማው አድርጐ በከተማ አስተዳደሩ እየተገነባ ይገኛል ።
የሰላምና የፍቅር ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ የኮንቬንሽን ማዕከል ለመሆን የተመረጠችበት በርካታ ምክንያቶች አሉ የሚሉት አቶ ገበየሁ፣ ከዚህም ውስጥ አንዱ ድሬዳዋ የምሥራቅ ኢትዮጵያ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንትና የባህል ማዕከል ተደርጋ መመረጧ እንደሆነ ጠቁመዋል ። ለጅቡቲ፣ ለሐርጌሳና ለዘይላ ወደብ ቅርብ፤ ለምሥራቅ ኢትዮጵያ አማካኝ ከተማ መሆኗ ከጂኦ ፖለቲካ አስፈላጊነቷ አኳያ ተመራጭ እንዳደረጋትም አመልክተዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ 2009/10 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት አካባቢ የፕሮጀክቱን ግንባታ የጀመረው ተቋራጭ (አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን) በነበረው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ፕሮጀክቱን አቋርጦ መውጣቱን የሚያስታውሱት አቶ ገበየሁ፣ በዚህም ፕሮጀክቱ ለተወሰኑ ዓመታት ለመዘግየት እንደተገደደ ይናገራሉ።
ያለው አመራር ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላም ረጅም ጊዜ ወስዶ ፕሮጀክቱን ከመጀመሪያ አንስቶ ያለበትን ችግር ገምግሞና ለይቶ አስፈላጊውን ሀብት በመበጀት ለአዲስ ተቋራጭ ሥራውን መስጠቱን አስታውቀዋል ።
“ፕሮጀክቱ በአስተዳደሩ አቅም እየተሠራ የሚገኝ ነው።” የሚሉት አቶ ገበየሁ፣ የአፍሪካ ኅብረትና የጅቡቲ አዲስ አበባ ምድር ባቡርን የገነባው ዓለም አቀፉ ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CCECC) ኩባንያ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኝ ተቋራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የግንባታው አፈፃፀም ከግማሽ በላይ መጠናቀቁን አመልክተው፣ ዲዛይኑን/ንድፉን ሆነ የማማከር ሥራው ሀገር በቀል በሆነው፤ ኢቲጂ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።
እንደ አቶ ገበየሁ ማብራሪያ፣ የኮንቬንሽን ማዕከሉ አጠቃላይ የመዋቅር (physical) ግንባታው ከሞላ ጎደል ተጠናቋል። ፕሮጀክቱ ውስብስብ እንደመሆኑ የኢንተሪየር/ፊኒሺንግ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው። የፕሮጀክቱ ከፍተኛ ወጪም ይሄ ነው።
ማዕከሉ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች እንዳሉት አመልክተው፣ የአዳራሾቹ ግንባታ፤ በተለይ የዲጂታል ኮንፍረንስ ኔትዎርክ ዝርጋታ ሥራዎች ጊዜና ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን አመልክተዋል። የኢንተሪየር ሥራዎች ለማከናወን አብዛኛው ቁሳቁስ የሚመጣው ከውጪ ሀገር መሆኑንም አስታውቀዋል።
“ለዚህም ግንባታውን ከሚያከናውነው ተቋራጭ፣ ከአማካሪው ኩባንያና ከባለድርሻ አካላት የተቋቋመ የቴክኒክ ቡድን በቅርቡ ወደ ቻይና የሚጓዝ ይሆናል። አብዛኛው የኢንተሪየር ሥራም እዚያ ተጠናቆ ቁሶቹ ወደ ሀገር ከመጡ በኋላ ባጭር ጊዜ ተገጥመው ማዕከሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ድሬዳዋን በጎበኙበት ወቅት ፕሮጀክቱን ተመልክተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገበየሁ፣ “ይሄን ፕሮጀክት ባጭር ጊዜ ጨርሳችሁ ለአገልግሎት ካበቃችሁ ኮንፍረንስና ጉባዔ እዚህ እናደርጋለን” ብለው ቃል መግባታቸውን ገልፀው።
ይህም ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ተነሳሽነትን እንደፈጠረ፤ በዚህም በአመራሩና በባለድርሻ አካላት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል ።
ፕሮጀክቱ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደመሆኑ ብዙ ተግባርና አገልግሎቶችን ይሰጣል። የኮንፍረንስ ቱሪዝም ሲታሰብ የኮንቬንሽን ማዕከሉ ከሁለት ሺ እስከ ሦስት መቶ ሰው የሚይዙ ሦስት ትልልቅ የስብሰባ አዳራሾች ይኖሩታል ብለዋል።
እነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾችም በአምስት ቋንቋዎች ቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ እንዲችሉ ተደርገው የሚገነቡ መሆኑን አመልክተው፤ አረብኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ሶማልኛ፣ አማርኛና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ እንደሚችሉ፤ በቀጣይም በአፍሪካ ብዙ ተናጋሪ ያላቸው ስዋሂሊና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን የማካተት እቅድ እንዳለ አቶ ገበየሁ ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር የኮንቬንሽን ማዕከሉ በተለይ የፈጠራ ጥበብን ለማበረታታት ትልቅ ዕድል ስለሆነ በውስጡ ቤተ መጽሐፍ፣ የፎቶ ግራፍ ጋለሪ፣ ሙዚየም፣ የቢዝነስ ሩሞች፣ ሁለት አይነት ቪአይፒ ላውንጆች፣ ሬስቶራንትና ሌሎች ክፍሎችን አካቶ እንደተገነባ አቶ ገበየሁ ይዘረዝራሉ። ከ120-130 የሚሆን ከወለል በታች መኪና ማቆሚያ እንዳለውም ጠቁመዋል ።
ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ድሬዳዋ ላይ ረጅም ዓመት የኖሩ የከተማዋ ወዳጆች፣ ባለሀብቶችና አመራሮች ስኬትና ተሞክሯቸውን ለወጣቱ ትውልድ የሚያስተላልፉባቸው ፕሮግራሞችን ወደ ፊት እንዲያስተናግድ ሰፊ እቅድ መኖሩን፤ ከዚህ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ፊልምና ቲያትሮችን ለማበረታታት ራሱን የቻለ አንድ ክፍል እንዳለው አስታውቀዋል ።ይህም የከተማው ሕዝብ ፊልምና ቲያትር ገብቶ ማየትና ኪነ ጥበብን የማበረታታት ባህልን እንዲያዳብር እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም