በከተማዋ በተሠሩ ሥራዎች ሴቶች ግንባር ቀደም ሚናቸውን ተወጥተዋል

አዲስ አበባ፦ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ በተሠሩ ሥራዎች ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ። ከፊታችን ያለው ጊዜ ብሩህ ተስፋ የሞላበት፤ በእምነት የነገውን ብልፅግና ለማሳካት የምንጥርበት እና ስንቅ የምሰንቅበት መሆኑንም አመለከቱ።

“የሴቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ የሴቶች መድረክ ማጠቃለያ ውይይት ላይ ከንቲባ አዳነች እንዳስታወቁት፤ መንግሥት ከሴቶች ጋር በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና በመመካከር ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ሥራዎች ሠርቷል።

ሴቶች በሀገርና ትውልድ ግንባታ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ በተሠሩ ሥራዎች ሴቶች ግንባር ቀደም ሚናቸውን መወጣታቸውን አስታውቀዋል።

ለውጥ የጥረት ውጤት ነው፤ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት መንግሥት ከሕዝብ ጋር በትብብር እየሠራ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ሴቶች ከሃሳብ ጀምሮ እስከ ተግባር በልማት እንዲሳተፉ ለማስቻል መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ሴቶች ለሀገራቸው ጉዳይ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን አመልክተው፤ ከፊታችን ያለው ጊዜ ብሩህ ተስፋ የሞላበት በእምነት የነገውን ብልፅግና ለማሳካት የምንጥርበትና ስንቅ የምሰንቅበት ነውም ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያን ጨምሮ የገበያ ማዕከላት እንደሚስፋፉ እና በቅርቡም ሁለት የገበያ ማዕከላት ተመርቀው ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

የቤት ችግርን ለመቅረፍም የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡ መሆኑን አንስተው፤ በመድረኩ የተነሱ ሌሎች ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሠራ እና እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በተለይም በሚቀጥለው ዓመት የመጠጥ ውሃና የቤት አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አመልክተዋል።

የማያግባቡ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በሠለጠነ መንገድ ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ ሴቶች እንደ ሁልጊዜው ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ እና ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው፤ በመድረኩ እንደ ችግር የተነሱ ጉዳዮችን በቀጣይ በጀት ዓመት በእቅድ ተካትተው ምላሽ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

በመድረኩ የተወከሉ ሴቶች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄያዎችን አቅርበዋል። በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪዶር ልማትና የተማሪዎች ምገባን ጨምሮ የዜጎችን በተለይም የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን አድንቀዋል፤ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም የልማት ሥራ ውስጥ የሴቶች ተሳታፊነት ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ይበልጥ የሚያስደስት ነውም ብለዋል። ከኑሮ ውድነት፣ ከመኖሪያ ቤት ችግር፣ የሥራ ዕድል እንዲሁም ከጤና መድኅን ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ ከመዲናዋ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተወከሉ ሴቶች ተሳትፈዋል ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You