ከሳምንት በፊት ከአትላንታ ከተማ የሚሰራጨው አድማስ ራዲዮ እንዳስደመጠው የ 34 ዓመቷ ኮረዳ ሳራ ኤድዋርድ እና የ36 ዓመቱ ጎረምሳ ፖል ኤድዋርድ ከገና በዓል 15 ቀን ቀደም ብሎ በአንድ የተፈላላጊዎች አገናኝ ድህረገጽ (ዴቲንግ ዌብሳይት) ላይ ተዋወቁ። በድህረገጽ ከተዋወቁ ከአንድ ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ አወሩ። በማግሥቱም እንደገና በስልክ አወሩ፡፡ በዚህ ወቅት ግን ምንም ሳያመነቱ ለመጋባት ተስማሙ። ልብ በሉ እስካሁን ገና አልተያዩም፡፡ ሰርጋቸውን የገና በዓል ዕለት ለማድረግ ቆረጡ፡፡ ቬጋስ ወስጥ ከሚገኘው ቤላጂዮ ሆቴል የሠርግ አዳራሽ ተከራዩ፡፡ በሰርጋቸው ላይ እንዲገኙ የሚያውቋቸውን ሰዎች ሁሉ ጠሩ፡፡ እነርሱ ግን አሁንም ገና አልተያዩም።
የገና ዕለት በእንግሊዙ ጋትዊክ አየር ማረፊያ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ፡፡ በዕለቱ እርሱ በሱፍ ልብስ ተውቦ፣ እርሷም በሙሽራ ልብስ ተንቆጥቁጣ በአየር ማረፊያው ለመጀመሪያ ጊዜ ተያዩ፡፡ ከዚያም የሰርግ ስነስርዓታቸውን ለማከናወን በቀጥታ ወደ ቬጋሱ ሆቴል በረሩ።
ሳራ ብዙዎችን ስላስገረመው ጥምረታቸው ምን እንደሚሰማት ስትገልጽ ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ስናወራ ነው አንዳችን ለአንዳችን የምንሆን መሆኑን የተረዳነው›› ብላለች ፡፡ ጥንዶቹ በዙሪያቸው ያሉ የቅርብ ሰዎቻቸው ክስተቱን እንዴት እንደተመለከቱት ተጠይቀው ‹‹የሚያውቁን ሰዎች ይህ የእብድ ሃሳብ ነው ብለውናል፡፡ ነገር ግን ፍቅር በጊዜ እርዝመት ብቻ አይለካም፡፡ እኛ ገና ስናወራ ተዋደናል፡፡ ስንተያይ ደግሞ ባሰብን፤ ሠርጋችንም ያማረ ሆነ ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
እጃችሁን በአፋችሁ ጭናችሁ ተገረማችሁ ? እንደኔ ያን ያህል ባትገረሙ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ያነሳነው ጉዳይ ለኛ (ለወግና ባህል አጥባቂዎቹ) ብዙም ሩቅ አይደለም፡፡ ትዳርና ፍቅረኛ እናገናኛለን ብለው ንግድ ፈቃድ ያወጡ ደላሎች በእጅ ስልኮቻችን ሰላሳ መልዕክቶችን እየላኩ ለኛ ሶስት ጉልቻ ለራሳቸው ደግሞ እንጎቻ ለማስገኘት ላይ ታች እያሉ ነው፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ራሳቸውን ኤጀንሲ እያሉ መጥራት ጀምረዋል፡፡ እኔም ስለመንደሬ ደላሎች የማወራ ተደርጌ ከምቆጠር ኤጀንሲ የሚለውን ስማቸውን አጽድቄላቸው ስለኤጀንሲዎች ነው የሚያወራው መባል ፈልጌያለሁ፡፡ ስለዚህ ኤጀንሲ እያልኩ ጨዋታዬን እቀጥላለው፡፡
አሁን አሁን ትዳር አገናኝ ኤጀንሲዎች በሀገራችን እየተስፋፉና ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን የሚቃወሙ መንፈሳዊያን ክስተቱን የስምንተኛው ሺህ የመጨረሻ ምልክት አድርገው እስከመቁጠር እየደረሱ ነው፡፡ በዚህ ሀሳብ የማይስማሙ ብዙሃን ደግሞ ‹‹ጥንትም ቢሆን በሀገራችን ወላጆቻቸው ‘ልጅህን ለልጄ’ ተባብለው ባሰሩት ቃል ኪዳን ታስረው አሊያም የወላጆቻቸውን ፈቃድ ለመፈጸም ብለው የማይተዋወቁ ጥንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ በተያዩበት ዕለት ተጋብተው ሰላሳና አርባ ዓመት በፍቅር ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ ተያይተው የማያውቁ ሰዎች በትዳር አገናኝ ደላሎች ትዳር መመስረታቸው ለምን ያስገርማል? እንደውም የዛሬዎቹ ተጣማሪዎች መስፈረት አውጥተው የሚፈልጉትን ሰው መርጠው ነው የሚጎዳኙት›› ሲሉ መንፈሳዊያኑን ይሞግታለ፡፡
እኔም ኤጀንሲዎቹን ደግፈው ከቆሙት ሞጋቾች አንዱ ሳልሆን አልቀርም፡፡ ሳስበው በተለይ ለወንዶች የትዳር አጋር ለማግኘት ተንከራቶ ፤ አጥንቶ፤ ደጅ ጠንቶ ፤ አግባብቶ እና አዝናንቶ ብዙ ጊዜ ፈጅቶ በመጨረሻ ሽማግሌ ከመላክ ይህን ሁሉ ጣጣ ራሱ ጨርሶ ሚስት ለሚያቀርበው ትዳር አገናኝ ኤጀንሲ መልእክት መላክ ይቀላል፡፡
እነዚህ ትዳር አገናኝ ኤጀንሲዎች ባለ አራት ዲጅት የስልክ መስመር ባለቤቶች ናቸው፡፡ ታዲያ ስልካቸውን ማስተዋወቅ ይችሉበታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተገኘ ክፍት ቦታ ሁሉ ሕንጻ እንደሚደነቀር እነርሱም ባገኙት ክፍት ቦታ ሁሉ ስልክ ቁጥራቸውን ይለጥፋሉ፡፡ ጥናት ቢሰራ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ባለ ሶስት ዲጅት ስልክ ቁጥር ይልቅ የኤጀንሲዎቹን ባለ አራት ዲጂት ስልክ ቁጥር በቃሉ መውጣት እንደሚቀለው የሚረጋገጥ ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ ተፈላላጊዎችን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች ደግሞ ሰዎች ትዳር እንዲመሰርቱ የሚያግባቡበት መንገድ ፈግግ ያደርጋል፡፡ የዶላር ምንዛሬ ከፍ እንዲል በተደረገ ሰሞን አንድ ትዳር አገናኝ ደንበኞች ለማግኘት ማስታወቂያ በሚለፍፍበት የፌስ ቡክ ገጹ ‹‹ ውድ የፔጃችን ተከታዮች ዛሬ ምን ያህል ትዳር አስፈላጊ መሆኑን የተረዳንበት ቀን ነው። ምክንያቱም በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሰማችሁት የውጪ ምንዛሬ ሰማይ ነክቷል።_ስለዚህ መረዳዳቱ ነው የሚሻለው፡፡ አዎ ትዳር ነው መድሃኒቱ_” ብሎ የእለቱን የምንዛሬ መረጃ በዝርዝር አቅርቦ ነበር፡፡
የኛ ሀገሮቹ ኤጀንሲዎች እንደ ውጭ ሀገሮቹ ተፈላላጊ አገናኞች ስራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም የደንበኞቻቸው መስፈርቶች አንድ ሺ አንድ ናቸው፡፡ ዕድሜ፣ ቁመት፣ ክብደት፣ ቀለም፣ብሔር፣ባህሪ፣ ሰፈር፣ ሃይማኖት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የስራ አይነት እና ደሞዝ አንድ በአንድ ተጣርተው ነው ትዳር የሚሸመተው፡፡ የሚገርመው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ መስፈርት አውጪዎቹ ትዳር ፈላጊዎች የትዳር አጋር እንዲሆናቸው የሚፈልጉት ሰው ማሟላት አለበት ብለው ከሚዘረዘሩት ነጥብ አንዱን እንኳን ራሳቸው ላያሟሉ ይችላሉ፡፡ ቁመቱ በሽቦ አልጋ ስፋት ሜትር ከሃያ የሆነ ትዳር ፈላጊ ተጣማሪዬ ሜትር ከሰማኒያ የምትረዝም ካልሆነች ሞቼ እገኛለው ይላል፡፡
የትዳር አገናኞች ትልቅ ፈተና ያለው የትዳር ፈላጊዎቹን አያሌ ፍላጎቶች አንድ በአንድ ፈትሾ ሊጣጣሙ የሚችሉትን ማግባባት ላይ ነው፡፡ ደንበኞቻቸው በብዙ ጉዳዮች ተስማምተው በአንድ ነጥብ ከተቃረኑ የገነቡት ሁሉ የእንቧይ ካብ ይሆናል፡፡ ቅዳሜ ምሽት በቀጥታ በሚተላለፍ የራዲዮ ስርጭት ትዳር ፈላጊዎችን ኦን ላይን አስገብቶ የማይታረቁ ፍላጎቶቻቸው መካከል ገብቶ መከራውን የሚበላው ሰይፉ ፋንታሁን ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ትዳር አገናኝ ኤጀንሲዎችን ለቀቅ አድርገን ስለ ጎብኚዎቻቸው እንጫወት፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ መጥበስና መጀንጀን የጂኒ ያህል የሚፈሩ ድንጉጦች፣ ሰው ቀና ብለው የማያዩ አይንአፋሮች ፣ በቀጥታ ትዳር ውስጥ መግባት የሚፈልጉ ‹‹ጠንቃቆች››፣በትምህርታቸው ጫፍ ለመድረስ በትዳር ዳር የቀሩ ቆብ ጫኞች፣ በባዕድ አገራት ረጅም ዓመታትን ያሳለፉ ተመላሾች ፣ ሞክረው ያልተሳካላቸው ተሸናፊዎች እና በቀደመ የፍቅር ህይወታቸው ‹‹ተጎዳን›› የሚሉ ካሳ ፈላጊዎች የትዳር አገናኝ ኤጀንሲዎች ዋነኛ ደንበኞች ናቸው፡፡
እነዚህ ትዳር ፈላጊዎች አብዛኛውን ጊዜ በሶስት ነገሮች ይመሳሰላሉ፡፡ አንደኛ ጊዜ ማባከን አይፈልጉም፣ ቀጥታ ወደ ትዳር መግባት ነው ዓላማቸው፡፡ ሁለተኛ ‹‹የውስጥ ቁንጅና›› የሚል ዲስኩር አላቸው (የውስጥ ቁንጅና የደም ንጽህና እና የሳንባ፣ የኩላሊት እንዲሁም የጉበት አቀማመጥ ሳይሆን አይቀርም)፡፡ ሶስተኛ ትዳር ፈላጊዎቹ ሴትም ይሆኑ ወንድ በገንዘብ አይደራደሩም፡፡ ጥሩ ገቢ ያለው (ያላት) የትዳር አጋር ነው የሚፈልጉት፡፡ ቤት ፣ መኪና ፣ ንብረትና ተቆጥሮ የማያልቅ ጥሬ ገንዘብ ያለው ተጣማሪ የቀን ህልም የሌሊት ቅዠታቸው ነው፡፡ ሶስት ጉልቻ የሚመሰርቱት ወፍራም እንጎቻ መኖሩን አረጋግጠው ነው፡፡ ይህን የምለው ቁሳዊ ለሆነ ነገር ደንታ የሌላቸው ሰብዕናን የሚያስቀድሙ እውነተኛ ትዳር ፈላጊዎች ቁጥር ትንሽ አለመሆኑን ሳልክድ ነው፡፡
የትዳር ፈላጊዎች መንገድ ቀጥ ያለ በመሆኑ የወንድ ልጅ ደመወዝና የሴት ልጅ ዕድሜ አይጠየቅም ብሎ እጥፍ ለማለት አይመችም፡፡ የወንድ ልጅ ኪስ ይፈተሻል፤የሴት ልጅ ግንባርም ይነበባል፡፡ የኪስን ጉዳይ ቀደም ብለን ስላነሳን እስኪ ስለ ዕድሜ እንጫወት፡፡ የምንኖርበት ማህበረሰብ ጋብቻ የመመስረቻ ዕድሜን በጾታ ለይቶ ሲገልጽ፣ ወንድ ልጅ ምራቁን ዋጥ ያደረገ (ዘሎ ዘሎ የበቃው) መሆን አለበት፤ ሴት ልጅ ደግሞ ክብሯን ጠብቃ የኖረች መሆን አለባት ይላል፡፡ እንግዲህ እንደተባለው ሴቶች ሁሉ ክብራቸውን ጠብቀው ከቆዩ ጋብቻ ለመፈጸም ብቁ ይሆናሉ፡፡ ወንድ ልጆች ግን የት ነው ምራቃቸውን የሚውጡት ? አብዛኞቹ ትዳር ፈላጊ ዕንስቶች ያደጉበት ማህበረሰብ ባህል እስረኞች ናቸውና ለዚህ አስተሳሰብ እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ በዕድሜ በአስርና ሃያ ዓመት የሚበልጣቸውን ወንድ ማግባትን አሜን ብለው ይቀበላሉ፡፡
አንድ ሴት በዕድሜ የምትበልጠውን ወንድ ብታገባ ምን ችግር አለው ? እንደኛ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ችግር አለው አትሉኝም፡፡ እዚህች ጋር አንዲት ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡ አራት ጓደኛሞች ለመዝናናት ወደ ምሽት መዝናኛ ይሄዳሉ፡፡ አንድ ሁለት ሲሉ ይቆዩና ሞቅ ሲላቸው መወዛወዝ ይጀምራሉ፡፡ በመሃል የድምጻዊ ዳዊት መለስ ‹‹ወጣቷ ልጅ›› የተሰኘ ሙዚቃ ሲከፈት የሴት ጓደኛው በዕድሜ የምትበልጠው ጓደኛቸውን ‹‹አንተን አይመለከትህም›› ተቀመጥ ይሉታል፡፡ እርሱም የዋዛ አልነበረምና ‹‹እውቀት የሚገኘው ከቆየ መጽሐፍ ነው›› ሲል መለሰላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
የትናየት ፈሩ