የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ ባለው የቆይታ ጊዜው የተለያዩ መብቶች እና ግዴታዎች አሉት። ከዚህ ውስጥም ንብረት የማፍራት መብት የሚጠቀስ ነው። ይህን ንብረት በምድር ላይ እስካለ ብቻ ነው የሚጠቀምበት። ሕይወቱ ካለፈች በኋላ ይህን ያፈራውን ንብረት በሕይወት ያሉ የሱ የቅርብ ሰዎች ናቸው የሚጠቀሙበት። ለመሆኑ ይህንን ንብረት የመጠቀም መብት ያላቸው እነማን ይሆኑ? በፌዴራል የአቃቤ ህግ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሸዋረጋ ወልደማርያም ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ከውርስ ጋር በተያያዘ ስለ ቤተሰብ ሲነሳ ወራሽ የሆኑ ሰዎች እነማ ናቸው የሚለው ጉዳይ ነው። በዚህ ሂደት በህጉ ቋንቋ አንድ ሰው ወራሽ ለመሆን አውራሹ በሚሞትበት ወቅት በሕይወት ያለ መሆን አለበት።
ቤተሰብ የሚለው ቃል ምን ድረስ እንደሆነ በህጉ በትክክል ባይቀመጥም በአውራሹ ወደ ላይና ወደታች የሚቆጠሩ የቤተሰብ ሰንሰለትን ያካተተ ነው።
በአውራሹ ወደ ታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ወይም ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት ወይም በመግደል ሙከራ የተቀጣ ወይም በሀሰት በመወንጀል ወይም በመመስከር አንደኛውን የሞት ፍርድ ወይም ከአስር ዓመት በበለጠ የፅኑ እሥራት ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ የተቀጣ ከሆነ ከወራሽነት መብት ይገለላል። የዚህ ህግ ዋና ዓላማውም ሰው በጥፋቱ መጠቀም የለበትም ከሚል እሳቤ የሚነሳ ነው።
ከወራሾች መካከል ቤተሰብ አንደኛው ሲሆን፤ በወራሽነት ከሚጠቀሱት የቤተሰብ አባላት የመጀመሪያዎቹ ደግሞ ልጆች ናቸው። ልጆች ሲባል በጋብቻ ውስጥ የተወለዱና ከጋብቻ ውጪ የተወለዱ ናቸው። ይህ ደግሞ የጉዲፈቻ ልጅንም ያጠቃልላል።
ያልተወለደ ልጅ ለመብቶቹ ዓላማ እንደተወለደ ተቆጥሮ የውርስ ባለቤት የመሆን መብት እንዳለውም ህጉ ይደነግጋል። ለምሳሌ አንድ ሰው አባቱ ሲሞት የ7ወር ጽንስ ቢሆን መብቶቹን በተመለከተ እንደወራሽ ይቆጠራል።
በፍትሐብሄር ህጉ ላይ እንደሰፈረው ከተወላጆች ቀጥሎ ወላጆችም ወራሾች ናቸው። ልጅ ከሞተ በምትክነት የልጅ ልጅ ወራሽ ይሆናል። ከዚህ ወጪ ወደ ወላጆች ይሄዳል። ሟች ልጅ ከሌለው እናትና አባቱ የመውረስ መብት ይኖራቸዋል።
በተለምዶ ሚስት ወራሽ ናት የሚባለው ነገር ስህተት ነው። ምክንያቱም ሚስት ካለው ሀብት ውስጥ የጋራ ንበረት የሆነውን ድርሻዋን ብቻ ነው መውሰድ የምትችለው።
ውርስ ተፈጻሚ የሚሆነው በኑዛዜ አሊያም ያለ ኑዛዜ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የቤተሰብ አባላት የሆኑና ልጆች ሳይሆኑ ወራሽ የሚሆኑበት አግባብነትም አለ። መጨረሻ ላይ ወራሽ ያጣ ንብረት በመንግስት ይወረሳል።
ለወራሽነት ብቁ የሚያደርጉ በሕጉ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ እንዲሁም በስመ ወላጅነት ወይም ተወላጅነት ብቻ ወራሽ መሆን አይቻልም። ይልቁንም በሕጉ የተቀመጡትን ወራሽ ለመሆን መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት አለባቸው።
ውርስ ተፈጻሚ የሚሆነውም ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በፍላጎቱ መሠረት ለተተኪዎቹ የሚያስተላልፍበት ሕጋዊ መንገድ ነው። በሌላ በኩል አውራሽ (ሟች) ኑዛዜ ሳያደርግ ሲሞት ወይም ያደረገው ኑዛዜ ፈራሽ በሚሆንበት ጊዜ የአውራሽ ንብረት ለወራሾች የሚከፋፈለው በሕጉ በተቀመጠው መሠረት ያለ ኑዛዜ ውርስ ይሆናል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
አዲሱ ገረመው