ህይወት ረዥም መንገድ ናት። ጉዞዋም ቀጥተኛ፣ ገባ ወጣ፣ አቀበትና ቁልቁለት የበዛበት፤ መዳረሻዋም እሩቅ ሊሆን ይችላል። በህይወት መንገድ ላይ ወደ ሚፈልጉበት የስኬት ቦታ ለመድረስ ወድቆ መነሳት ወይም ስህተት መስራት አንድ አጋዥ የህይወት ምርኩዝ ነው። ነገር ግን ስንቶቻችን ስህተት መስራት ለነገ ስኬትና ጠንካራ ማንነት እንደሚያበቃን እናውቅ ይሆን? ከዚያ ይልቅ ስህተት አለመስራትና ፍጹምነት የጠንካራ ስብዕና መገለጫ ተደርጎ አንቱታን እንደሚያጎናጽፍ ነው የምናውቀው። ሌሎቻችን ደግሞ ከነ ስህተታችን ዘመናትን እንሻገራለን። የዚህ ጽሁፍ ዓላምም በማህበረሰባችን ውስጥ የሚታዩ ስህተቶች እንዲታረሙ ለማሳሰብም ጭምር ነው።
የሰዎችን ደስታና ሃዘን መካፈል፣ ለሰዎች በችግራቸው ጊዜ የአቅምን ማድረግ አብዛኞቻችን ያስደስተናል፤ እርካታም ይሰጣል። ይሁን እንጂ እንደ ልማድ ሆኖ ነገሮችን ሁሉ የምናደርገው ከቀጠሮአችን ዘግይተን ነው።
ከዋናው መንገድ ተገንጥሎ በሚገባ አገናኝ መንገድ ዳር ላይ ነኝ። ሰፈሩ ደግሞ፤ አፍንጮ በር አካባቢ ነው። አንዱን ጓደኛዬን ለማግኘት ከያዝኩት የቀጠሮ ሰዓት 40 ደቂቃዎች ያህል አልፈዋል። በተሰላቸ እይታ ሰዓቴን ተመልክቼ ከወዲያ ወዲህ ጎርደድ ጎርደድ ስል ተንቀሳቃሽ ስልኬ ጠራ። ጓደኛዬ ነበር፤ በማርፈዱ ምክንያት የሚያበሳጩ የቃላት ጥይቶችን ከማዝነቤ በፊት ምን ሊነግረኝ እንዳሰበ ለማዳመጥ ጆሮዬን አዘጋጀሁ።
እናም የቀጠረኝ አርፋጁ ጓደኛዬ በእኔ የጊዜ መብትና ስልጣን ያለው ይመስል የአርፋጅነት ስሜት እንኳን ሳይንጸባረቅበት በተረጋጋ መንፈስ ‹‹የት ነህ›› አለኝ።
ምንም እንኳ የትራፊኩ መጨናነቅ የመዲናችን የየዕለት ግብር ቢሆንም፣ ባልንጀራዬ ወደቀጠሮ ቦታው የመምጫ ጊዜውን አስረዝሞ፣ ቀድሞ ለመነሳት ይሞክራል እንጂ በምንም መልኩ ይዘገያል ብዬ አላሰብኩም ነበር። በወጉ በማላውቀው ሰፈር አቁሞ ከግማሽ ሰዓት በላይ ከቆየ በኋላ ስልክ ደውሎ የተለመደውን ‹‹እየደረስኩ ነው መንገድ ተዘጋግቶ ነው›› የሚል ምክንያት አቀረበልኝ።
ይሄ መነሻ ነው እንግዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያጣውን የቀጠሮ መጥፎ ልማድ ምን ማድረግ ይኖርብን ይሆን የሚል ሀሳብ እንዳቀብል የጋበዘኝ።
በትራፊክ መጨናነቅ፣ በታክሲ ወረፋ ወይም በሌሎች ማኅበራዊ እክሎች ሳቢያ የሚፈጠር የቀጠሮ መዘግየት እንዳለ ባምንም ቀድሞ በመነሳት ማካካስ ይቻላል የሚል ቆራጥ አብዮታዊም በሉት ልማታዊ አቋም ነው የማራምደው። በመሆኑም በቀጠሮ ሰዓት ላለመገኘት የሚቀርብን ምንም አይነት ሰበብ አልቀበልም።
የሀበሻ ቀጠሮ የሚለው ልማዳዊ ጎጂ አስተሳሰባችን ዛሬም ድረስ አብሮን በመጓዝ በተለያዩ የፊልምና የመጻሕፍት ምረቃ ላይ እንዲሁም ህዝባዊ መድረኮች ላይ በተለይ የክብር እንግዳ በመጠበቅ የመርሀ ግብሩን ሥነ ሥርዓት ከተባለው ጊዜ ሲዘገይ፣ ታዳሚው በጥበቃ ሲሰለቸው በየመሀሉ ጥሎ ሲሄድ በተደጋጋሚ አስተውያለሁ።
የቀጠሮ ሰዓት በማያከብረው ላይ ማህበራዊ ቅጣት ቢጣልበት፣ ዘግይቶ ሲመጣ ለመሰብሰቢያ አዳራሹ ኪራይ የወጣውን ወጪ ለማካካስ የሚረዳ የገንዘብ ቅጣት ቢከፍል፣ ወይም ዘግይቶ የመጣ የሚቀመጥበት ቦታ ተለይቶ ቢዘጋጅ እስከዛሬ የሀበሻ ቀጠሮ እያልን ባልዘመርንለት ነበር።
ኧረ ወገን እኛ አንቀላፍተን ስለ ቀጠሮ መዘግየት ስናወራ ዓለም ቀድሞን ጨረቃ ላይ ህንጻ እያስመረቀ ነው። በነገራችን ላይ በማህበረሰባችን ቀጠሮን አለማክበር የግል ግንዛቤ እንጂ፤ ከፍተኛ ትምህርት ወይም ዕድሜን የሚጠይቁ እውቀቶች አይደሉም። ይህ እንደ ህዝብም ትልቅ በሽታ የሆነው ልማድ በራስ ውሳኔ የሚሻሻልና የሚወገድ ድክመት ነው።
የሀበሻ ቀጠሮ የሚለው ብሂል ለረጅም ጊዜ በውስጣችን ከመዋሀዱ የተነሳ የሰዓት፣የቀን፣የሳምንት፣የወርና የዓመት ትርጉሙ ሳይገባን ይኸው ክፍለ ዘመናትን ተሻግረናል። አንዳንዴማ የመኖርና ያለመኖር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በጊዜ ገደብ መሆኑን እንኳን በቅጡ አንገነዘብም እኮ። በየሰከንድ፣ደቂቃና ሰዓት ጥርቅም ወይም ድምር እኮ ነው የኛ ህላዌ የሚወሰነው።
እንደውም በሥነ ህይወት አስተምሮ ሀሰብ የሚሰጡ ሰዎች አፈጣጠራችን ሳይቀር በሰከንድ ውስጥ በሚከናወን አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም ቅንብር መሆኑን ነው የሚናገሩት። በዚህም ምክንያት ጊዜ ትልቅ ትርጉምና ዋጋ እንዳለው አበክረው ይገልጻሉ።
ነጮች አንድን ሥራ ለማከናወን ሥራው የሚፈጀውን ጊዜ ከሰአት አልፎ በደቂቃ ከዚያም አለፍ ሲል በሴኮንዶች ከፋፍለው ወደ ገንዘብ ይለውጣሉ። ለእነርሱ አምስት ደቂቃ ማባከን ከህይወታቸው አንድ ክፍለ ዘመን የተቀነሰ ያህል ቁጭት ይፈጥርባቸዋል። እኛ ደግሞ ጊዜው በራሱ ሽራፊ ሆኖ ‹‹እባካችሁ ተሳፈሩብኝ›› ቢል እንኳን ‹‹ምን ይላል ይሄ የት ሊደረስ ነው፣ ቀስ ብለን እንሄዳለን፣ ምን አጋፋን›› የምንል ትውልዶች ነን።
ከብዙ አመት በፊት የወጣልንን የ ‹‹ሀበሻ ቀጠሮ›› ስያሜ ለማስቀየር ጥረት ባለማድረጋችን ዛሬም እዚያው ነን። ነገስ? ጊዜው ራሱ ይመልሰው።
በብዛት ለሰርገኞች በሚሰጥ የጥሪ ካርድ ላይ ለልጆች ቦታ የለንምና ሰዓት ይከበር የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ይጻፋል። ለዚህም ነው ታዳሚዎች ሙሽራው ከመምጣቱ በፊት አንድ ሰዓት ያህል ቀድመው የሚገኙት። ይሁንና ሙሽሮቹ በጊዜ ባለመገኘታቸው ለምሳ የተጠራው ታዳሚ እስከ እራት ሰዓት እንዲቆይ ይገደዳል። የሚገርመው የዘገዩበትን ምክንያት የሚገልጽም ይቅርታ የሚጠይቅም ኃላፊነት የሚወስድም አካል የለም። በቃ ተለምዷል።
ይህ አይነት ሁነት ታዲያ በሰርግ ብቻ ሳይሆን ህይወታችን በንፍሮ በሚጠናቀቅበት የህልፈት ቀንም ያጋጥማል። በተለይ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ። ‹‹አስክሬኑ›› ቶሎ አይደርስም። ያው እንግዲህ በዚህ አውድ ውስጥ መፍረድ የሚቻለው አስክሬኑን በተሸከሙ ሰዎች እንጂ በሟች አይደለም። በዚህ ወቅት ለቀስተኛው የቀብሩን ሰዓት በመጠባበቅ እንባው ደርቆ ቢገኝ የሟች ቤተሰብ ለምን ለሞተው ዘመዴ አላለቀስክም ብሎ መታዘብ አይገባውም።
ቃሉን የሚያከብር ቀጠሮ አክባሪ ኩሩና ሙሉ ሰው መሆኑን ብቻ ሳይሆን የጊዜ አርበኛነትንም ያስመሰክራል። መዘግየት ልማድ ሆኖበት ያለውን የማያከብር ቃላባይ ደግሞ ውስጡ እንደሚነዝረውና እንደሚሳቀቅ መገመት ከባድ አይደለም። ከዚህ ሁሉ በራሳችን ላይ ሂስ አቅርበን እንታረም። ሰዓት የማክበሩን ባህል ወርሰን እናውርስ። በጊዜው መድረስ የማይቻልበት ብዙ አጋጣሚ ይኖራል፤ ድንገተኛ አደጋ፣ የትራፊክ ጫና፣የመጓጓዣ መስተጓጉል፣ የመሳሰሉት ያልተጠበቁ ደንቃራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በመንገድ ላይ እያሉ አሊያም መንገድ ከመጀመር በፊት ደውሎ ማሳወቅ ይቻላል።
ቀጠሮን አለማክበር ጊዜን በከንቱ ከማሳለፍም አልፎ ለሌላው ሰው ጦስ ሲሆን የምናይበት አጋጣሚም ብዙ ነው። የኛ ሰፈር መደዳውን ቡና ቤት ነው። አንድ ቀን ጠዋት ወደ ክፍለ ሀገር አውቶቡስ ተራ ልሄድ አስር ሰአት ተነስቼ ታክሲ ስጠብቅ፤ አንዲቷን ድሀ ጸጉሩዋን ይዞ መሬት ለመሬት እየጎተተ በግንባሯ ያዳፋታል፤ ከቡና ቤት አውጥቶ አስፋልት ላይ ይረግጣታል። ኡ ኡ እያለች…ገደለኝ እያለች ሊገላግላት የመጣ ወንድ ጠፋ። ሰው ሁሉ ሰምቶ እንዳልሰማ እየሆነ ብቅ አላለም። በስካር መንፈስ እንኳ እነዚህን ሰዎች የሚደፍር ጠፋ? አልኩና ውስጤ በሀዘን ተመታ። ሰዓቴ እስከሚደርስ ሰብዓዊነት ከሚሰማቸው ጋር ተሯሩጠን ፖሊስ ጠራን። በነገራችን ላይ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ አንዳንድ ፖሊሶች ‹‹ኮሚሽን ካልተከፈላቸው›› ዝርም አይሉም። ነገሩን በሌላ የትዝብት ርዕሰ ጉዳዬ እመለስበታለሁ።
የሆነው ሆኖ በጊዜው የመጡ ፖሊሶች ጉዳዩን ሲያጣሩ ልጅቷን በዚያ ውድቅት ሌሊት ቀጥሯት የነበረው ዘመዷ በሰዓቱ ባለመድረሱ ምክንያት እየጠበቀችው ባለችበት ወቅት ነው ለእንዲህ አይነት ጉዳት የተዳረገችው።
በጠዋት ተነስታ ቄጠማውን ጎዝጉዛ፤ አጫጭሳ፤ ቡናውን አቀራርባ፤ ሞቅ ሞቅ አድርጋ ባሏን ለማስደሰት የምትታትር ሚስት ባሏ ስፖርት ስሰራ ቆይቼ ነው በሚል ተልካሻ ምክንያት ዘግይቶ ወደ ቤት ሲገባ አንጀቷ ቅጥል የሚለውንም ቤት ይቁጠረው።
በየትምህርት ቤቱ ግድግዳ ላይ ተለጥፈው የሚታዩ ማርፈድን የሚያወግዙ ጽሁፎችና ጥቅሶች ከአይን እይታ በዘለለ ልብ ላይ ጠብ አላሉም። ዛሬም ብዙ ተማሪዎች አርፍደው በር ላይ ሲተረማመሱ ይታያሉ፤ ዛሬም ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍል ከገቡ ብዙ ደቂቃዎች በኋላ ዘግይቶ የሚገባ መምህር አለ።
ከሁሉም በላይ በውጭ አገር የሚኖሩ ወገኖቻችን ብዙዎቹ ማለት ይቻላል ለሚኖሩበት አገር ሕዝብ የቀጠሮ ባህል ባዕዳና እንግዳ በመሆናቸው ስማችንን በአሉታዊ ስያሜ ያስጠሩናል። እንዳልፈርድባቸው ስብሰባ ሲጠራ አበሻ በሰዓቱ አይመጣም፣ለምን ባዶ አዳራሽ ውስጥ እጎለታለሁ በሚል ማህበረሰብ ውስጥ ነው ያደጉት። በዚህ ምክንያት ልማዳቸው ከአገር ውጭም መንጸባረቁ አልቀረም።
ስብሰባ ትልቅ አገራዊ ወይም ማህበረሰብአዊ ጉዳይን የሚመለከት፣ ችግርን ለማስወገድ የሚደረግ ሲሆን በቦታውና በጊዜው የመገኘት ግዴታ ይጠይቃል። ሆኖም ግን በተደጋጋሚ በየቦታው ሰዓት ያለማክበር ድክመት ይታያል።ለትልቁ ችግር ስናስብ ትንሹዋን የሰዓት አለማክበር በሽታ ግን ማስወገድ አልቻልንም።
<< ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው >> በሚለው አባባል ውስጥ ‹‹ ምልክት›› ነገሮችን ለመጠቆሚያና ለማሳያ የምንጠቀምበት ሲሆን፤ ማርፈድ ግን ከስንፍና አልፎ መድኃኒት ያልተገኘለት በሽታ ሆኗል። እኔም እላለሁ እባካችሁ! በጊዜ ላይ ማግለልና መድሎ ይቅር! ማርፈድ የስንፍና ብቻ ሳይሆን የድህነትም ምልክት ነውና አናርፍድ።
ወገኔ ሆይ ብትሰማ በነጻ ትማራለህ ። ምክርን አልሰማ ብትል ግን በዋጋ እንደምትማር እወቀው ። በዋጋ መማር ግን አድካሚ ደግሞም የሚያስመርር ነው። ብልህ ከሆንህ በሰው ከደረሰው ትማራለህ ፣ ሞኝ ከሆንህ ግን በራስህ ሲደርስ ትማራለህ ።
የሀበሻ ቀጠሮ በሚል ሰበብ ራስን ለማስደሰት የሌሎችን ፍላጎት መጎተት ከኔ ሌላ ላሳር እንደማለት ነው። ለዚህ ሁነኛ መፍትሄው ይሉኝታም ጥሩ ይመስለኛል። ምክንያቱም ይሉኝታ የሚያጠቃቸው ሰዎች ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነት እና ግዴታ በላይ የሌሎችን ጉዳይ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ብዙ ርቀት ይጓዛሉ። ይሉኝታ የራሳችንን ስራና አጀንዳ ወደ ጎን አድርገን ፤ ፍላጎታችንና እና ምርጫችን ተጭነን ሌሎችን ለማስደሰት የመፈለግ ውጤት ነውና።
‹‹አርቆ ማሰቢያ እያለን አእምሮ እንደምን ተሳነን ለማክበር ቀጠሮ… ቸልተኞች ሆነን ወደ ኋላ እንዳንቀር በሁላችንም ዘንድ ቀጠሮ ይከበር›› አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ይህንን ዘፈን ካሰማን ጊዜያት ነጎዱ። አርቲስቱ በነበረበት ዘመን ያስተዋለውን ቀጠሮ ላይ የማርፈድ ችግሮች በጥዑመ ዜማ አሰምቶ ዛሬም ድረስ ነገሩ አለመስተካከሉ ይገርማል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
አዲሱ ገረመው