በጤና የመኖርን ዋጋ መቼም ቀምሰህ እየው አይባልም::ተፈጥሮ ችሮታዋን አብዝታ ከለገሰቻቸው አገራት ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትጠቀሳለች ብትባሉ ልትገረሙ ትችሉ ይሆናል::እውነታው ግን እሱ ነው::
ሌላው አለም ራሱን ከአካባቢው ጋር አዋህዶ በጤና ለመኖር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም::ከአካባቢው ተፈጥሮ እስከ ራሱ ድረስ እያከመ ለመኖር ይውተረተራል::እኛ ደግሞ ተፈጥሮ በለገሰችን ችሮታ ላይ ቅድመ ምርመራ ብናክልበት ኖሮ ጤናማ ሕይወት መኖር እንደምንችል አስባችሁት ታውቃላችሁ? ነገሩን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም::የዛሬው የማህደረ ጤና አምዳችን በዚሁ ዙሪያ ያተኮረ በመሆኑ ነው::ኢትዮጵያውያን ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› ከሚለው የአበው ተረት በዘለለ የቅድመ ምርመራ ባህላችን ምን ይመስላል? ፋይዳውስ ምንድን ነው? አለማድረጋችንስ አደጋ ያስከትል ይሆን? በሚለው ሃሳብ ዙሪያ የባለሙያና የባለጉዳይ አስተያየት አክለን አቅርበናል::
የሕክምና ክትትላቸውን ለማድረግ ተራ ሲጠብቁ በዘውዲቱ ሆስፒታል ያገኘናቸው አቶ ከድር ሸምሴ እንደሚሉት፤ ቅድመ ምርመራ ብሎ ነገርን ማን ያውቀዋል ይላሉ::አሁን ላይ የስኳርና የደም ግፊት ክትትል እንደሚያደርጉ የሚናገሩት አቶ ከድር፤ ቅድመ ምርመራ አድርጌ ቢሆን ቢያንስ እንደዚህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ መከላከል ይቻል እንደነበር ሐኪሞች እንደመከሯቸው ያስታውሳሉ::
አቶ ከድር እንደሚሉት፤ የጤና ማጣታቸው አሁን ላይ ያስቸገራቸው ሲሆን በየጊዜው የስኳር መጠናቸው እንደሚጨምር ይናገራሉ::መድሃኒት እየተከታተሉ በዚህ አይነት ሁኔታ ከአስር አመታት በላይ መኖራቸውን ገልጸው፣ ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ ጤናውን ቢያንስ ባጭር ባጭር ጊዜ ሊከታተል ይገባዋል::አሁን ላይ ምን ችግር አለ? ሰፊ የሕክምና አማራጮች በየአካባቢው ይገኛሉ ሲሉ ይገልጻሉ::
እርሳቸው ይስተዋሉባቸው ከነበሩ ምልክቶች ተነስተው አቶ ከድር ሲናገሩ፤ ‹‹ እኔ ከፍተኛ የውሃ ጥም፣ ቶሎ ቶሎ ብዙ ሽንት መሸናት፣ ከፍተኛ የርሃብ ስሜት፣ ድካም፣ ሀይል ማጣት እና አልፎ አልፎ ከብደቴ ሲቀንስ በግልጽ አስታውሳለሁ::ነገር ግን ምንም መመርመርን አስቤ አላውቅም::እንደ አሁኑ ምቹ ሁኔታ አልነበረም::በዚያ ወቅት መከታተል ችዬ ቢሆን ጥሩ መፍትሄ አላጣም ነበር›› ሲሉ ከተሞክሯቸው በመነሳት ማህበረሰቡን ይመክራሉ፡፡
አቶ ከድር አክለው እንዳሉት፤ እንኳን ብዙ ምልክቶች ሲታዩ ቀርቶ አንድ ሰው ከሁልጊዜው የተለመደ ባህሪው የተለየ ነገር ሲገጥመው ጤናውን ማረጋገጥ ይኖርበታል::ወጣቶች ስፖርት መድሃኒት በሆነበት በዚህ ዘመን ማቋረጥ የለባቸውም፤ አመጋገባቸውንም ማስተካከል ይገባቸዋል ይላሉ::
አሁን በተለይ የሚያሳስበው የወጣቶችና የሕጻናቱ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው በየመንገዱ የሚሸጡ ፈጣን ምግቦች በጤናቸው ላይ ችግር ያስከትላሉ::ከዚህ እንዲቆጠቡ ማድረግ ቤተሰቦቻቸው ይኖርባቸዋል::አሁን በየሐኪም ቤቶች ብትሄድ ብዙ ታካሚዎች ተደርድረው የሚታየው በሌላ በሽታ ሳይሆን እነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሚባሉና በቀላሉ ሊለቁ በማይችሉ በሽታዎች ነው::መፍትሔው እንደምንም ጤናቸውን ቅድመ ምርመራ በማድረግ እንዲያውቁ አድርጎ በቀጣይ በተገቢው እንዲጠነቀቁ ማድረግ ብቻ ነው ሲሉ አቶ ከድር ተናግረዋል::
ማህበረሰቡ የሕክምና ተቋማትን የመጎብኘት ልማዱ በፊት ከነበረው አንጻር በእጅጉ መጨመሩን በመግለጽ ሐሳባቸውን የጀመሩት በአለርት ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለምሰገድ ጫኔ ናቸው::
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በአለርት ሆስፒታል በየቀኑ የሚመጣው የሕብረተሰብ ብዛት በፊት ከነበረው እየጨመረ መጥቷል::ይሄ የሆነው የሕክምና ተቋሙ በሰራው የቅስቀሳ ሥራ ሳይሆን ማህበረሰቡ ስለጤናው ያለው አተያይ እየተሻሻለና እያደገ በመምጣቱ እንደሆነ ይናገራሉ:: ይሁን እንጂ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ እና በሚፈለገው አይነት ነወይ የሚለው ሲነሳ ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሳሉ::
ማህበረሰቡ ቅድመ ምርመራ የማድረግ ልማዱ ብቻ ሳይሆን ሲታመምስ ቶሎ ሳይጎዳ ይታከማል ወይ? የሚለውን ብናነሳ እንኳን ምንም እንኳን ወደጤና ተቋማት የመምጣቱ ልምዱ እያደገ ቢሆንም አሁንም ብዙ መስራት ይጠይቃል::ከገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ለሕክምና የሚመጡት ሰዎች በበሽታው በእጅጉ ከተዳከሙ በኋላ እንደሆነ ዳይሬክተሩ በማሳያነት አንስተዋል፡፡
እንኳን ሳይታመሙ የሚያደርጉት የቅድመ ምርመራ የራስን ጤና የማረጋገጥ ሂደት ቀርቶ ሲታመሙ እንኳን ፈጥነው መምጣታቸው በሕክምናው ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ ሚና ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ አለምሰገድ፤ ታካሚዎች ወደ ሕክምና ተቋም መምጣታቸውን ባፈጠኑት ቁጥር ታክመው የመዳን እድላቸውን እያሰፉት እንደሚመጡ ሊገነዘቡ ይገባል ይላሉ::
ታክመው በቀላሉ መዳን የሚችሉት በሽታዎች እንኳን ታካሚዎች ጊዜ በወሰዱ ቁጥር እያዳከሙ ለሌሎች በሽታዎች በቀላሉ ተጋላጭነትን በማሳደግ ለሞት ያደርሳሉ::የዚህ አይነት ሁኔታ በተለይም ከክልሎች የሚመጡ ታካሚዎች ለረዥም ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድና ሕክምና ማድረግ እንዳልቻሉ የሚያሳዩ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል::
ሰዎች ሥለጤናቸው አስቀድመው ለማወቅ ፈልገው ሙሉ ምርመራ ለማድረግ መምጣታቸው መልካም እንደሆነና ሆስፒታሉም ሊያስተናግዳቸው ሃላፊነት እንዳለበት የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን አሁን ባለው የአሰራር ሁኔታ ሰዎች ታመው ሕክምና ለማድረግም ሆነ ስለጤናቸው ለማወቅ ቅድመ ምርመራ በሚፈልጉበት ወቅት በመጀመሪያ ደረጃ መሄድ የሚገባቸው በአቅራቢቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ እንደሆነ ይገልጻሉ::በጤና ጣቢያዎች ደረጃ መሰራትና መታየት ያልቻሉ እና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጉዳይ የገጠማቸው ታካሚዎች ብቻ ወደ ሆስፒታሎች በደብዳቤ እንደሚላኩ ገልጸዋል::ይሄ የሆነበት ምክንያትም ሆስፒታሎች ከመላው አገሪቱ የሚመጡ ታካሚዎችን የሚያስተናግዱ በመሆናቸው የሚፈጠሩ አላስፈላጊ መጨናነቆችን ለማስቀረት ሲባል እንደሆነ አቶ አለምሰገድ አብራርተዋል::
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ሕብረተሰቡ ባሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቃባቸው የሚገኙ ውስን የበሽታ አይነቶች መኖራቸውን ያነሳሉ::ከእነዚህ መካከልም ኮሌስትሮል፣ የደም ግፊት፣ ሥኳር እና የመሳሰሉት በሽታዎች ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ መቆጣጠር የሚቻልባቸው ሰፊ እድሎች በመኖራቸው ቅድመ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ::በዚህ ረገድ ሲታይ የሕብረተሰቡ ልማድ የተሻሻለ ነው ተብሎ የሚወሰድ እንዳልሆነና ብዙ እንደሚቀረው አስረድተዋል::
ሰዎች በጤናቸው ሆነው የመምጣት ልምድ የላቸውም፤ ነገር ግን ጥርጣሬዎች ሲያድሩባቸው ለዚያውም በተደጋጋሚ ከሆነ ነው መጥተው ሊታዩ የሚደፍሩት ይላሉ::በመሆኑም ማህበረሰቡ በጤናው በኩል የሚያደርጋቸው ቅድመ ምርመራዎች ከሚደርስበት አደጋ ይታደገዋል::ለበሽታዎች ተጋላጭ ከሆነም በቀላሉ ለመቆጣጠር እድሎች ያገኛል ብለዋል::
አቶ ዓለምሰገድ እንደሚሉት ሰዎች “በድንገት አረፍ እንዳለ እኮ ነው የሞተው” ሲባል መስማት እየተለመደ መጥቷል::ቅድመ ምርመራ የማድረግ ባህሉ አናሳ በመሆኑ በድንገት ለሞት በሚዳርጉ በሽታዎች መያዛቸውን ጭምር ሰዎች አያውቁም::በዚህ የተነሳ እንደወጡ መቅረት ይመጣል::ሥለዚህ በዚህ ዘመን የአኗኗር ሁኔታን ከማስተካከል ጀምሮ ክብደትን በመቆጣጠር ቢያንስ በአመት ሁለት ጊዜ አጠቃላይ የጤና ሁኔታን ተመርምሮ ማወቅ አስፈላጊ ነው::
በደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ የደጎሎ ጤና ጣቢያ ዳይሬክተሩ አለሜነህ ዳምጠው በበኩላቸው፤ ማህበረሰቡ ሳይታመም ወደ ጤና ጣቢያዎች በራሱ ፈቃድ በመምጣት ቅድመ ምርመራ የማድረግ ባህሉ አነስተኛ መሆኑን ተናግረው፤ አንድ ሰው የሕመም ስሜት ሲሰማውና በሚታመምበት ወቅት ግን ወደ ጤና ጣቢያዎች የመምጣት ባህሉ ጨምሯል ይላሉ::ሕብረተሰቡ ጤናውን ቅድመ ምርመራ በማድረግ የማወቅ ልምድ ቢኖረው በድንገት ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች ራሱን የመከላከል እድል እንዳለው የሚናገሩት የጤና ጣቢያው ዳይሬክተር፤ የበሽታው ሁኔታ ለከፋ ደረጃ ሳይደርስ መቀነስ በሚቻልባቸው አማራጮች ሁሉ በመጠቀም በሙሉ ጤንነት መደበኛ ሕይወታቸውን ያለ አንዳች ችግርና ሥጋት የሚመሩበት ሁኔታ እንደሚኖርም ያስረዳሉ::በተለይም እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ቅድመ ምርመራ ማድረጋቸው አስፈላጊና ተማራጭ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
ሙሐመድ ሁሴን