ሀገሩን የሚወድ ማኅበረሰብ መሪዎቹን መልሶ ይመራል ይባላል፤ ግዴታውን እየተወጣ መብቱንም ያስከብራልና! ሁላችንም የተሳፈርነው በአንዲት መርከብ ውስጥ ነው፤ ለመርከቧ ትክክለኛ ጉዞ የየድርሻችንን ካልተወጣን፣ የመርከቧ አቅጣጫ ወደተቃራኒው ይሆንና፣ ጉዟችን ይጨናገፋል፡፡
ጥቂት ሰዎች የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም በስህተት ጎዳና ሊመሩን ሲፈልጉ ድርጊታቸውን በጋራ በማስቆም «አይቻልም» ማለት አለብን፡፡ ሁላችንም ሀገራችንን እንወዳለን፤ ሁላችንም ሕዝባችንን እናከብ ራለን፡፡ መርጠን፣ ፈቅደንና ወደንም ባይሆን፣ ሁላችንም በዚህች እናት ምድር ተፈጥረናል፤ ከከርሰ ምድሯ በቅለን፣ ከአፈሯ ተፈልፍለን ወጥተናል፡፡ በዚህ ምክንያት አንተ ትብስ አንች ትብሽ በሚለው የመተሳሰብ እሴታችን እየታገዝን በመኖር፣ የሀገራችንን አንድነትና እድገት ማስጠበቅ ይገባናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከ ዛሬ በመተባበርና በመተጋገዝ፣ የሀገራችንን ደስታም ሆነ መከራ ተጋርተን በፍቅር ተቻችለን ኖረናል፡፡ ይህ በዚህች ምድር ላይ በሕይወት እስካለን ድረስ፣ በሰውነትና በዜጋነትም ጭምር፣ መልካም ማኅበረሰባዊ ትስስር ሆኖ ይቀጥላል፡፡
በትውልድ ቅብብሎሽ ካገኘናቸው ብርቅ ሀገራዊ አሻራዎችና መዛግብት እንደምንረዳው፣ እኛ የዚህች ሀገር ዜጎች፣ በሥልጣኔ ታላቅ ሕዝቦች ነበርን፡፡ በጥንታዊው የሰው ልጆች ረጅም ታሪክ ውስጥ ሌሎች ዓለማት ዛሬ በሚገኙበት ቅርጽና ደረጃ ከመገኘታቸው በፊት፣ ኢትዮጵያ በብዙ ሁኔታ ቀድማ የነበረች፣ ሰው የተባለው ፍጡር መገኛ የሆነች…ምድር ነበረች፡፡ የኛ አያት ቅድመ አያቶች በአስተሳሰብ ልዕልና የተሻገሩ፣ በጥበብ፣ በሥነ ፈለክ፣ በአርክቴክት፣ በጥንታዊ ምህንድስና የተጠበቡ፣ በመድኃኒት ቅመማና በሥነ ጽሑፍ እና በሌሎችም ዕውቀቶች የተመራመሩ…ኃያል ሕዝቦች ነበሩ፡፡
ቀደምቶቻችን በጦር ጀግንነትም ቢሆን ተወዳዳሪ ስላልነበራቸው፣ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ የነበሯትን ግዛቶች፣ በስፋትም በርዝመትም በማስጠበቅ፣ ከዛሬው የበለጠ ርቀት የነበራቸውን ግዛቶች ታስተዳድር እንደነበር ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ይሁን’ንጅ፣ በየዘመናቱ በተፈራረቁባት የውጭ ጠላቶቿና የውስጥ ልጆቿ አለመስማማት ምክንያት፣ ያንን ገናናነት አስጠብቃ ለመዝለቅ ትልቅ ተግዳሮት እንዳጋጠማት እንመለከታለን፡፡ ይሁን’ንጅ፣ እኛ የዚህ ትውልድ ተዋናዮች ይበልጥ ለሕግና ለሥርዓት የተገዛን፣ ለሥራና ለምርታማነት የተጋን፤ ከኛ የተሻለ ትውልድ ለመተካት በቁጭት የተነሳሳን፣ ጊዜያችንን በአግባቡ እየተጠቀምን፣ ሞትን በመልካም ተግባር የቀደምን…ቀናኢ ዜጎች በመሆን በቁጭት መነሳሳት ይገባናል፡፡
አዎ! ጥንት በሥልጣኔ ከዓለማት በፊት ነበርን፤ ዛሬ ግን ርሀብና በሽታ የሚያንገላታን ጉስቋላ ማኅበረሰብ ሆነናል፡፡ ውብ ሀገር ይዘን፣ ነገር ግን በሥንፍና እና በግዴለሽነት እጅ ከወርች ስለተጠፈርን፣ ለዕለት ጉርሳችን ሳይቀር የሌሎች ችሮታ ጠባቂ ሆነናል፡፡ ይህም ሳያንሰን አንዳችን ላንዳችን ሴራና ተንኮል እየጠነሰስን፣ ገዳይና ሟች፣ አባራሪና ተባራሪ፣ አሳዳጅና ተሰዳጅ ሆነን፣ የዓለም ሕዝብ መሳለቂያ ሆነናል፡፡ ጥቂቶቻችን የሕዝብ ሀብት እየዘረፍን፣ ነጋ ጠባ በጥጋብ እናገሳለን፤ አብዛኞቻችን ግን የዕለት ጉርስና መጠለያ ጥግ አጥተን፣ በችጋር እንቆራመዳለን፤ግን ለምን?
ድሮ የምናውቀው፣ ሰው ከባዕድ ሀገር በሌሎች ዜጎች ተገዶ ተሰደደ የሚባለውን «ተረት» ነበር፡፡ ዛሬ ግን በዚችው የራሴ በምንላት ሀገር ተወልደን፣ ነገር ግን ተሰምቶ በማይታወቅ ጭካኔ፣ ከገዛ ሀገራችን፣ ከኖርንበት መንደራችን እና ቀያችን፣ በራሳችን ወገኖች «መጤ» በመባል እየተፈናቀልን ተሳዳጅ ሆነናል፤ግን ለምን?
ወገኖቼ ሆይ ግንሳ! ወዴት እያመራን ይሆን!? ይህች ሀገር ጥንት «የተቀደደ ሰማይ የሚሰፉ» አስታራቂ ሽማግሌዎች ያልነበሯትን ያህል፣ ዛሬ «ሀይ» ብሎ የሚገስጸን «አንችም ተይ፣ አንተም ተው…» ብሎ የሚገላግለን ሽማግሌ አጥተን፣ እርስ በእርሳችን እንጠፋፋለን፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሚባል ሰዋዊ ባሕርይ ጎድሎብን፣ ሌላው ቀርቶ ሴቶችን እና ሕጻናትን ሳይቀር የጭካኔያችን ሰለባ እናደርጋለን፡፡ ይህ ትልቅ ማኅበረሰባዊ ውድቀት ነውና በአፋጣኝ መታረም ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ቢጠቀስ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ያደርገው ይሆናል፡፡
መንገድ ላይ የመሸባቸው ሁለት ጓደኛሞች ጫካ ውስጥ ተኝተው ሳለ፣ አንደኛው «ኸረ! ምንድን አውሬ ነው? የሆነ ድምጽ ይሰማኛል» ቢለው፣ ጓደኛውም መልሶ «ዝም ብለህ ተኛ፣ አንድ ጅብ መጥቶ የኔን እግር እየቆረጠመ ነው» አለው ይባላል፡፡ ከሩቅ በሚመስለን ርቀት በወገኖቻችን ላይ ጥቃት ሲደርስ፣ አብዛኞቻችን «በኔ ካልደረሰ ምን ከዕዳዬ…» ብለን በቸልታ ተመልክተናል፡፡ ይህን መጥፎ የጭካኔ መንፈስ፣ በአንድነት ሆነን በመመከት፣ ማስቆም ሲገባን፣ በችልታና በታዛቢነት ብቻ ከተውነው፣ ነገ ስለራሳችን ደኅንነት ዋስትና እናጣለን፡፡
ተደጋግሞ እንደሚባለው፣ በመግደል፣ ወገንን በማሳደድ፣ ጀግንነት አይገኝም፡፡ ይልቁንስ ጀግንነት ማለት በዚች አጭር ዕድሜ ለራስም ሆነ ለወገን በጎ ሥራ ሠርቶ፣ የኅሊና ነጻነትን መጎናጸፍ ነው፡፡ ጀግንነት ማለት ከራስ በላይ ስለሌሎች በማሰብ የጋራ ደኅንነትን ማረጋገጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ መኖር ማለት ለራስ ኖሮ፣ ራስን ብቻ አስቀድሞ፣ የዕድሜ ጣራ ሲጠናቀቅ ያለምንም አሻራ ማለፍ፣ ከሆነ ምኑን ሰው ሆንነው? ቢያንስ ከእንግዲህ ሁላችን ኢትዮጵያውያን «ይህ ማኅበረሰባዊ ውርደትና ግለሰባዊ ጉስቁልና ይብቃን» ብለን በቀናይነት መነሳት አለብን!
ከእንግዲህ እኛ ኢትዮጵያውያን ሌብነትንና ዝርፊያን ተጸይፈን በምንሠራው መልካም ሥራ፣ከኛ አልፎ ለወገኖቻችን የመልካም ኑሮ ምክንያት ሆነን መቆም ይኖርብናል፡፡ ከእንግዲህ በምናከናውነው መልካም ተግባር፣ የምንወዳትን ሀገራችንን እና ሕዝባችንን፣ ወደላቀ የእድገት ደረጃ በማሸጋገር፣ ከፍ ወዳለ እድገት ማብቃት አለብን፡፡
ሁላችንም ዜጎቿ ከምንቸገረኝነት እና ከተለያዩ ማኅበረሰባዊ ሳንካዎች ተላቀን፣በተሻለ የሞራል ከፍታ፣ ወደፊት እየተራመድን፣ የሀገራችንን የታላቅነት ታሪክ ለመመለስ የሁላችንም የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡ ወገኖቼ! እኛ ጉዞውን በዚህ መልክ ካልደገፍን፣ ሀገርኮ በምኞት አያድግም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
ውዳላት ገዳሙ