ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ዓለም በሁለት ጎራ የተከፈለበት ነባራዊ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በተለይ በቀዝቃዛው ጦርነት የአሜሪካና የወቅቱ ሶቪየት ህብረት ትልቅ ፉክክር ውስጥ የነበሩበት ሁኔታ እንደነበር ድርሳናት ያወሳሉ፡ ፡ ከነበረው የፉክክር ሜዳ ውስጥ አንዱ ደግሞ ቴክኖሎጂ ነበር፡፡ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ደግሞ በሁለቱ ሃያላን አገራት መካከል ትልቅ ግምት የሚሰጠው የውድድር ሜዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በዚህ ፉክክር ውስጥ የመጀመሪያውን ሳተላይት በማምጠቅ የተሳካላት ደግሞ ሶቪየት ህብረት ነበረች፡፡ በ1957 “ስፑንቲኒክ” የተሰኘውን የመጀመሪያውን ሳተላይት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ጥቅምት 4 ቀን 1957 ወደህዋ ስታመጥቅ አሜሪካም ይህን ተከትሎ ባደረገችው ጥረት ከአራት ወራት በኋላ “ኤክስፕሎረር 1” የተሰኘውን ሳተላይት ወደህዋ በማምጠቅ ከፉክክሩ ውጭ አለመሆኗን በተግባር አስመስክራለች፡፡
የሁለቱን አገራት ሳተላይት ማምጠቅ ተከትሎ በርካታ አገራት ፉክክሩ ውስጥ ራሳቸውን ማስገባት ችለዋል:: በአሁኑ ወቅት ከአርባ በላይ ሃገራት የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል ደግሞ ስምንቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው፡፡
“ሳተላይት” በትላልቅ ቁሶች ዙሪያ የሚሽከረከሩ አካላት የሚል ስያሜን ያዘለ ሲሆን ተፈጥሮኣዊና ሰው ሰራሽ በመባልም በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የተፈጥሮ ሳተላይት የሚባሉት መሬት እና ጨረቃ ናቸው፡፡ መሬት በፀሃይ ዙሪያ በመሽከርከርና ጨረቃ ደግሞ በመሬት ዙሪያ በመዞር “የተፈጥሮ ሳተላይት” የሚል ስያሜ አግኝተዋል፡፡ ሰው ሰራሾቹ ሳተላይቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ዛሬ የምታመጥቀው ሳተላይትን ጨምሮ ላለፉት 62 አመታት የመጠቁት ከአራት ሺህ የሚበልጡ ሳተላይቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሳተላይቶች በመሬት ዙሪያ፣ በህዋ ውስጥ እንዲሁም በጨረቃና ሌሎች ፕላኔቶች ዙሪያ በመሽከርከር መረጃዎችን ወደመሬት የሚልኩ ናቸው፡፡
በዓለም ላይ የመጀመሪያው ሳተላይት ከመጠቀች በኋላ እስካሁን 8378 ሳተላይቶች ወደህዋ መላካቸውን ከአለምአቀፉ የህዋ ምርምር ማዕከል የተገኘው መረጃ ያሳያል:: ከነዚህ ውስጥ በምህዋራቸው ላይ በመሽከርከር የሚገኙት 4994 ሳተላይቶች መሆናቸውም መረጃው ያሳያል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ሰባቱ በፕላኔቶች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡
ዓለም አሁን የደረሰችበት የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰችው በቴክሎጂ እገዛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የቴክኖሎጂ እድገት ከሰው ልጅ አፈጣጠር አንፃር ሲታይ ገና ጨቅላ እድሜ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ለሰው ልጅ ትልቁ የስልጣኔ በር ከፋች መሆን ግን ችሏል፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በዚህ ዘመን ሳተላይት በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ግብርና፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኢኮኖሚ፣ የአየር ትራንስፖርት፣ ወዘተ ያለ ሳተላይት ድጋፍ የሚታሰቡ አይደሉም፡፡ ከሳተላይት ውጭ የሚከናወኑ ስራዎች ዓለምን ወደፊት የሚራምዱ አይደሉም፡፡
ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይት ያልነበራት በመሆኑ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት በየዓመቱ ለምስሎች ግዢ ብቻ እስከ 600 ሚሊየን ዶላር እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አሁን የጀመረችው የሳተላይት ማምጠቅ ስራ እውን ሲሆንና በቀጣይ የተያዙ መርሃግብሮች ተግባራዊ ሲሆኑ ይህን ወጪ ከማስቀረቱም በላይ በርካታ ተጨማሪ ስራዎችን ለማከናወን ያስችላታል፡፡
አሁን የምታመጥቀው ሳተላይት በዋናነት ለግብርና፣ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ስራችን ጠቃሚ እንደሆነ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በተለይ ግብርና የአገራችን የጀርባ አጥንት ከመሆኑ አንጻር ሳተላይቱ ለዘርፉ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
ይህ ሳተላይት የአየር ፀባይን በመቆጣጠር፣ ያልተገቡ ተባዮችን በተመለከተ መረጃ ከመስጠት፣ መጤ ተምችን ከመከላከል፣ የአየር ንብረትን ሁኔታ ከመገመት ፣ ወዘተ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአገራችንን የውሃ ሃብት ለመቆጣጠር ሳተላይቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን አሁን ኢትዮጵያ ለዘርፉ አዲስ እንደመሆኗ በዘርፉ ከፍተኛ አቅምና ልምድ ካላት ቻይና ጋር በጋራ እየሰራች ሲሆን በቀጣይ ይህንን ስራ የሚቆጣጠሩና የሚከታተሉ 20 ኢንጂነሮችም በቻይና ስልጠና እንደወሰዱ ታውቋል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎችም በቀጣይ ለሚደረጉ ስራዎች ትልቅ ልምድ እንዲያገኙ እድል የፈጠረ ሲሆን የቴክኖሎጂ ሽግግሩን እውን ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከአራት አመታት በኋላ በተጨማሪ ለማምጠቅ ለያዘችው ሳተላይትም ከወዲሁ የተሻለ አቅም እንዲኖርና የበለጠ እንድንጓጓ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡
አሁን የተጀመረው ስራም በቀጣይ በትምህርት ተቋማት የበለጠ ለመስራትና አዳዲስ ተመራማሪዎችን ለማፍራት ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ነው፡፡ እንዲህ በተግባር የሚታዩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እውቀቶች እየተበራከቱ መምጣት ለዘርፉ እድገት ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ አገራዊ ብልፅና ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የጀመረቻቸው ትላልቅ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋን የሚያጭሩ የብልጽግና ጅምሮች ናቸው፡፡ ዓለም ከዛሬ ስልሳ አመታት በፊት የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተከትለን እድገታችንን የምናፋጥን ከሆነ ወደ ብልፅግናው ማማ ለመውጣት የሚቸግረን አንዳንችም ሃይል እንደማይኖር ያመላክታል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ የተስፋ አገር እየሆነች ነው፡፡ በአገራችን በርካታ ትላልቅ ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ:: በተለይ በያዝነው አመት ኢትዮጵያ እየሄደችበት ላለችው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ዓለም እውቅና የሰጠበት ወቅት ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጎልቶ የሚወጣው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትራችን የኖቤል ሽልማት ነው፡፡
ከዓለም ጋር በሚደረግ ውድድር አሸናፊው የሚለይበትና የዓለምን ቀልብ በእጅጉ የሚስበው የኖቤል ሽልማት በቀላሉ የሚገኝ ሳይሆን በከፍተኛ ጥረትና ስኬት የሚገኝ ትልቅ ዓለም አቀፍ እውቅና ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሽልማትም ኢትዮጵያ ስለሰላም ምን ያህል አጥብቃ እየሰራች መሆኑን አለም የመሰከረበት ትልቅ ተግባር ነው፡፡
ከዚያም በተጨማሪ በዓለም ላይ ከሚገኙ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መካተታቸው ይፋ የሆነውም በያዝነው ወር ነው:: ፍሬወይኒ መብራህቱ፣ ፕሮፌሰር አታላይ አለም፣ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶክተር ግርማይ አረጋዊ፣ ሶስና ወጋየሁ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ዶክተር ሃረገወይን አሰፋ፣ ዶክተር ህይወት ጥላሁን፣ ዓለም አቀፍ ሞዴል ሊያ ከበደ፣ ማርታ ገበየሁ እና ዶክተር ዘቢባ የኑስ በዓለም አደባባይ በተለያዩ ዘርፎች እውቅና የተቸራቸውም በዚሁ አመት ነው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ከዳር የሚደርሰው ግን በውስጥ ያለው ሰላማችን ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ህይወት በመቅጠፍ የሚያልፉት ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀሎች፣ የህግ የበላይነት መጣስ እና ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮሩ ግንኙነቶች መሻሻል አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉም ዜጋ ርብርብና ጥረት ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ ከዚህ አንጻር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አክቲቪስቶች፣ ምሁራንና መላው ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ ለጋራ ሰላም ዘብ መቆም አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ በአንድ በኩል እየገነባን በሌላ በኩል ደግሞ የምናፈርስበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ኢትዮጵያም አሁን የጀመረችው ጎዳና በአጭር ጊዜ ወደ ብልጽግና ለመሄድ ትልቁ መስመር በመሆኑ በዚህ መስመር ለመጓዝ እያንዳንዳችን ሃላፊነቱን ልንወስድ ይገባል:: ነገ የሚመጣው እድገት የጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አይደለም፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን እድገት ነው፡፡ በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ለማውረስ ዛሬን በአግባቡ መጠቀምና መስራት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ በመሆኑ ሁላችንም የየበኩላችን ልንወጣ የግድ ይላል፡፡
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
ውቤ ከልደታ