ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የተመለሱት ከ33 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ነው፡፡ የሐረር ጦር አካዳሚ ሁለተኛ ኮርስ ምሩቅ፤ የጦር መኮንን፤ ዲፕሎማት፤ ደራሲ፤ የሕግ ባለሙያ፤ የጸጥታ ደህንነት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ተንታኝም ናቸው፡፡ በስፔሻል ፎርስና አየር ወለድ ልዩ ወታደራዊ ትምህርት በሀገር ውስጥና በውጭ ተምረዋል፡፡ በውጊያ ወረዳም በኤርትራ የስፔሻል ፎርስ አዛዥና አሠልጣኝ በመሆን በተለያዩ ግንባሮች ተሳትፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቅ፣ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ዶክተር ኦፍ ጁደሰ ብሩደንስ (በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ) ወስደዋል፡፡ በአሜሪካ ሀገር ከእግረኛ አዛዥነት ኮሎጅ ፎርት ቤንኒንግ እንዲሁም ዩኒክስ ከሚገኘው ከፍተኛ የወታደራዊ አዛዥነት ኮሌጅ፤ ከስፔሻል ፎርስ (ልዩ ኃይል) ኮሌጅና የዘመኑ ጦርነት ከሆነው የባዮሎጂካልና ኬሚካል ጦርነት ትምህርት ቤትም ተምረው ተመርቀዋል፡፡
በደርግ ዘመን የደርግ አባል ባይሆኑም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት፤ በእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነርነት፤ በኤርትራ የኢሠፓአኮ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን) ዋና ተጠሪ እንዲሁም የኤርትራ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሀገራቸውን ለቀው በስደት እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ከሀገር ከወጡም በኋላ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በዋና አማካሪነት ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ሴክዩሪቲ ስትራቴጂካል ስተዲስ (የአፍሪካ ደህንነት ስትራቴጂክ ጥናት) ተቋም ጀኔራል ዳይሬክተርነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የደም እንባ እና የሌሎችም መጻህፍቶች ደራሲ ሲሆኑ በደህንነትና ሴክዩሪቲ፤ በወቅታዊ ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ጽሁፎች ጽፈዋል፡፡ ስለትናንት እና ዛሬ አነጋግረናቸዋል፤ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ማን ናቸው ?
ሻለቃ ዳዊት፡- አባቴ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ይባላሉ፡፡ በ1933ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲጀመር የመጀመሪያው መስራችና ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡ ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ቄስ ሰፈር ነው፡፡ ወደቀጨኔ ሲወረድ ከድልድዩ በስተግራ ያለው ቄስ ሰፈር ይባላል፡፡ ቄስ ሰፈር የሚባለው የማርቆስ ካህን አገልጋዮች መሬት ተመርተው ቤት የሠሩበት ስፍራ ስለነበር ነው፡፡ ለቤተሰቤ አራተኛ ልጅ ስሆን፤ ቁጭ ብዬ ረጋ ብዬ ቤተሰብ ለማፍራት አልቻልኩም፡፡ አሁን ግን አግብቼ አንድ ልጅ ወልጄ እኖራለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በውትድርና ያሳለፉበትን ታሪክ ያስታውሱኝ ?
ሻለቃ ዳዊት፡- የሐረር ጦር አካዳሚ ሁለተኛ ኮርስ ምሩቅ ነኝ፡፡ ከሚሊተሪ አካዳሚ ሦስት ዓመት ስንጨርስ የመረቁን ጃንሆይ ናቸው፡፡ ቀጥዬ አየር ወለድ ገባሁ፡፡ ስፔሻል ፎርስ ሰለጠንኩኝ፡፡ ጠቅላላ ስልጠናው ሦስት ዓመት ተኩል መሆኑ ነው፡፡ ከዛ ኤርትራ ገባሁ፡፡ ኤርትራ እኔ በገባሁ ጊዜ ፌዴሬሽኑ አላለቀም ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ዘጠኝ ወር አስር ወር ሲቀረው ነው ኤርትራ የገባሁት፡፡ ፌዴሬሽኑ ጉባኤው ተሰብስቦ ከኢትዮጵያ ጋር እንዋሀድ ሲል የዛን ጊዜ ጦር ይዤ ጸጥታ አስከብር ነበር፡፡ አስመራ ከተማ ውስጥ፡፡
ከዛ በኋላ ሰባትና ስምንት ዓመት ውጊያ ውስጥ ተሳትፌአለሁ፡፡ የዛን ጊዜ እንደዚህ አልነበረም ውጊያ ትናንሽ አፈንጋጮች ነበሩ፡፡ በኤርትራ ለነበረው ሁለተኛ ክፍለ ጦር የመጀመሪያው አዛዥ ጀኔራል አበበ ገመዳ ነበሩ፡፡ በኋላ ጀኔራል ሽፈራው መጡ፡፡ ከእሳቸው በኋላ ጀኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ፡፡ ቀጥለው ጀኔራል ተሾመ እርገቱ መጡ፡፡ እሳቸው በተገደሉ ጊዜ ነው እኔ የቆሰልኩት፡፡ ሲሞቱ እዛው አካባቢ ነበርኩ፡፡ የእኔ ጦር የነበረው ከከረን በታች ነው፡፡ በውጊያ ቆስዬ ዩኒቨርሲቲ እንድገባ ተፈቅዶልኝ ለትምህርት መጥቼ፣ ነገር ግን እረፍት ሲኖር ለክረምት ሲዘጋ ሁለት ወር ሦስት ወር ተመልሼ ሠራዊቱ ውስጥ ገብቼ ሳልጠየቅ መለዮ ለብሼ ጦሩ ውስጥ አገለግላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በንጉሡ ዘመን አኛኚያ የተባለ አንድ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ሠራዊትን ስታሰለጥኑ ነበር፡፡ ሁኔታውን ቢነግሩን ?
ሻለቃ ዳዊት፡- የዛን ጊዜ ፖለቲካ ብዙ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ግራ ያጋባኝ ነበር፡፡ አኛኚያ (ነጻ አውጪ ምልምል ጦሩ) ንቅናቄን ካድሬዎቹንና ታጣቂዎቹን ከኡጋንዳና ከደቡብ ሱዳን ጠረፍ ላይ ነው የሚያመጣው፡፡ ከዛ እስራኤሎች በተሸፈነ አውሮፕላን አዲስ አበባ ያመጡዋቸውና ከአዲስ አበባ በተሸፈነ አውሮፕላን አስመራ ይመጣሉ፡፡ ከአስመራ እኔ በተሸፈነ አውቶቡስ አድርጌ አጓጉዤ ውቅሮ ወስጄ ሦስት ወር ኮማንዶ አሰልጥኜ ወደ ሱዳን እንልካቸው ነበር፡፡ እንዲያውም ከአንዱ ጦር ጋር ዘምቼአለሁ፡፡ የዛን ጊዜ የሚደረገው ሁሉ ምስጢር ነው፡፡ አሁን ይወራል፡፡ ይህ ሁሉ በሚደረግበት ጊዜ ጃንሆይ ከሱዳን ጋር የሞቀ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ምንም አይታወቅም፡፡
አሠልጣኞቹ ልዑል አስራተ ካሳ ፣እኔና ጀኔራል እርቅይሁን ባይሳ ነበርን፡፡ ውቅሮ የፈራረሱ ቤቶች አሉ፡፡ ሰው አያውቅም፡፡ እዛ ገብተው ሠልጥነው ይወጣሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ከፍተኛ ምስጢር ነው፡፡ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ጃንሆይ ሚዛን መጠበቅ የምችለው የኤርትራንም ችግር ቢሆን በእንደዚህ አይነት ነው ብለው አምነውበት ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዛሬ ላይ ሁነው ሲያዩት የደርግ ስብስብ ምን ይመስል ነበር፤ በመጀመሪያዎቹ የአብዮቱ ወቅቶች የነበረው ተቀባይነት እያሽቆለቆለ ሄዶ ለውድቀት ያበቃው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ ?
ሻለቃ ዳዊት፡- እኔ እንግዲህ ወታደር ነኝ፡፡ ሻለቃም የሆንኩት ሕግ ትምህርት ቤት እያለሁ ነው፡፡ በእረፍቱም እየመጣ በፈቃዱ እያገለገለ ነው፤ ሕግ ትምህርት ቤትም ቢሆን ይሄ አገልግሎቱ ሊቆጠርለት ይገባል ተብሎ ሻለቃ አደረጉኝ፡፡ ሻለቃ ሆንኩኝ፡፡ አሜሪካ በሄድኩበት ጊዜ ትንሽ ያፈነገጠ አስተሳሰብ ጀመርኩኝ፡፡ ኢትዮጵያ አብዮት ያስፈልጋታል፤ የመሬት ይዞታ የአንዳንድ ነገሮች በሚል እዛ ውስጥ ገባንና ደርግ አብዮቱን ሲጀምር ደግፌአለሁ፡፡ የደርግ አባል አልነበርኩም ፡፡ ጃንሆይ ተነሱ ሲባል መጣሁ፡፡ የካቲት ነው አብዮቱ የተነሳው እኔ መስከረም ውስጥ ነው የመጣሁት፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም ፍርድቤት ውስጥ እንድገባ ፈልጎ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ የእኔም ጁኒየር ነው፡፡ አንተ ነው የምለው፡፡ በግልጽ ነው የምናወራው፡፡ እኔ እሱን አልፈልግም አልኩት፡፡
የደርግን ስብስብ በተመለከተ እንደዚህ ደረጃ ይደርሳሉ ብለን አላሰብንም፡፡ ምክንያቱም በጣም ጁኒየሮች ናቸው፡፡ የበታች ሹሞችም ይበዛሉ፡፡ አንድ አራቱ ለምሳሌ ኤርትራ በነበርኩበት ጊዜ የመልእክት ሠራተኛ የሆኑ ወታደሮች ነበሩ፡፡ የጽሕፈት ሥራ የታይፕ ሥራ የሚሠሩ፡፡ ሌሎችም ከየቦታው የመጡት ሁሉ ተመሳሳይ ስብስቦች ነበሩ፡፡ በሀገር ደረጃ ቀርቶ በክፍለ ሀገር ደረጃም ምንም እውቀት ያልነበራቸው ስለነበሩ ሀገር ይመራሉ ተብሎ አልታሰበም፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም እራሱ የተላከው በቅጣት መልክ ነው፡፡ ከዚህ ይሂድልን እዛ ይተራመስ ተብሎ ነው እነጀኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ ያባረሩት፡፡ ማናቸውም ለከፍተኛ ኃላፊነት የመጡ አልመሰላቸውም፡፡ ነገሮች እየተንከባለሉ እንደዛ ሆኑ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኃላፊነት ላይ እያሉ ይኖሩበት በነበረው አፓርታማ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎቦት ነበር ?
ሻለቃ ዳዊት፡- አዎ ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎብኛል፡፡ ከቴዎድሮስ አደባባይ ወደ ተክለሃይማኖት የሚወስድ ቀጭን አስፋልት አለች፡፡ እዛ ጋ ናድል የሚባል ሕንጻ አለ፡፡ 8 ቁጥር ላይ ነበር የምኖረው፡፡ ከደርግ ጽሕፈት ቤት ለተላኩት ገዳዮች በእኔ ቤት ቁጥር እዛ ያለውን ሰው አውጥታችሁ ግደሉ ተብሎ ነው የተላኩት፡፡ መጥተው ክፈት አሉ፡፡ አልከፈትኩም፡፡ ብዙ ተንኳኳ፡፡ የወታደሮች ኮቴና እንቅስቃሴ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ማናችሁ እኔ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊርጊስ ነኝ አልኩ፡፡ ራሴን ለመከላከል ዝግጁ ሆኜ ነበር የማናግራቸው፡፡ አለቃቸው ለየኝ፡፡ ጌታዬ እርስዎ ነዎት እንዴ ይቅርታ አለ፡፡ ያው ተረፍኩ፡፡
የተሰጠው ትእዛዝ እዛ ቤት ያገኛችሁትን ሰው አውጥታችሁ ግደሉ ነው የተባልነው ስም አልተነገረንም አለ፡፡ እሱ ነው ያዳነኝ፡፡ እዛ ቤት የምኖረው እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ሌላ ሰው አይኖርም፡፡ የታዘዙት ወታደሮች ትእዛዙን ለመፈጸም ተንቀሳቀሱ እንጂ እዛ ቤት ውስጥ የሚኖረው ወንድማቸው አለቃቸው ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ መሆኑን በፍጹም አያውቁም፡፡ይህን የመሰለ ነፍሰ ገዳይነት ጨካኝነትና አረመኔነት ነበር የሚፈጸመው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ካለዎት እጅግ ሰፊ የሕግ፤ የዲፕሎማሲ፤ የወታደራዊ አዛዥነትና ኢንተለጀንስ እውቀት በመነሳት ኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነቷንና ደህንነቷን ጠብቃ ለመራመድ ምን ማድረግ አለባት ይላሉ ?
ሻለቃ ዳዊት፡- ያልጠበቅነው ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ እኔም ከ33 ዓመት በኋላ ብዙ ለውጥ አየሁ፡፡ ብዙ እከታተላለሁ፡፡ ብዙ እጽፋለሁ፡፡ ብዙ እናገራለሁ፡፡ ሀገር ወገን የሚያቀና፤ የሚሻል ነገር ፤ ይሄ ጎዳና ይያዝ ይሄ አቅጣጫ ይያዝ እያልኩ ነው የምናገረው፡፡ ከሀገሬ በላይ የማፈቅረው ነገር የለኝም፡፡ ሁሉን አልፈን እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁንም በጣም የተመሰቃቀለ ነገር ያለበት ነው፡፡ መፍትሄው ይሄ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
በቀደም ንግግር ሳደርግ የኢትዮጵያን ዲሞግራፊ ስንመለከተው በአሁኑ ጊዜ በዚህ ዓመተ ምህረት ከ 0 እስከ 14 ድረስ ያለው 27 በመቶ ያሳያል፡፡ ከ14 እስከ 25 ያለው ወደ 25 በመቶ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱን ብቻ የወሰድን እንደሆነ ወደ 47 በመቶ ይሆናሉ፡፡ ከ25 እስከ 54 ያለው ወደ 27 በመቶ ገደማ ነው፡፡ ሦስቱ ተደምሮ እስከ 54 ዓመት ድረስ ያለው ወደ 80 በመቶ ይሆናል ፡፡ 27 ዓመቱን እንኳን ብንወስድ በ27 ዓመት ውስጥ ዛሬ 54 ዓመት የሆነው ሰው ይሄ ሥርዓት ሲመጣ የ27 ዓመት ሰው ነበር ማለት ነው፡፡ ወጣት ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ባለው ፖለቲካ ውስጥ የተበረዘ የኖረ ስለሆነ አዲስ ባህል ነው ያለው፡፡ ስትነጋገር ከሰው ጋር ያለው ባህሉ የተለየ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የአደግንበት የኖርንበት ባህል አይደለም፡፡ በተለይ የዘር ፖለቲካ፡፡በዘር አካባቢ ነው ሁሉም ነገር የሚታየው፡፡
የዚህን መፍትሄ ለማቃናት ለማበጀት መስራት አለብን፡፡ 54 ዓመት እድሜ የደረሰው እንኳን ሌላ ባህል አያውቅም፡፡ የሚያውቀው ባህል የዘር ፖለቲካ ባህል ነው፡፡ ይሄን ለማስወገድ ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ ደፋር አመራር ይጠይቃል፡፡ ብዙ ትምህርት ይጠይቃል፡፡ ብዙ ፍጥጫ ይጠይቃል፡፡ ይሄ የአመራር ጉዳይ ነው፡፡ እንዴት አድርገን ይሄን ባሕል እንለውጠው ነው፡፡ ፈቃደኛ የሆኑ መሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ አሁን ተስፋና ጭላንጭል ያለ ይመስላል፡፡ እሱን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አላውቅም፡፡ በአጠቃላይ ግን ብዙ ችግር ነው፡፡ መፍትሄው ይሄ ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ተሰደው ከወጡ በኋላ በውጭ ሆነው በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ታግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ነጻ ወታደሮች እንቅስቃሴ የሚል መስርተው እስከ ኤርትራ በረሀ ድረስ ሄደው ተነጋግረዋል፡፡ የግንቦቱን የጀኔራሎቹን መፈንቅለ መንግሥት፤ በኋላም በደርግ የመጨረሻ ሰአት አካባቢ በጀኔራል ገዝሙ በዛወርቅ መሪነት ታቅዶ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ከውጭ ሆነው የመሩት እርስዎ እንደነበሩ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ አስተያየትዎ ምንድነው ?
ሻለቃ ዳዊት፡- እኔ የጠቅላላው መሪ አልነበርኩም፡፡ ከወጣሁ በኋላ ከውስጥ ያሉና ከውጭ ያሉ ናቸው፡፡ ከውጭ ያለውን የማስተባብረው እኔ ነበርኩ፡፡ ከመውጣቴም በፊት ከጀኔራል ፋንታ በላይ ጋር ተነጋግረን ነው የወጣነው፡፡ በአንዳንድ ነገር ተግባብተን ከውጭ ምን ማድረግ እችላለሁ በሚለው ነገር ነው ተስማምተን ይቻላል በሚል መንፈስ ነው የወጣሁት፡፡
የእኔ የሥራ ኃላፊነት ምንድነው በዛን ጊዜ ዋናው ችግሩ ጦርነቱ እየተስፋፋ መጣ፡፡ በጣም እየሰፋ መጣ፡፡ ህዝባዊ ግንባር ሃርነት ኤርትራ (ኢፒኤልኤፍ) በኩል ያለው በጣም እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በሁሉም ግንባር ጦርነት መጣ፡፡ ይህቺ ኢትዮጵያ ትጠፋለች፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ በጦርነት ሳይሆን ሽብር ውስጥ ሊከተን ይችላል፡፡ አለጦርነት፤ አለውጊያ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን የደርግ ሥርዓት አስወግዶ በአዲስ ሥርዓት መተካት የሚቻለው እንዴት ነው፡፡ ስለዚህ ውስጥ ያለው ወታደሩ ምን ማድረግ አለበት በሚለው ነው የተማመነው፡፡ ወታደሩ ስልጣን ለመውሰድ ሳይሆን መንግስቱ ኃይለማርያምን አስወግዶ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያቀፈ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ነበር፡፡ እንግዲህ እኔ በውጭ የምሰራው ምንድነው የፖለቲካ ኃይሎችን የማቀፍ፣እነሱን እዚህ ውስጥ የማስገባትና ሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ነበር፡፡ ውስጥ ያለውን የውስጥ ኃይሉ ይሠራል፡፡ ያስወግዳል፡፡ ወዲያው ይሄ እንደተደረገ የውጭ ኃይሎች ገብተው የሽግግር መንግሥት እንዲያቋቋሙ፤ አቋቁመው ወደ ምርጫ እንዲገባ ነበር፤ ያንን ከውጭ የማደርገው እኔ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጀኔራሎቹ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት በኢትዮጵያ ሠራዊትና በሻዕቢያ ጦር መካከል በነበረው ውጊያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ያደረጉት እርስዎ እንደሆኑ የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉና፤ ቢያስረዱን?
ሻለቃ ዳዊት፡- አዎን በሁለቱ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ያደረኩት እኔ ነኝ፡፡ በዚሁ መሰረት ዋናው በሻዕቢያ የሚደረገው ትልቁ ጦርነት ስለሆነ ከኤርትራውያን ጋር ብዙ ውይይት አደረኩኝ፡፡ ኢትዮጵያም በጀርባ ገባሁ፡፡ ናቅፋ ገባሁ
፡፡ የኤርትራ ገዢ ሆኜ ከኤርትራውያን ጋር ብዙ ወዳጅነት ስለነበረኝ ብዙ ጊዜ አምስት ስድስት ሰባት ጊዜ ንግግር አድርገናል ከኤርትራ ኃላፊዎች ጋር፡፡ ጦርነቱን አቁሙ የሚል፡፡ ሕወሃትም እስከዚህ አልጠነከረም ነበር፡፡ ግን እነሱም እንዲያቆሙ ኤርትራውያኖቹ እንዲያደርጉ፡፡ ኢህአፓና ሌሎችን ያሉትን ሁሉ አነጋግረን ለውጥ ከተደረገ የሽግግር መንግሥት አብራችሁ አቋቁሙ አልን፡፡ በተለይ ሻዕቢያ ተስማማ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር በመሆን የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ነው ?
ሻለቃ ዳዊት፡- አዎ፡፡ ተስማምተን ተፈራርመን ነው፡፡ መጨረሻው ላይ በተለይ መፈንቅለ መንግሥቱ ከመካሄዱ ከአስራ አምስት ቀን በፊት እኔና ወዳጆቼ ሁለት ሦስት ሰዎች ሆነን ናቅፋ መጣን፡፡ ጠቅላላ ከሻእቢያ አመራር ጋር ተሰባሰብን ተነጋገርን፡፡ ተፈራረምን፡፡ እነሱ በዚያን ጊዜ ያሉት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሽግግሩ መንግሥት አባል እንሆናለን አሉ፡፡ የኤርትራንም ጉዳይ እዛው ላይ እንወያያለን አሉ እንጂ ትገንጠል የሚል ነገር አልነበረም፡፡ በግምታችን ወደ ቀድሞው ፌዴሬሽን የመመለስ ጉዳይ እሱን እንደራደራለን ነው እንጂ ነጻነት የሚል ነገር አልነበረም፡፡
እንግሊዝ ሀገር ሆኜ ለጀኔራል ፋንታ በላይ ደውዬ ነገርኩት፡፡ በእዚህ በኩል ሁሉ ነገር አልቋል ስለው እንግዲያው እኛ በሚቀጥለው ሳምንት እናከናውናለን አለ፡፡ የውስጡን ሁኔታ ለመናገር ውስጥ የለሁም፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት ነው የማውቀው፡፡ በኋላ ጀኔራል ቁምላቸው ሲወጣ እኔ ነኝ አሜሪካን ሀገር የተቀበልኩትና እሱ ከሰጠኝ ወሬ ጋር ነው እንጂ ሌላው ሁሉ የሚወራው ወሬ በምርመራ የወጣውን ነው የምናውቀው እንጂ የራሴ የግል እውቀት የለኝም፡፡ እዛ ደረጃ አድርሰነው ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሁለተኛው ዙር በእነ ጀኔራል ገዝሙ በዛወርቅ ተወጥኖ ሳይሳካ የቀረ መፈንቅለ መንግሥት ነበረ ይባላል እውነት ነው ?
ሻለቃ ዳዊት፡- ሁለተኛ ዙር ሙከራ አደረግን፡፡ ምክንያቱም ሁለተኛ ዙር ሙከራ ስናደርግ ጀኔራል ገዝሙና ጀኔራል ጌታቸው ገዳሙ ነበሩ፡፡ ጀኔራል ገዝሙ በጣም ደፋር ሰው ነበር፡፡ የጦሩን በሸዋ በኩል የያዘው እሱ ነበር፡፡ እሱ ፈቃደኛ ሆነ፡፡ እናንተ እዛ ጨርሱ እንጂ እኔ አደርጋለሁኝ አለ፡፡ የዛን ጊዜ ያ ሁሉ ኮሚኒኬሽን አስቸጋሪ ነበር፡፡ በድብቅ ነው፡፡ የሞባይል ስልክ የለም፡፡ መሀከል ገብቶ አንድ የሚያይዘን ሰው ማድረግ አስፈላጊ ነበር፡፡በጣም ደፋር ሰዎች ነበሩ፡፡አንድ ኤልያስ የሚባል ደፋር በጣም ጎበዝ ልጅ ነበር፡፡ እሱ እያገናኘን ተነጋገርን ግን ንግግሩ ትንሽ ዘገየ፤ የዛን ግዜ ህወሃት አብጧል፡፡ቦታ ይዟል፡፡ ንግግሩ ከበድ አለ፡፡ እንዴ ቆይ እንጂ የሚል ነገር አመጡ፡፡ ሁለቱም ከህዝባዊ ግንባር ሃርነት ኤርትራ ጋር ሆነው እየተጠጉ መጡ፡፡ በዚህ በኩል ዝግጅቱ አልቋል ግን እየተጠጉ ሲመጡ ብትፈልጉ ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ እኛ ግን አዲስ አበባ ለመግባት ወስነናል አሉ፡፡ በድሮው ሀሳባችን እኛ ያልነው እናንተ አትግቡ ትርምስ ይፈጠራል፤ እናንተ ውጭ ቆዩ፡፡ ትጠራላችሁ ሌሎችንም አካተን የሽግግር መንግሥት እናቋቁማለን ነው ያልናቸው፡፡እነሱ ግን አዲስ አበባ እንገባለን አሉ ገቡ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው ሠራዊት እንዲፈርስ ሲደረግስ ምን ተሰማዎት ?
ሻለቃ ዳዊት፡- ብዙ ሰዎች በዛን ጊዜ ወታደሩ ተሸንፎአል ይላሉ፡፡ አልተሸነፈም፡፡ ወታደሩ ሲዋጋ የነበረው ከውጭ ጦር ጋር አልነበረም፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው የነበረው፡፡ ትግራይ ኢትዮጵያዊ ነች፡፡ የህወሃት ሠራዊትም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ግጭቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ነበር፡፡ ወታደሩ ከጣሊያን ሀገር ወይ ከሶማሊያ ሀገር የመጣ ጠላት ቢሆን ኖሮ እስከ መጨረሻው ይዋጋ ነበር፡፡
እያንዳንዱ ወታደር የራሱ አስተያየት አለው፡፡ አንዱ ለምን ከራሳችን ህዝብ ጋር እንዋጋለን የሚለው ነው፡፡ ህወሃት ሲገባ ደግሞ ብዙ ሰው ተስፋ ነበረው፡፡ በዛም ተስፋ ነው እንጂ በተሸናፊነት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትና የህወሃት ሠራዊት ይላሉ፡፡ የተሳሳተ መጥፎ አነጋገር ነው፡፡እነሱም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የተበተነው ሠራዊት እጅግ ያሳዝናል፡፡
ከሁሉ የሚያሳዝነው ምንድነው በተለይ ከኤርትራ ተገፍቶ የወጣው ሠራዊት ምንም ክፍያ ሳይኖራቸው በዘጠኝ ወር ደመወዝ እየተከፈላቸው ቱታ ጫማ ሳይለውጡ እዛው የሞቱ የቆሰሉ ወታደሮች እጅግ ያሳዝናሉ፡፡ በየክፍለ ሀገሩ ለማኞች ሁነው መኖራቸው እንደዛ ተገፍተው መጣላቸው በጣም ያሳዝናል፡፡
በቀደም በቪዥን ኢትዮጵያ ስብሰባ ላይ አንዱም የተናገርኩት ኤርትራ ላይ በ30 ዓመቱ ጦርነት ብዙ ሠራዊት ሞቷል፡፡ ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላ ለታጋዮቻቸው ሐውልት ሠርተዋል፡፡ የእኛ ሠራዊት ኤርትራ መሬት ላለቀው ለምንድነው ማስታወሻ የማይተከልለት፡፡ አስመራን የሚያቅ ሰው ያውቀዋል፡፡ በእንግሊዞች ጊዜ በተደረገ ጦርነት ለወደቁ እንግሊዞች የመቃብር ቦታና ሐውልት አላቸው፡፡ ህንዶችም የእንግሊዞች ተከታይ ሁነው የመጡ ነበሩ፡፡ የእንግሊዝ መቃብር አለ፡፡ የኢጣሊያ መቃብር አለ እዛ፡፡ ኤርትራ ብትገነጠልም ኤርትራ ውስጥ ላለቀው የኢትዮጵያ ሰራዊት የግድ ማስታወሻ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ጠይቄአለሁ፡፡እሱን ደግሞ እከታተላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራ መልካም ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ በውል የታሰረ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ ሁኔታውን እንዴት ያዩታል ?
ሻለቃ ዳዊት፡- እደግፈዋለሁ፡፡ ድሮም ቢሆን እንደምታውቁት ብዙ ሰው እያለፈ ወጣቱ አጭር ማስታወሻ ነው ያለው፡፡ የትናንትና ነገር ነው የሚያስታውሰው የድሮውን ነገር አያስታውስም፡፡ አንድ መጽሀፍ ጽፌአለሁ፡፡ ክህደት በደም መሬት የሚል፡፡ ረጅም መጽሀፍ ነው፡፡ መጽሀፉ አንድ ምእራፍ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ያስተማሩን ኤርትራውያኖች ይላል፤ ያስደነግጣል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን፤ አርበኝነትን፤ ታጋይነትን፤ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የመሞትን መስዋዕትን ቁም ነገር አድርጎ የቆጠረ ሕዝብ ያየሁት ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡ በጣም ብዙ ጀግኖች ሀገር ፍቅር ማህበር ብለው ለኢትዮጵያ የሞቱ የቆሰሉ የታገሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በሰራየ አውራጃ ቋሂን የሚባሉ አሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሲታገሉ አለቁ፡፡ በዛን ግዜ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ስትዋሀድ የተለያየ ግንዛቤ አለ፡፡ የፈለጉትን ሊሉ ይችላሉ፡፡ በዓይን ያየን በዓይን የመሰከርን ሰዎች በዛን ግዜ የሀገር ፍቅር ማህበር ከባድ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር አብረን እንሁን ፌዴሬሽን እንሁን ብለው ከዛም በኋላ ደግሞ ኤርትራውያን ራሳቸው ገፍተው ነው አንድነቱ የመጣው፡፡
ምናልባት አሁን ወደኋላ ስንመለስ ባይደረግ ኖሮ ይበጅ ነበር እንላለን፡፡ ፈልገው ነው፡፡ ከዛ በኋላ በተለያየ ምክንያት አፈንጋጮች በዙ፡፡ ጦርነቱም እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስና አብዛኛው የኤርትራ ወጣት መገንጠልን እንዲደግፍ ያደረገው የራሳችን መንግሥት ስህተት ነው፡፡ በተከታታይ የነበረው የመንግሰት ስህተት ነው፡፡ ማሰሩን፣ መግረፉን፣ መግደሉን ብናቆም ብዙ ሰው እኮ የሚሸፍተው ብዙ ወጣት ውጭ የሚወጣው ኢትዮጵያዊነትን ጠልቶ አይደለም፡፡ ነገር ግን እስራትን ግርፋትን መገፋትን እየፈራ ነው፡፡ ያንን ብናቆመው ሕዝቡን ልናረጋጋው እንችላለን ብዬ ቀጠልኩ፡፡
በዚህ መንፈስ ሦስት ዓመት በተቀመጥኩበት ጊዜ ፖሊሲ ስናደርግ ራሱ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በአንደበቱ የነገረኝ ነው፡፡ ሌሎችም አብረውት የነበሩ ሰዎች የነገሩኝ ነው፡፡ በዛ ጊዜ የነበሩ የኤርትራ ታጋዮች ቢጠየቁ ይነግሯችኋል፡፡ የኤርትራ ትግል ፈተና ነበረበት እኔና ጓደኞቼ እዛ በነበርንበት ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላም መሰረትን ፡፡ ይሄንን ለወጣቱ መውጣት ምክንያት የሆነውን ነገር አጠፋነው፡፡ ማሰር የለም፡፡ የሻዕቢያ ወረቀት አነበብክ ተብሎ መቀጣት የለም፡፡ በሆነ ባልሆነው ያለ ሥርዓት ያለ ህግ ሰውን መቅጣት ሰውን ይገፋዋል፡፡ ያስከፋዋል በሚል ያንን የሰላም እምነት ስለተከተልን በጠቅላላው በሦሰት ዓመት ተኩል ውስጥ ኤርትራ ልዩ ቦታ ሆነች፡፡ እነሱ ብዙ የሚወጣ ሰው አጡ፡፡ ትግሉ በጣም ወደተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ ሄደ፡፡ ወደ ናቅፋ አካባቢ እንጂ ሌላው አካባቢ በጣም የተረጋጋ ሆነ፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም በኃይል ሁሉን ነገር እናደርጋለን ነው የሚለው፡፡ ሕዝብ ስሜት አለው፡፡ መብት አለው፡፡
ኢትዮጵያዊነት እንጀራ አይደለም፡፡ በልተህ ብቻ አትኖርም፡፡ ኢትዮጵያዊነት መብት ሲሰጥህ ነው፡፡ ሲጠብቅህ ነው፡፡ ሲታገልልህ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የምትኮራበት እንጂ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ይዘህ የት ትደርሳለህ፡፡ የትም አትደርስም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከመብት ጋር አብሮ መሄድ አለበት፡፡ከደህንነት ጋር አብሮ መሄድ አለበት፡፡ አልሄደም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በ1977 በሀገራችን በተከሰተው ድርቅ ያንን ለመከላከል እጅግ ከፍተኛ ትግልና ጥረት አድርገዋል፤ ቢያብራሩልን?
ሻለቃ ዳዊት፡- ከሁሉም መጥፎ ጊዜ ነበር፡፡ ወደእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ስመጣ በእውነቱ በጠቅላላው ብዙ ሕዝብ እልቂት ላይ ሊደርስ በነበረበት ጊዜ ላይ ነው የደረስኩት፡፡ በጣም ታሪካዊ ነው፡፡ የዓለም ሕብረተሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተሰባሰበበት ትልቁ ኦፕሬሽን (ዘመቻ) ይሄ ነው፡፡ በዛን ጊዜ እኛ የማርክሲስት መንግሥት ነበረን፡፡ ነገር ግን ምስራቅና ምእራብን ያገናኘ ትልቅ ኦፕሬሽን ነበረ፡፡ ይሄንን በይፋ ያወጣው እርዳታና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ነው፡፡ የእኔ የግሌ ሳይሆን በጠቅላላው በእርዳታና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ውስጥ ከነበሩ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ጋር ነው የሰራሁትና በእውነቱ ያንን አፍረጥርጠን አውጥተን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አቅርበን ያንን ሁሉ እርዳታ ለማምጣት ቻልን፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ አስረኛው አብዮት በዓል የሚከበርበት ጊዜ ነበር፡፡ ዓላማው ምን ነበር የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ምእራፍ ፤ የእድገት የሰላም ምእራፍ ውስጥ ገብቷል፤ ገበሬው ከብሯል፤ ሕዝብ ተረጋግቷል፤ አብዮቱ እኩልነትን አጎናጽፏል የሚል መርህ ይዞ ነው የተነሳው፡፡
እርዳታ ማስተባበሪያ ደግሞ የሚለው ስንት ሚሊዮን ሕዝብ ለረሀብ እየተጋለጠ ነው፡፡ ይሄ ተጣረሰ፡፡ ከሊቀመንበሩ ጋር ችግር ተፈጠረ፡፡ ዝም ማለትም ለሕሊናችን ልክ አልመጣም፡፡ ስለዚህ ይህንን ለኢንተርናሽናል ኮሚኒቲ አቀረብነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ ወዲያው በአንድ ጊዜ መልስ ሰጠ፡፡ ምላሹ አንዱ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ሌላው ሰብዓዊ ነው፡፡ይሄንን የማርክሲስቱን መንግሥት የምናሳጣበት አንድ መሳሪያ ሆነ፡፡ ሌላው ደግሞ እውነትም በሰብዓዊነት ብዙ አደረገ፡፡ ዊ አር ዘ ወርልድን ያመጣነው እኔም ሆሊውድ ተጠርቼ ሄጄ እነ ማይክል ጃክሰን እነ ላፎንቴ ይሄንን ልናደርግ አስበናል ብለው ሲነግሩኝ በጣም ጥሩ አልኳቸው፡፡ ዘፈኑ ወጣ፡፡ብዙ ገንዘብ ተሰበሰበ ፡፡ እነሱም መጡ፡፡የሕዝብ ሕይወት መዳን ቻለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም በእርስዎ እይታ ምን አይነት ሰው ነበሩ ? ዛሬ ላይ ሆነው ትናንትን ሲያስታውሱት ምን ይሰማዎታል ?
ሻለቃ ዳዊት፡- ለጊዜው እኛ እንሳሳታለን፡፡ ሰውን አይተን ቶሎ እንፈርዳለን፡፡ ለመፍረድ እንቸኩላለን፡፡ ለመኮነንም ይፈርዳል፡፡ ለማሞገስም ይፈርዳል፡፡ መሪን ለመገመት ጥሞና ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም የሰው ፍጡር ደካማ ነን፡፡ እራስ ወዳድነት አለ፡፡ እኔ ብቻ የሚል፡፡የራስ ፍላጎት አለና ያ ያሸንፈናል፡፡ በዛ እንዳንሸነፍ የሚያደርግን ሰው ነው፡፡ ወይ ሀይማኖት ነው፡፡ ወይ እምነት ነው፡፡ ወይ ባሕል ነው፡፡ ያ የሚገታን ነገር ሲጠፋ ጨካኞች እንሆናለን፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም ያንን መስመር አለፈው፡፡ ያንን መስመር አለፈና ሁሉን አውቃለሁ ባይ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ራሱ የግል ንብረት ወሰዳት፡፡የግል ንብረት አደረጋት፡፡ ከእኔ በኋላም ከእኔ በፊትም የለም የሚል አቋም ወሰደ፡፡ የራሱ ኤጎ አሸነፈው፡፡ እኔ ከወጣሁ በኋላ ብዙ ግድያ ተፈጸመ፡፡ እኔ እያለሁም ሰው ይሞት ነበር፡፡ ለምን፡፡ የተሳሳት አስተሳሰብ ነው፡፡
መጀመሪያ እንዳልኳችሁ ሰው ማዳመጥ ይችል ነበር፡፡
እኔ ሄጄ አንድ ሰአት ሙሉ ብለፈልፍ ያዳምጠኛል፡፡ አቁም አይለኝም፡፡ መጀመሪያ ጊዜ መንግስቱ ኃይለማርያም እንደዚህ ቁጭ ብዬ ወይ ደግሞ አንተ መጀመሪያ ሄደህ በተመሳሳይ ጉዳይ አነጋግረሀው እኔ ደግሞ በዛው ርእስ ላይ ሄጄ ባነጋግረው ያዳምጣል፡፡ ያንን ጸባይ ወደድነው፡፡ ይማራል፡፡ ያቺን ሰበሰበና መናገር ጀመረ፡፡ አዋቂ መሰለ፡፡ ያንኑ ሲደግም እውቀት አጣ፡፡ መማር አልፈለገም፡፡ጨካኝ ሆነ፡፡ በኃይል መግዛት ነበረበት፡፡ድሮ እንደ ልብ የምንናገረውን ሰዎች አራቀን፡፡ ርቀት ፈጠረ፡፡ አንቱ በሉን መጣ፡፡ ከእዚህ እዛ ድረስ ነው ርቀቱ እሱን ለማናገር፡፡ብዙ ሰው ሲሞት ደግሞ ሰው ፈራ፡፡ እሞታለሁ በሚል፡፡ አበላሸ፡፡ ሁሉን ነገር በኃይልና በራስ ወዳድነት የሚያሸንፍ መሰለው፡፡ በደም ተቀባ፡፡ እንደዚህ አይነት ጨካኝ ሰው የለም፡፡ ወደኋላ ስትመለስ በኋላ መነጽር ሁሉ ነገር ትክክል ነው፡፡ በወቅቱ ጥሩ ሰው መስሎን ነበር፡፡ የዛን ጊዜ አይተሀል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እሱን ለመደገፍ ፈንቅሎ ነበር የወጣው፡፡ በአነጋገሩ እውነተኛ እኩልነት የሚያሰፍን ይመስል ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከ33 ዓመት ስደት በኋላ ሲመለሱባት ምን ተሰማዎ ?
ሻለቃ ዳዊት፡- መጀመሪያ ብዙ አልተሰማኝም ነበር፡፡ ግን ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስቃረብ አለቀስኩ፡፡ ብዙ ወታደሮች አልቀውብኛል፡፡ የሞቱት ጓደኞቼ ሁሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አቅፈው ነው፡፡ ብዙ ጽፌአለሁ ስለኢትዮጵያ ባንዲራ ስለወታደሮች፡፡ብዙ ሠራዊት አለቀ፡፡የቱንም ያህል በፈተናና በመከራ ውስጥ ያሳለፍኩ ወታደር ብሆንም እነዛን ትናንት አብረውኝ የነበሩ ለኢትዮጵያ ክብር የታገሉ፤ የደሙ የቆሰሉ፤ በየበረሀው የወደቁ የሞቱ ጓደኞቼን ወታደሮቼን በአጠቃላይ ያንን ኩሩና ጀግና ሠራዊት ወደኋላ መለስ ብዬ ለአፍታ ሳስታውሰው ሰውነቴ ከሚሸከመው በላይ ሆነ፡፡ እንባዬ እየገነፈለ ወረደ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በኢትዮጵያ ለውጥ ቢመጣም በየቦታው ግጭቶች አሉ፡፡ የሰላምና መረጋጋት ችግሮች ገዝፈው ይታያሉ፡፡ እርስዎ በተለያዩ ዘርፎች ካለዎት ሰፊ ሙያዊ እውቀትና ልምድ በመነሳት ለችግሮቹ መንስኤና መፍትሄዎቹስ ምንድናቸው ብለው ያስባሉ?
ሻለቃ ዳዊት፡- እኔ ሊቅ ባልሆንም የተሞክሮ ሊቅ ነኝ፡፡ የአፍሪካን ሕዝብ የሚያፋጨው አይዲዮሎጂ አይደለም፡፡ ሁሉም ቦታ አይዲዮሎጂውን ለራሳቸው እንደሚመቻቸው አድርገው የሚፈጥሩት መሪዎች ናቸው ፡፡ የጦርነት መንስኤዎቹ ሁሉም ቦታ ላይ መሪዎች ናቸው፡፡ መሪዎቹን የሚቆጣጠር ሥርዓት አለመኖሩ ነው ትልቁ ችግር፡፡ ሲሳሳቱ የሚያርማቸው፤ የሚገታቸው፤ የሚያቆማቸው፤ ሥርዓት አለመኖሩ ነው፡፡ መሪዎች ከሕግ በላይ ሲሆኑ ከዛ በኋላ ግጭት ይፈጠራል፡፡ ደቡብ ሱዳን ብናየው ሰሜን ሱዳን ኮንጎ ታያላችሁ፤፤ መሪዎች ጊዜያቸውንና ወሰናቸውን አያውቁም ፡፡ያ ሲያልፍ የአደጋ ደውል ነው፡፡ ያንን የአደጋ ደወል አያዳምጡም፡፡ ያንን መስመር ካቋረጡ በኋላ ጦርነት ይጀመራል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በእነ ክሊንተን ጊዜ የአፍሪካ ሕዳሴ ተብሎ መለስ፣ ኢሳያስ፣ ሙሴቬኒ፣ ካጋሜ፣ ምቤኪ፣ ካቢላ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ነበር፡፡ የትም ቀሩ፡፡ እንደዛ ዓለም ደግፏቸው ሕዳሴ ሊያመጡ ነው ሲባል ሁሉም በራሳቸው ጥፋት ተሸነፉ፡፡ ሁሉም ችግር አለባቸው፡፡ ችግሮቹ መሪዎች ናቸው፡፡ሕዝቡ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አማሟቱ እስከዛሬም በግልጽ ያልታወቀው ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የቅርብ ወዳጅዎ ነበር ይባላል፡፡ ኦሮማይ መጽሀፉ ውስጥ በብሄራዊ ፍቅር በምሁራዊ ብቃትና በጀግንነት የወከለው መሪ ገጸ ባህርይ ሰለሞን በትረጊዮርጊስ እርስዎ ዳዊት ወልድጊዮርጊስ እንደሆኑ ይነገራል፤ እውነት ነው ?
ሻለቃ ዳዊት፡- የበዓሉ ግርማ ጽሁፉ ራቅ ብሎ ነው የሚመለከተው፡፡ ውስጡ እንዳለ ሰው አይደለም፡፡ አደጋ ላይም የጣለው በዛ ምክንያት ነው፡፡ እሱ በወቅቱ የመንግሥት አካል ነው፡፡ የመንግሥት ተሿሚ ነው እንዴት አድርጎ ይሄን ይጽፋል በሚል ነገር ነው አደጋ ላይ የወደቀው፡፡ በዓሉ ሲጽፍ ሁልጊዜ የተለየ መነጽር አለው፡፡እኛ በምናይበት ነገር እሱ ነገሮችን አያይም፡፡የእሱ አመለካከት ለየት ያለ መሆኑን ነው መጽሀፉ የሚያሳየው፡፡
በተለይ ሰዎችን ፐርሰናሊቲያቸውን እየለዋወጠ ሲገልጽ ውስጡን የሚያውቁ ሰዎች ማን ምን እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ልዩ የአጻጻፍ ስልት ነው ያለው፡፡ ድንቅ ብእረኛና ታላቅ ደራሲ ነበር፡፡ ኦሮማይን በጻፈበት የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ እኔ የክፍለ ሀገሩ የኢሠፓ ዋና ጸሀፊና ተጠሪ የቀይ ኮከብ ዘመቻም የፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ሌላው ዋናው ኃላፊ መንግስቱ ኃይለማርያም ነው፡፡ ለተወሰኑ ወራቶች እዛው ነበር፡፡ በዓሉ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ነበር፡፡ የቡድኑ አካል ለመሆን እዛ መጣ፡፡ ሌሎችም መጡ፡፡ የማስታወቂያ የፕሮፓጋንዳ ኢንፎርሜሽን ኃላፊ ሁኖ የሚሠራው እሱ ነበር፡፡ሽመልስ ማዘንጊያ የፓርቲው የርእዮተ ዓለም ኃላፊ ስለነበረ እሱ ደግሞ ከላይ ይመለከታል የእነሱን፡፡ ግን ሁሉም በእኔ ክፍል ውስጥ ነበሩ፡፡
ናቅፋና በየቦታው እየሄዱ ዶክመንቴሽን ያደርጋሉ፡፡ በዓሉ ጸሀፊ ፈለገ፡፡ ያስፈልገውም ነበር፡፡ የራሱን ጸሀፊ ከዚህ ወስዶ እዛ ማድረግ ፈልጎ ነበር፡፡ አይ እኔ ግዴለም ጸሀፊ እሰጥሀለሁ ብዬ እኔ ጋ የነበረች ፊዮሬላ የምትባል ልጅ የእሱ ጸሀፊ አደረኳት፡፡ ሦስቱ ሴንተር የሚያደርገው ጌታቸው ኃይለማርያምና በዓሉን አንድ ፐርሰናሊቲ አድርጎ ነው እዛ ላይ ያቀረባቸው፡፡ ስታነቡት የበዓሉም የጌታቸውም ጸባይ አለበት፡፡ ፊዮሬላ ደግሞ ፊያሜታ እሷ ነች፡፡ ቢሮ አካባቢ ስለነበረች ያናግራታል፡፡ ያጫውታታል፡፡ ያዝናናታል፡፡ ኢንተርቪው ያደርጋታል፡፡ ከዛ የሕብረተሰቡን ሀሳብ ለማግኘት ቻለ፡፡ በሕይወት አለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፊያሜታ ጊላይ ገጸ ባህርይ አድርጎ ቢስላትም እንደ ደራሲ የሳላቸውን ሰዎች መግደል ማንሳት ቢችልም ግን በሕይወት አለች ?
ሻለቃ ዳዊት፡- አዎን በሕይወት አለች፡፡ አንዴ ሰው አገናኝቶኝ አግኝቼአት በመጽሀፉ ላይ ገደለሽ አልኳት፤ሳቀች፡፡ ሲወጣ የሚያገኛቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እዛ ውስጥ የነበሩት ሰዎች በሙሉ እዛው አካባቢ የምንሠራ ሰዎች ነበርን፡፡ ብዙ ሰዎች ኦሮማይ መጽሀፉን ይወዱታል፡፡ግን ዝርዝሩን አያውቁም፡፡አሁን በቅርቡ በፌስ ቡክ ላይ አወጣሁና ግልጽ እንዲሆንላችሁ ማን ምን እንደሆነ ገለጽኩ፡፡ ሰለሞን በትረጊዮርጊስ፤ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ነው፡፡ አንዳንዶቹን ይዘልፋቸዋል፡፡እኔን አንዱም ከመንግሥት ጋር ያጣላኝ አንተን ብቻ አመስግኖ እኛን አወገዘ የሚሉ ኃይሎች ነበሩ ፓርቲው ውስጥ ፡፡
አዲስ ዘመን፡-የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን አመራር እንዴት ያዩታል ? ለውጡን ጠብቆ ለመዝለቅ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ሻለቃ ዳዊት፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጽፌአሁ፡፡ የመጀመሪያው ሰው በዳያስፖራው የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራር በመደገፍ ሌትስ ራሊ አራውንድ ዘ ፕራይም ሚኒስትር በሚል የጻፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ደግፌያለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ከመጥፋት አደጋና ጫፍ ነው ያወጧት፡፡ ይሄንን ድጋፍ አለምንም ቅድመ ሁኔታ መደገፍ አለብን፡፡ኢትዮጵያን ሊያሸጋግሩ የሚችሉ መሪ ናቸው ብዬ ጽፌአለሁ፡፡ ሲኤን ኤን ላይ ብዙ አርቲክል አውጥቻለሁ፡፡ ብዙ ተሰራጭቶአል፡፡ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ደፋር ሰው ነው፡፡ በድንገት ነው በማናውቀው ሁኔታ ትግሉ ውስጥ የመጣው፡፡ እኔ ኢትዮጵያን በተመለከተ ብዙ እሰራ ነበር፡፡በአለፈው አራት ዓመት ውስጥ እንሰራ የነበረው የኢትዮጵያን አንድነት ሊያረጋግጡልን የሚችሉት የኦሮሞና የአማራ አንድነት ነው፡፡ የሌሎቹ ብሄረሰቦች ብዙ አያስቸግረንም፡፡ ኦሮሞና አማራ አንድ ከሆኑ ሊያረጋግጡት ይችላሉ በሚል ጉዳይ በጣም ብዙ ሠርቻለሁ፡፡ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፍሮንት ከነዲማ፤ ከነሌንጮ ለታ ጋር በጣም በቅርብ ሠርቻለሁ፡፡ብዙ መግለጫ አውጥተናል፡፡አማራን ደግሞ በተመለከተ እኔ አማራነቴን አላውቅም ነበር፡፡ በአማራነትም ደግሞ አልገባሁም፤ አማራውን ደግሞ ፈልገን አደራጅተን አብረው እንዲሠሩ ብዙ ነገር አድርገናል፡፡ አማራነትም ሳይሆን የጊዜው ፖለቲካ የሚጠይቀው ስለሆነ ሁለቱን ለማቀራረብ ብዙ ሰርተናል፤ ያን የምናደርገው ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው የሚል ስጋት ስለነበረ ነው፡፡
የዶክተር አብይ መምጣት ብዙ መፍትሄ ነው የፈጠረው፡፡ እንግዲህ ብርታቱን ይስጥ ነው የምንለው፡፡ በጸሎትም በሀሳብም እንደገፋለን፡፡ ትግሉ ቀላል አይደለም፡፡ በቀደም እለት ስናገርም ገልጬአለሁ፡፡ እዚህ ደረጃ ብንደርስም ቀጣዩ ደግሞ ከዚህ የባሰ የተወሳሰበ ነው፡፡ ታውቁታላችሁ፡፡ በተለይ ደግሞ በአካባቢያችን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ጠላትዋ ከውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም ነው፡፡ ብዙ ጠላት አላት፡፡ ያንን ሁሉ ማየት ያስፈልጋል፡፡
አሁን ጅቡቲ ላይ ስምንት የጦር ሰፈሮች አሉ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በዓለም ውስጥ እጅግ የተወሳሰበው የሴክዩሪቲ ቀጣና ነው፡፡ በጣም የተወሳሰበ የሚሊተሪ ዞን በዓለም ውስጥ አንደኛ የአፍሪካ ቀንድ ነው፡፡ የሚገርም ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡ የአሜሪካ፤ የፈረንሳይ፤ የቻይና፤ ጃፓን ፤ ኢጣሊያ፤ እንግሊዝ ፤ ዩናይትድ አረብ ኢምሬት፤ የሳኡዲ አረቢያ ታላላቅ ጦር ሰፈሮች እዛ ተቀምጠዋል፡፡ በኤርትራ የጦር ሰፈሮች እየተቋቋሙ ናቸው፡፡ በሶማሊያ ቱርክ፤ ኳታር ገብተዋል፡፡ በሱዳን ሌላ ግንባር ነው፡፡ ምንድነው እየተደረገ ያለው ብሎ ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡የዚህ ሁሉ ማእክል ኢትዮጵያ ነች፡፡
በስትራቴጂክ ጠቀሜታዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች፡፡ ሁሉ የሚያተኩርባት ሀገር ነች፡፡ እነዚህ ሁሉ ዙሪያችንን ያሉ ኃይሎች የኢኮኖሚ አጀንዳ አላቸው፡፡ የቀይ ባህር አጀንዳ አላቸው፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ኢትዮጵያን አተኩረው ይመለከታሉ፡፡ የውጭ ጣልቃገብነት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ወይንም ደግሞ በዓይነ ቁራኛ አይመለከቱንም ማለት አይቻልም፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህን አያውቁም፡፡ኢትዮጵያ እግዚአብሄር ነው እዚህ ያደረሳት እንጂ ለማፍረስ ብዙ ኃይሎች ይሞክራሉ፡፡መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ቃለ ምልልስ ከልብ እናመሰግናለን!
ሻለቃ ዳዊት፡- አመሰግናለሁ !
በወንድወሰን መኮንን