ዛሬ ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ ካፈራቻቸውና ካየቻቸው ታላላቅ የእግር ኳስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነውን የዝነኛውን መንግሥቱ ወርቁን ወርቃማ ታሪክ በጥቂቱ እንመለከታለን።
መንግሥቱ የተወለደው በ1932 ዓ.ም በቀድሞው በጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት፣ ቋራ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው። ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ‹‹አሻግራቸው›› ነበር። አባቱ ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ ፀረ-ፋሺስት አርበኛ ስለነበሩና ለፋሺስት ኢጣሊያ ባለስልጣናት በማስቸገራቸው እርሳቸውን ለመያዝ በማሰብ ሕፃኑ አሻግራቸው ወርቁ ከእናቱ ከወይዘሮ እማዋይሽ አብተው ጋር ታሠረ። ‹‹አሻግራቸው›› የሚለው ስሙ ወደ ‹‹መንግሥቱ›› የተለወጠው ከእናቱ ጋር ታስሮ በነበረበት ወቅት በፋሺስቶች ቢሆንም እንዴት እንደተለወጠ የሚገልጹት መረጃዎች ግን ሁለት ዓይነት ናቸው።
አንደኛው የአባቱ የፊታውራሪ ወርቁ ወንድም ፊታውራሪ ዓለሙ በፋሺስቶች ከተያዙ በኋላ ፋሺስቶች ፊታውራሪ ወርቁ ወንድማቸውን በጣም ይወዱ እንደነበር ስለሰሙ ‹‹ወንድምህን እንድንለቀው ከፈለግህ መጥተህ እጅህን ስጥ። አለበለዚያ በወንድምህ ላይ አደጋ ይደርሳል›› የሚል መልዕክት ላኩባቸው። ፊታውራሪ ወርቁም እጃቸውን ሰጥተው ወንድማቸውን ካስፈቱ በኋላ ከእስር ቤት አምልጠው ስለጠፉ ፋሺስቶች ‹‹መንግሥቱን (ንጉሰ ነገሥቱ በስደት እየኖሩና አገሪቱ በጠላት ኃይል እየተገዛች ስለነበር) ሊፈልግ ነው ያመለጠው›› ብለው ሕፃን አሻግራቸውን ‹‹መንግሥቱ›› አሉት የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹በልጅነቱ ከእናቱ ጋር በእሥር ላይ የነበረው አሻግራቸው ጣሊያኖች ሁኔታውን አይተው ‹አንተ መንግሥት ለመሆን ነው የምትፈልገው› በሚል ‹መንግሥቱ› ብለው ስም እንደሰጡት የሚገልጽ ነው።
የሆነው ሆኖ ‹‹አሻግራቸው›› የሚለው ስሙ እየተረሳ በ‹‹መንግሥቱ›› እየታወቀ ሄደ። መንግሥቱም ‹‹እንዴት ፋሺስት ባወጣልህ ስም ትጠራለህ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ስሜ የኢትዮጵያዊ እንጂ የፋሺስት ስም አይደለም፤ እንዲያውም ስሜ የአባቴን ሙያ ያስገነዝበኛል›› ብሏል።
የትምህርት ቤት ቆይታው
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ድል ሆኖ ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ መንግሥቱ የቅኔ ትምህርት ቤት ገብቶ ዳዊት ደግሟል። ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ ከጠላት ጋር ሲፋለሙ መሞታቸውን በማሰብ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሕፃኑ መንግሥቱ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በቤተ-መንግሥት እንዲቀመጥ አደረጉ። በ1940 ዓ.ም መድሐኔዓለም ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርት መማር ጀመረ። በዚሁ ትምህርት ቤትም ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተማረ።
መንግሥቱ በአንድ ወቅት ስለ ትምህርት ቤት ቆይታው ሲናገር ‹‹በ … ተማሪ ቤት እያለሁ ተማሪ ሁሉ ዘመዱ ሲጠይቀው እኔ ግን የዘመድ ጠያቂ ባለማግኘቴ እብሰለሰል ነበር። ግርማዊነታቸው ትምህርት ቤቱን ለመጎብኘት ሲመጡ የ‹‹ወርቁ ልጅ የት አለ›› ብለው አስፈልገው አነጋግረው አስፈላጊውን ሁሉ ፈፅመውልኝ ‹በርታ› ይሉኝ ስለነበር በጣም ደስ ብሎኝ እፅናና ነበር…›› ብሏል።
በቀለም ትምህርት ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አንዱ የነበረው መንግሥቱ፣ በትምህርት ቤቱ በሚከናወኑ የስፖርት ውድድሮች (በመረብ ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በሩጫ፣ በእግር ኳስ … በመሳተፍ ሁለገብ ስፖርተኛ መሆኑን አሳይቷል። በኢትዮጵያ ተማሪዎች መካከል በተደረገ ውድድርም በአንድ መቶ ሜትር ተወዳድሮ አሸናፊ ሆኗል። መንግሥቱ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ተሰጥዖ የነበረው ቢሆንም ትኩረት ማድረግ የፈለገው ግን በእግር ኳስ ላይ ነበር።
በአንድ ወቅት ከሌሎች የስፖርት ጨዋታዎች ሁሉ ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር እንዴት እንዳደረበት ተጠይቆ ‹‹ … ከጓደኞቼ ጋር እየሆንን ጢቢ ጢቢ እንጫወት ነበር። ያለማቋረጥ ብዙ እመታለሁ፤ በኋላ ገንዘብ አዋጥተን ትንሽ ሸራ ኳስ ገዛንና ራስ ኃይሉ ሜዳ እየሄድን ቅዳሜና ዕሁድ ስንፋተግ እንውላለን። እንዲህ እዲህ እየተጫወትን ባለንበት ወቅት ሚስተር ሒውዝ የተባሉ የስፖርት መምህራችን ‹‹ኤ››/‹‹ቢ››/‹‹ሲ›› የተሰኙ ቡድኖች አቋቋሙ። እኔ በሲ ቡድን ውስጥ ተመደብኩ። በኋላም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጋር ውድድር ተመሰረተና በሁለት ቁጥር ቦታ እየተጫወትኩ ድሉ የትምህርት ቤታችን ሆነ … በ‹‹ሲ›› ቡድን ጥሩ እጫወት ስለነበር በቀጥታ በቁመትም ሆነ በዕድሜ አቻዬ ካልሆኑት ከ‹‹ኤ›› ቡድን አባላት ጋር በአምስት ቁጥር ቦታ ተሰልፌ እንድጫወት ተመደብኩ። በ‹‹ኤ›› ቡድን ተጫዋች በነበርኩበት ዘመን አከታትለን ሻምፒዮን ሆነናል …›› በማለት የኳስ አጀማመሩንና የመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ትዝታውን ገልፆ ነበር።
መንግሥቱ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ
መንግሥቱ የመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ በአካባቢው ለነበረው የጉለሌ ቡድን ለመጫወት ልምምድ ጀመረ። በወቅቱ ጉለሌ በኢትዮጰያ እግር ኳስ ያልተመዘገበ የሰፈር ክለብ ነበር። ታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ የነበሩት አቶ ቱፋ ሻይና ተጫዋቹ ነፀረ ወልደ ሥላሴ መንግሥቱን አይተውት ስለነበር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን እንዲገባ አግባቡት። በተለይ አቶ ቱፋ ደጋግመው ስለጠየቁት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በ1949 ዓ.ም ክረምት ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስን ቡድን ተቀላቀለ።
በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ወደ ድሬዳዋ ሄዶ ይለማመድ ስለነበር ከቡድኑ ጋር አብሮ ተጓዘ። ቡድኑ ከጥጥ ማህበር ቡድን ጋር ሲጫወት መንግሥቱ ተጠባባቂ (ተቀያሪ) ሆኖ ተመደበ። ጥጥ ማኅበር ሦስት ለአንድ በሆነ ልዩነት እየመራ የቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተጫዋች ተጎዳና መንግሥቱ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ገባ። ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑን ከሽንፈት ታደገው። ቀዳሚዋን የቅዱስ ጊዮርጊስን አንዷን ጎል ያስቆጠረው ይድነቃቸው ተሰማ ነበር።
በቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ በስምንት ቁጥር መለያ ተሰለፈ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስት ለሁለት በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈ። ቅዱስ ጊዮርጊስና መንግሥቱ ውል አሠሩ፤የቅዱስ ጊዮርጊስ ስምንት ቁጥር መለያ የመንግሥቱ ሆነ። በዚህ የተጀመረው የመንግሥቱና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ትስስር እየጠነከረ ሄዶ በቡድኑ ታሪክ እስከአሁን ድረስ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ባለታሪክ ለመሆን በቃ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ማለት መንግሥቱ፤ መንግሥቱ ማለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆኑ!
መንግሥቱ ከ1951 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫውቷል። በተጫዋችነት ዘመኑ የሌላ ክለብ መለያ አልለበሰም። ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫን፤ በ1965 እና 1966 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጋር አሸንፏል።
የቴክኒክና ሙያ ምሩቅ የነበረው መንግሥቱ ከተመረቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የተቀጠረው መብራት ኃይል መስሪያ ቤት ውስጥ ነው። በወቅቱ መብራት ኃይል የእግር ኳስ ቡድን ነበረው። መንግሥቱ ግን የሚጫወተው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር። በ1955 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መብራት ኃይል በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ተገናኙ። ቅዱስ ጊዮርጊስ መብራት ኃይልን አራት ለአንድ አሸንፎ ዋንጫውን ሲያነሳ ሦስቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ግቦች መብራት ኃይል ላይ ያስቆጠረው የመብራት ኃይሉ ሠራተኛ መንግሥቱ ነበር። የመብራት ኃይል ሠራተኞች ‹‹እኛ ዘንድ እየሠራና ደመወዝ እየበላ እንዴት መጫወቻ ያደርገናል?›› ብለው ተቆጡ። የሠራተኞቹ ተቃውሞ እያየለ ሄዶ የድርጅቱ ኃላፊዎች ‹‹ለእኛ መጫወት አለብህ፤ አቋምህን አሳውቅ›› አሉት። እርሱም ‹‹ለጊዮርጊስ መጫወት አላቆምም … ጊዮርጊስንም አልለቅም …›› ብሎ ከመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ሥራውን ጥሎ ወጣ።
መንግሥቱ ወርቁ ለሌሎች የእግር ኳስ ክለቦች እንዲጫወት ተጠይቆ ነበር። ነገር ግን ስምንት ቁጥርንና የ ‹‹V›› ምልክት ያለበትን የቅዱስ ጊዮርጊስ መለያን ጥሎ መውጣትን እንደ ክህደት ስለቆጠረው የእግር ኳስ ዘመኑን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ብቻ በታማኝነት አገልግሏል።
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ መንግሥቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በታማኝነትና በትጋት እያገለገለ ምንም ዓይነት ክፍያ ጠይቆ አለማወቁ ነው። ስለዚህ ጉዳይ መንግሥቱ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር …
‹‹ … የሚያጫውትህ የሕዝብ ፍቅር ነው። ከማልያው ጋር ተዋህጄ ስለነበር ትቼ መሄድ አልፈለግሁም … ደምተህና ተፈንክተህ ቡድኑን እዚህ ካደረስክ በኋላ እንዴት ጥለህ ትሄዳለህ? ስለዚህ ‹ጊዮርጊስ አልከፈለኝም› ብዬ አንድም ቀን እንኳን ገንዘብ ጠይቄ ሰንፌም አላውቅም … ›› … መንግሥቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የነበረው ፍቅርና ታማኝነት እንዲህ ያለ ነው።
ከይድነቃቸው ተሰማ (ለ23 ዓመታት) ቀጥሎ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ረዥም ጊዜያት በመሰለፍ ሁለተኛ ሰው መንግሥቱ ወርቁ (ለ16 ዓመታት) ነው።
መንግሥቱ በተጫዋችነት ዘመኑ በእግር ኳስ ችሎታውና ‹‹አብዶ›› በመሥራት በሚያሳየው ጥበብ ተማርከው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። እንዲያውም ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያልና የብዙ ደጋፊ ባለቤት መሆን የቻለው በመንግሥቱ ምክንያት ነው›› ብለው የሚናገሩ ወገኖች በርካታ ናቸው።
የብሔራዊ ቡድን አገልግሎቱ
መንግሥቱ ከክለብ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ በመጫወት እስከዛሬም ድረስ በማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ያልተደፈሩ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረው በ1951 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ (CAF Africa Cup of Nations) ነው። በ1954 ዓ.ም ኢትዮጵያ ባስተናገደችው ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩን ኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን ከግብፁ መሐመድ በደዊ አብደል ፋታህ ጋር በጋራ ተቀዳጅቷል። የውድደሩ ኮከብ ተጫዋችም እርሱ ነበር። ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ አንድ ለእናቱ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫን (1954) እንድታሸንፍ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ ያበረከተው መንግሥቱ ነበር።
እስከ ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ የብሔራዊ ቡድኑን መለያ ለብሶ አገሩን አገልግሏል። በአጠቃላይ ከ1951 እስከ 1964 ዓ.ም ድረስ 102 ጊዜ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ ተጫውቷል፤ 62 ግቦችን ለብሔራዊ ቡድኑ በማስቆጠር እስከአሁን ድረስ ባለክብረወሰን ነው። በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይም በርካታ ጊዜያት ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችሏል። መንግሥቱ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ እስከአሁን ድረስ ብዙ ግብ ካስቆጠሩ አፍሪካውያን ተጫዋቾች መካከል አንዱ በመሆን ከአፍሪካ ኮኮብ ግብ አግቢዎች ተርታ መሰለፍ የቻለበትን ደማቅ ታሪክም መፃፍ ችሏል። ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ በተሳተፈችባቸው የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ከመንግሥቱ በስተቀር ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ (የተሸለመ) ተጫዋች የላትም።
መንግሥቱ አገሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ እንድትሆን ቢያደርግም እርካታ አላገኘም። የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ለኢትዮጵያ ማስገኘትን አልሞ የነበረው መንግሥቱ፣ ኳስ መጫወት ለማቆም በወሰነበት ወቅት ‹‹ላሳደገኝና ለወደደኝ ሕዝብ ውለታውን ሳልመልስ ከኳስ ተጫዋችነት መገለሌ እየፀፀተኝ ነው። ነገር ግን አገራችን ጥሩ ተጫዋቾች እንዲኖሯት በአሰልጣኝነትና በአማካሪነት ለማገልገል ከመጣር አልቦዝንም›› ብሎ ተናግሮ ነበር።
የአሰልጣኝነት ሕይወቱ
መንግሥቱ ከተጫዋችነቱ ባሻገር በአሰልጣኝነትም ሠርቷል። በአሰልጣኝነት ሥራውም ውጤታማ መሆን ችሏል። በአሰልጣኝነቱ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ጎበዝ ተጫዋች በመሆኑ የተገኙ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ የስልጠና ኮርሶችን ወስዶ በአንደኛነት በማጠናቀቁም ጭምር የተገኙ ናቸው። የእግር ኳስ ችሎታና ልምድ ብቻውን ጥሩ አሰልጣኝ እንደማያደርግ የተረዳው መንግሥቱ፣ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ና በሌሎች ተቋማት የተዘጋጁ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን ተከታትሎ አንደኛ በመውጣት ሰርተፊኬት፣ ዋንጫና ሜዳልያዎችን አግኝቷል።
ካሰለጠናቸው ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መብራት ኃይል፣ ኢትዮጵያ መድኅን፣ አየር መንገድ፣ ባንኮች እና ወንጂ ስኳር ይገኙበታል። ከአዲስ አበባ ከተማ 190 ኪሎ ሜትር እየተመላለሰ ‹‹ሕፃናት አምባ›› ውስጥ የነበሩ ታዳጊዎችንም አሰልጥኗል። በ‹‹ምርጥ›› ደረጃ ደግሞ ‹‹የአዲስ አበባ ምርጥ››፣ ‹‹የሸዋ ምርጥ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ተስፋ›› ቡድኖችን አሰልጥኗል።
መንግሥቱ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸውን ልጆች የማወቅ ልዩ ተሰጥዖ እንደነበረው የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ክለብ ለማሰልጠን ከመስማማቱ በፊት ከክለቡ ጋር ከፍተኛ ድርድር የሚያደርገው በደመወዝ ጉዳይ ላይ ሳይሆን በሜዳ ላይ ነው። ቡድኑ የተስተካከለ መለማመጃ ሜዳ እንዲኖረው ግፊት ያደርጋል። መብራት ኃይልና መድኅን ሜዳ እንዲኖራቸው ያደረገው መንግሥቱ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆንም ሀገሩን አገልግሏል። በአሰልጣኝነት ሥራ ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው በ1968 ዓ.ም በረዳት አሰልጣኝነት ነው። ቀጥሎም ዋና አሰልጣኝነቱን በመረከብና በወጣቶች የተገነባ ቡድን በመሥራት ኢትዮጵያ ለ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ አድርጓል። በአፍሪካ ዋንጫ በተጫዋችነት ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቶ በአሰልጣኝነት ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፈ ብቸኛው ሰው መንግሥቱ ወርቁ ነው። ከአሰልጣኝነቱ በተጓዳኝም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኃላፊ ሆኖ ለአሰልጣኞች ኮርስ ሰጥቷል፤ የቴክኒክ ኮሚቴን አዋቅሯል። የክለቦችን ሥልጠና በንቃት ተከታትሏል።
መንግሥቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንስትራክተር (የአሰልጣኞች አሰልጣኝ) ነው። የአፍሪካ የእግር ኳስ አሰልጣኞች አሰልጣኝ በመሆን በናይጄሪያ፣ በታንዛኒያ፣ በኡጋንዳ እንዲሁም በስዋዚላንድ በመዘዋወር ለአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ሰጥቷል። በርካታ ተተኪ አሰልጣኞችንም አፍርቷል። መንግሥቱ በኤርትራና በሱዳንም ከፍ ያለ ዝናና ተወዳጅነት ነበረው።
መንግሥቱና ስምንት ቁጥር (8)
መንግሥቱና ስምንት (8) ቁጥር የተዛመዱ ናቸው። ‹‹መንግሥቱ ወርቁ›› የሚለውም ስም ስምንት ፊደሎች አሉት። ክለቡ ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ››ም ባለስምንት ፊደል ነው። የሚቆርጠው ሎተሪና የሚነዳው መኪና የመጨረሻ ቁጥራቸው እንዲሁም ለክለብም ሆነ ለብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የሚለብሰው የመለያ ቁጥር ስምንት ነበር።
በባህርይው ኮስተር ያለ (ቁጡ) እንደነበር የሚነገርለት መንግሥቱ፣ ‹‹በባህሪዬ ቁጡ ነኝ፤ አኩራፊም ነኝ። አሁን ዕድሜዬ በመግፋቱ ሁሉንም ትቻለሁ። ግን ኳስ ተጫዋች ለመሆን በትንሹ ቁጡ መሆን ያስፈልጋል›› ብሏል። አንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማም …
‹‹በቴክኒክም ሆነ አይቻል በግፊያ፣
እግዚአብሔር አያድርስ የመንግሥቱን ኩርፊያ›› በማለት የመንግሥቱን ችሎታና ጸባይ በግጥም ገልጸውታል።
ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለሌሎች ክለቦች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባከናወናቸው ዘመን አይሽሬ ወርቃማ ተግባራት አሁንም ድረስ በበርካታ አድናቂዎቹና የእግር ኳስ ቤተሰቦች ዘንድ ልብ ውስጥ ላቅ ያለ ቦታ ያለው መንግሥቱ ወርቁ፣ የጤና እክል አጋጥሞት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ በታኅሣሥ ወር 2003 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
አንተነህ ቸሬ