ለ100 ዓመታት ያልነጠፈ ውለታ

በ1915 ዓ.ም ነበር በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ የነበሩት ልዑል ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለሥላሴ) የዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጡ። በቃላቸው መሠረትም የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቅቆ ሚያዚያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደቱን ‘ሀ’ ብሎ ጀመረ። “ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት” በሚል ስያሜም ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ እንዲሁም አዳሪ ትምህርት ቤት በመሆን አገልግሏል።

ትምህርት ቤቱ በ1917 ዓ.ም የማስተማር ሥራውን ሲጀምር 30 አዳሪና 50 ተመላላሽ በድምሩ 80 ተማሪዎች ነበሩት። ይህ የትምህርት ተቋም በቅርቡ ስያሜውን ከእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወደ “ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ” ቀይሯል፡፡

ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ፋሽስት ወረራ ወቅት በጣሊያኖች ቁጥጥር ስር በመሆኑ በወቅቱ ለጣሊያኖች ብቻ መማሪያ በመሆንም አገልግሏል። ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመማር ማስተማሩን የቀጠለ ሲሆን ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቱን በመሠረቱት በልዑል ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለሥላሴ) መጠራቱ ተቀይሮ፤ “እንጦጦ የቀለምና ቴክኒክ ትምህርት ቤት” በመባል ተሰየመ።

በ1994 ዓ.ም ደግሞ የእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋም በሚል ስያሜ ሲሠራ ቆይቶ በ1996 ዓ.ም ወደ ኮሌጅነት በማደግ ስያሜው እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ተባለ። በኋላም እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመባል እስከ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ስም ሲጠራ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ “ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ” ለመባል በአዲስ አበባ ምክር ቤት ፀድቆ ስያሜውን ማግኘት ችሏል፡፡

ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያብራራው እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ስያሜውን መቀየር ያስፈለገበት ምክንያት ኮሌጁ የመቶ ዓመት ታሪክ ያለው እንዲሁም የተመሠረተው በተፈሪ መኮንን በመሆኑና ኮሌጁ ሲመሠረት በስማቸው በመሆኑ፣ የሠሩት ሥራ ታሪካቸውን ለማስታወስ ነው። በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም የቀድሞው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከኮሌጁ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ስያሜው እንዲቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ኮሌጁ በተለያዩ ጊዜያት ስያሜውን መቀየሩ ሲመሠረት የነበረውን ስም ከማጣቱ ጋር ተያይዞ የነበረው ዝናና ታሪካዊነቱ በተገቢው መንገድ እንዳይገልጽ ሆኗል። የኮሌጁ አዲሱ ስያሜ ገፅታውን ከመገንባት አንፃር፣ የነበረውን ገናናነትና ታዋቂነት ለመመለስ ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ችግር ፈቺ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራት ለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ራስ ገዝ ኮሌጅ እንዲሆን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱልበር ከወራት በኋላ የመቶኛ ዓመቱ የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓሉን ለማክበር እና ተቋሙን ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መቶ (100) ዓመት ሊሆነው የአንድ ወር ጊዜ ነው የቀረው። ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳው። በያኔው የቀለም (አካዳሚክ) ትምህርት፤ በአየርና በየብስ፣ በምህንድስና፣ በሳይንስ፣ በሂሣብ እና በሌሎችም ዘርፎች ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸውን ምሁራን ያፈራ ስለመሆኑ አብዝቶ ይነገርለታል። የዚህ ትምህርት ቤት ፍሬ የሆኑ አንዳንዶችም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ይገኛሉ።

በተለያየ የትውልድ ዘመን ውስጥ ዘመንን የተሻገረው ይህ ትምህርት ቤት አሁን ላይ ደግሞ ፖሊ ቴክኒክ ሆኖ በሥነ ጥበብ፣ በእደ ጥበብና በሙዚቃ ዘርፎች በማስተማር ላይ ነው። ትምህርት ቤቱን ያቋቋሙት ኢትዮጵያን ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ እንዳስተዳደሯት የሚነገርላቸው አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው። ትምህርት ቤቱንም ተፈሪ መኮንን ብለው ነበር የሰየሙት።

የአፄው አስተዳደራዊ ሥርዓት ከተለወጠ በኋላ ግን ትምህርት ቤቱ ስሙ ተቀይሮ እንጦጦ በሚል ስያሜ ነው ሲጠራ ቆይቷል። ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል ወሮ በነበረበት ጊዜም ቪክቶር አማኑኤል ተብሎ ተሰይሞ ነበር። ለአራት ዓመታትም ጣሊያውያን ብቻ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው የነበረው። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ከአንድ ወር በፊት በቀደመው ስሙ ተፈሪ መኮንን ተብሎ እንዲጠራ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ አግኝቷል፡

ትምህርት ቤቱ በቀድሞ ስሙ እንዲጠራ የቀደሙት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ብዙ ደክመዋል። የቀድሞ ተማሪዎች ተቆርቋሪነታቸውን ያሳዩት ወደ ቀደመ መጠሪያ ስሙ እንዲመለስ ብቻ አይደለም። ትምህርት ቤቱ ቀድሞ ያፈራቸው ተማሪዎቹ እንደኮሩበት ሁሉ የአሁኖቹም በተመሳሳይ የሚኮሩበትና ለሀገር የሚያኮሩ ሙያተኞችም እንዲወጡ የቀድሞ ተማሪዎች በሃሳብ፣ በገንዘብና በቻሉት ሁሉ እያገዙት ይገኛሉ።

ቀደምቶቹ የጀመሩትን መልካም ሥራ የሚያስቀጥሉ ተተኪ ማፍራትም ሌላው የእንቅስቃሴያቸው አካል ነው። የቀድሞ ተማሪዎች፤ ትምህርት ቤቱ የተመሠረተበትን አንድ መቶ ዓመት ለማክበርም ከትምህርት ቤቱ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችን ኢትዮጵያን በኃይል ሲወር ቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል ተብሎ በዚያን ጊዜ ተማሪዎች ሆለታ ወደሚገኘው የጦር አካዳሚ እንዲሄዱ ተደረገ። በወቅቱም በትምህርት ቤቱ ተምረው ጀነራል ደረጃ የደረሱ እነ ጀነራል ከበደ ገብሬ፣ ጀኔራል እያሱ መንገሻ፣ ዋቅጅራ ሰበዳ እና ሌሎችም ተማሪዎች ናቸው የነበሩት።

ተማሪዎቹ ወደ ሆለታ እንደተዘዋወሩ ብዙም ሳይቆይ ጦርነቱ ተጀመረ። በወቅቱም ግማሾቹ ተማሪዎች ወደ አርበኞቹ ተቀላቀሉ። ገሚሶቹ ደግሞ ከሀገር ወጡ።

በጦርነቱ ወቅት የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እጣ ፈንታም በጣሊያን እጅ ላይ ነው የነበረው። ተፈሪ መኮንን መሆኑ ቀርቶ ቪክቶር አማኑኤል ትምህርት ቤት ተብሎ ተሰየመ። በወቅቱም ኢትዮጵያውያን በትምህርት ቤቱ መማር እንደማይችሉ ተከልክለው ጣሊያኖች ብቻ ነበሩ ለአራት ዓመታት የተማሩበት። ፋሽስት ጣሊያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ እና አፄ ኃይለሥላሴም በስደት ከቆዩበት ከእንግሊዝ ሀገር ተመልሰው ሀገራቸው ሲገቡ ትምህርት ቤቱን መልሰው አደራጁት።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሐኪም ተብለው የሚታወቁት ሐኪም ወርቅነህ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን አስተዳዳሪ ሆነው ሲሠሩ ነበር። በኋላ ላይ ግን አፄ ኃይለሥላሴ አሜሪካንንም እንግሊዝንም ወደ ጎን ብለው ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የወጡ የትምህርት ዓላማ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ በትምህርት የላቁ ናቸው ያሏቸውን ከውጭ ሰው ፈለጉ። ምርጫቸው ያደረጉት ካናዳን ነበር።

ካናዳዊያኑ ጀስዊቶች እንዲመጡ አደረጉ። በወቅቱ አፄ ኃይለሥላሴ ያስጠነቀቁት ኃይማኖታቸውን የሚያንፀባርቅ አለባበስ እንዳይለብሱ፣ ኃይማኖታዊ ትምህርትም እንዳይሰጡ፤ ፋዘርና ብራዘር የሚለውን አጠራርም እንዳይጠቀሙ፣ ሚስተር መባል እንዳለባቸው ነበር። እነርሱም ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው በኮሌጅ ደረጃ ኃላፊነት ላይ የሠራ ዶክተር ማት የሚባል ሰው አንድ አምስት ሰው ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ትምህርት ቤቱንም ማስተዳደር ጀመረ።

በወቅቱም ኢትዮጵያውያን፣ አሜሪካውያን፣ ህንዳውያን መምህራን ናቸው ያስተማሩን። በነበረኝ የትምህርት ቆይታ ትምህርት ቤቱ የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሀገሩን የሚወድ፣ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ዜጋ ለማፍራትም ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። አንድ ሰው ሙሉ ሰው መሆን የሚችለው በሥነ ምግባሩም የታነፀ ሲሆን እንደሆነ በወቅቱ ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳድሩት ካናዳዊ ይከተሉት የነበረ መርህ ነው። ተማሪዎች ምግብ ሲመገቡ እንኳን በልተው እስኪጨርሱ ድረስ ወሬ አያወሩም። ተማሪውን በሥነ ምግባር ማነጽ የካናዳዊያን መርህ ነው ማለት ይቻላል።

ከትምህርት ሰዓት ውጭ በተለያዩ ጉዳዮች ተማሪዎች ክርክር(ዲቤት) የሚያደርጉባቸው፣ የስካውት፣ የስፖርት እና ሌሎችም ተማሪዎች የሚሳተፉባቸው ክበባት ነበሩ። ተማሪዎች ማህበራዊ ተሳትፎ እንዲለማመዱም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የግንባታ ሥራዎችን በመሥራት ጭምር እንዲሠሩ ይደረጋል። ሌላው የትምህርት ቤቱ ጥንካሬ የነበረው የጥናት አዳራሽ (ሆል) በማዘጋጀት ተማሪዎች በትምህርታቸው የበረቱ እንዲሆኑ ጥረት ይደረግ ነበር።

የቀኑ ትምህርት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሲያበቃ ሁሉም ተማሪ ወደ ጥናት አዳራሽ ገብቶ የተሰጠውን የቤት ሥራ ይሠራል። የተማረውን ይከልሳል። ተቆጣጣሪ መምህርም ስላለ የትምህርት ጥያቄ ያለው ተማሪ ጠይቆ መልስ ያገኛል። ተማሪ ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣ ተገቢው ክትትል ይደረግ ነበር። የነበረው የትምህርት ሥርዓት በራሱ የሚተማመን ጎበዝ ተማሪ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን በሥራ ዓለምም ከፍ ያለ ቦታ እንዲደርስ መሠረት ሆኖኛል፡፡

መጀመሪያ ላይ ሴት ተማሪዎች አልነበሩም። በኋላ ላይ ግን ኮሜርስና ሆሚኢኮኖሚክስ የሚባሉ የትምህርት ዓይነቶች መሰጠት ሲጀምሩ ሴቶችም መማር ጀመሩ።

ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በብዙ ለውጦች ውስጥ አልፏል። ቀደም ሲል የቀለም(አካዳሚክ) ትምህርት ነበር የሚሰጠው። አሁን ደግሞ የተለያየ የሙያ ትምህርት እየተሰጠ ነው። የትምህርት ሥርዓት ለውጥ አለ ማለት ነው። ከተማሪ ቁጥር አኳያም በርካታ ለውጦች አሉ። አሁን ሰፊ ቁጥር ያለው ተማሪ ነው እየተማረ ያለው።

ዘመን ተሻጋሪው የእውቀት ቤት በተለያዩ ሙያዎች ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን በማፍራት ሂደት ቀዳሚ ነው። በሀገራችን አንቱታን ያተረፉ በርካታ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችንም አፍርቷል። በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፉም ፍሬያማ ተግባራትን አከናውኗል። በአሁኑ ወቅት በ11 የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን 3 ሺህ 668 ሰልጣኞችን በቀንና በማታ መርሀ ግብር እያሰለጠነ ይገኛል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You