
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል:: በተለይም ወደ ውጪ ሀገር ኤክስፖርት የሚደረጉና ወደ ሀገር የሚገቡ የግብርና ምርቶችን ደህንነትና ጥራት በመቆጣጠር ረገድ ሚናውን በመወጣት ላይ ያለ ተቋም ነው:: ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ የሆነው ግብርና፣ የምርቱን ደህንነትና ጥራት በመጠበቅ ወደ ውጭ ገበያ ይቀርብ ዘንድ የተቀባይ ሀገራትን መስፈርት በማሟላቱ ረገድ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፣ ባለስልጣኑ ተልዕኮውን ምን ያህል እየተወጣ ነው ? ሲል ሳምንት ክፍል አንድ ቃለ ምልልሱን ማስነበቡ ይታወሳል:: ዛሬ ደግሞ ለአርሶ አደሩ የሚቀርበው የዘር ብዜት አካሔዱ፣ የግብርና ምርት የምስክር ወረቀት አሰጣጡ፣ በተለይም ከቡና ምርት ደህንነትና ግብይት ጋር እንዲሁም ከአበባ ምርት ጋር ተያይዞ ያለው የቁጥጥር ስርዓት ምን ይመስላል? የሚለውን አስመልክቶ ከባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ጋር ያደረገውን የመጨረሻውንና ክፍል ሁለቱን ቃለ ምልልስ ይዞ ቀርቧል::
አዲስ ዘመን፡- የዘር ብዜቱ ትክክለኛነት ተከትሎ ምን የመጣ ለውጥ አለ ? ትክክለኛነቱን ፈትሻችሁ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ባታደርጉ ኖሮ የሚያመጣው ጉዳት ምን ያህል ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡- በመጀመሪያ ዘርን አንድ ተመራማሪ እንደግልም ሆነ እንደተቋም ተመራምሮ የደረሰበትን ያመጣል:: የሚመራመርባቸው የእርሻ ምርምሮች ደግሞ የክልል አሊያም ደግሞ የፌዴራል ሊሆን ይችላል:: የእርሻ ምርምሩ ተመራምሮ ዘሩ የተሻሻለ ወይም ደግሞ የተዳቀለ ዝርያን አውጥቶ ይሆናል:: ለምሳሌ ምርምሩ የተካሔደው የስንዴ ዘር ላይ ከሆነ ሰላሳ ወይም ሃያ አሊያም ደግሞ አስር በመቶ ምርት መጨመር ይጠበቅበታል:: በእኛ መስፈርት ቢያንስ አስር በመቶ ያህል መጨመር የግድ ነው:: አንድ የምርምር ተቋም አዲስ የማሽላ ዘር አምጥቼያለሁ ካለ ከአስር በመቶ በላይ የምርት ጭማሪ የሚያደርግ መሆን አለበት::
በሁለተኛ ደረጃ የምናየው በሽታን የመቋቋም አቅም የሚባለውን ነው:: ለምሳሌ ኢትዮጵያ በጣም ብዙ የአግሮኢኮሎጂ አላት:: ይህ አይነቱ የአየር ሁኔታ ከፍተኛ ቅዝቃዜ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ሙቀት ያለበትም ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ የወጣው ዘር የሚያገለግለው ለየትኛው አግሮኢኮሎጂ አካባቢ ነው? በዚያ አካባቢ የሚታወቁ በሽታዎች ለምሳሌ እንደባክቴሪያ ወይም ተምች አይነቱን በምርምር የወጣው ዘር ሊቋቋመው ይችላል ወይ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው::
ዘንድሮ በምርምር የቀረቡ ከመቶ በላይ የሆኑ ዘሮች በመጀመሪያ ከምርምር፣ ከተቋማችንና ከተለያየ አካላት የተውጣጣ የቴክኒክ ተመራማሪ ቡድን ሔዶ ያያል:: ውጤቱን ካየ በኋላ ለብሔራዊ የዘር አጽዳቂ ኮሚቴ እንዲቀርብ ይደረጋል:: የብሔራዊ የዘር አጽዳቂ ኮሚቴ የዘርፉ ባለሙያዎች ስብስብ ነው:: በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ተቋማችን ያለበት ነው:: ከቀረቡት ዘሮች ውስጥ መስፈርቱን ያሟላሉ ብለው ያሏቸውን ይለያሉ:: መስፈርቱን ያላሟሉ ደግሞ መሻሻል የሚችሉት ተሻሽለው እንዲቀርቡ የሚደረግ ሲሆን፣ መስፈርቱን ሙሉ ለሙሉ የማያሟሉ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚደረጉ ይሆናል:: ስለዚህ ጉዳዩ ዘር ስለሆነ የሚያልፍበት መስፈርት በጣም ጥብቅ የሆነ ነው::
በሁለተኛ ደረጃ ሌላው ቀርቶ ከዚህ መስፈርቱን አልፎ ከተዘራ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ የተባለው ምርታማነት የሚጨምር ወይም የማይጨምር እንደሆነ ክትትል ይደረግበታል:: ውጤቱን በተመለከተ የታየበት ጉድለት በማደግ ሒደት ውስጥ የሚያሳይ ከሆነ ተመራማሪው በቀጣይ ምን ምን ማካተት ይጠበቅበታል የሚለውን እንዲያጤነው ይደረጋል:: በዚህ ልክ ክትትል የማይደረግ ከሆነ ጥራት የሌለው ዘር ወደ አርሶ አደሩ ዘንድ ሊሔድ ይችላል:: ይህ ከሆነ ደግሞ ለአርሶ አደሩም ሆነ በጥቅሉ ለምርምሩ ዘርፍ ጉዳት ስላላው የዘር ሁኔታ የሚታየው በጥንቃቄ ነው::
ነገር ግን በአጠቃላይ በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ድረስ ዘር ለአርሶ አደሩ ይቀርባል:: ይህን አንድ ሚሊዮን ኩንታል ዘር ባሉን ሃያ ላቦራቶሪዎች ውስጥ ከማሳ ናሙና በመውሰድ የምንመረምረው እኛ ነን:: አብዛኛው ዘር የሚመረተው በአማራና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው:: በሀገሪቱ 60 በመቶ የሚሆነው ዘር የሚመረተው በኦሮሚያ ሲሆን፣ ቀጥሎ ትልቁ የሚመረተው በአማራ ክልል ነው:: እነዚህን ዘሮች ባለሙያዎች ናሙና ይወስዱና ወደላቦራቶሪ ይገባል፤ ዘሩ ያንን ሒደት ካጠናቀቀ በኋላ ለምርጥ ዘር ያገለግላል ተብሎ ‘ታግ’ ይደረግበታል:: ከዚያም ለአምራቹ እንዲቀርብ ይደረጋል::
አምራቹ ኮሜርሻል እርሻ ሊሆን ይችላል:: ይህ ግን ብዙ አይደለም፤ የሚያቀርቡት ትንሽ ነው:: አብዛኛው የሚመረተው የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እና የሕብረት ሥራ ማሕበራት ማሳ ላይ ነው:: ነገር ግን አጠቃላይ በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ ከሚፈልገው ዘር ውስጥ የሚቀርበው የዘር መጠን ከ25 በመቶ አይበልጥም:: የቀረው አርሶ አደሩ በየአካባቢው የሚዋዋሳቸው የዘር አይነቶች አሉ::
የግብርና ሚኒስትር የሚመሩት የጋራ ኮሚቴ አለ፤ ይህ ኮሚቴ ቢያንስ የሚቀርበውን የዘር መጠን 50 በመቶ ለማድረስ በመታቀዱ ዘንድሮ እንቅስቃሴውን ጀምረናል:: የዘር ምርቱ በእያንዳንዱ ክልል በእጥፍ እንዲጨምር፤ እነርሱ በእጥፍ ሲጨምሩ ደግሞ እኛ የቁጥጥር ስርዓቱን በእጥፍ ለመጨመር እየሠራን ነው:: ስለዚህ አሁን በተቀናጀ ሁኔታ ኮሜርሻል እርሻዎች ዘር ወደማምረት እንዲገቡ ለማድረግ እየታሰበ ሲሆን፣ አዲስ ሕግም ወጥቷል::
ከዚህ ቀደም ጠቅላላ ዘር የሚያመርተው መንግሥት ነበር:: በአሁን ጊዜ ግን አዋጁ የግሉ ሴክተር ዘር ማምረት እንዲችል የሚያደርግ ነው፤ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ደግሞ ዘር ወደ አፍሪካ ሀገሮች ኤክስፖርት ለማድረግ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በኩል ሰፊ ውይይት አድርጓል፤ በጉዳዩ ላይ ሰፊ የጋራ ማሕቀፍም ፈጥረናል:: ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ዘር ከኬንያ ሊመጣ ይችላል:: እዚያ ያለው ባለስልጣን ቁጥጥሩን አረጋግጦ ያመጣል::
እኛ የሆርቲካልቸር ዘር ከአውሮፓ ኔዘርላንድስና ከሕንድ እናስገባለን:: በዚህ መልኩ ከ24 ሺህ እስከ 30 ሺህ ኩንታል ይገባል:: ስለዚህ አሁን እየታሰበ ያለው ለኢትዮጵያ እርሻ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮችም ለአፍሪካም ጭምር ነው:: ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ሁሉም አይነት አግሮ- ኢኮሎጂ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ለዓለምም ጭምር በማሰብ ላይ እንገኛለን:: ባለሀብቱ ኤክስፖርት እንዲያደርግ እኛም ደግሞ እኛ ሀገር የማይመረቱትን ከውጭ በማስገባት ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ጭምር እንዲሸጋገር ለማድረግ አስበን እየሠራን እንገኛለን:: ከዚህ አኳያ በጣም በርካታ ሥራ አለ፤ ግብርና ሚኒስቴርም የዘር መጠን ለመጨመር በዚህ ላይ በጣም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ምርቶች ደኅንነታቸውና ጥራታቸው ተጠብቆ ወደ ገበያ እንዲቀርቡ ከማድረግ አኳያ የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ቢያብራሩልን?
አምባሳደር ድሪባ፡– ወደ ውጭ በዋናነት የሚላኩት ሁሉ ላይ የጥራት ቁጥጥር ይደረግባቸዋል:: የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ መነሻችን ወደ ውጭ የሚላኩትን ምርት በተመለከተ የተቀባይ ሀገሮችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነው:: ለምሳሌ የአበባ እርሻ እና የሆርቲካልቸር እርሻ በተመለከተ የአውሮፓ ሕብረት የቁጥጥር ደረጃውን አስቀምጧል:: እነርሱ ያስቀመጡትንና ምክረ ሐሳብና የሰጡትን ስርዓትን መሰረት ያደረገ አሠራር (System Approach) አምጥተን ኢትዮጵያ ላይ ተግብረናል:: ምርቱን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከእርሻ እስከ ኢንስፔክሽን ያለውን አካትቶ የተባይ (Pest) ቁጥጥር ስርዓቱን አስቀምጠን እየሠራን ነው::
ሁለተኛ ቡናን በተመለከተ ሲሆን፣ በተለይ የኢትዮጵያ ቡና አረቢካ የተባለው የቡና አይነት እንደመሆኑ በጣም በብዙ ሀገሮች ተወዳጅም ተፈላጊም እየሆነ መጥቷል:: ዘንድሮ በተለይ ኤክስፖርቱ በስፋት ጨምሯል:: ስለዚህ በእኛ በኩል የቡናን የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንሰጣለን:: የምንሰጠው በቡና ቦርድ ውስጥ ራሱን የቻለ ቢሮ ያለን ሲሆን፣ በዚያ ነው፤ እያንዳንዱ ባለሀብት የቡናውን ጥራት አረጋግጦ ያቀርባል፤ ካቀረበ በኋላ በእኛ በኩል አጣርተን ወደቻይና ወደ አውሮፓ የሚላክ የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንሰጣለን::
የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማለት የምርት ፓስፖርት እንደማለት ነው:: ስለዚህ የትኞቹም የግብርና ምርቶች የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የሚሰጠውን ፓስፖርት ሳይዙ ድንበር አቋርጠው ሊሔዱ አይችሉም:: እኛ የምንሰጠው የጥራትና የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ደግሞ የሚያልፈው በአይፒፒሲ (IPPC) በኩል ነው:: አይፒፒሲ ማለት የተባበሩት መንግሥታት የእጽዋትን ምርት ደኅንነት የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ቀጥታ ኦንላይን እነርሱ ዘንድ ይሄዳል:: እነርሱ ደግሞ አጽድቀው ወደ ተለያየ ሀገር ይሄዳል:: ስለዚህ ሲስተሙ በጣም ጥብቅ ነው:: ሕጎች አሉ፤ ስለዚህ የቁጥጥር ስርዓቱ የወጡ ሕጎችን ተከትሎ የሚካሔድ ነው::
ለምሳሌ ኢትዮጵያ፣ ወደቻይና ገበያ የስጋ ምርት መላክ ከፈለገች በመጀመሪያ እኔ ያስቀመጥኩትን ስታንዳርድ ማሟላት አለባት ስትል ምክረ ሐሳብ ሰጥታለች:: ቻይናውያን በጠየቁን ልክ መሠራት ያለበት ነገር ቢሆንም፤ ሥራው በጣም አስጨናቂ ነበር፤ ቴክኖሎጂው፣ ጽሑፉ በጣም ከባድ ነበር:: ባለሙያዎች ጊዜ ወስደው ሠርተውና እኛም አጢነን አረጋግጠናል:: ስለዚህ እኛ ሁሉንም ምርቶች የእኛን ምርት ተቀባይ ሀገሮች ወደሚፈልጉት የቁጥጥር ደረጃና ስርዓት ማሳደግ የግድ ይለናል::
ሁለተኛው ቁጥጥር ሲባል ሕግ፣ ቴክኖሎጂና የሰው ኃይል መኖሩ ብቻ አይደለም:: ይህ ተቋም በአግባቡ ይቆጣጠራል የሚል እምነት መፍጠር ያስፈልጋል:: ከአጋሮቻችን ዘንድ እምነት መምጣት መቻል አለበት:: አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የሚባል ተቋም የምርት ጥራትና ደኅንነትን በአግባቡ የሚቆጣጠር ነው:: ተቋሙ ጥሩ ሕግም አለው፤ በጉዳዩ ላይ በጥሩ ሁኔታ ይሰራል:: ቴክኖሎጂውም ጥሩ ነው፤ መረጃ ሲጠየቅም የሚሰጠው ወዲያውኑ ነው በሚል ጥሩ የቁጥጥር ተቋም ስለመሆኑ ምርቶቻችን ተቀባይ ሀገሮች ላይና ገና ለመቀበል በሚሹ ሀገሮች ላይ እምነት መፍጠር አለብን:: ስለዚህ እምነት መፍጠር እንዲያስችል ሀገሮች የጠየቁትን በሙሉ ከእኛም ከውጭም ጭምር ባለሙያዎችን በማስመጣት በምንችለው አቅም እየሰራን እንገኛለን::
ከዚያ በላይ ደግሞ በርካታ አጋሮች አቅማችንን ማስተዋወቅ በጀመርን በአንድ ዓመት ውስጥ ፍላጎት እያሳደሩ እና ሪሶርስም እየላኩልን በብዙ መልኩ ከእኛ ጋር እየሠሩ ነው:: ዩኤስአይዲም ሆነ የአውሮፓ ሕብረት በብዙ መስኩ እያገዙን ነው:: የኔዘርላንድስ መንግሥትም ከእኛ ጋር ይሠራል:: ጂአይዜድም በጣም ብዙ ሥራ ከእኛ ጋር ይሠራል:: ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ረገድም እንሠራለን::
ትልቁ ሥራ ማምረት አይደለም፤ ምርት የሚያመርተው አርሶ አደርና ‘ኮሜርሻል ፋርሙ’ ነው፤ መንግሥት የሚቆጣጠረው ጥራቱን ነው:: ስለዚህ ግብርና ሲባል በዋናነት የሚከፈለው በሶስት ነው:: አንዱ ምርምር ሲሆን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማውጣትና ግብርና በቴክኖሎጂ እንዲጠቀም ማድረግ ነው:: ስለዚህ በጣም ብዙ ምርት ማስገኘት የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን ለማውጣት አንደኛውና ዋና ቁልፉ ምርምር ነው:: ለምሳሌ አንድ በሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ምርትን ቢያጠቃ የበሽታው ምንጭ ምንድን ነው? የመጣውስ ከየት ነው? መከላከያ ዘዴውስ ምንድን ነው? የሚለውን የሚሰራው ምርምር ነው:: እርሻን ለመጠበቅም ይሁን ለማስፋፋት ቁልፉ ምርምር ነው:: ሁለተኛው ማምረት ነው:: ሶስተኛው ደግሞ ‘ሬጉላቶሪ’ ነው::
ይህን መሰረት አድርገን ስናጤን በርካታ ተቋማት ለእኛ ተቋም ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው:: እኛም በመጠናከር ላይ እንገኛለን:: የተለያዩ ሕጎችንም በማጸደቅ ላይ እንገኛለን:: ከሰሞኑ ብቻ የጸረ ተባይ ቁጥጥር ሕግና የዘር ምዝገባ ስርዓት መመሪያ ጸድቋል:: ከ15 በላይ መመሪያዎች፣ አዋጆችና ደንቦች አሁን መስመር ውስጥ ገብተዋል:: ይህ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የሕግ ማሕቀፍ ለማሟላት የሠራነው ሥራ ነው:: ስለዚህ በዚህ መልኩ በርካታ ሥራ እየተሠራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- የፍተሻ የምስክር ወረቀት ለአንድ ምርት ሲሰጥ ከበሽታ፣ ከተባይ፣ ወይም ከማንኛውም አይነት ተዋህሲያን ነጻ መሆኑ ተረጋግጦ ነው፤ ታድያ ስጋትን ከመቀነስ አኳያ ባለስልጣኑ ያለው ዝግጁነት እስከ ምን ድረስ ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡– ይህ ተቋም በዋናነት የሚሠራው የእርሻ የ’ባዮሴኪዩሪቲ’ ሥራ ነው:: የ’ባዮሴኪዩሪቲ’’ ሲባል ትልቁ ነገር በሽታ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የእርሻ በሽታዎች ይከሰታሉ:: ለምሳሌ ዋናው የኢትዮጵያ ኦሪጅናል ማንጎ ጠፍቷል:: ቅርብ ጊዜም ሎሚ ላይ እንዲሁም አፕል ላይ እንዲሁም የተለያየ እርሻ ምርቶች ላይ አሁንም በቅርቡ አቮካዶ ላይ የሙዝና የኮባ ምርት ላይ በሽታ በመከሰቱ ከምርምርም ጋር ተሳስረን በሽታውን የመቆጣጠርና የመግታት ሥራ እየሠራን ነው::
ስለዚህ በዋናነት ሰርተፍኬት ስንሰጥ የምንከተለው የሕግ ማኅቀፉን ነው:: ለምሳሌ አንድ ኢንስፔክተር አንድ ምርት ሲመረምር የሚመረምረው በነጻነት ነው:: ለአብነት ቄራ የሚገባ አንድ ከብት ካለ እሱ አሰራር የራሱ የሆነ መስፈርቶች ያሉት ነው:: በመጀመሪያ በአቋም በኩል ይታያል፤ ቀጥሎም የጤና ምርመራ ይደረግለታል:: የጤና ምርመራ ሲደረግለት እንሰሳው ምን ምን አይነት በሽታ ሲኖርበት ነው እንዲታከም ወይም ክትባት እንዲያገኝ የሚደረገው የሚለው በመመሪያው ላይ የተቀመጠ ነው:: እንሰሳው ከታረደ በኋላ ስጋው ላይም እንደገና ተመሳሳይ ምርመራ ይደረጋል:: ከተመረመረ በኋላ የምርመራውን ውጤት ተከትሎ የምርመራው መስፈርት የሚያመለክተውን የሚያሟላ ከሆነ ኢንስፔክተሩ ሰርተፍኬት ይሰጣል:: እሱ ምርት የሆነ ሀገር ተልኮ በሽታ ቢገኝበት ምርመራውን ያካሔደው ኢንስፔክተር ተጠያቂ ይሆናል:: ስለዚህ ስርዓቱ ጥብቅ ነው::
የአበባ እርሻም እንደዚሁ ነው:: እርሻ ላይ ይመረመራል:: ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ላይም የመመርመሪያ መሳሪዎች አሉን:: እዚያ ላይ ምርመራ ይካሔዳል:: ከሔደም በኋላ የአውሮፓ ድንበር ላይ አንድ ተባይ ቢገኝበት ወዲያው እንዲህ አይነት ምርት ላይ እንዲህ አይነት ተባይ አግኝተናል የሚል ኦንላይን ሪፖርት ይመጣልናል:: ይህ ነገር ከኢንስፔክተሩ ቁጥጥር በላይ ነው ወይስ በታች ነው በሚል በእኛ ግምገማ ይደረጋል:: ተባዩ ከምርቱ ጋር የተጓዘው በግዴለሽነት ከሆነ ኢንስፔክተሩ ተጠያቂ ይሆናል:: ከአቅሙ በላይ ሆኖ ከሆነ ደግሞ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ላቦራቶሪ ይላካል::
ሀገር ውስጥም ከአንዱ ወደሌላ ቦታ የሚላኩ ለምሳሌ የመኖ፣ የእንስሳት መድኃኒት የተለያዩ የእርሻ ምርቶች ሲመረመሩ የምንጠቀመው ወይ የላቦራቶሪ ውጤት ነው ወይም ደግሞ ኢንስፔክተሩ ያቀረበውን ነው:: ላቦራቶሪ ከሆነ ውጤቱ ግራ ቀኝ የሚያሰኝ አይደለም፤ ውጤቱ ታይቶ ወይ ይለፍ ሊባል ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ውድቅ ይሁን የሚለው ይወሰዳል::
በአሁኑ ጊዜ ሥራዎች እንደጅምር በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ ነው:: ነገር ግን ከባዱ ፈተና ምንድን ነው ከተባለ ሁሉም ቦታ መድረስ አስቸጋሪ መሆኑ ላይ ነው፤ በተለይ ክልሎች መጠናከር አለባቸው:: በየላቦራቶሪው ውስጥ ብቁ ኢንስፔከተሮችን በመመደብና ኢንስፔክተሩ እራሱ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ይገባል:: በሚሠራው ሥራ ግዴለሽነትን ካሳየ አሊያም ደግሞ ሙያውን በአግባቡ ካልተገበረ (ከአቅሙ በላይ ከሆነ ሌላ ተጨማሪ ሥራ ይሰራል) እንደዚህም በማድረግ በተቻለ መጠን ወደውጭ የሚላኩ በሀገር ውስጥም ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች ከበሽታ እና ከተለያየ የኬሚካል ቅሪቶች እንዲሁም ደግሞ የምርቱ ይዘት ማለትም የ’ኒውትሬሽናል’ ደረጃው የተሻለ ሆኖ ማሕበረሱ እንዲጠቀምበት ለማድረግ የሞከርናቸው ሥራዎች አሉ:: አንድ አደገኛ ነገር ነው ሊባል የሚችል ጉዳይ ስለምርት ደኅንነት የማሕበረሰብን እውቀት መጨመር የማንችል ከሆነ ነው:: ስለዚህ በምርት ደኅንነት ዙሪያ የማሕበረሰቡን እውቀት መጨመር አለብን:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ድሮ ምርትን ሊበክል የሚችል ነገር እምብዛም የለም:: በአሁኑ ጊዜ ግን ከተማም ፋብሪካም እየተስፋፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተሞችም ፋብሪካዎችም ቆሻሻቸውን የሚያስወግዱበትን መንገድ ዘመናዊ በማድረጉ በኩል ገና ብዙ የሚቀራቸው ነገር አለ::
ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣቸው ምክንያት ለዜጎች ደኅንነትና ውጭ ለምንልከው ምርት ደኅንነት አደገኛ ስለሆኑ የቁጥጥር ስርዓቱ የበለጠ እንዲጠብቅ ማድረጉ ወሳኝ ነው:: በተለይ ደግሞ ከተለያየ ተቋም የሚወጣው ዝቃጭ በአግባቡ ተለይቶ ለሰው፣ ለእንስሳትና ለምርት በጥቅሉ ለአካባቢው አፈር እና የከርሰ ምድር ውሃን እና አየርንም ጭምር ሊበክሉ ይችላሉ:: እነዚህ ደግሞ መልሰው የዜጎችን ጤና ሊጎዱ ይችላሉና እነዚህን ሁሉ አስተሳስረን መሥራት ስላለብን ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና ከሌሎችም በዚህ ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር በመሆን ቁጥጥራችንን በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል:: ምክንያቱም ብቻችን አንወጣውምና ነው::
በፖሊሲ አውጪዎችም የእርሻ የ‘ባዮሴኪዩሪቲ’ ጉዳይ ኤክስፖርት ወይም ምርትን መከታተል ብቻ ሳይሆን የቁጥጥርና የምርት ደህንነት ሥራ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው የሚለውን እንዲያውቁና እንዲቆጣጠሩ ነው:: ይህን አንድ ላይ ደምረን ከሰራን እና ቴክኖሎጂ ከተጠቀምን እርግጠኛ ነኝ የኢትዮጵያን እርሻ የደኅንነትና የጥራት ደረጃ ወደላቀ ከፍታ ማድረስ ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- ከምርት ደህንነትና ግብይት ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ገበያ ካወጣቸው ሕጎች መካከል አንዱ “ጫካ ከተጨፈጨፈ ቡና አንገዛም” እስከ ማለት የደረሰ ውሳኔ ነው:: ከዚህ አኳያ እንደሀገር የቡና ግብይቱን እዳይፈትን ምን ታስቧል?
አምባሳደር ድሪባ፡– በእርግጥ ቡናን እኛ በቀጥታ የምንከታተለው ባይሆንም የምንሠራው በጋራ ስለሆነ በዚህ መልክ ልዳስሰው እችላለሁ:: የአውሮፖ ሕብረት የሚባለው የተለያዩ ሀገሮች ፍላጎት ያለበት ስብስብ ነው:: ሕብረቱ አንድ ተቋም ቢመስልም ወደ 27 ያህል ሀገሮች ያሉበት ነው:: ከዚህ አኳያ የሚመጣው የተለያየ ፍላጎት ነው::
ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቡና እንደሚታወቀው በቤተሰብ ደረጃ ባለ እርሻ የሚመረት እንጂ ትልልቅ የኮሜርሻል እርሻ ላይ የሚመረት አይደለም:: የቤተሰብ እርሻ ሲባል ደግሞ እያንዳንዱ ቤተሰብ ከልጆቹ ጋር በመሆን በእነርሱ ጉልበት የሚሠራው ነው:: በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ቡና የሚበቅለው በአብዛኛው በዛፍ ስር ነው:: ዛፍ ተመንጥሮ የሚበቅል አይደለም:: ስለዚህ ለዛፍ ምንጣሮ የሚያጋልጥ አይደለም:: በተፈጥሮ ቡና ጥላ ስለሚፈልግ የሚበቅለው የግድ ዛፍ ስር ስለሆነ አባባሉ አንዳንድ ጊዜ እውን ለደን ታስቦ ነው ወይስ ሀሳቡ የመጣው ከምንድን ነው? ቢያስብልም የሚያውቁት እነርሱ ናቸው:: ነገር ግን እንዲሁ ስገምት እውን ከደን ምንጣሮ ጋር ብቻ የተያያዘ አይመስለኝም:: ምክንያቱም የደሃ ሀገሮችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች በተለያየ መንገድ የዓለም ገበያ ውስጥ እንዳይገባ የሚደረግ አካሔድ ይመስላል፤ ከዚህ የተነሳ ብዙ ፈተናዎች አሉ::
በእርግጥ በሕብረቱ ካሉ ሀገሮች መካከል አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ቡና የበለጠ እንዲያድግ የሚፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ የእራሳቸው የገበያ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል:: ይህን ሐሳብ እውነታውን በማጤንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ቡና ዛፍ ስር የሚበቅል ነው:: በአብዛኛው ትልልቅ ዘመናዊ እርሻዎች የሚያመርቱት አይደለም:: ከ90 እስከ 95 በመቶው የሚሆነው የሚመረተው በአነስተኛ ማሳ ላይ ነው:: ስለዚህ የቡናን ኤክስፖርት ሲያቆሙ መውሰድ ያለበት የእነዚህን ቤተሰቦች ሕይወት የሚጎዳ ጭምር ተደርጎ ነው:: በአንድ በኩል በአደጉት ሀገራት ድኅነትንና ኋላቀርነትን ለማጥፋት ሀገሮች ሁሉ ወደብልጽግና እንዲሔዱ ለማድረግ እናግዛለን የሚል አለ::
በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ አይነት አነስተኛ ቤተሰብን ሳይቀር የሚጎዳ አይነት ፖሊሲ ይወጣል:: ለማንኛውም የእኛ መንግሥት ይህን በመረዳት በጣም ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው:: ‘ጂኦሎኬሽኑ’ በሙሉ ተጠንቶ እያለቀ ነው:: ቡና ከደን ጋር እንዴት አብሮ እየለማ እንደሆነ ሊያሳይ የሚችልም ነገር አለ:: ከፈለጉ ደግሞ እዚያው ቢሯቸው ሆነው በቴክኖሎጂ እራሳቸው እንዲያዩ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ጥናት ተደርጎበታል፤ እሱም በሚቀጥለው ዓመት ታሕሳስ ወር አካባቢ ሥራ ላይ ሊውል የሚችል ነው:: እስከዚያ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከባለሙዎች ጋር ከሀገር ውስጥም ከውጭም በማስተባበር ምላሽ የሚሰጥ ሥራ እየተሠራ ስለሆነ ብዙም ስጋት ይሆናል ብዬ አላስብም::
ነገር ግን ጉዳዩ እንደጉዳይ የእኛ ቡና ኮፊ አረቢካ እንደመሆኑ እንደ ሮቡስታ ቡና አይነት አይደለም:: ጠቅላላ በደን ስር የሚበቅል ስለሆነ እንዲያውም ለደን መጠበቅ እና ለደን መስፋፋት ትልቅ ጥቅም ያለው ነው:: ይህን እንዲገነዘቡ ደግሞ መሥራት አለብን:: በእርግጥ ሄደንም ጉዳዩን በቡና እና ሻይ ባለስልጣን አማካይነት ያስረዳን በመሆኑም በተወሰነ ደረጃ ይህን ስለተገነዘቡ ይመስለለኛል ተጨማሪ አንድ ዓመት ጊዜ ሰጥተውናል:: ጉዳዩን በተመለከተ ጥናት እየተጠና ሲሆን፣ ጥናቱም በጥሩ በሁኔታ እየሔደ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ ላይ የአውሮፓ ኮሚሽን “የእሳት እራት” ከሚባል ተባይ ጋር ተያይዞ ያስተላለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ ምርት ላይ ያለው ጫናን ለመቀነስ ምን አሠራር ተቀምጧል?
አምባሳደር ድሪባ፡– ይህን ሥራ መቶ በመቶ የምንሠራው እኛ ነን:: ኮቪድ የነበረ ጊዜ ከ2019 እስከ 2023 ድረስ ወደ አውሮፓ ገበያ የምንልከው ምርት ላይ የእሳት እራት በ48 ማጓጓዣ (consignment) ላይ ትገኛለች:: እነርሱ ደግሞ ይህ የእሳት እራት ተባይ ወደ ሀገራችን ከገባ ምርታችንን ያጠፋል፤ ስለዚህ አቁሙልን:: ተባዮቹን ተቆጣጠሯቸው የሚል መረጃ አደረሱን:: መረጃውን ተከትለን አቻምና እንዴት ተባዩን ማቆም እንዳለብን ተወያየን::
ተባዩ በሀገራችን በየሰው ቤት የሚገኝ ነው:: እንደሚታወቀው ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳት አያደርስም:: ወደ እነርሱ ሀገር ሲሄድ የተወሰነ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል:: ከዚህ የተነሳ ያነሱት ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል:: በተለይ ደግሞ ሜዴትራኒያን አካባቢ ያሉ ሀገሮች እንደ እነ ስፔን የመሳሰሉ ሀገራት ስጋታቸው ትንሽ ስለጨመረ ይህ ተባይ ድንበር አቋርጦ ወደአውሮፓ እንዳይገባ አድርጉ የሚል ግብረ መልስ ስለመጣ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት አካሔድን:: ጥናት ካደረግን በኋላ ተባዩ የሚከሰተው ከአስር የአበባ እርሻዎች የሚበልጥ አለመሆኑን አረጋገጥን:: አብዛኛዎቹ እርሻዎች ነጻ ናቸው:: ተባዩ የታየው በሪፍት ቫሊ ውስጥ ከሚገኙ አስር እርሻዎች ውስጥ ነው:: ይህን ተከትሎ የሚከሰተው ለምንድን ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው? የሚለውን አጠናንና ሰፊ የኢንስፔክሽን ስርዓት ዘረጋን:: የኢንስፔክሽን ስርዓቱ ላይ ከአበባ እርሻ ባለቤቶቹም ጋር ተወያየን:: ከአበባ እርሻ ማኅበሩ እና ከግብርና ሚኒስቴርም ጋር ሆነን ሰፊ የኢንስፔክሽን ስርዓት ዘረጋን:: በቁጥጥሩም በአንድ ጊዜ ከታየው በግማሽ ያህል መቀነሰ ቻልን:: ከተወሰኑ ወራት በኋላ ደግሞ ወደ ‘ዜሮ’ አቀረብነው::
ነገር ግን ወደ አውሮፓ ድንበር ሲደርስ ኢንስፔክሽን ይካሔዳል:: በፊት ኢንስፔክት የሚያደርጉት አምስት በመቶ ነበር:: አሁን ግን ስጋት ስለያዛቸው የኢንስፔክሽን ደረጃውን ወደ 25 በመቶ ከፍ አደረጉት:: ይህ ማለት ከሚሄደው ውስጥ 25 በመቶውን ኢንስፔክት ያደርጋሉ ማለት ነው:: 25 በመቶ ኢንስፔክት ማድረግ የጀመሩት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር:: በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ግን ብዙም አልተገኘም:: የተገኘው የተወሰነ ነው:: ምክንያቱም እኛም የኢንስፔክሽን ስርዓቱን ጥብቅ ስላደረግን ነው::
የአበባ እርሻዎችም እውነት ለመናገር በሙሉ ሰራተኞቻቸውን፣ የኮች ማናጀራቸውን አሰለጠኑ:: እኛም ደግሞ የኢንስፔክሽን ፕሮቶኮል አወጣን:: ያደረግነው ጥሩ እንደሆነና የኢንተርሰፕሽን መጠኑ እንደቀነሰ ገልጸውልን የኢንስፔክሽን ስርዓቱን ግን ከ‘ሲንግል አፕሮች’ ወደ ‘ሲስተም አፕሮች’ ቀይሩ ሲሉ ግብረ መልስ ሰጡን:: ከዚያ በኋላ ከኔዘርላንድስ ሶስት ባለሙያዎችን አመጣን:: ከእና ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በማደግ ‘ሲስተም አፕሮች’ ምንድን ነው? የሚለውን አጠናን:: ይህም ስድስት ወር ፈጀብን:: እሱን ወደ አውሮፓ ሕብረት ልከን የተቀበሉን ሲሆን፣ የተወሰነ አስተያየትም ጠይቀውን ሰጥተናል:: በቀጣይ ደግሞ እኛ ወደዚያ ሔደን በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንሰጣለን::
ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሌሎቹን ሀገሮች መቶ በመቶ ኢንስፔክት የሚያደርጉ ሲሆን እኛን እና ኬንያን ግን ኢንስፔክት የሚያደርጉን 25 በመቶ ብቻ ነው:: እኛ የአበባ እርሻችንን እስካሁን ድረስ መከላከል ችለናል ማለት ነው:: የአበባ እርሻ ባለቤቶቹም ሆኑ በተለይ ደግሞ ማሕበሩ በጣም ጠንካራ ነው:: ማሕበሩ ቴክኖሎጂ ያመጣል፤ ሐሳብ ያመጣል:: ይበልጡኑ ደግሞ እዚያ ያሉ ኃላፊው በጣም ጎበዝ የሚባሉ ናቸው:: ከቦርዱ ጋር በጋራ ይሰራሉ:: ስለሆነም የአበባ እርሻችን በአሁኑ ጊዜ አስተማማኝ ነው ማለት ይቻላል:: ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተባይ ባህሪውን የሚቀያይር አይነት ስለሆነ በተለይ ደግሞ የተወሰኑ ‘ሎኬሽኖች’ አሉ:: አካባቢው ትንሽ ሙቀት የሆነበት ቦታ አንዳንድ ማስተካከል ያለብን ክፍተት እንዳለ አስተውለናል:: አሁን የ‘ሲስተም አፕሮች’ን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አድርገናል:: ስለዚህ የአበባ ምርታችንም ወደ አውሮፓ ገበያ የመግባቱ ነገር ቀጥሏል:: በዓመት እስከ ከ500 እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ ከዘርፉ ገቢ ታገኝበታለችና ይህ ገቢ ቢቆም ከባድ ችግር እንደሚያመጣ በማሰብ ወደስርዓት አስገብተነዋል::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
አምባሳደር ድሪባ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም