ያለፉት ሰባት ዓመታት እንደ ሀገር ምን ይዘው መጡ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቃለ መሐላ ፈጽመው በትረ መንግሥቱን ከጨበጡ ትናንት ሰባተኛ ዓመት ሞላቸው:: የለውጡ ዕደሜ አንድ ሁለት ሦስት እየተባለ የተቆጠረው እንዲሁ እንደዋዛ አልነበረም:: ብዙ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል:: በብዙ የምስራቾች ምስር በልተናል:: በአያሌ መጥፎ ሰበር ዜናዎች ተሰብረናል::

ለውጥ በባህሪው ደፍርሶ የሚጠራ ነው እያልን ታግሰናልም፤ አግዘናልም:: እውነታውም እንዲያ ነው:: ረጅም ጊዜ በመውሰድ በሂደት የሚደረጉ ዘገምተኛ ለውጦች በቀላሉ ሊሰምሩ ይችላሉ:: በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደረጉ የአብዮት መልክ ያላቸው ለውጦች ግን ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል። የብዙኋኑን ይሁንታ ያገኙና እጅግ የተዋቡ ለውጦች ቢሆኑ እንኳን በለውጦቹ የሚጎዱ ሰዎች መኖራቸው አይቀሬ ነው። ቀደም ሲል ሲያገኙ የነበረውን ጥቅም የሚቋረጥባቸው እና ትናንት በፈጸሙት በደል ነገ በለውጡ ኃይል ተጠያቂ እንሆናለን ብለው የሚሰጉ ወገኖች እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም::

ከቻሉ ለውጡን ለመቀልበስ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ:: ካልቻሉ ደግሞ ባልበላው ጭሬ አፈሰዋለሁ እንዳለችው ጭሮ አዳሪ ሀገርን ብጥብጥና ትርምስ ውስጥ ለማስገባት ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው በመስራት ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን በማድረግ ጊዜ ለመግዛት ይታትራሉ:: ትናንት ሰባተኛ ዓመት ልደቱን ያከበረው ለውጥ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈ ነው::

የ2010 ዓ.ም. መጋቢት 24 ከዚያ በፊት ከነበሩት መጋቢት 24 ቀናት ልዩ ያደረጉት ክስተቶች ተመዝግበውበታል:: እነዚህ ክስተቶች ሁሉ የታጨቁት ዐቢይ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ባደረጉት ንግግር ነው::

ለ27 ዓመታት ከላይ እስከታች ባሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች “ሀገሪቱ” እየተባለች እንደ ባዕድ የሩቅ ሩቅ ተደርጋ ስትጠራ የነበረችው ሀገር በፓርላማ ውስጥ ሊያውም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ በአንድ ንግግር ከደርዘን ጊዜ በላይ ስሟ በክብር እና በፍቅር ተጠራ:: አንድነትን የሚሰብኩ ከኢትዮጵያውን እውነታ የተቀዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች የበርካቶችን ስሜት የኮረኮሩና ስለሀገራቸው መጻኢ ዕድል ተስፋን እንዲሰንቁ የሚያደርጉ ነበሩ::

አሁንም ድረስ በሚሊየኖች ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ የቀረው ታወቂው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ንግግር በመጀመር አንድ ሁለቱን በምልሰት እንቃኝ::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት ቆመው ባደረጉት እጅን በአፍ ባስጫነ ንግግራቸው እንዲህ ብለው ነበር::

“…አማራው በካራማራ ለአገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋዩ በመተማ ከአገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤኒሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ሥልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያውና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፤”

ቀጥለውም ኃላፊነት በመተመላ መንገድ ከለውጡ በፊት ለተፈጸሙ ጥፋቶች በፍጹም ትህትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው፣ ወደፊት ሕዝባቸውን ለመካስ እንደሚሰሩ ቃል ገቡ:: እንዲህ ሲሉ፡-

“በዜጎቻችን ሕይወት እና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል። ይኼንን ሁላችንም ማስቀረት እንችል እና ይገባንም ነበር። በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቧርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፣ ለሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ::”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጀመሪያው መጋቢት 24 በኋላ አንድ ሁለት ሦስት እያሉ ሰባተኛው ላይ የደሩሱት በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር በተግባር እየተረጎሙ ነው:: አንድ ሁለት ጉዳዮችን ለአብነት ማንሳት እንችላለን:: በመጀመሪያው መጋቢት 24 ባደረጉት ንግግር “ተፎካካሪ” ብለው የጠሯቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አብረዋቸው እንዲሰሩ ጠይቀው ነበር:: ምንም እንኳን በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት ወንበሮች ያሸነፈ ቢሆንም መንግሥት ሲመሰርቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በካቢኒያቸው አካትተዋል::

በፌዴራል ደረጃ ከሚኒስትርነት አንስቶ የጀመረው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ የመንግሥት ኃላፊነት የማምጣት እርምጃ በክልል ደረጃ እስከሚገኙ የስልጣን እርከኖች ተተግብሯል:: “ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር” ሆኖባቸው ተዋርደው የወረዱ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችን ተመልክተናል:: የተቀበሉትን ኃላፊነት እየተወጡ የሚገኙም አሉ::

በመጀመሪያው መጋቢት ባደረጉት ንግግር በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክት “ለሁላችሁም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ አገር አለችን። ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሀገራችሁ መመለስና ሀገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን፤” ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር:: እስከ ሰባተኛው መጋቢት ለዚህ ጥሪም ሁለት መልክ ያለው መልስ አስተናግደዋል:: እውነተኛ የሀገር ውለታን አሳቢዎች እና ባለውለታዎች አለሁ ብለው ከተፍ ብለዋል:: እያደር ግን ሰርቶ አደሩ እና ሆድ አደሩ ተለይቷል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከፓርላማው ንግግራቸው በኋላም እስከ ሰባተኛው ድረስ ባሉት መጋቢት 24ቶች በየጊዜው የሚያደርጓቸውን ንግግሮች በተግባር ለመተርጎም ተንቀሳቅሰዋል:: በአንድ መድረክ ባደረጉት “አሸባሪዎቹስ እኛ ነን” ሲሉ በተደመጡበት ብዙዎችን ባስገረመ ንግግራቸው አሸባሪ ተብለው በየእስር ቤቱ የታጎሩ ኢትዮጵያውያንን ነጻነት አውጀዋል:: በዚህም በአሸባሪነት ተፈርጀው በውጭ ሀገር በስደት እና በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡና በርካቶችም ከእስር እንዲለቀቁ ሆኗል:: የተቃዋሚ መሪዎች ወደ ሀገር ተመልሰው የፖለቲካ ተሳፏቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል::

እስከ ሰባተኛው መጋቢት 24 ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል:: ነጻና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተቋቁሟል:: የኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሆኖ በርካታ ሪፖርቶች እያወጣ ይገኛል:: መንግሥት ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ላይ የራሱ እይታ እንዳለውና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሪፖርቶቹን እስከማጣጣል እንደደረሰ የሚታወቅ ቢሆንም ኮሚሽኑ በነጻነት ሥራውን እንዲከውን አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸው ትልቅ ስኬት ነው::

ጠንካራ ምርጫ ቦርድ ማደራጀትና የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ አረጋግጧል:: ምርጫ 2013 በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተካሄደው ምርጫ ነዋሪዎች በስፋት በመሳተፍ ድምፃቸውን የሰጡበትና ከዚህ በፊት ከተካሄዱት አምስት ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመካሄዱ ረገድ የተሻለ እንደነበር በብዙዎች መነገሩ የሚታወስ ነው::

በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር እንዲቻል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል:: ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ በማድረጉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል። ይህ ኮሚሽንም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር የማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ሂደትን በጥሩ ሁኔታ በመምራት የታለመለትን ግብ ለመምታት ጫፍ ደርሷል።

በተለያዩ ተቋማት ላይ በስፋት የሪፎርም ሥራዎች ተሰርተዋል:: የትምህርት፣ የማይክሮ ኢኮኖሚ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የፍትሕ ዘርፍ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሚዲያ እና የሌሎችም ተቋማት ሪፎርሞች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው::

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ያከናውን የነበረውና ለግንባታው መጓተት ምክንያት እንደነበር ሲጠቀስ የቆየው ሜቴክ በግንባታው የነበረው ጉልህ ተሳትፎ እንዲቋረጥ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ የነበረበትን ደረጃ ገምግመው የማስተካካያ እርምጃዎችን ከወሰዱ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ፕሮጀክቱ በነበረው አመራር በነበረው አካሄድ ቢቀጥል ምንም አትጠራጠር እንኳን ዘንድሮ በሁለት ሶስት ዓመታት ውሃውን መያዝ አይችልም። ግድቡም አይገደብም፤ ሥራውም አይሰራም” ብለውም ነበር። እናም ተደረጉ በተባሉ ማስተካከያዎች ዛሬ ግድቡ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ ችሏል። በአንድ መንፈቅ ውስጥ ተመርቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምርም ተገልጿል::

የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታም ተቀላጥፏል:: ለዚህም በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተካሄዱ የሚገኙት የሸገር ወንዝ ልማት፣ ለሚ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ፣ አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል እና በተለያዩ ከተሞች በስፋት እየተካሄደ ያለው የኮሪዶር ልማት ተጠቃሾች ናቸው::

ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር በተያያዘም ለዘመናት ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት ተግባራዊ ምላሽ ማግኘት ጀምረዋል:: በዚህ መሰረት አራት ተጨማሪ አዲስ ክልሎች ተፈጥረዋል:: የሲዳማ ዞን ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ተለይቶ ራሱን የቻለ ክልል መሆን ችሏል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተካሄደ ማግስት አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ አካሂደዋል። በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ መሰረትም የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን በጋራ 11ኛውን ክልል በመሆን በይፋ ተመስርተዋል።

የስንዴ የወጪ ንግድን በይፋ መጀመሯ አዲስ ምዕራፍ የከፍታ ታሪካዊ ስኬት ሆኗል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ ስንዴ አማራች በሆነው በባሌ ዞን ተገኝተው ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን በይፋ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ልትጀምር መሆኑን ባበሰሩበት ንግግራቸው የስንዴ ኤክስፖርትም አዲስ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኛ እንደሚሆንም ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ አታስገባም የሚለው ራዕይ ለብዙዎች የሚዋጥ አልነበረም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ማኅበረሰቡም ሆነ በርካታ የመንግሥት አመራሮች ይህንን ሐሳብ ተጋርተው ለመሥራት ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል:: አሁን ግን ይህንን ውጥን ማሳካት ስለመቻሉ በተግባር ማሳየት ተችሏል ብለዋል::

የለውጡ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም:: አኩርፎ መቀሌ በከተመው በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የነበረው አለመግባባት ተካሮ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ክህደት ኢትዮጵያን አስከፊው ጦርነት ውስጥ ከቷታል:: በሦስት ዙር ከተደረገ አስከፊ ጦርነት በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በሕወሓት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ጦርነቱ መቋጫ አግኝቷል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም ፈትኗል:: በተለይ በምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች እየፈተነ ይገኛል:: የኑሮ ውድነቱ ጥልቅ የቤት ሥራ ነው:: ቀጣይ መጋቢት 24ቶች የሚቆጠሩት የሕዝብን ኑሮ በመሻሻልና መሰረታዊ ችግሮችን በመቅርፍ ሊሆን ይገባል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሰባቱ መጋቢት 24ቶች በአንዱ ካደረጉት ንግግር በወሰድኩት ሀሳብ ጽሁፌን ልቋጭ “ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ የአፍሪካ የኃይል ምንጭ ትሆናለች፤ በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ተደማጭነት ካላቸው ሀገራት ትሆናለች፤ በውስጣችን ጥቃቅን ችግሮች አሉ፤ እነሱ እየተፈቱ፣ አንድ እየሆንን፣ እየተደመርን፣ ለልጆቻችን የኩራት ምንጭ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ይኖርብናል። ጉዟችን ይሄ ነው”

መግነጢስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You