
ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያረጋግጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናዊ ትምህርት መጀመር እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ ያገለገለው ለዘመናት በክርስትናና በእስልምና የሃይማኖት ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የማንበብና የመፃፍ ትምህርት ነው:: በዚህም የሃይማኖት ትምህርቱን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማጣጣም ብዙ የተማሩ ሰዎችን ማፍራት ችለዋል::
ዘመናዊ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለያዩ የውጭ ሀገር ሰዎች በዋናነት በሚሲዮናውያን እንደገባ ይታመናል:: የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ተጀመረ::
ትምህርትን ወደ ሌሎቹም የሀገሪቷ ክፍሎች ለማስፋፋት አጼ ምኒልክ የተለያዩ ርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የልዑካን ቡድን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የሌሎች ሀገራትን የትምህርት ልማት ልምዶችን ቀስመው እንዲመጡ የተደረገበት እና ብዙ ተማሪዎችን ወደ አውሮፓ ሀገራት በመላክ የአውሮፓውያንን ትምህርት እንዲማሩ መደረጉን ማንሳት ይቻላል። በዚህም መሠረት በአጼ ምኒልክ ዘመን ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች በአንኮበር ሙቅ ምድር አካባቢ፣ በደሴ ወ/ሮ ስህን እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ የአልያንስ ፍራንሴዝ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመው ነበር።
ዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን የተጀመረው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነበር:: የትምህርት ቤቱም ስም ዳግማዊ ምኒልክ ይሰኛል:: ዳግማዊ ምኒልክም ሰኔ 26 ቀን 1898 በጻፉት ደብዳቤ ልዩ ችሎታ ያላቸው ግብጻውያን መምህራን እንዲልኩላቸው ጠይቀው ነበር::
በጠየቁት መሠረትም በሙሴ ሀና ሳሌብ የሚመራ 3 ግብጻውያን በጥር 1899 መጥተው ትምህርት በ1900 ተጀመረ:: በጊዜው ይሰጥ የነበረው ትምህርት በይበልጥ ቋንቋ ነበር:: ከሀገር ውስጥ ቋንቋ ከአማርኛ እና ከግዕዝ ሌላ እንግሊዝኛ፤ ፈረንሳይኛ፤ ጣሊያንኛ ስዕል እንዲሁም የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ይሰጥ ነበር::
ዳግማዊ ምኒልክ አሁን ያለበት ሕንፃ ከመሠራቱ በፊት ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው እሪ በከንቱ አካባቢ በሚገኘው በሙሴ ኢልግ ቤት ነበር:: ዳግማዊ ምኒልክ በሌሎች ከተሞችም ተማሪ ቤቶች እንዲከፈቱ በማድረጋቸው በድሬዳዋ ፤ በደሴ እና በሀረር ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ችለዋል::
በጠቅላላ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሀገራችን እስከተ ጀመረበት ጊዜ ድረስ 30 የሚጠጉ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ነበሩ:: በዛን ወቅት የነበሩ አጠቃላይ የተማሪዎች ብዛትም ወደ 5000 ይጠጋ ነበር::
የእነዚህ ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ ብቁ ሆኖ መገኘት ኮሌጅን በሀገራችን ለመጀመር እንደ ዋና ምክንያት የሚቆጠር ነበር:: ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር ቤት በወጣ ልክ በ9 ዓመቱ ሀገራችን የመጀመሪያውን ዩኒቨርሲቲ ለመመሥረት የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠች::
‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› በሚል ስያሜ ጥቅምት 23 ቀን 1942 ዓ.ም ይህ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ በኋላ ሀገራችን ወደ አንድ እድገት የምትገሰግስበት ጎዳና ተጠረገ:: በታኅሣሥ 1 ቀን 1943 ዓ.ም የዛሬ 74 ዓመት በይፋ ሥራውን የጀመረው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲጀመር 9 መምህራን ነበሩት:: ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡት ተማሪዎች ቁጥርም 72 ይጠጋ ነበር::
ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥም 13ቱ በነሐሴ 1946 በዲግሪ ለመመረቅ ችለዋል:: ከ13ቱ የመጀመሪያ ምሩቃን መካከል የሕግ ምሁሩ አቶ ተሾመ ገብረማሪያም ይነሳሉ:: ከ8 ዓመት ቀደም ብሎ ሕይወታቸው ያለፈውና ከዚህ በፊት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ታሪካቸውን ያስነበብናችሁ አቶ ተሾመ ገብረማርያም የዩኒቨርሲቲ ትዝታቸውን ሲያወጉ ብዙ ቁም ነገር የቀሰሙበት ማዕከል እንደሆነ ያስረዳሉ::
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ባለፉት 74 ዓመታት፤ ከ12 በላይ ሰዎች በፕሬዚዳንትነት መርተውታል:: በ1943 ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዚዳንት የመሩት ዶክተር ሉሲዮ ማት ናቸው:: ከእርሳቸው በመቀጠል ከ1954- 1961 ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ልጅ ካሳ ወልደማሪያም ናቸው::
ልጅ ካሳ ወልደማሪያምን ዩኒቨርሲቲን በመምራት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ያደርጋቸዋል:: በ1946 ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ 13 ተማሪዎች ሲመረቁ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴም አንዱ ነበሩ:: በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካን ሀገር የሚኖሩት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ከ1961-1966 ድረስ 3ኛው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል:: እርሳቸውም ከ13ቱ ምሩቃን አንዱ ነበሩ::
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት ለረጅም ዓመታት በማገልገል ስማቸው የሚጠራው ዶክተር ዱሪ መሐመድ ናቸው:: እርሳቸውም ከ1969-1977 እንዲሁም ደግሞ በድጋሚ ከ1985-1988 ድረስ ዩኒቨርሲቲውን በመሪነት አገልግለዋል::
ዶክተር ዱሪ ሕይወታቸው ካለፈ 12 ዓመት ተቆጥሯል:: ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› በዚህ ስሙ እየተጠራ ለ11 ዓመት ከዘለቀ በኋላ፣ በ1954 ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ›› ተባለ::
ይህን ስያሜ ካገኘ በኋላ፣ ከዩኒቨርሲቲው የተመረቁት ወይዘሮ ሂሩት በፍቃዱ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የሕይወት መሠረት አስቀምጦላቸው እንዳለፈ ይናገራሉ:: በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የተመረቁት ወይዘሮ ሂሩት በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በሌሎችም ታዋቂ መሥሪያ ቤቶች ሠርተዋል::
በ1954 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ 2ሺ047 ተማሪዎችን ሲመዘግብ ከእነዚህ ውስጥ በ6ኪሎ 536ቱ፣ በእርሻ ኮሌጅ 224፣ በመሀንዲስ ኮሌጅ 167 ፣ በሕንፃ ኮሌጅ 108 ፣ በጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 261፣ በመንፈሳዊ ኮሌጅ ደግሞ 11 ተማሪዎች ተመዝግበው ነበር::
በዛን ጊዜ አንድ ተማሪ በዩኒቨርሲቲ ለመመዝገብ ከ50-59 ውጤት ማግኘት አለበት:: አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም የጽሑፍና የቃል የመግቢያ ፈተና ይሰጥ ነበር:: የያኔው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረት፣ ከ216 በላይ እንግዶች በልደት አዳራሽ ታድመው ነበር::
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥታቸውን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ያበረከቱበት ታኅሣሥ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ነው። ከቤተ መጻሕፍት የተገኘው የጥሪ ካርድ ጃንሆይ የግል ርስታቸው የሆነውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን ዩኒቨርሲቲ ሲያደርጉት ትልቅ በዓል መደረጉን ይናገራል::
የጥሪ ካርዱ እንዲህ ይላል፦‹‹……. ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስመ ጥር አባታቸው ከልዑል ራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን የግል ርስታቸውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥታቸውን ለዩኒቨርሲቲ በሰጡበት ቀን ሰኞ ታኅሣሥ 9 ቀን 1954 ከጠዋቱ 4ሰዓት ከ45 በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት እንዲገኙ መጠራትዎንና ከበዓሉም በኋላ በልደት አዳራሽ ምሳ መጋበዝዎን እናሳውቃለን›› ይላል።
በታይፕራይተር በተፃፈውና ከንጉሠ ነገሥቱ የልፍኝ አስከልካይ መዝገብ ቤት የተገኘ ባለ 3 ገጽ ሰነድ ላይ እነማን በዩኒቨርሲቲው ምሥረታ በዓል ላይ እንደታደሙ ይነግረናል:: በዚህ ሰነድ ላይ ማን ከማን ጎን ተቀምጦ ምሳ ይመገብ እንደነበር ሰነዱ ላይ ሰፍሯል::
በዚህ ግብዣ ላይ ከታደሙ ዋና ዋናዎቹ እንግዶች መሀልም ልዑል አልጋ ወራሽ፣ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፤ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፤ ክቡር ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ሌሎችም ተገኝተው ነበር።
በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውን መምህራን ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምና አቶ መሐመድ ዩሱፍ ናቸው:: የዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው ሬጅስትራር ዶክተር ማርጋሬት ጂሌት ይባላሉ:: የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ዓይነቶች የሚገልጸውን ካታሎግ በመጋቢት ወር 1954 ታትሞ እንዲወጣ ትልቅ ሚና ያበረከቱ ሰው ናቸው::
በሀገራችን የሕክምና ትምህርት በ1950ዎቹ ሲጀመር የዛን ጊዜው የልዑል መኮንን ሆስፒታል የአሁኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የግንባታ ሥራ ተጀምሮ ነበርና ለጤናው ዘርፍ አንድ መፍትሔ ተገኝቶ ነበር፤ የሆስፒታሉን የግንባታ ሥራ ያከናወነው የዩጎዝላቪያ ኩባንያ ዩኒየን ኢንጂነሪንግ የግንባታ ሥራውን በ40 ወራት ውስጥ ያጠናቀቀ ሲሆን ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት 15 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።
ከታካሚዎች ባሻገር የሕክምና ተማሪዎች እውቀት ሲቀስሙበት የነበረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሀገሪቱ የዩኒቨርሲቲ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ለማበርከት የቻለ ስለመሆኑ በብዙዎች ይመሰከርለታል:: በአሁኑ ሰዓት በሕይወት የሌሉትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋክልቲ ቀደምት መምህር በመሆን ያገለገሉት፤ ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር በርካታ ሐኪሞችን በማፍራት ታላቅ ውለታ የዋሉ ምሁር ናቸው::
በውስጥ ደዌ ሐኪምነታቸው ስመ ጥር የነበሩት ፕሮፌሰር ጀማል በተለይ ከማስተማር ሥራቸው ሌላ የዩኒቨርሲቲው የሜዲካል ጆርናል የበላይ ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል:: ከአዲስ አበባ ባሻገር በሀገራችን የዩኒቨርሲቲ መከፈት ታምኖበት በሰሜኑና በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ዩኒቨርሲቲዎች ተመሥርተዋል:: ‹‹ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ›› በዚህ መልክ ከተመሠረቱት መካከል አንዱ ነበር::
ታኅሣሥ 21 ቀን 1954 የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠለት፣ ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ባለፉት 63 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በርካታ የእድገት ደረጃዎችን አልፏል:: መስከረም 19 ቀን 1956 ላይ 250 ተማሪዎችን በመቀበል የማስተማሩን ሥራ አሀዱ ያለው ‹‹ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ››፣ ዛሬ በስኳር፣ በጨርቃ ጨርቅ ፣ በኬሚካልና በሌሎችም የኢንዱስትሪ ዘርፎች ባለሙያዎች በማፍራት ላይ ይገኛል::
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ መመሥረት ጉልህ ሚና ነበረው፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም ካፒታል በጀቱ 50ሺህ ብር ነበር:: በ1961 ዩኒቨርሲቲው 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ባከበረ ጊዜ 133 ወጣቶች ዲግሪና ዲፕሎማቸውን ተቀብለዋል::
ሐምሌ 12 ቀን 1946 የተመሠረተው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ በ65 ዓመታት ውስጥ ከ30ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችን አስመርቋል:: ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚሆኑት በዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በምርምርና በማስተማር ሥራ ላይ እያገለገሉ ይገኛሉ:: ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች መካከል፣ ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም ይጠቀሳሉ::
የመጀመሪያው የሀገራችን የቴክኖሎጂ ፋክሊቲ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ኢንጂነሪንግ በሚል ስያሜ በ1945 በሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው አንድ ጥንታዊ ሕንፃ ውስጥ ነበር የተመሠረተው:: በዚህ ተቋም ውስጥ የነበረው፤ በውጭ ሀገር የምህንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሚችሉ ተማሪዎች የሚረዳ የ2 ዓመት የመሰናዶ ትምህርት ነበር::
ይህ ተቋም እኤአ ከ1969 ጀምሮ ወደ 5ኪሎ ካምፓስ በመሸጋገር አሁን ባለበት ሁኔታ በ3 የምህንድስና ዘርፍ ማለትም በሲቪል፣ በኤሌክትሪክ እና በሜካኒካል ትምህርቱ በሀገር ውስጥ በሰፊው መሰጠት ተጀምሮ እስከ ዛሬ ዘልቋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የነፃ ትምህርት እድል ተጠቃሚዎች በ1951 ነበር ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት፤ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከልም ኬንያዊው ኦሞጊ ካሌብ በ1952 የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች ምክር ቤት ፀሐፊ በመሆን አገልግሏል።
በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ለአፍሪካ ወንድሞቻቸው ያላቸውን በጎ እሳቤ አሳይተዋል፤ ከአፍሪካ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች በቅኝ ግዛት ባልተገዛች ሀገር በኢትዮጵያ የተመሠረተው ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› ከሁሉም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በእድሜ አንጋፋው ነው::
ተቋሙ ለ75 ዓመታት ብዙዎችን እውቀት በማስታጠቅ ዘልቋል:: ባለፉት ዓመታት ከ2 መቶ 20ሺህ በላይ ተማሪዎች ከዚህ አንጋፋ ተቋም ተመርቀዋል::
ይህ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ከ2016 ጀምሮ ደግሞ ራስ ገዝ በመሆን በአዲስ ጎዳና መራመድ ጀምሯል:: መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነፃነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን የሚያካሂዱ እንዲሆኑ ለማስቻል የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አዋጅ በማውጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝን ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን አድርጓል::
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች እንዲሁም ስመ ጥር ታሪክ ያላቸውን የሀገራችንን ተቋማት ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ የአንጋፋውን የትምህርት ተቋም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ በማውሳት ለተቋሙ መመሥረት አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሁሉ አመሰገንን ሰላም!
ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እና የትምህርት ሚኒስቴርን ድረ ገጾች ተጠቅመናል!
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም