የወጣቶቹን ሁኔታ ከሩቅ ለተመለከተው እጆቻቸው፣ ዓይኖቻቸውን መላ ትኩረታቸውን ጠምዶ የያዘውን ጉዳይ ለማወቅ ያጓጓል። እግሮቼን ወጣቶቹ ተደርድረው ወደተቀመጡበት አቅጣጫ መሰንዘር ጀመርኩ። በእጆቻቸው የያዟቸውን ትኬቶች በዓይኖቻቸው እየቃረሙ በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ የተለያዩ መረጃዎችን ሲሞሉ ይታያል። ቀረብ ብዬ ስለሁኔታው ለመጠየቅ ሞከርኩ። ድርጊቱ የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) እንደሚባል አንገታቸውን እንዳቀረቀሩ ምላሻቸውን ሰጡኝ።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት በአገሪቱ እየተስተዋለ የሚገኘው ይህ ድርጊት ልጆችን ትምህርታቸውን አስቶ፣ የመንግሥት ሠራተኛውም የተጣለበትን ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት ወደጎን አስትቶ የሁሉም መገኛ በአቋማሪ ድርጅቶቹ ደጃፍ ከሆነ ዋል አደ ብሏል። እኛም ዘገባውን ለመሥራት ባንኳኳናቸው የመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ወላጆች ‹‹እባካችሁ ልጆቻችንን ታደጉልን›› የሚል መማፀን ደርሶናል። ከዚህም አልፎ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁትም ሆኑ በሥራ ላይ የሚገኙት ራሳቸውን ለውጠው ያመርታሉ ብላ አደራዋን ያስጨበጠቻቸው፣ስራ ፈጣሪ ዜጋ ሆነው እንደሚለውጧት ተስፋ የጣለችባቸው አገርም እንዲህ በመጤ ድርጊት አዕምሯቸው ሲያዝ ፍረዱኝ ትላለች።
ከወጣቶቹ አንደበት
‹‹በግምትዎ ብቻ በአጭር ጊዜ በቀላሉ ሕይወትዎን የሚቀይሩበት ታላቁ ዘዴ›› በሚል ማስታወቂያ ተስቦ ወደ ቁማሩ እንደገባ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አርባ ምንጭ ከተማ መናኸሪያ ሼል አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት አለምሰገድ ይፍሩ ያስታውሳል። በውርርዱ እስከ 350 ሺህ ብር ማግኘት እንደሚቻል አቋማሪ ድርጅቶቹ በየሰፈሩ በተሽከርካሪ እየተዟዟሩ ሲያደርጉ የነበሩትን ቅስቀሳ በማድመጥ በ2011 ዓ.ም ማብቂያ ላይ ውርርድ ማድረግ ይጀምራል። ምንም እንኳ ቁማሩን ከጀመረ ዓመት ያልሞላ ጊዜ ቢያስቆጥርም ለዓመታት በረሀ ለበረሀ ዞሮ ላቡን አፍስሶ ያጠራቀመውን አንጡራ ሀብቱን ሲያጣ ግን የወራት ጊዜ አልፈጀበትም ።
ሁኔታው ያላማራትና ቀድሞ ኑሯቸውን ለመለወጥ ደፋ ቀና ይል የነበረ ውሃ አጣጯ ጉዳይ አልዋጥልሽ ያላት የትዳር አጋሩም ሁለተኛ ልጃቸውን በሆዷ እንደያዘች ጥላው እንደሄደች ነው የሚናገረው። ‹‹ይህን ባውቅ ባልጀመርኩት ነበር›› በማለት ቁማር ያደረሰበትን ችግር በመግለጽ የሚፀፀተው ወጣት አለምሰገድ፤ በአሁኑ ወቅት የሞቀ ቤቱ ተበትኖ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ በሐዘን ይናገራል።
መንግሥትና የሚመለከተው አካል ወጣቱን ለማዳን መረባረብ ይገባቸዋል የሚለው ወጣቱ፤ በሚኖርበት ከተማ እንደ እርሱ ሁሉ በቁማሩ እየተሳቡ የሚገቡት ዜጎች ቀጣይ ሕይወት እንደሚያሳስበው ይገልፃል። በተለይም በድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው የሚታዩት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁ ታዳጊ ሕፃናት መሆናቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል ይላል። ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ሺህ ብር አግኝቶ በመሳቡ በአንድ ጊዜ ብዙ ደረሠኞችን በመቁረጥ ዕድሉን መሞከር የዕለት ተዕለት ተግባሩ አድርጎት የነበረው ወጣት አለምሰገድ፤ ‹‹ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ›› እንደሚባለው ታዳጊዎቹም ስለ ትምህርታቸው ከማሰብ ይልቅ ስለነገ የቁማር ደረሠኝ መቁረጫ ገንዘብ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።
የራሳቸው መተዳደሪያና የገቢ ምንጭ የሌላቸው ልጆች ደረሠኝ መቁረጫ ለማግኘት ይታትራሉ። ከቻሉ ከወላጆቻቸው ኪስ፤ ካልቻሉም ወጣ ብለው ይሠርቃሉ። ይህም ድርጊቱ በዕድሜ በስለዋል፣ የራሳቸውን ኑሮ መሥርተዋል ከሚባሉት ውጪ የሕፃናቱንም አዕምሮ ምን ያህል እየተቆጣጠረው እንደሆነ ያመላክታል። እያደረሰ ያለውን ጉዳት ሲመለከትም ‹‹መንግሥት ያውቀው ይሆን፣ ሕግ ያለበትስ አገር ነውን›› የሚል ጥያቄን እንደሚያጭርበት ወጣት አለምሰገድ ይናገራል። ቁማር ቤቱን በዕድሜ ያልበሰሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም መዋያቸው ማድረጋቸውን ተገንዝቦ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሊታደጋቸው ይገባል ባይ ነው።
ሌላኛው በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የሠጠን በጎንደር የአማራ ወጣቶች ማህበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቢኒያም ፀጋዬ፤ ውርርድ በሚል ሥም ቁማር ቤቶቹ ወደ ከተማው ከገቡ በኋላ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ከመሄዳቸው አስቀድመው የሚገኙት ትኬት መቁረጫ ስፍራ ላይ ነው ። በዚህም ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ከመከታተል ይልቅ ቀኑን ሙሉ ጊዜያቸውን ቁማር ላይ እንደሚያጠፉ ነው የሚናገረው። የባጃጅ ሹፌሮችም ሥራቸውን አቁመው በተግባሩ ተጠምደው ይታያሉ የሚለው ቢኒያም፤ የከተማው ባለሀብቶችና የመንግሥት ሠራተኞች ሳይቀሩ በዚህ የቁማር ጨዋታ ላይ ትኩረታቸውን እንዳደረጉ ይናገራል።
ድርጊቱ ከግለሰብ አልፎ በአገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ባይ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የአራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪው ዘላለም አባተ ምንም እንኳ ውርርዱን ተጫውቶ ባያውቅም በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ወጣቶች ሲጠቀሙና የተወራረዱባቸውን ደረሠኞች ይዘው እንደሚመለከት፤ በተለይም ማምሻውን የአውሮፓ የእግር ኳስ ቡድኖች ግጥሚያ ካለ ወጣቶቹ ቀኑን ሙሉ ሲወራረዱ መዋላቸው ትውልዱ ለሱሱ ሰለባ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው። ድርጊቱ ውርርድ ተባለ እንጂ ቁማር ነው በእጅጉ እየተባባሰም መምጣቱን ይናገራል።
ውርርዱ በአገሪቱ ካለው ባህልም ሆነ እሴት አንፃር ሲታይ ቁማር ነው የሚለው ወጣት ዘላለም፤ ቤተሰብ እርስ በእርስ ያለውን ግንኙነት የሚያጠፋ ልጆችን ከወላጅ የሚለይ ሲብስም ቤተሰብን እስከማፍረስ የሚደርስ አቅም አለው። ውርርድ ተብሎ በፊት ከተለመዱት ዓይነት ቁማሮች በቴክኖሎጂ ተደግፎ መምጣቱ ብቻ ለየት የሚያርገው የስፖርት ውርርድ ወይንም ቤቲንግ ተጠቃሚዎቹ የወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የጉዳት መጠኑን እንደሚጨምረው ያስረዳል።
አገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለው የኢኮኖሚ፣ የሥራ አጥነት፣ የድህነትና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ባለችበትና ዜጎቿ ከዚህ ውስጥ እንዲያወጧት ስትጠባበቅ በዚህ መልኩ ጤናማ የሆነ አስተሳሰብ እንዳያስቡ በሚያደርግ ተግባር መጠመዳቸው አስጊና አሳሳቢ ይሆናል። ወጣቶችም በቀጣይ ሕይወታቸው ሠርተው ለመለወጥ የሚያደርጉትን ሩጫ የሚገታ ነው በማለት ሁኔታውን ይተቸዋል።
ድርጊቱ ‹‹ሥራ ሠርቼ እለወጣለሁ›› ሳይሆን በቁማር እንደሚያልፍለት የሚያስብ ትውልድን እየፈጠረ ነው። ጤናማ ያልሆነ የዕድገት ሁኔታን ለወጣቶች የሚያስተምርና የአገሪቱን እሴትና ባህሎችንም የሚሸረሽር ነው። በተለይ በአገሪቱ ከሚስተዋለው ችግር ዋነኛው የአስተሳሰብ ድህነት በመሆኑ ወጣቱ ንቃተ ሕሊናው መልማት እንዳለበት ዕሙን ነው። በመሆኑም መማር፣ መሰልጠንና ለውጤታማነት መትጋት ይገባዋል። ካልሆነ ግን ይህን መሰሉ ድርጊት ትውልድና አገርን ገዳይ ይሆናል።
የሥራ ባልደረባው ከ16 ዓመት ባልዘለለው ልጁ ምን ያህል እንደተቸገረ ሲናገር መስማቱን የሚያስታውሰው ወጣት ዘላለም፤ በዚህም ቀድሞ በሥነሥርዓት የሚታወቅ የነበረው ልጅ የወላጆቹን ኪስ ወደ መዳበስና ወደ ስርቆት እንደገባ ብሎም ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነበትና በሰፈር ከሚገኙ መሰል የዕድሜ እኩዮቹ ጋር በቁማሩ ተስበው ለቤተሰብ ሁሉ እንዳስቸገሩ በቅርብ ያደመጠውን ገጠመኝ በማንሳት ስለሁኔታው አስከፊነት ይናገራል።
በመሆኑም ወላጆች ብሎም መንግሥት ወጣቱን ቁማር አጥፊ እንደሆነና በዚህ መልኩ ሊያልፍለት እንደማይችል የሥራ ባህልንም እንደሚገድል ማስተማርና ማነጽ ይገባቸዋል። በአገሪቱ የመንግሥት አቅምና የወጣቶች ንቃተ ሕሊና ደረጃ ባልዳበረበት ሁኔታ የሚታሰብ አይደለም በማለትም ጉዳዩን የፈቀደ አካል ቆም ብሎ ማጤን እንደሚጠበቅበት ይጠቁማል።
ፈቃድ ሰጪው አካል
የስፖርት ውርርድ ቁማር ባለመሆኑ ፈቃድ እንደተሰጠው የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ገዛኸኝ ይልማ ይናገራሉ። ተቋሙ ለአራት ዓይነት የሎተሪ ዓይነቶች ፈቃድ እንደሚሰጥ በመግለጽ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ነው። ይህ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ 135/1999 በመመሪያ 83/2005 መሠረት የሚሰጥ የፈቃድ አሰጣጥ እንደሆነም ያስረዳሉ። በመመሪያውም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ውርርዱን ማድረግ እንደማይችሉ ስለፀደቀ ቤቶቹ ይህንን መሠረት አድርገው ይሠራሉ።
መመሪያው የወጣው 2005 ዓ.ም ሲሆን፣ ፈቃድ አሰጣጡም ቆይቷል። ነገር ግን ድርጅቶቹ ሥራ በትክክል የጀመሩት ከ2008 ዓ.ም በኋላ ነው። ‹‹ፈቃድ መስጠት እንደተጀመረ ሥራው ያልገባቸው አካላት የወሰዱትን ፈቃድ ሲመልሱ ነበር።›› በቆይታ ግን እየተስፋፉ ገበያው እየሰፋ ሕብረተሰቡም እየተሳተፈበት በመሆኑ ለ36 ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል። ከእነዚህ መካከል 22 የሚሆኑት በተግባር ሥራቸውን እየሠሩ ነው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች በማሟላት ላይ ይገኛሉ።
መንግሥት ከድርጅቶቹ በአማካይ በየወሩ እስከ
ስድስት ሚሊየን ብር ገቢ እንደሚያገኝ የሚናገሩት አቶ ገዛኸኝ፤ ካገኙት ትርፍ ላይ 20 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ሥራውን ሲጀምሩ ለተዋዋሉት በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ እንደሚያደርጉ ይገልፃሉ።
ፈቃዱ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ሕገወጥ ውርርዶች ነበሩ የሚሉት ቡድን መሪው፤ ይህም ገንዘቡን ለአንድ ግለሰብ እንዲገባ ከማድረጉ ባሻገር ሠዎች እንዲጋጩና ለማህበራዊ ቀውስም ይዳርግ እንደነበር ያስታውሳሉ። ፈቃዱ መሰጠቱም ችግሮቹን አስቀርቷል ሲሉም ያረጋግጣሉ። በሌላ በኩል በዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑት ባለዕድለኞች ወደኪሳቸው ከሚያስገቡት ገቢ በተጨማሪ ከአንድ ሺህ ብር በላይ አሸናፊ ሲሆኑ፤ ለመንግሥት 15 በመቶ ገቢ ያስገባሉ። ይህንን መሰል ከዕድል ሙከራ የሚገኙ ገቢዎችን አስተዳደሩ እንዲሰበሰብ ለገቢዎች ሚኒስቴር በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት ባለው መረጃ ከአጠቃላይ በድርጅቶቹ ለአንድ ሺህ 200 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረና ‹‹ፈቃድ ሰጥተን ሕብረተሰቡም እየተጠቀመ ነው።›› ሲሉ ከጉዳቱ ጠቀሜታው እንደሚያመዝን በመግለጽ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚያነሱትን ሐሳብ ውድቅ ያደርጉታል።
እርሳቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቋማቱን አቋማሪ ድርጅቶች አድርጎ የማሰብ ዝንባሌዎች ይስተዋላሉ። ካርታ እንኳን ቁማር ቢባልም ቁማር ተደርጎ የማይወሰድበት አገር አለ። በዚህ ውርርድ ግን ሰዎች ግምታቸውን በማስቀመጥ ለአጫዋቹ ብር ከፍለው ደረሠኝ ይቀበላሉ። በአስተዳደሩ ፈቃድ ተሰጥቶት ለሚሠራው ለዚህ ውርርድ ሠዎች ‹‹ያሸንፋል›› ብለው ለሚገምቱት የእግር ኳስ ቡድን ግምት መስጠት መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹አንድ አዲስ ሥራ ሲጀመር በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ አነስተኛ ከሆነ ማስረዳት ይገባል›› የሚሉት አቶ ገዛኸኝ፤ መንግሥት እንዴት ለቁማር ፈቃድ ይሰጣል ይላሉ። ሆኖም የስፖርት ውርርድ ይቅር ቢባል እንኳን ድርጊቱ በሕገወጥ መልኩ መደረጉ አይቀርም፤በመሆኑም አስተዳደሩ ፈቃድ መስጠቱ ለተግባሩ ሕግና ሥርዓት እንዳበጀለት ነው መወሰድ ያለበት እዚህ ላይ የቁጥጥር ስራው ክፍተት እንዳለው እንደሚያምኑ አብራርተዋል።
በቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚነሳው “ወጣቱ ተጎድቷል፣ ሱሰኛ ሆኗል፣ ጊዜውን የሚያሳልፈው ውርርድ በማድረግ ነው›› የሚለው አስተሳሰብም ከግምት ያልዘለለና በጥናት ያልተደገፈ በመሆኑ ምላሽ ለመስጠት አዳጋች ይሆናል ይላሉ።
ወጣቶች ውርርድ ለማድረግ ብዙ ጊዜ እንደማያሳልፉ በመግለጽ፤ አገሪቱ ከወጣቶች የምትጠብቀውን አምራችና ፈጣሪ ዜጋ የመሆን ተስፋ ይገድላል በማለት የሚነሳው ቅሬታ ተገቢነት የጎደለው የስፖርት ውርርድ የሚደረግባቸው ቤቶች ቢዘጉ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ይፈጠራል ብሎ ማሰብም የተሳሳተ አመለካከት ነው ሲሉም ቅሬታቸውን ይተቻሉ። በውርርዱ ላይ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች እንደሚጠቀሙና ብዙ ጊዜም እንደማይወስድባቸው በመጠቆም፤ ‹‹ወጣቱ ኃይል ውርርድ ማድረጉ ከአምራችነቱ ጋር አይገናኝም በተቃራኒው ብዙ በፈጠራ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በሥፍራው ሊገኙ ይችላሉ›› ሲሉም ስለሁኔታው ያስረዳሉ።
በስፖርት ውርርድ ላይ የተሳሳተ አመለካከት አለ። ነገር ግን ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት የተቋቋመው በዋናነት ሕብረተሰቡን ከሕገወጥ የዕድል ጨዋታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ነው። ውርርዱ የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ ዜጎች የሚወዱትን የእግር ኳስ ቡድን እየደገፉ መሆናቸውን፣ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢ እያገኘ ስለመሆኑ ፣ በግለሰቦች መካከል የነበረውን የእርስ በእርስ ግጭት አስቀርቶ ወደተሻለ መግባባት መቀየሩን፣ ድርጅቶቹ ከሚያገኙት ትርፍ በማህበራዊ ተሳትፎ ዘርፍ ለበጎ አድራጎት ማስገባታቸውን መመልከት ይገባል። በቁጥጥር ሥራው ግን ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዳይገቡና ወጣቱ በሱስ እንዳይያዝ ማድረግ ይገባል በማለት ያብራራሉ።
በሌላ በኩል አስተዳደሩ ፈቃድ የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው በመሆኑ ከተለያዩ አገራት የተባረሩ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከዕውነት የራቀ መሆኑን አስተባብለዋል።
ሕጉ ምን ይላል?
የሕግ ባለሙያና በማንኛውም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ አቶ ፍጹም አስራት፤ በተለምዶ ውርርድ በሚል ሽፋን ስሙን ለውጦ የመጣው ‹‹ቁማር›› ነው ይላሉ። ቁማር ማለት በአነስተኛ የገንዘብ ወጪ አንድን ያልተገባ ነገር ለማግኘት ማሰብ ነው የሚሉት ጠበቃው፤ ውርርዱ የስፖርት ጨዋታዎችን በመገመት ግምቱ ትክክለኛ ከሆነ የሚገኝ ገንዘብ ነው። ያልተገባ ክፍያ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ውርርድ ወይንም ቁማር መሆኑንም ያስረዳሉ።
በኢፌዴሪ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 789 ሎተሪዎችንና ውርርዶችን የሚመለከቱ ሕጎችን መጣስ አስመልክቶ “ውርርድ ፈቃድ ኖራቸውም አልኖራቸውም ማድረግ የተከለከለ እንደሆነ ያስቀምጣል”። ለመሰብሰቢያ በተዘጋጀ ስፍራ የቁማር ጨዋታ ወይንም ውርርዶችን ወይንም በመንግሥት ክልከላ የተደረገባቸው ሌሎች የዕድል ጨዋታዎችን ከልክሏል። በዚህም ቤቲንግ ወይንም የስፖርት ውርርድ ማድረግ እንደማይቻል ሕጉ አስቀምጧል።
በሕግ አተረጓጎምም አዋጅ ደንብ ቀጥሎም መመሪያ ነው የሚሉት አቶ ፍጹም፤ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አዋጅ በመሆኑ ማንኛውም ይህንን የሚጣረስ መመሪያ ተገቢነትም ሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ያስረዳሉ። ስለሆነም ፈቃድ ሰጪው አካል በምን አግባብ እንደሰጠ መመርመር ይገባዋል ሲሉ ይመክራሉ።
ሚኒስቴሩ
በሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ አለሙ ሠዒድ ድርጊቱን ቁማር ነው ሲሉ ይኮንኑታል። ችግሩ በቅርብ የመጣና በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ የሚገኝ አሉታዊ መጤ ድርጊት ነው። በርካታ ጠቀሜታ የሌላቸው ጎጂ እንዲሁም የነበሩ እሴቶች፣ ባህሎች፣ የወጣቶችን ባህሪ የሚሸረሽሩ፣ ጤናማ ሕይወታቸውን ብሎም የማህበረሰቡን ኢኮኖሚ የሚጎዳ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ዳይሬክተሩ ድርጊቱ በተለያዩ አገራት የተለመደ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ላለ ታዳጊ አገር ግን በወጣቶች ላይም ሆነ በአገር ደረጃ ጠቀሜታ የሌለው ተግባር ሲሉ ያወግዙታል። የሥራ ጊዜያቸውን የሚሻማና በቂ የሆነ ብሎም የራሳቸው ገቢ የሌላቸውን ወጣቶች የሚያሳትፍ ነው። ‹‹በትንሽ ብር ከፍለው በመቶ ሺዎች ማግኘት ይችላሉ›› የሚል አሳሳች ማስታወቂያ ከአቋማሪዎቹ ይገለፃል። ወጣቶቹ ደግሞ የራሳቸው ገቢ ሳይኖራቸው በዚህ ተግባር ላይ ሲሰማሩ ለስርቆትና ተያያዥ ወንጀሎች ለመሠማራት ዝንባሌ ይኖራቸዋል። ከቤተሰብ አልያም በሌላም መልኩ ሰርቆ የማምጣት ዝንባሌን ያሰርፃል ባይ ናቸው።
ቁማር ሕጋዊ አይደለም የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን መሠል ድርጊት ጠቃሚ ሆኖ አያውቅም። ስለዚህ ውጤቱ ከኢኮኖሚም ባሻገር የወጣቶችን ጊዜ የሚሻማና በቤተሠብ ደረጃ ሠላም እንዳይኖር በማድረግ ግጭትን የሚያሰፈን በመሆኑ እንደ አንድ አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል ከሚከናወኑ ተግባሮች አንዱ ተደርጎ ተወስዶ በቀጣይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ እየታሰበ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ድርጊቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተስፋፋ በመሆኑ በተግባር ደረጃ የተወሰደ የእርምት እርምጃ እንደሌለ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የቁማሩ ዓይነት የስፖርት ውርርድ መባሉ ብቻ ሳይሆን ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ችግር እንዳለ ይገልፃሉ። ለአደንዛዥ ዕፅ ንግድም ፈቃድ ይሰጣል። ይህም ትልቁ ክፍተት ያለው ፈቃድ ሰጪ አካል ዘንድ ነው ። ፈቃድ ሲሰጥ ለአገሪቱ ያለው መልካም ገፀበረከትና ጉዳት በሚገባ ለይተው መመርመር ላይ በርካታ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ከዚህ አንፃር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከንግድ እንዲሁም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች 26 አጋር አካላትን በማስተባበር ችግሮቹን ለመከላከል እየሠራ ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችንና አደንዛዥ ዕፆችን የመከላከል ግብረ ኃይሉ በፌዴራል ደረጃ 26 የመንግሥት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፤ ሥራ መሠራት ከተጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። ሰብሳቢውም ሚኒስቴሩ ነው። ግብረ ኃይሉ ይህን መሰል የወጣቶችን ሕይወት ጤና ሥነምግባር ስብዕናቸውን ሊጎዱ የሚችል ተግባር በመከላከል ላይ እየሠራ ነው። በዚህም የመጡ ለውጦች አሉ።
ቁማሩ በቀላል ገንዘብ ተሳታፊ የሚያደርግ በመሆኑ በቀላሉ ሱስ ይሆንና ለመውጣት አዳጋች ይሆናል። የፀጥታ ችግር ከግለሰብ ጀምሮ ወደ ቤተሰብ ከተዛመተ የአገር ሆኖ መታየቱ አይቀርም። ይህም ችግር ተደማምሮ ለማህበረሰቡ ብሎም ለአገር ፀጥታ አስጊ ሁኔታ ሊፈጥር መቻሉ አያጠራጥርም። በመሆኑም ጉዳዩ ለግብረ ኃይሉ ቀርቦ መፍትሔ የሚሰጥበት ሲሆን፤ ግብረ ኃይሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔውን እንደሚያደርግና በመጪው ጥር ወር በሚካሄደው መድረክ የቴክኒክ ኮሚቴው ጉዳዩን አውቆት ሰፊ ውይይት በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ያመላክታሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
ፍዮሪ ተወልደ