አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን ባገለገለችበት ወቅት የወሰደቻቸውና ያንጸባረቀቻቸው አቋሞች ዲፕሎማሲያዊ ከበሬታ እንዳስገኙላት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ታዬ እጽቀስላሴ ገለፁ፡፡
አምባሳደር ታዬ እጽቀስላሴ ትናንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በሰጡት በመግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እ.አ.አ. ከ 2017 እስከ 2018 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን ባገለገለችበት ወቅት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች፡፡ በጸጥታው ምክር ቤት ቆይታዋ ከሰላም ማስከበር ጋር በተያያዘ ያከናወነቻቸው ተግባራት እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ የቻለች ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአብዬ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታው እንዲራዘምና ተልዕኮ ስኬታማ እንዲሆን ከሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር ውሳኔ እንዲተላለፍ አድርጋለች፡፡
በሶማሊያ ማዕከላዊው መንግሥት መጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ድጋፍ በማሰማት እንዲሁም አሚሶም የሚባለው የሰላም አስከባሪ ኃይል አስፈላጊውን ድጋፍ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከጸጥታው ምክር ቤት እንዲያገኝ በማድረግ ደረጃ ሰፊ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቡሩንዲ በተለይም ከአሩሻ ስምምነት ጋር ተያይዞ ሰላም እንዲኖር፣ እንዲሁም በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሰላም እንዲሰፍን ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን የውሳኔ ረቂቅ ሀሳብ በማቅረብ ደረጃ ተሳትፋለች፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሶሪያ ቀውስን፣ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችንና በሀገር ውስጥ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት የበኩሏን ተሳትፎ አድርጋለች፡፡ በተለይ የመን ውስጥ ያለውን ሰፊ የሰባዊ ቀውስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲታደግ በዋነኛነት አጀንዳውን በማራመድ ሰፊ አስተዋጽኦ ማድረግ ችላለች፡፡
እንደ አምባሳደር ታዬ ማብራሪያ፤ በጸጥታው ምክር ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው በሚገመቱ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰዎች ፍልሰትና መሰል ጉዳዮች ላይ የርዕሰ ጉዳይ ክርክር በሚደረግበት ጊዜ ኢትዮጵያ በጉዳዮቹ ላይ ሰፊ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ በተጨማሪም ከእስራኤል እና ፍልስጤም እንዲሁም ከሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ሙከራዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ወጥነት ያላቸው የጠነከሩ አቋሞችን በመውሰድ ድምፅዋን አሰምታለች፡፡
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ለጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ስትመረጥ ከ 190 ሀገራት የ185ቱን ይሁንታ አግኝታ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
በየትናየት ፈሩ