አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል መረጋጋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ለመሰብሰብ ከታቀደው ገቢ በላይ መሰብሰቡን እንዲሁም ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የታቀደውን ያህል ገቢ መሰብሰብ አለመቻሉን የክልሉ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በባለሥልጣኑ የግብር ከፋዮች ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ስመኝ ንጉሴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይ እንደገለጹት፤ ተጠሪነታቸው ለኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን የሆኑ 20 ዞኖች እና 19 ትላልቅ ከተሞች አሉ፡፡
ባለፉት አራት ወራት የነበረው የገቢ አሰባሰብ ከዞን ዞን፤ ከከተማ ከተማ የጎላ ልዩነት ታይቶበታል፡፡ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ተስፋ ሰጪ የገቢ አሰባሰብ ያለ ሲሆን፤ በተለይም አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ፣ ዱከም እና ሌሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ለአብነት ያህል በዱከም ከተማ ከታቀደው በላይ 163 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡
እንደ አቶ ስመኝ ማብራሪያ፤ ለተመዘገበው ጥሩ ውጤት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የደንበኞች አገልግሎትን ቀልጣፋ እንዲሆን መደረጉ፤ አመራሩና ሠራተኛው ከሌሎች ባለድርሻ ጋር በቅንጅት መሥራታቸው፤ በዞኖቹ ያሉ ችግሮችን ጥናት በማካሄድ ለመፍታት በመቻሉ ሲሆን፤ የግብር ሥርዓት ውስጥ ሳይገቡ የነበሩት ወደ ግብር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሆኖም መልካም ውጤት ተመዝግቧል በተባለባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ጭምር መሰብሰብ የነበረበት ሙሉ በሙሉ ተሰብስቧል ማለት አይቻልም፡፡ ለእዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አሁንም በትክክል ደረሰኝ የሚቆርጡ ነጋዴዎች ከ10 በመቶ አይበልጡም፡፡
በክልሉ በሚገኙ ስድስት ዞኖች በተለያዩ ጊዜያት ይከሰቱ በነበሩ ግጭቶችና የሰላም እጦት ምክንያት ግብር በአግባቡ መሰብሰብ አልተቻለም ያሉት አቶ ስመኝ፤ በአንዳንድ ዞኖች ለመሰብሰብ ከታቀደው ከግማሽ በታች መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ ለአብነት በቄሌም ወለጋ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ 43 በመቶ ብቻ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በምስራቅ ሐረርጌ፣ በባሌ፣ በጉጂ፣ በቄለም ወለጋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች የተሰበሰበው የገቢ መጠን ከእቅድ አንጻር ሲታይ እጅግ አነስተኛ ነው፤ በእነዚህ ዞኖች የነበረው አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ከ10 እስከ 13 በመቶ ቅናሽ መታየቱንም አመልክተዋል፡፡ በስድስቱ ዞኖች ያለው ዝቅተኛ የገቢ አሰባሰብ የሚቀጥል ከሆነ በዞኖች ለልማት የታቀደውን በጀት እንኳ ላይሸፍን ይችላል ብለዋል፡፡
አቶ ስመኝ እንደሚሉት፤ በስድስቱ ዞኖች በነበረው የጸጥታ እጦት ምክንያት ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱና ግብር ከፋይ ማህበረሰብ ግብር ለመሰብሰብና ለመክፈል የሚያስችል የሥነ ልቦና ዝግጁነት አልነበራቸውም፡፡ እንዲሁም ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ሎጅስቲኮች (መኪና እና ሞተር ሳይክሎች) ሰላም ወደ ማስከበር እንዲገቡ መደረጉ ለገቢ መቀነስ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመንግሥት ውጪ ሌሎች አካላት ግብር እየሰበሰቡ ነው ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚወራው ሐሰት ነው ያሉት አቶ ስመኝ፤ ህዝቡ ለሚደግፈውና ለሚያደላው ወገን በሌላ መንገድ ድጋፍ አድርጎ ሊሆን ይችላል እንጂ ግብር አልከፈለም፤ አይከፍልምም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ስመኝ ማብራሪያ፤ ባለስልጣኑ ባለፉት አራት ወራት የገቢ አሰባሰብ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ከችግር ለማላቀቅና ጠንካራ አፈጻጻም የታየባቸው አካባቢዎችን ጥንካሬ ለማስቀጠል የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት አቅዷል፡፡ የተቋሙን አደረጃጃት ወደ ህብረተሰቡ በማውረድ ተደራሽነት ለማስፋት ሲሠሩ የነበሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ ግብር ከፋዩ እና ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት መካከል ቅሬታ እንዳይኖር የግብር ሥርዓቱን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎችን በአፋጣኝ ወደ ተግባር ለማስገባት ይሠራል፡፡ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ባለሥልጣኑ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 4 ነጥብ 92 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 5 ነጥብ 234 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ከኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት 15 ቢሊዮን ብር መደበኛ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ባሉት አራት ወራት አራት ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ አምስት ነጥብ 234 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ከእቅዱ በላይ 106 በመቶ ጭማሪ ማሳካት መቻሉን ያሳያል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 942 ሚሊዮን ብር ብልጫ ወይም 22 በመቶ ጭማሪ ተመዝግቧል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት በክልሉ 12 ነጥብ 45 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 13 ነጥብ 2 ቢሊዮን መሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡
ለተጨማሪ ንባብ ሊንኩን ይጫኑ
መላኩ ኤሮሴ