በቅርቡ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተደረገው የንግድ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ጭማሪ በተገቢው ጥናት ያልተደገፈና በነጋዴው ላይም ጫና እያሳደረ መሆኑን የተከራይ ነጋዴዎቹ ተወካዮች ይናገራሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ፣ የኪራይ ዋጋ ማሻሻያው በተገቢው ጥናት ተደግፎ የተከናወነ ቢሆንም ነጋዴዎቹ እንደ ችግር የቀረቡትን ጥያቄዎች ወስዶ በትኩረት እያየ መሆኑንና ለጥያቄዎቹም መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ አስታውቋል፡፡
የተከራይ ነጋዴዎች ተወካይ ነን በማለት ፊርማና በየቀጣናቸው የተወከሉበትን ወረቀት ይዘው የመጡ 11 ግለሰቦች፤ የዋጋ ጭማሪውን ሙሉ በሙሉ ባይቃወሙም የወጣው የዋጋ ማሻሻያ ተመን የተጋነነ በመሆኑ ለችግር እያጋለጠን ነው፤ ማሻሻያውም በተገቢ ጥናት የተደገፈ ነው የሚል እምነት ስለሌለን በዚህ ልክ መጋነኑን እንቃወማለን ብለዋል፡፡ ባደረግነው የዳሰሳ ጥናትም ማሻሻያው እጅጉን የተጋነነ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንና አካባቢያዊ ተጽዕኖን ያላገናዘበ መሆኑን፤ ይልቁንም በጭማሪው ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን የሚያመላክት የተጽዕኖ ጥናት ያልተከናወነበት ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አሰምተዋል፡፡
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ ኮርፖሬሽኑ ከ6ሺ600 በላይ ተከራዮች ያሉት ቢሆንም የኪራይ ዋጋ ጭማሪው ሁሉምንም በአንድ ዐይን ተመልክቶ ተግባራዊ የተደረገ ነው፡፡ አስር በማይሞሉ ገናና ንግድ ቤቶች ምክንያትም ዝቅተኛና መካከለኛ አቅም ያላቸው በአንጻሩ በርካታ ሰው ቀጥረው የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ላይ ጫና ፈጥሯል፤ የዳቦ ቤቶች፣ ዕድር ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶችና ሌሎች በተመጣጣኝ አንዳንዴም ከአካባቢው ባነሰ ዋጋ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚያቀርቡ ንግድ ቤቶች ጭምር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪው ተጠቂ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሰፋፊ ቦታ ላላቸው ቤቶች ለማይጠቀሙበት ቦታ እንዲከፍሉም ተገድደዋል፡፡ በመሆኑም በተቋሙ የአሠራር ሥርዓት ችግር ምክንያት ለረዥም ጊዜ ኪራይ ሳይከልሱ ኖሮ አሁን ላይ በአንድ ጊዜ በመቶና በሺ እጥፍ ኪራይ መጨመር ተገቢ አይደለም፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቦታም ሆነ በአንድ አፓርታማ ፎቆች ላይ ያደረገው የዋጋ ተመን ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፣ እስጢፋኖስ ፊት ለፊት በሚገኘው ፊንፊኔ ህንፃ ላይ ለተመሳሳይ ልኬት ለ1ኛ ፎቅ 43ሺ500 ብር፣ ለሁለተኛ ፎቅ 46ሺ770 ብር፣ ለሦስተኛ ፎቅ 53ሺ500 ብር ተጠይቋል፡፡ መስቀል አደባባይ ፊት ለፊት ላለ ኬክ ቤትም 23ሺ ብር ሲጠየቅ በኋላ በኩል ለሚገኝ ስፋቱ ተመሳሳይ ለሆነ ሌላ ኬክ ቤት 44ሺ ብር ጠይቋል፡፡ ይህ ደግሞ ጥናቱ በተገቢው ጥራት እና አሳታፊነት እንዳልተሠራ የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም የተጋነነው ጭማሪ በነጋዴው ላይ ጫና ስለፈጠረ የነጋዴው ጥያቄ ተገቢው ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከ44 ዓመታት በፊት የተወረሱ ቤቶችን በቅርቡ ከተገነቡ ዘመናዊና ምቹ የግል ቤቶች ጋር ለማወዳደር መሞከሩ አግባብነት የለውም፡፡ በዚህ መልኩ በመንግሥት የሚደረግ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ በግል ይዞታ ባሉ ቤቶች ያለውን ኪራይ ስለሚያንረው እና ተከራዩም ይህን የኪራይ ጭማሪ የሚያስተላልፈው በሚሸጠው ምርት እና አገልግሎት ላይ ስለሆነ አጠቃላይ የዋጋ ንረት ላይ የሚኖረው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረመድህን በበኩላቸው እንዳሉት፤ ማሻሻያው እንደሚባለው ከፍተኛ ሳይሆን የተወሰነ የማስተካከያ ጭማሪ ነው የተደረገው፡፡ ይህ የማሻሻያ ጭማሪም የመኪና ማቆሚያ፣ የኮሪደርና ሌሎች ቦታዎችም ቅንስናሽ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚለካው የተገነባው ቤት ብቻ ነው፤ ሰፊ ሜዳ ቢኖረው እንኳን በነጻ ነው የሚገለገሉበት፡፡ ምንም እንኳን ብዙ እጥፍ ተጨመረብን ቢባልም፤ አሁን ካለው የኪራይ ዋጋ አኳያ ሲታይ በዝቅተኛ ዋጋ የሚከራዩት የኮርፖሬሽኑ ቤቶች ናቸው፡፡ የዋጋ ተመኑም በካሬ ሜትር ከ509 ብር ጀምሮ እስከ 73 ብር እየቀነሰ የሚሄድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከግሉ ቀርቶ ከሌሎች ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡
ሁሉም በአንድ ቋት ታይተዋል፤ ከትልልቆቹ ጋር እኩል ታይተናል የሚለውም ልክ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተመኑ ሲሠራ ቅድሚያ የቤቶቹም ሆነ የቦታ ደረጃ፣ የቤቶቹ ጥራትና ሌሎችም ነገሮች በጥናቱ ከግንዛቤ ገብተዋል፡፡ ጥናቱም እነዚህን ጉዳዮች በአግባቡ የለየ ሲሆን፤ የኪራይና የዋጋ አለመረጋጋትን ይፈጥራል የሚለውን ስጋት በተመለከተም የኪራይ ማሻሻያው በዚህ መልኩ በግል ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር አይደለም፤ ይልቁንም ፍትሃዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሰፍንና ገበያውንም ወደመረጋጋት የሚያመጣ ነው፡፡
ከካሬ ሜትር ልኬትና ፍላጎት ጋር የተያያዘው ጉዳይ በኮርፖሬሽኑም ግንዛቤ የተወሰደበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ክብሮም፤ ችግሩን ለማቃለል ሲባል ተከራዮች በግቢ ስፋት ሳይሆን በቤት ብቻ እንዲከፍሉ፤ ከኮሪደር ሁለት ሦስተኛና ከበረንዳ ሦስት አራተኛ ተቀናሽ መደረጉን እንዲሁም ቤቱ እየሰፋ በሄደ ቁጥር እስከ 75 በመቶ ቅናሽ መደረጉን አብራርተዋል፡፡ የዳቦ፣ የእድርና መሰል ቤቶችን በተመለከተም ቤቶቹ በዚህ ሥራ የማያወጣቸው ሆኖ ሲገኝ ወደ ሌላ የንግድ ዘርፍ የሚቀይሩበት እድል መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ የቀረቡት ጥያቄዎች በትኩረት እየታዩ መሆኑንና መፍትሄ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
ወንድወሰን ሽመልስ