ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአራት ወራት በፊት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተዋቀረውን የሕግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ አባላት ሰሞኑን በጽህፈት ቤታቸው ማነጋገራቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት አራት ወራት የሕግ ማሻሻያዎችን በመከለስና ምክረ ሀሳብ በመስጠት ላደረጉት የነፃ አገልግሎት የጉባዔውን አባላት አመስግነዋል።ከሕግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ 13 አባላት መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ ቀንዓን ናቸው፡፡ ከእኝህ አንጋፋ ምሁር ጋር ነጻ አገልግሎት ለመስጠት ለምን እንደተነሳሱ፤ የሚሻሻሉት ህጎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡እንሆ
አዲስ ዘመን፡-የነጻ አገልግሎት ለመስጠት ምን አነሳሳችሁ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡- ለተጀመረው አገራዊ ለውጥ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት አለብን በሚል ነው የተነሳሳነው፡፡ እውነት ነው ጊዜያችንን መስዋዕት አድርገን ስንሰራ በሰዓት፣ በቀንና በወር ተምነን ማስከፈል እንችላለን፡፡ ግን እኛ በመንግሥት ስንጠየቅ እሺ ያልነው ለውጡን ለመደገፍ ካለን ቁርጠኝነት ነው፡፡ዓላማችን የምንችለውንና በአቅማችን ልክ አስተዋጸኦ ለማድረግ ነው፡፡እናም ምንም አይነት ክፍያ አይከፈለንም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ደግሞ በነጻ ለማገልገል ፈቃደኛ ስለሆናችሁ አመስግናለሁ ብለውናል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ እየሰጠን ላለው ነጻ አገልግሎት በይፋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ገንዘብ ሳትጠይቁ ይህን በመስራታችሁ ትመሰገናላችሁ መባሉም ጥሩና ያልተለመደ ነገር ነው፡፡እዚህ አገር ብዙ ጊዜ ይለፋል ምስጋና የለም፤ ገንዘብም አታገኝም፡፡ መጨረሻ ላይ ከምስጋናውም ይልቅ ብዙ ነገር ይደርስብካል፡፡ ስለዚህ ምስጋና መጀመሩ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-እናንተ ለአገራችሁ ብላችሁ በነጻ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ሆናችሁ ለትውልድ የሚሆኑ ህጎችን የማሻሻል ስራ እየሰራችሁ ነው፡፡ በሌሎች የሙያ መስኮች የተሰማሩ ከእናንተ ምን መማር አለባቸው ይላሉ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-ሌሎቹ ከእኛ መማር ያለባቸው ሁልጊዜም ቢሆን ለገንዘብ ሲባል ብቻ አይሰራም፡፡እርግጥ ነው ለገንዘብ ሲባል የሚሰራባቸው ብዙ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ በተለይ አንድ ባለሙያ ለሚሰጠው አገልግሎት ተመጣጣኝ ገንዘብ ማስከፈሉ ተገቢም ነው፡፡ ሆኖም ሁልጊዜ ለገንዘብ ብቻ አይሰራም፡፡እናም መንግሥት እባካችሁ አግዙኝ፣እርዱኝ ሲል ካልከፈልከን አናግዝህም፣ አንተባባርህም ማለት ልክ አይደለም፡፡ስለዚህ በሌላ የሙያ መስክ የተሰማሩ ዜጎች ከእኛ መማር ያለባቸው ሁልጊዜ ለገንዘብ አይሰራም፡፡ ለአገርና ለህዝብ አስተዋጸኦ ለማድረግ ሲባልም ነጻ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ዩኒቨርስቲ ውስጥ ብዙ ሰዎች የህግ ምክር ይጠይቃሉ፡፡እኔ ባለሙያ ነኝና ትከፍይኛለሽ ወይም ትክፍለኛለህ አልልም፡፡ የምትችለውን ትረዳለህ፡፡ ትጸፍላቸዋለህ፤ ምክር ትሰጣቸዋለህ፤ አስፈላጊ ከሆነም አንዳንዴም ጠበቃ ሆነህ ትቆምላቸዋለህ፡፡ እኔ ለአንድ አነስተኛ ገቢ ላለው ሰው ጥብቅና በነጻ ቆሚያለሁ፡፡ እና ብዙ ሰዎች ምክር ይጠይቃሉ፤ ከጊዜ አኳያ ስታስበው ገንዘብ ልታስከፍል ትችላለህ ግን ሁልጊዜ አታስከፍልም፡፡ ሁልጊዜ ገንዘብ ካልተከፈለኝ የሚል ሰው አንደኛ በማህበረሰቡም ይጠላል፡፡ ሌላው ደግሞ ማህበራዊ ኃላፊነትም አለብን፡፡ እርግጥ ነው ገንዘብ ካላቸው ሰዎች አንተ ለምትሰጠው አገልግሎት ተመጣጠኝ ክፍያ ብትቀበል ትክክል ነው፡፡ እናም ይህ ለአገር አስተዋጸኦ የማድረግ ጉዳይ ነውና ሁልጊዜ በገንዘብ አይሰራም፡፡አገር ትጠቀም እንጂ በነጻም ይሰራል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ነጻ አገልግሎት የምትሰጡት እስከ መቼ ድረስ ነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-ለጊዜው የተባባልነው ለሶስት ዓመታት ነው፡፡ ከዚያ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በሕግና ፍትህ አማካሪ በአባልነት የሚሳተፉት13 ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን በስራችን ብዙ ግብረ ኃይሎች ተደራጅተው ነጻ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ ጥናት የሚያጠኑና መነሻ ሀሳቦችን ይዘው የሚመጡ አሉ፡፡ እነዚህም በነጻ ነው የሚያገለግሉት፡፡በፈቃደኝነት ለአገራችን የበኩላችንን ሚና ለመወጣት እየተረባረብን ነው፡፡እኛን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያናገሩን በሕግና ፍትህ አማካሪ ደረጃ ስላለን እንጂ የማይታወቁ ነገር ግን ከእኛ ጋር የሚሰሩ በጣም ብዙ ግብረ ኃይሎች አሉ፡፡አዲስ ዘመን፡-በቡድን የመስራት መንፈሳችሁ እንዴት ነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡- በጣም ጥሩ ነው፡፡ ያማ ባይሆን ኖሮ አንድም ህግ ማሻሻያ አድርገን አናቀርብም ነበር፡፡በሕግና ፍትህ አማካሪ ሆነ በግብረ ኃይል ደረጃም በቡድን የመስራት መንፈስ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡መነሻ ሀሳብ ሲያመጡልን እኛም ተባብረን የምንሰራበት መንፈስ የሚያረካ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-እናንተ ለአገራችሁ ነጻ አገልግሎት መስጠት መጀመራችሁ ለሌሎች ባለሙያዎች መነሳሳት ይፈጥራል የሚል እምነት አልዎት?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡- ለአገር ነጻ አገልግሎት ማበርከት የግል ውሳኔ ነው፡፡ ግን አገሬን መርዳትና መደገፍ አለብኝ በሚል ሁሉም የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ባላቸው አቅም ልክ ተነሳስተው መደግፍ አለባቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ የእኛ ጅማሮ ተነሳሽነት ያመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛም በሙያችን በአቅማችን ለአገራችን አስተዋጸኦ እናድርግ ብለው የሚያስቡ ሁሉ ይነሳሳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን አይነት መልዕክት ያስተላልፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተነሳስቶ ነጻ አገልግሎት ቢሰጥ በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ሁሉም ደጁን ቢጠርግ ፓሪስ በአንድ ቀን ትጸዳለች እንደሚባለው ሁሉ ሁሉም በሙያው ለአገሩ በቅንነት ነጻ አገልግሎት ቢሰጥ ለአገራችን ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ለወገኑና ለአገሩ በየሙያው አስተዋጸኦ ቢያደርግ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሚሻሻሉት ህጎች በምን ሂደት ላይ ይገኛሉ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡- በዋናነት አሻሽለን ያጠናቀቅነው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የማህበራት አዋጅን ነው፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል፡፡ስለ ምርጫ ህግን በተለይ ደግሞ የምርጫ ቦርድን በተመለከተ የማሻሻያ ረቂቅ ህግ ቀርቦ ተወያይተንበታል፡፡ በጸረ ሽብሩ አዋጅ ላይም ውይይት ላይ ነን፡፡ የሚዲያ ህግም የሚሻሻል ነው የሚሆነው፡፡ እንደ ቅደም ተከተል መሻሻል ያለባቸውና የምንወያይባቸው ሌሎች በርካታ ህጎችም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡-በቀጣይስ የሚሻሻሉ ህጎች ምን ምንድናቸው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡- ይህን የሚመለከተው የሕግና ፍትህ አማካሪ ያቋቋመው መንግሥት ነው፡፡መንግሥት ይህ ህግ ይጠናልኝ እንዲያውም ለዚህኛው ቅድሚያ ስጡልኝ ሲል እኛ እንሰራለን፡፡ እኛ አማካሪ ነን፡፡ስራችንም ማማከር ነው፡፡ ስለዚህ ህጉ እነዚህ መሻሻያዎች ቢደረጉበት በሚል እስከእነ ምክንያቶቹ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ እናቀርባለን፡፡ጠቅላይ አቃቤ ህግ ደግሞ አይቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ይልከዋል፡፡ሚኒስተሮች ምክር ቤት ደግሞ አይቶ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይመራዋል፡፡እናም ይህን መንግሥት ህግ አጥኑልኝ ሲል ነው እኛም በዚህ መልኩ መሻሻል አለበት ብለን የምናማክረው፡፡
አዲስ ዘመን፡-አሁን የሚሻሻሉት ህጎች ጨቋኝና አፋኝ ህጎች ነበሩ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አልዎት?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-አንድን ህግ ስራ ላይ ስናውለው መጨቆኛ መሳሪያ ማድረግና ህጉ ከመሰረቱ ጨቋኝ ነው ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የመጨቆኛ መሳሪያ እንዲሆኑ ተደረጉ እንጂ በራሳቸው ህጎቹ ሰው አይናደፉም፡፡እናም መሳሪያ፣ መግረፊያና መጨቆኛ እንዲሆኑ ተደርገው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ተደረጉ እንጂ ህግ በመሰረቱ ተነስቶ አይናከስም፡፡ የጸረ ሽብር አዋጅ ቢሆን ስራ ላይ ሲውል መንግሥት የተጠቀመበት መንገድ ነው ችግር የፈጠረው፡፡ ስለዚህ አላሰራ ያሉትንና ችግር ያመጡትን ህጎች እየፈተሸናቸው ነው፡፡የለውጡን መንፈስ ተከትለው እንዲሂዱ የማድረግ ስራ ነው እየሰራን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የለውጡ መንፈስ ምንድነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-ለውጡ ያተኮረባቸው ጉዳዮች መካካል አንዱ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበሩ ማድረግ ነው፡፡እንዲሁም ህገ መንግሥት ነጻነቶችም እንዲከበሩ ማድረግንም ይጨምራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ስራ ሰርተናል የሚል እምነት አላችሁ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡- አዎ፤መንግሥት ብቻውን ቢሰራ ኖሮ በአጭር ጊዜ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅን ብቻ ሰርቶ አይጨርስም ብዬ አምናለሁ፡፡ከዚህም በተጨማሪ እኛ እነዚህ ህጎች ዝም ብለን ለአቃቤ ህግ አናቀርባቸውም፡፡ የህዝብ ጉዳዮች ናቸው በሚል ብዙ ህዝብ እንዲወያይባቸው ነው ያደረግነው፡፡ስለዚህ የህዝብ ተሳተፎም አለባቸው፡፡ስራችንን ውጤታማ የሚያደርገው አንደኛ ከመሰረቱ የህዝብ ተሳትፎ መኖሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የምርጫ ቦርድ የሚመለከተውን የማሻሻያ ረቂቅ ህግ ሂደት ላይ ናችሁ፡፡ብዙ ጊዜ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድ የገለልተኛነት ጉዳይ ጥያቄ ያነሱበታል፡፡ይህንን ህግ ስታሻሽሉ እንዴት አያችሁት?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-በህግ ደረጃ ያስኬዳል ያልነውን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲወያዩበት አድርገናል ፡፡ከአንድም ሁለት ጊዜ የምክክር መድረክ አካሄደናል፡፡እነሱም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ስለዚህ ለጊዜውም ቢሆን ያሰራል የምንለውን አማካኝ ሀሳብ አስቀመጠን ነው የተሰራው፡፡የሚያጨቃጭቅ ከሆነ ደግሞ አማራጮችን ነው ያቀረብነው፡፡የመጨረሻው ውሳኔ ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ገለልተኝነት ምን ያህል ነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-እኛ ገለልተኞች ነን፡፡ በፖለቲካ ውስጥም ተሳትፎ የለንም፡፡እኛ ደግሞ ህጎቹ መሻሻል ያለባቸውን የሃሳብ አማራጮችን ነው የምናቀርበው፡፡‹‹ይህ ሀሳብ ጠንካራ ድጋፍ አለው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ውስንም ድጋፍ ቢኖረውም ይህም ሀሳብ ተነስቷል፡፡ይህን መንግሥት የሚከተል ከሆነ በዚህ መልኩ ቢሆን የተሻለ ነው›› የሚል ምክረ ሀሳብ ነው የምንሰጠው፡፡የእኛን ምክር የመቀበልና ያለመቀበል የመንግሥት ፈንታ ነው፡፡ስለዚህ መንግሥት የእናንተን ሀሳብ ጨርሶ አልቀበልም ካለ መብቱ ነው፡፡እኛ ከማማከር ያለፈ ስልጣን የለንም፡፡እኛ ነጻም ገለልተኛም ነን፡፡በስራችን ወቅት ፍጹም የፖለቲካ ዝንባሌ አላየሁም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የማሻሻያ ሀሳቦችን የመቀበል የመንግሥት ውሳኔ ነው ብለውኛል፡፡እስካሁን ባለው ሂደት በመንግሥት በኩል ሀሳቦቻችሁ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝተዋል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡እርግጥ ነው በአብዛኛው ሀሳቦቻችን ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ግን መንግሥት የለወጣቸው ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ምክንያቱም እኛ የመሻሻያ ሀሳቦችን ነው ከእነማብራሪያቸው የምናቀርበው፡፡ስለዚህ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ደግሞ እኛ የምናቀርበውን የማሻሻያ ሃሳቦች የሉም እንደዚህ ቢሻሻሉ ይሻላል ብሎ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመራበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም በአብዛኛው እኛ ያልናቸው ጉዳዮች ተቀባይነት አላቸው፡፡አንዳንድ ለውጦች ግን አሉ፡፡ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በስራ ሂደት ያጋጠማችሁ ችግር ይኖራል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-ብዙም ችግር አላጋጠመንም፡፡ እኛ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር ነው የምንሰራው፡፡ስለዚህ ችግር ካጋጠመን ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው የምናሳውቀው፡፡እሱም ችግሩን ተቀብሎ ለማስተካካልና መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ያደርጋል፡፡እናም እስካሁን የጎላ ችግር ገጥሞናል ብሎ ለመግለፅ ያስቸግረኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናንተ ቢሻሻሉ ብላችሁ ሃሳብ ያቀረባችሁባቸው ህጎች የፖለቲካ ምህዳሩን ምን ያህል ያሰፉታል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-በደንብ እንጂ፡፡ የሚሻሻሉት ህጎች የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፉታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ለምሳሌ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ረቂቅ አዋጅ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ትልቅ ሚና አለው፡፡አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ እኮ እንዳይንቀሳቀሱ ቀይዶ ነው የያዛቸው፡፡በበጎ አድራጎትና ማህበራት ተሳትፎ ብዙ ጥቅም ይገኛል፡፡ይህ ማለት መንግሥት አይቆጣጠራቸው ማለት አይደለም፡፡በተገቢው መንገድ እየተከታተላቸው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጸኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ልምድ ያካፍላሉ፣ስልጠና ይሰጣሉ፡፡ስለዚህ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ እንዲሰሩና እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ ለዲሞክራሲ ስርዓት መጎልበትና ለሰብዓዊ መብት መከበር የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ፡፡
በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ እንዲሁም በጸረ ሽብር አዋጅ ዙሪያ ብዙ እሮሮ ይሰማ ነበር፡፡ከዚህ አኳያ የተሻሻሉ ህጎች መውጣት የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ለምሳሌ ዝርዝር የምርጫ ህጉም ሲሻሻል አንደኛው የዲሞክራሲያዊ ተቋማት ከሚባሉት መካካል አንዱ የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን ነው፡፡ስለዚህ የምርጫ ቦርድ አስተዳዳሩ ምን ይሆን የሚለውን መጀመሪያ መታየት ስላላበት ማሻሻያ ሀሳብ አቀረብን እንጂ ዝርዝር የምርጫ ህግ መሻሻሉ አይቀርም፡፡እናም የህጎቹ መሻሻል ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡አሁን ዝም ተብሎ የሚያልፍ ህግ የለም፡፡ታሽቶና በደንብ ታይቶ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-በአሁኑ ጊዜ ባለው የአገሪቱ ለውጥ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-የአገሪቱ ለውጥ በህግ ብቻ መሆን የለበትም፡፡እርግጥ ነው ህግ አንዱ ዘርፍ ነው፡፡ፖሊሲዎችም መፈተሽ አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ አቃፊ፣አሳታፊ መሆን አለበት፡፡እናም ጅምሩ ጥሩ ነው ግን ይበልጥ የተሻለ እንዲሆን ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ተነጋግረን፣ ተወያይተን የወደፊቱን የአገራችንን አቅጣጫ መወሰን አለብን፡፡ኳሱ ህዝቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ነው ያለው፡፡ስለዚህ ሁላችንም በምንችለው ሁሉ ተረባርበን አቅጣጫ አሲዘን የፖለቲካ ምህዳሩንም አስፍተን፣አቃፊ እንዲሆን አድርገን ከሁሉ በላይ ተቻችለንና ተከባብረን አሁን እየታዩ ያሉትን መጥፎ ክስተቶችን አስወግደን የዲሞክራሲ ባህልን ቀስ በቀስ እየገነባን መሄድ አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡-የምርጫ ቦርድ እንዴት መተዳዳር እንዳለበት የማሻሻያ ህግ እየሰራችሁ ነው፡፡ገና ደግሞ ዝርዝር የምርጫ ህግ ማሻሻያ ሃሳብ ታቀርባላችሁ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ይህ ሂደት በመጪው ዓመት የሚካሄደው ምርጫ አያዘገየውም ወይ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-በቀጣይ የምርጫ ዝርዝር ህጉን ለማሻሻል ይጠናል ወይ የሚለውን አላውቅም፡፡ግን ቦርዱን በምንና ማን ይመራው የሚለው የማሻሻያ ረቂቅ ህግ ሰርተናል፡፡ይህ ህግ አጨቃጫቂና አወዛጋቢ ነበር፡፡ይህን በተመለከተ ለመንግሥት ይህ ነገር ይታይ ብለናል፡፡ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባርና የምዝገባ ህጎች ገና ወደፊት የሚሻሻሉ ይመስለኛል፡፡ስለዚህ ህጎቹ የሚሻሻሉበትን ጊዜ ስለማላውቅ ምርጫውን ያዘገየዋል ወይም አያዘገየውም ማለት አልችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንድ ህግ ለማሻሻል ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-እንደ ህጉ አይነት ቢለያይም ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የማህበራት አዋጅ እና የጸረ ሽብር ህጉ ብዙ ጊዜያትን ፈጅተዋል፡፡እናም እንደ አጨቃጫቂነቱ፣ አወዛጋቢነቱ፣ ስፋቱና መጥበቡ ነው ጊዜ የሚፈጀው፡፡ለምሳሌ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የማህበራት አዋጅ ሶስት ወር ፈጅቶብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡-እስካሁን አጠናቃችሁ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የተመራ የማሻሻያ ረቂቅ ህግ ስንት ናቸው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-አንድ ነው፡፡እሱም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ነው፡፡ሌሎቹ ገና በሂደት ላይ ናቸው፡፡እኛን ያቋቋመን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው፡፡ተጠሪነታችንም ለእሱ ነው፡፡ሰርተን የምንሰጠውም ለእሱ ነው፡፡ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሲያምንበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርበዋል፡፡የምርጫ ቦርዱን በተመለከተም ሰርተን ለጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሰጥተናል፡፡የጸረ ሽብር ህጉ ግን ገና ብዙ ውይይት የሚፈልግ ነው፡፡እያንዳንዱን አንቀፅ ፈትሸን ለረቂቅነት መቅርብ ይችላል ብለን ስናምን ነው የምናቀርበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለመንግሥትም ሆነ ለህዝቡ የሚሉት ምክረ ሀሳብ አለዎት?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-ሁላችንም በአቅማችን ልክ የሚጠበቅብን አስተዋጸኦ በተነሳሽነት ብናደርግ የምንወዳትን አገርና ህዝብ መጥቀም ይቻላል፡፡በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ፍሬያማ እንዲሆን ሁላችንንም የበኩላችንን ድጋፍና እገዛ እናድርግ እላለሁ ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካሪያስ፡-እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2011