የታወቀ ነው፤ የተለመደ በየተረቶቻችንና ሥነ ቃሎቻችን ሲነገረን የኖረ።ምኑ ካላችሁ ደግሞ እንግዳን በቤታችን ሲመጣ እግር አጥቦ የተመቻቸ ስፍራ አዘጋጅቶ አረፍ በሉ ማለት፤ ተንከባክቦና ጋብዞ መሸኘት እላችኋለሁ። የዛሬ ችግራችን መልካም የሆነውን የኋላ እሴቶቻችንን አለመያዝ መሆኑ በብዛት ቢነገርም ሙሉ ለሙሉ እንዳለቀቅነው ግን አንዳንድ ተግባሮቻችን ያስረዱልናል። በተለይ የገጠሩን የአገሪቱ ክፍል ስንጎበኝ እውነትነቱን በሚገባ እናረጋግጣለን።
በእርግጥ አንዳንዶች ጉዳዩን በቀጥታ ከሀይማኖት ጋር ብቻ የሚያያይዙ አሉ። ሆኖም ባህል ያለ እምነት ሊፈጠር አይችልም። አምነንና አንድን ነገር ደጋግመን ስናደርገው ባህላችን ይሆናል። ዋሀደናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሰሞኑን በአደባባይ ያየነው የአክሱም ጽዮን ክብረ በዓል የእንግዳ አቀባበል ስነ ስርአት ነው። ይህ ባህል በየቤታችን እንደ ወግና ባህል ባይኖር ለአደባባይ እይታ በቅቶ ባላየነው ነበር። ግና ይህ ልምድ ከቤት የነበረ በመሆኑ እማኝ ሳያስፈልገን እንግዳ ተቀባይነታችንን አስመሰከርንበት። በረከት ለማግኘት ዘር፣ ቀለምና ሰፈር ሳንለይ ተከባበርንበት።
ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ሲቀበሉ ፍቅር የሚያሳዩ በትን ስርዓት በአደባባይ ደገሙት። በእርግጥ ይህ ባህል ዛሬ ላይ ድንገት የተፈጠረ እንዳልሆነ ከመጽሀፍ ቅዱስ እንረዳለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ሆኖ ሳለ የደቀ መዛሙርቱን እግር ስለማጠቡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.13፡4-5 ላይ ተፅፎ ይገኛል።ይህ ደግሞ ጌታ ሎሌ ሳይባል እግር ማጠብ መልካም እንጂ መጥፎ እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው። ብዙዎችም ከዚህ ተምረው ይመስላል ዝቅ ብለው ታናናሾቻቸውን የሚያጥቡት። ዝቅ ብለው የሚታዘዙት። ከእምነቱ ስንወጣ ደግሞ እግር አጠባ በማህበረሰቡ ዘንድ ሌላም መልዕክትና ትርጓሜ አለው። ይኸውም ዝቅ ብሎ እግር ማጠብ ለበረከትና ለምርቃት ያበቃል የሚለው ነው።
በቤታችን በምሽት እንግዳ ከመጣ ብዙ ጊዜ ከምግብ ይልቅ ቀድሞ የሚቀርብለት ሞቅ ያለ የእግር ውሃ የመሆኑ ምስጢር ማህበረሰቡ የእንግዳ ክቡርነትን ከምንም በላይ ስለሚያምን ነው። እናም ሁልጊዜ ፍቅራቸውን ለመግለጽ ልጅ ካለ ልጁ ጎንበስ ብሎ እንዲያጥብ ይታዘዛል። ልጅ ከሌለ ደግሞ ራሱ ባለቤቱ እግሩን ያጥብና በመሳም እንኳን ደህና መጣህልን በማለት የሚበላውን ያቀርብለታል።ፍቅር ይደረጃል። መከባበር ያብባል። ምርቃት ይጎርፋል።
በእግር አጠባ ጊዜ ባላንጣዬ ነው፤ ተቀያይመናል የሚል የለም። ይልቁንም እንግዳውን ይቅር ብሎ ያስተናግደዋል።ይህ ባህል ከአባቶች የተወረሰ ነው። ይቅር ባይነትንና ዝቅ ብሎ ማገልገልን ከጥንት ጀምሮ ተለማምዶታል፤ ተምሯል። ስለዚህ ይተገብረዋል።
የእግር አጠባ ስርዓት ብሔር፣ እውቅናንና ሀይማኖትን ማዕከል አድርጎ የሚተገበር አይደለም። ሰው በሰውነቱ ወይም በእንግድነቱ የሚሰጠው ልዩ ክብር ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያዊያን ለማንኛውም ዜጋ ይህንን ከማድረግ አይቆጠቡም።ግን ይህ ለምን ሆነ ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? አዎ ከሆነ መልስዎ መስፈርቱ ብዙ መሆኑን ይረዳሉ። ዋናው ግን የመጣው እንግዳ እኛን አምኖ፤ ከፈጣሪ በረከት ሊያሰጠን ነው የሚለው መሆኑን አይዘነጉም።
“አሳድሩኝ ያለ እንግዳ በአግባቡ ካላስተናገድኩ በረከት አጣለሁ፤ ልጆቼ ፣ ቤተሰቤ መልካም ነገር አይገጥማቸውም፤ እኔም ማደሪያ ባጣ የሚያስጠጋኝ አይኖርም “ ብሎ ያምናል። በዚህም ከዋናው የእንግዳ አቀባበል ስርዓት ማለትም ከእግር አጠባው ጀምሮ ለመጣው እንግዳ መልካም አቀባበል ያደርጋል።
የእግር አጠባ ሌላው ባህሪ አዛውንት ወጣትና ልጅ ሳይባል እንደ እንግዳ ክብር ተሰጥቷቸው የሚስተናገዱበት መሆኑ ነው።በእምነት የሚተገበርም ነው።ስለሆነም የትህትና እና ፍቅርን ጥግ ለማሳየት ሲሉ ይተገብሩታል። ዝቅ ብሎ ሌሎችን በማገልገል የሚሰማን ስሜት ያስተጋቡበታል።
ይህንን ባህል ቀደምት አባቶች ሲያደርጉት የኖሩት የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነት፤ የመረዳዳት ባህልን በየብሔረሰቡ ልቦና ውስጥ ለማስቀመጥ ነው። ምሽት ላይ እግር ጥልዎት ማደሪያ ካጡና ወደ አንድ መኖሪያ ቤት አምርተው እንዲያሳድርዎ ጠይቀው አላሳድርም የማይባሉት ለዚህ ነው። ተፈቅዶልዎ ወደ ቤቱ ከገቡ በኋላም እንዳይበርድዎ ውሃ ሞቆልዎት የደከመ ሰውነትዎን እንዲያፍታቱ ተደርገው እግርዎን የሚታጠቡትም ለዚሁ ነው፡፡
እስቲ አሁንም በእግር አጠባ ስርዓት ወቅት የሚደረግን ባህሪ እናንሳ። ራሴ እታጠባለሁም ማለት አይፈቀድም። ምክንያቱም ይህንን ባህል ልምድ ያደረገው ማህበረሰባችን ድርጊቱ ትህትና የሚያሳይበት እንደሆነ ያምናል። ስለዚህ በረከቱን እንደወሰደበት ይሰማዋልና እንቢ ቢል እንኳን አይቀበለውም።
በእግር አጠባ ስርዓት ሌላው የሚታየው ባህሪ ትንሽ ትልቅ፤ ድሃ ሀብታም፣ ወንድ ሴት፤ ህጻን አዋቂ ብሎ የሚከፋፈልበት አይደለም፤ በፍፁም ፍቅር የሚተገበር ነው፡፡
ከእኔ ይልቅ እንግዳ ክቡር ነው የሚባልበትም ነው። እናም ስርዓቱ የሰውን ልብ የሚያሳርፍ፤ ለዕይታ የሚማርክና ትህትና የተሞላበት ነው። በተለይ እግር አጠባው በአዛውንቶች ሲከወን የተለየ ትርጉም ይሰጣል። ይህ ባህላችን የቀደመ ፍቅራችንን የምናስብበት ነውና መለስ ብለን ስናየው የሚሰማን ደስታ ልዩ ነው። እንኳን ለራሳችን ለሌላ የሚተርፍ ባህል ባለቤቶች ነንና ልንጠብቀው ይገባል በሚለው መልዕክት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2012
ጽጌረዳ ጫንያለው