ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ዘር … በሱማሌ የሚያቀራርብ እንጂ የሚያራርቅ መለያ አይደለም። ምክንያቱም በእነርሱ ዘንድ ችግር ቢኖር የሚፈታበት፣ የተጣላ ቢኖር የሚታረቅበት፣ ትስስርና ጥብቅ ቤተሰባዊነት የሚመሰረትበት ልዩ ባህል አላቸው። ልዩነቶች ውበት የሚሆኑበት ማስተሳሰሪያ ገመድም በእጃቸው ነው።
መቼም ሰው ከሰው ጋር ቀርቶ እግር ከእግርም መጋጨቱ ይቀራል ተብሎ አይታሰብም።ስለዚህም ሱማሌዎችም ይህንን አምነው መፍትሄ የሚሆን የችግር መፍቻ ቁልፍ አዘጋጅተዋል። ችግሮቻቸውን በአንድ ጥላ ሥር ተሰባስበው ልዩነቶቻቸውን የሚያጠቡበት ሥርዓት ፈጥረዋል። ባህላዊ የፍትህ ስርዓቱ የሚከናወነው በዛፍ ጥላ ሥር ንጹህ አየር እየተቀበሉ ሲሆን፤ እኩል ሀሳባቸውን የሚያወጡበት፣ ቅሬታቸውን የሚገልጹበትና የሚወያዩበትም መድረክ ነው።ለመሆኑ እንዴት ይከወናል ስንልም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊን አቶ ሙሀመድ አብዱላሂ አነጋግረናል።
በሱማሌ ልዩነት የማይፈቀድበትና አንድነት የሚሰበክበት እንዲሁም በእኩል ዳኝነት ፍትህ የሚገኝበት መድረክ ነው ይሉታል ጌድ ሆስትን። ይህ ባህላዊ የችግር መፍቻ ሥርዓት የሚከወነው በዛፍ ጥላ ስር ሲሆን፤ ልዩ እሴታቸው መሆኑን ይናገራሉ። በአካባቢያቸው የጸብ ህመም ሳይጠና ፈውስ የሚሰጡት በዚህ ባህላዊ የግጭት መፍቻቸው መንገድ ነው። ችግሩ የጸናባቸው ሰዎች ፈውስ ሊሹ ከወዲያ ወዲህ እያሉም በአንድነት ለሰላማቸው የሚሰብኩበት ቦታ ላይ ይሄዳሉ።ለሽማግሌዎቹም አምላክ ምስክራቸው እንደሆነ በማሰብ ሳይደብቁ የውስጣቸውን ይናገራሉ።
‹‹ጌድ ሆስት» በሱማሌ ክልል በዛፍ ጥላ ስር የሚደረግ የሽምግልና ሥነ ሥርዓት ነውና ችግራቸውን ካስረዱ በኋላ ትክክለኛ ፍትህ እንደሚያገኙ የሚያምኑበት መድረክ ነው። ይህ ባህል በተለይ ለዛሬው ብሄር ተኮር ግጭቶች መፍትሄ የሚሰጥ በመሆኑ ወደኋላ መለስ ብለን ባህላዊ የፍትህ ስርዓታችንን መመልከት ያሻል።
ጌድ ሆስት ሽምግልናን መፈለግ የደካማነት ምልክት ሳይሆን የእውነተኛ ጀግንነትን ጥበብ የሚያመላክት መሆኑ የሚታይበት ነው። ምክንያቱም በዚህ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓት ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን ከማሸነፍ በስተጀርባ ያለውን ሁሉ ፍጹምነት ያሳያል። በመሸነፍ ውስጥ ያለውን መጸጸትንም በሚገባ ያመላክታል። በተለይ በደለኛው በበደሉ የማይጸጸትበትና ንስሀ የሚገባበትም መሆኑን በፍጹም ፍቅር እያስተማረ ያሳያል።
ጌድ ሆስት እርቅን አውርዶ ሰላምን የሚያረጋግጥ፤ ቂም በቀልን የሚያስረሳ፣ እንደ ሆነ ሃላፊው ይናገራሉ። ለዚህም ማሳየው ከመደበኛ ፍርድ ቤት ቅድሚያ የሚሰጠው ነ ው ይላሉ። ምክንያቱም ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች ግልጽ፣ በአጭር ጊዜ ውሳኔ የሚሰጠው እና ከእምነት ጋር ተሳስሮ የሚጓዝ ነው። ስለሆነም ውሸት አይታሰብም፣ አድሏዊ ያልሆነ ከማንም ያልወገነና እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥባቸው ናቸው። ስለ ዚህም አምኖ የተሰራ ነገር አይጸጽትምና ሁሌ ትክክል መሆናቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ይታመናል።እናም ጌት ሆስትም ይሄ ባህሪ አለው ይላሉ።
ጌድ ሆስት በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ሽምግልና ነው። ግብና ዓላማው አንድነትን የሚያመጣ፣ በውይ ይትና በመግባባት በሰላማዊ መንገድ ወደ ዘላቂ ዲሞክራሲ ፍትህ እኩልነትና ዕድገት መም ራት የሚያስችል ነው። በደለኛ ትክክል ነኝ ብሎ እንዳይጓዝ የሚያደርግ የራሱ ቅጣትን የሚያስተላልፍ ስርዓትም አለው። በክልሉ ውስጥ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለያየ መንገድ ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ለአብነት አንዱ ጎሳ ከአንዱ ጋር በግድያ፣ በሴት ጠለፋና በግጦሽ ቦታ ሊጣላ ይችላል። እናም ይህንን ለማብረድ በዳይና ተበዳይ በአንድ መድረክ መገናኘታቸው ግድ ነው። እናም በጌድ ሆስት ስርዓት ሽማግሌዎቹ እርቀሰላም ለማውረድ ይታደማሉ።
ቀድመው የሰሙትን ችግር አንተም አንቺም ተው በማለት የበዳይና የተበዳይን ችግር አድምጠው ዳኝነት ይሳጠሉ። እንደየጥፋቱ ክብደት በማየትም አጥፊው ካሳ እንዲክስ ይደረጋል። የካሳው አይነት የተለያየ ሲሆን በዋናነት ግን አራቱ ነገሮች ተጠቃሽ ናቸው። ብር፣ ፈረስ፣ ግመልና የጦር መሳሪያ።
የሱማሌ ማህበረሰብ በአብዛኛው ከብት በማርባት የሚተዳደር በመሆኑ የግጦሽ መሬት ትልቁ የጸብ ምንጭ ነው። በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት ቀለል ያለ ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል። ከዚያ ያለፈ ነገር ከተፈጠረ ማለትም እንደ ግድያ አይነት ከሆነ ደግሞ የግድያው ሁኔታ ታይቶ ግመል ወይም ጦር መሳሪያ እንዲከፍል ነው የሚፈረድበት።
ሌላው የካሳ ክፍያ አይነት በጣም የከበደው ሲሆን፤ዳግም መገዳደል(ቂም በቀል) እንዳይፈጸም በማሰብ የሚከናወነው ነው። እናም በባህሉ ዘንድ ‹‹አበታከሜድ›› እየተባሉ የሚጠሩት ሽማግሌዎች የጋብቻ ትስስር በመሀከላቸው እንዲፈጠር ያደር ጋሉ። ምክንያቱም ቤተሰቡን በጋብቻ ያስተሳሰረ ሰው ይጣላል ተብሎ አይታመንም። ስለዚህም በተለይ ሆን ብሎ ግድያ የፈጸመ አካል ከዚህ ውጪ ሊያስታርቀው የሚችል እንደሌለ ይነገራል፡፡
በሱማሌ ባህላዊ በዛፍ ጥላ ሥር የእርቅ ስርዓቱ ከተፈጸመ በኋላ በአንድነት ቁጭ ተብሎ የመመገብ ስርዓት ይቀጥላል ።ምክንያቱም በካሳ ደም የሚደርቀው፤ በካሳ ሀዘን የሚጠፋው፤ በካሳ ወዳጅነት የሚጠነክረው በፍቅር ማዕድ ሲታሰር መሆኑ ስለሚታመንበት ነው።አብሮ መብላት ያፋቅራል፤ ቂምንም ከሆድ ያወጣል ተብሎ ይታሰባል። እናም በጌትሆስት ችግሮቻቸውን ፈተተው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው ይገባሉ።
እናም ‹‹ማንነታችንን አንዘንጋ፣ ባህላችንን አንርሳ ኑና በዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበን ልዩነታችንን በምክክር እንፍታ» የማለታቸው ምስጢር እምቅ ሀብት አለውና እንተግብረው መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2012
ጽጌረዳ ጫንያለው