የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጥምቀት በዓልን በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረውን የጥምቀት በዓልን ዩኔስኮ የመዘገበው ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ ይህንን ውሳኔ ያደረገው በኮሎምቢያ፣ቦጎታ ባካሄደው ስብሰባው መሆኑም ተሰምቷል፡፡
የዩኔስኮ የዕውቅና መነሻ
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥምቀት ክብረ በዓልን በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንዲገባ፣ ለመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ በላከው ሰነድ እንደተመለከተው፣ ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ታሪካዊ መሠረቱን ሳይለቅ አሁን እንዳለው መከበር የጀመረው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሐ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብለው ብሔራዊ ሃይማኖት ሲያደርጉ የጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ሲከበር የኖረ ‹‹የበዓለ መጸለት/የዳስ በዓል›› የሚባል ስለነበር ጥምቀት በእሱ ምትክ የጉዞና የአደባባይ በዓል ሆኖ እንዲከበርም አድርገዋል፡፡
ለሦስት ቀናት ያህል (ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ) በተከታታይ በሚከበረው በዚህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ መንፈሳዊ መዝሙሮች፣ የተለያየ ስልት ያላቸው ያሬዳዊ ዜማዎች ይደመጣሉ፡፡ በበዓሉ ላይ የየአካባቢው አገረሰባዊ ዘፈኖች፣ ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች በስፋት ይከናወናሉ፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፡፡ በዓሉም እነዚህን የትውን ጥበባትና የሥነ ቃል ሀብቶች ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ይላል፤ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለዩኔስኮ በላከው የይመዝገብልኝ ሰነድ፡፡
ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
የጥምቀት ክብረ-በዓል እና ፋይዳው
«ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ» በተከታታይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በተለይ በጎንደር ከተማ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም የጎላ ነው፡፡
ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም የጎላ ስለሆነ በሀገር ውስጥ ካለው ማኅበረሰብ በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና መንፈሳዊ ተጓዦች የሚታደሙበት በዓል በመሆኑ እንዲሁም የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ቀልብ እየሳበ በመምጣቱ የአከባበር ሥነ-ሥርዓቱን በተመለከተ የትምህርት፤የሳይንስና የባሕል ድርጅት በ«UNESCO» ጥበቃ ስር በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ሰሞኑን በድል መጠናቀቁ ተሰምቷል።
“ጥምቀት” ለሚለው ቃል መነከር፣ መታጠብ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይሰጡታል፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡ የከተራ እለት/ ጥር 10 ማለት ነው/ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ ፤ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ።
በየዓመቱ ጥር 11 ከዋዜማው የከተራ በዓል ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ነው የጥምቀት በዓል ዘንድሮም በድምቀት የሚከበረው።
ከአብያተ ክርስቲያናትም ታቦታቱ በጥምቀተ ባህር ለመገኘት ወደ ቦታው ይጓዛሉ፡፡
በተለይ በአዲስ አበባም 11 የሚሆኑት ታቦታት ከየቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በደማቅ አጀብ ጃን ሜዳ ወደ የሚገኘው ባህረ ጥምቀት በማምራት ነው የሚከበረው፡፡
በአርባ አራቱ ታቦት መናኸሪያ በጎንደር ከልጅነት እስከ እውቀት የማውቀው ታላቅ ህዝባዊ በዓል ቢኖር የጥምቀት በዓል ነው . . . የጎንደር አባቶችና እናቶች ባማረ የባህል ልብሶቻቸው ተውበው ደምቀው ጎንደርና ጥምቀትን ያደምቋታል። ጥምቀት ገና ከጥንት ከጠዋቱ የውጭ አገር ጎብኚዎችን ቀልብ ከሚስቡት በዓላት ቀዳሚ መሆኑንም አውቃለሁ ። አባቶች ጥንግ ድርብ እና አልፎ አልፎም ቀደምቱን ያማራ በርኖስ የባህል ልብሳቸውን ለብሰው ጥምቀትን ደምቀው ሲያደምቁት ፣ የቀረው ነዋሪም “ለጥምቀት ያልሆነ ልብስ ይበጣጠስ” ሆነና አቅሙ የፈቀደ አዲስ ልብስ አስገዝቶ ይለብሳል። ያጡ የነጡት ደግሞ ያላቸውን መላብስ አጣጥበውና በወግ በወጉ ጠቅመው በአደባባይ የሚታዩት በጥምቀት ነው፡፡ በጥምቀት የጎንደር ስመ ጥሩ የአርባ አራቱ ታቦት ፣ ሊቃውንት፤ ስመጥር የደብር አለቆችና ካህናት በሚያምረው ልብሰ ተክህኖ አምረውና ደምቀው ይታያሉ . . . በነጭ የባህል ልብሳቸው ላይ ጣል ከሚያደርጉት ጥቁር ካባቸውንና በራሳቸው ጥምጣም የሚታወቁት በጎንደር የቅኔ ፤ የመወድስና የአቋቋም ዝማሬ ሊቃውንት ባማረው አንደበታቸው የውዳሴ መዝሙር ጣዕመ ዜማ፣ ወርብና ሽብሸባውን በአደባባይ የሚያሰሙበት ልዩ አጋጣሚ ቢኖር ይህ የጥምቀት በዓል ነው፡፡
በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን እለት ለማሰብ የሚከበር ነው። በበዓሉ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ምእመናንና የተለያዩ አገራት ጎብኚዎች እንደሚገኙ ተነግሯል።
በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ አልባሳትን በመልበስ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት ምእመናን የተለያዩ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን እያቀረቡ አዳራቸውን ታቦታቱ ባረፉበት ጃን ሜዳ በማድረግ በዓሉን ያደምቁታል።
በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ›› በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡
ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው።
ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደየአመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።
በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድብል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባው… የጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት አንዳንዶችም ‹‹ጥምቀትን ለምን በቅርስነት አላስመዘገባችሁም?›› እያሉ ሠርክ መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከሁለት ዓመት ወዲህ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱም እነሆ ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገብ ቀደም ሲል በግዙፍ ቅርስነት ከተመዘገቡት ከአክሱም፣ ላሊበላ የጎንደሩ ፋሲል ግቢ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የሚከበር የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ መሆኑ፣ እንዲሁም በዓሉ ከ1,500 ዓመታት በላይ በተከታታይ የአገሪቱ ትውልዶችና ሥልጣኔዎች እየተከበረ ያለ ሕያው ቅርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የከተራው በዓል
ከተራ ምንድን ነው? ከሚለው ትርጓሜ እንነሳ … በየዓመቱ የጥምቀት በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡ ከበዓሉ በፊት የከተራ በዓል የሚከበርበትን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ገለጻ ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውሃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውሃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውሃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ፣ ጉድጓድ እየተቆፈረ ውሃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡
ከተራ በዓል በየዓመቱ በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ይውላል ። የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ምእመናን ሲወርድ ሲወራረድ ይዘው በመጡት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት መሰረት በጥምቀት በዓል ዋዜማ ወንዝ ምንጭ ውሃው ይገደባል ፣ ይከተራል። ውሃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው። ይህ በጥምቀት ዋዜማ የሚደረገው ውኃውን መከተርና መገደብ ስርአትም ” ከተራ ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ የማይለወጠውን ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ፤ ካህናተ ሐዲስም ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡ ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ እንደሚያድሩ የሃይማኖት ልሂቃን አባቶች ያስረዳሉ።
የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለማዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን” የሚለውን ዋዜማ ይቆማሉ፡፡ የዋዜማው ቀለም ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይጀመራል ። ከዚያም የዋዜማው ሥርዐት ቅዱስ ተብሎ እስከ ሰላም ያለው ቀለም ይደርሳል፡፡ በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን የሚያነሡት ሰሞነኛ ካህን ከምግበ ሥጋ ተከልክለው ለዕለቱ የሚገባውን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡
በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /ምጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ አዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው ህዝበ ክርስቲያኑ ያጅቧቸዋል። በአማሩ አልባሳት ተውበውም መንገዶች በእልልታ በሆታና በጭፈራ በማድመቅ ታቦቶችን በክብር ወደ ተዘጋጀው የበዓሉ ቦታ አጅበው ይደርሳሉ፡፡ በዓሉም በሆታና በጭፈራ ደምቆ ይውላል፡፡
እስካሁን ዩኔስኮ የመዘገባቸው የኢትዮጵያ ቅርሶች
1.የሚዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር
1.1. የአጼ ፋሲል ግንብ
1.2. የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት
1.3 የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
1.4 የታችኛው የኦሞ ሸለቆ
1.5 የታችኛው አዋሽ ሸለቆ
1.6 የሐረር ጀጎል ግንብና ከተማ
1.7 የኮንሶ ባህላዊ እርከን
1.8 የጢያ ትክል ድንጋይ
2. የማይዳሰሱ ቅርሶች
2.1. የመስቀል በዓል
2.2. የፊቼ ጨምበላላ በዓል
2.3 የገዳ ሥርዓት
2.4 የጥምቀት በዓል አከባበር ናቸው፡፡
(ማጣቀሻዎች፡- የጀርመን ድምጽ፣ ቢቢሲ፣ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች…)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ፍሬው አበበ