የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድ ምቀት እየተከበረ አይደለም። በመላው አገሪቱ ይከበር የነበረው አሁን ግን በአዘጋጆች አካባቢ ብቻ ሆኗል። እንዲያውም በአንድ የመንግሥት ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ለ12ኛ ጊዜ የሚል ተደጋጋሚ ስህተት ሰምቻለሁ። ዘንድሮ የሚከበረው ለ14ኛ ጊዜ ነው። ይሄ የሚያሳየው ይሰጥ የነበረው ትኩረት ስለቀነሰ ለስህተት መዳረጉ ነው። ስህተቱ ደግሞ በቀጥታ ሥርጭት ሳይሆን በቀረጻ (ፕሮዳክሽን) በተሰራ ፕሮግራም ነው።
ቀኑ የሚከበረው ገና የህዳር ወር ሲገባ ጀምሮ ነበር። በትምህርት ቤቶችና በተቋማት ደረጃም ይከበር ነበር።
አሁን ለምን ቀዘቀዘ ብሎ መንግሥትን ለመውቀስም አይመችም። ምክንያቱም ያኔ በድምቀት በሚከበርበት ጊዜም ወቀሳዎች ነበሩ። እንዲያውም አሁን ለምን ቀዘቀዘ ብሎ የወቀሰ የለም። ወደ ፖለቲከኞች ስንሄድ ደግሞ ከነአካቴውም መቅረት አለበት የሚሉም አይጠፉ። ግን ለምን ይሆን?
በቀኑ መከበር ላይ ቅሬታም ድጋፍም አለኝ። ከድጋፉ ልጀምር። አገራችን የበርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ናት። ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያሉ ባህሎች የተለያዩ ናቸው። አንድ ኢትዮጵያዊ እነዚህን የአገሩን ወግና ባህሎች ማወቅ አለበት። ኢትዮጵያ አገራችን የምንል ከሆነ አገር ማለት ደግሞ የተወለድንበት አካባቢ ብቻ አይደለም። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ ወደ ልጅነቴ ልመለስ።
የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ሬዲዮ እከታተል ነበር። ከምማረው መደበኛ ትምህርት ባሻገር የአገሬን ታሪክ፣ ባህልና ወግ የማውቀው በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ነው። በሬዲዮ የምሰማቸውን ዘፈኖች የማን እና በምን ቋንቋ እንደሆነ ሳላውቀው ደስ ይሉኝ ነበር። የዘፋኙን ስም ብይዝ እንኳን በምንኛ ቋንቋ እንደሆነ፣ ያ ቋንቋ የት አካባቢ እንደሚነገር አላውቅም። ህዳር 29 ደርሶ እንዲህ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሚከበርበት ሰሞን ግን ሬዲዮ ላይ ብዙ ሲወራ እሰማለሁ። በፊት በድምጽና በስም ብቻ የማውቀው ዘፋኝ ሙሉ ታሪኩ ይዘረዘራል። ቋንቋው ምንኛ እንደሆነ አውቃለሁ። ያ የምወደው ዘፈን አገሬ ውስጥ ያለ መሆኑን አወቅኩ ማለት ነው።
ቴሌቪዥን ማየት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የተለያዩ አይነት ባህሎችንና አለባበሶችን አያለሁ። አመጋገቦችንና የሥራ ባህሎችን አያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛው አካባቢ እንደሚገኙ ማወቅ እፈልጋለሁ። እንዲህ በህዳር 29 ሰሞን በሰፊው ሲወራ ስለምከታተል አወቅኳቸው ማለት ነው።
የመማሪያ መጽሐፍ ላይ የአገሬን ታሪካዊ ቅርሶች መገኛ አነባለሁ። ያ አካባቢ ግን የት እንደሆነ አላውቅም። የብሄር ብሄረሰቦች ፕሮግራም በሚሰራበት ሰሞን ግን በሰፊው ሲብራራ አያለሁ። ስለዚያ ክልል ምንነት፣ ታሪክ፣ ባህልና ወግ አውቅበታለሁ። በጥቅሉ አገሬን አውቅበታለሁ ማለት ነው። በልጅነት አዕምሯችን ደግሞ ከፉ ደጉን ስለማንለይ ለማወቅ ብቻ ነው የምንከታተለው።
ታዲያ እንዲህ ከሆነ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበር ለምን ሁሉንም አላስደሰተም? አገርን ማሳወቅ ከሆነ ለምን በጉጉት የምንጠብቀው ቀን አልሆነም?
አከባበሩን ተወዳጅ እንዳይሆን ያደረገው ራሱ መንግሥት ነው። ከታች እስከ ላይ ያሉ ባለሥልጣናት መድረክ ላይና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩት ነገር አገርን ማሳወቅ ሳይሆን የሥልጣን ማቆያ ነው። ለምሳሌ አንዱ የሚያስወቅሳቸው ነገር የአሁኑን ለማድነቅ ያለፈውን ማውገዝ ነው። አገሪቱ የብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤት እንደነበረች ይናገራሉ። ታፍናችሁ፣ ተረግጣችሁ፣ ተቆርጣችሁ፣ ተፈልጣችሁ… የሚሉ ቃላት ይበዛሉ። በፊት የነበረው የመደብ ትግል ነበር፤ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ግን ብሄር እየተለየ ጥቃት የደረሰ ይመስል ደጋግመው የሚናገሩት ‹‹ታፍናችሁ ተረግጣችሁ›› የሚል ነው። ይሄ ደግሞ እንኳን ታሪክ ለሚያነቡ ፖለቲከኞች ለማንም ደስ አይልም።
ከዚህ ባስ ሲል ደግሞ ወደ አንድ ብሄር የማጠጋጋት ዝንባሌም ነበር። ከኢህአዴግ በፊት የነበረው ሥርዓት ማንንም ብሄር ለይቶ እንዳልጠቀመ እየታወቀ የእነ እገሌ የበላይነት ይባል ነበር። እገሌ እገሌን ጨቁኗል ይባል ነበር። ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ እኔ ነኝ መብት የሰጠኋችሁ ለማለት ስለሚፈልግ ነው። ብሄር ብሄረሰቦች ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የተፈጠሩ ይመስል ከዚያ በፊት የሌሉ አስመስለው።
እንዲህ አይነት የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ በዓሉን አገርን ከማሳወቅ ይልቅ ፖለቲካ አደረገው። ፖለቲካዊ እንድምታ እንዲኖረው መደረጉ ደግሞ ወጣቶችና ታዳጊዎች እንዲጠሉት እንጂ እንዲወዱት አያደርግም። አንድን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ‹‹ይሄ የእገሌ አካባቢ ነው፣ ይሄ ቋንቋ እንዲህ ይባላል›› እያሉ ማሳወቅ ነው የሚሻል ወይስ እገሌ የሚባል ሰው (ብሄር) ሲረግጠው፣ ሲቆርጠው፣ ሲፈልጠው የኖረ የእገሌ ቋንቋና ባህል ነው ማለት ነው የሚሻለው?
አከባበሩ ሌላም ችግር አለበት። ጉዳዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ማስተዋወቅ፣ እርስ በርስ የባህልና ወግ ለውውጥ ከሆነ ማቅረብ ያለባቸው ራሳቸው የባህሉ ባለቤቶች ናቸው መከወን ያለባቸው። ብዙ ጊዜ የምንታዘበው ግን እንደዚህ አይደለም። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር አብዛኛውን በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት፤ አንዳንዱን ደግሞ ራሴው ታዳሚ ሆኜ ተከታትያለሁ። ትርዒት የሚያሳዩት ሰዎች አማተር የኪነ ጥበብ ሰዎች ናቸው። መቀሌ ላይ አቅርበው የነበሩት ናቸው በዓመቱ ሀዋሳ ወይም ጅግጅጋ የሚሄዱት። ባህርዳር ላይ የቀረበው ትርዒት ነው አሶሳ ወይም ጋምቤላ ወይም ሰመራ የሚቀርበው። ሰዎቹም ተመሳሳይ ናቸው። ይሄ ደግሞ ባህል ሳይሆን ተውኔት ነው። ተቀርፆ የተቀመጠ ድራማ ወይም ፊልም ማለት ነው። ባህል ከሆነ ግን ቀጥታ ራሳቸው የባህሉ ባለቤቶች ሲያቀርቡት ነው የሚያምረው። የሐመርን ባህል ለማሳየት ጎንደር ወይም መቀሌ ተወልዶ ያደገ የቴአትር ተማሪ ካቀረበው ይሄ ተውኔት ነው። ቀለም እየተቀቡ የዚያን አካባቢ ባህል በገጸ ባህሪ ከማላበስ ሕይወቱን የሚኖሩት ራሳቸው ባለቤቶች መሆን አለበት። ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች ቀን›› ከተባለ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን የሚያሳዩበት እንጂ ተዋናይ የሚተውንበት መሆን የለበትም። እንዲያ ከሆነ ከሲኒማ ቤት በምን ይለያል?
ይሄውም ትወናው እኮ ደግሞ በሥነ ሥርዓት ቢታይ ጥሩ ነበር። በዕለቱ አብዛኛውን ሰዓት የሚይዘው የባለሥልጣናቱ የፖለቲካ ዲስኩር ነው። ለባህል ትርዒት የተሰጠው ትንሽ ሰዓት ነው። መድረክ መሪው ‹‹አሁን የእገሌ ብሄር ያልፋል›› ይላል እየተደበላለቁ ያልፋሉ። የቱ የየትኛው እንደሆነ አይታወቅም። ምናልባት ከዚህ በፊት ስለምናውቀው ምንም አይመስለን ይሆናል፤ ለይቶ ለማያውቃቸው ግን የትኛው እንደሆነ አይብራራም።
በጽንፈኛ ፖለቲከኞች ዘንድ ደግሞ ሌላ መሰናክል አለ። እዚህ ጋ ‹‹መንግስት ወጣቱ ታሪክና ባህሉን እንዲያውቅ አላደረገም›› የሚል ወቀሳ አለ። መንግሥት መድረክ ሲፈጥር ደግሞ እነርሱም የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ ይነዛሉ። በዚህ መሃል ወጣቱ ወዴት ይሂድ? የማንን ይስማ? ወይስ አገሩን ማወቁን ይተወው?
የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የፖለቲከኞች ሳይሆን የህዝብ መሆን አለበት። ልጆችና ወጣቶች አገራቸውን የሚያውቁበት መሆን አለበት። በዓመት አንድ ቀን መድረክ ተዘጋጅቶ የአገሪቱ ብሄሮች ቢገናኙና የባህል ትርዒት ቢያሳዩ ምን ችግር አለው? ይሄ አገርን ማወቅና ማሳወቅ እንጂ ምንም ችግር አይኖረውም። ችግሩ ግን ያው የአከባበሩ ነገር ነው። ስለዚህ መንግሥትም ሆነ የመንግሥት ተቀናቃኞች ፖለቲካዊ አጀንዳችሁን ብትተውና ቀኑ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቢሆን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
ዋለልኝ አየለ