ነገሮችን የማራዘም ልማድና መፍትሄው

ትላልቅ የሚባል ሕልሞች አሏችሁ፤ ለወደፊት የምታስቡት ሂወት በጣም ውብ የሚባል ሂወት ነው:: በሂወት ዘመናችሁ ስኬታማ ሆኗችሁ የሕልም ሂወታችሁን መኖር ትፈልጋላችሁ:: ነገር ግን እዚህ ጋር አንድ ችግር ያጋጥማችኋል፤ ሰነፍ ናችሁ:: ማድረግ የሚገባችሁ ነገር እያንዳንዱን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ:: ነገር ግን እነዛን ነገር እያደረጋችሁ አይደለም:: ሕሊናችሁ እናንተን እየወቀሳችሁ ይሄዳል፤ የጥፋተኝነት ስሜትም እየተሰማችሁም ያልፋል:: ምክንያቱም ደግሞ ከዛ በላይ እንደሆናችሁ ስለምታውቁት ነው:: አሁን ላይ ከምትሠሩት በላይ መሥራት እንደምትችሉም ውስጣችሁ ያምናል:: በአጠቃላይ በቂ የሚባል ነገር እያደረጋችሁ እንዳልሆነ ውስጣችሁ ይነግራችኋል:: ይህ የጥፋተኝነት ስሜት ቀናቶችን፣ ሳምንታትን እንዲሁም ወራቶችን እያለ ዓመታት በማስቆጠር እናንተ ምንም መሥራት እንደማትችሉ እራሳችሁ እንድታምኑ ያደርጋችኋል::

እነዚህ ነገሮች ውስጣችሁ ስንፍናችሁን እንድትቀበሉ ያደርጋችኋል:: ከዛም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በዚህ አመትማ እለወጣለው ብላችሁ አዲስ ግብ ታስቀምጣላችሁ:: የመጀመሪያውን ጥቂት ሳምንታቶች እናንተ ከጠበቃችሁት በላይ ልትሠሩ ትችላላችሁ:: ሞራል አለ መነሳሳታችሁም እንዳለ ነው፤ አነቃቂ ንግግር ታዳምጣላችሁ ከዛም ትንሽ ሕልም የምትመስል ነገር ውስጥ ትገባላችሁ:: ከትንሽ ቀናት በኋላ ቀድሞ የነበራችሁበት ነገር ይመጣና ሶፋችሁ ላይ እራሳችሁን ታገኙታላችሁ:: ስልካችሁን ስትነካኩ አለበለዚም ቀኑን ሙሉ ፊልም ስትመለከቱ ትውላላችሁ:: ይህ ሁኔታ ነገሮችን የማራዘም ልማድ (ፕሮካስትኔሽን) በመባል ይጠራል:: ይህ አንድን ነገር ቆይ በኋላ ወይም ነገ አደርገዋለው ማለት ነው:: ይህ ነገሮችን የማራዘም ልማድ ነው::

የእናንተ ምርጥ ጓደኛ ምትሉት ሰው ከናንተ ጋር ብዙ ዓመታትን ስለቆየ ሁሌም ቤታችሁ ሳይጠራ ይመጣል:: እናንተ ሂወታችሁን ለመቀየር ተነሳስታችሁ እነዚህን ነገሮች በቀን ውስጥ እጨርሳለው ስትሉ ይህ ምርጥ የምትሉት ጓደኛችሁ ከየት መጣ ሳይባል ብቅ ይላል:: ከዛም ነገ አደርገዋለው ብላችሁ የጀመራሁትን ሥራ ትተዋላችሁ:: ነገሮችን የማራዘም ልምድ እየበዛ ሲመጣ እናንተም ነገሮችን ከመሥራት እየተቆጠባችሁ ለዚህ ልማዳችሁ እየተገዛችሁ ትሄዳላችሁ:: በዚህም እራሳችሁን እንደ ሰነፍ ሰው እየተመለከታችሁ ትመጣላችሁ:: በዚህ ጊዜ እራስን እንደ ሰነፍ መቀበል ይመጣል ማለት ነው:: ከዛም ማንነታችሁ አድርጋችሁ ወደ መኖር ትሸጋገራላችሁ::

ነገሮችን የማራዘም ልማዳችሁ መጨረሻው ስንፍና ቢሆንም ነገሮችን የማራዘም ምክንያታችሁ ግን ስንፍና ሊሆን አይችልም:: ስንፍና የመጨረሻው ውጤት እንጂ ምክንያት አይሆንም ማለት ነው:: ስለዚህ አንድን ሰው ሄዳችሁ ለምንድነው ነገሮችን የምታራዝመው፣ ለምንድነው አሁን ሰርተህ መጨረስ እየቻልክ ወደ በኋላ የምታራዝመው ብትሉት ሰነፍ ነኝ፣ ሰዓቴን በትክክል ስለማልጠቀም ነው አለበለዚ ሁሉም ነገር ፍፁም እንዲሆን ስለምፈልግ ነው ብሎ ሊመልስ ችሏል:: እውነታውን ከተመለከትነው ሶስቱም እንደምክንያት ሊቀመጡ አይችሉም::

ነገሮችን የማራዘም ልማድ ስንመለከት እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚቀመጠው እራስን ከመጠበቅ ጋር ይያያዛል:: ብዙ ጊዜ አዕምሯችን ከሆነ አደጋ ብሎ ከሚያስበው ነገር ጥበቃ ያደርግላችኋል:: ይህ ምን ማለት ነው ካልን አዕምሯችን ውስጥ የሚገኝ አሜግዶላ የተባለ አንድ ክፍል አለ:: ይህ የአዕምሯችን ክፍል ለፋይት፣ ለፍራይት እና ለፍሪዝ ኃላፊነት የሚወስድ ነው:: አሁን እዚህ ጋር ፕሮካስትኔሽን ትልቁ ችግር እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን:: ታድያ ችግራችን ምን ሊሆን ይችላል ብለን ስንመለከት ብዙ ማሰብና መጨነቅ የሚፈጥረው ነገር ነው:: ማንኛውንም ነገር ከማድረጋችሁ በፊት ያነገር ይዞባችሁ የሚመጣ መዘዝ ካለ አዕምሯችሁ እናንተን የሚያስጠነቅቅበት መንገዱ ነው ማለት ነው::

ለምሳሌ ሰዎችን እንቢ ይሉኛል (ፊር ኦፍ ሪጀክሽን) ብላችሁ የምትፈሩበት ሁኔታ ካለ አለበለዚያ ይሄንን ካደረኩ ልወድቅ እችላለው ብላችሁ ካሰባችሁ እንዲሁም ላይሳካልኝ ይችላል ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ነገሮችን ለማድረግ ከዛሬ ነገ እያላችሁ እንድታልፉ ወደ ማድረጉ ትሄዳላችሁ:: አዕምሯችሁ ውስጥ አለ ያልኳችሁ ክፍል ይህን እንድታስቡ በማድረግ እናንተን ከጉዳት እየጠበቀ ስለሚሄድ እናንተን ከዛ ተግባር እየቆጠባችሁ እና እያራቃችሁ ትሄዳላችሁ::

የዩቲዩብ ቻናል መጀመር የሚፈልግ በጣም ብዙ ሰው አለ፤ በተለይ ደግሞ ፊታቸውን እያሳዩ:: ነገር ግን አብዛኛው ሰው ዩቲዩብ የማይጀምርበት በጣም ትልቁ ነገር ሰው ምን ይለኛል፣ ይሄ ነገር አይሳካልኝም፣ ምንም የማወራው ነገር የለም እና የምጠቅመው ነገር የለም ብሎ ማሰቡ ነው:: እነዚህ ነገር የአሁን ሁኔታ ላይ ያሉ ነገሮች ናቸው:: ምንም እንኳን ኔጌቲቭም ፖዘቲቭም ቢሆኑ አዕምሯችንን የሚያስጨንቁ ናቸው:: ታድያ እነዚህ ሀሳቦች ከየት መጡ ካላችሁ አሜግዱላ የተባለው ክፍል እናንተን ለመጠበቅ የሚያመነጨው ሀሳብ በመሆኑ ነው:: ንቃተ ሕሊናችሁ ሳያውቀው ድብቁ ሕሊናችሁ እንድታስቡት የሚያደርገው ነገሮች ናቸው::

ስለዚህ እነዛን ተግባራት ከማድረግ የምትቆጠቡት በዚህ ምክንያት ነው:: ይህ ሁኔታ ከስንፍና ጋር የሚገናኝ አይደለም:: ለዚህ ነው ስንፍና እንደ ምክንያት ሊሆን የማይችለው:: ምንአልባት መጨረሻው መገኛ ነጥብ ሊሆን ይችላል:: ይህን ነገር እንዴት መቅረፍ እንችላለን ብለን ወደ መመልከቱ እንግባ::

ወደዚህ ከመግባታችን በፊት አንድ ጥያቄ ላቅርብ፤ የሙቀት ተቃራኒ ምንድነው ቅዝቃዜ አደል የቅዝቃዜ ተቃራኒ ምንድነው ተብላችሁ ብትጠየቁ ሙቀት ነው ብላችሁ ትመልሳላችሁ:: ታድያ እዚህ ጋር አንድ ነገር ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ ሙቀት የተባለው መቼ ነው ቀዘቀዘ የሚባለው የትኛው ዲግሪ ላይ ሲደርስ ነው 37 በመቶ ወይም እስከ 50 ባለው ብላችሁ እርግጡን መልስ መስጠት አትችሉም:: ይሄ በአንድ ስኬል ላይ ያለ ነገር ነው ይሄም ቴምፕሬቸር ይባላል::

ይህን ሁኔታ ወደ ስሜት እናምጣው ለጭንቀትና ለፍርሃት ተቃራኒ የምንላቸው ምንድናቸው:: ለነዚህ ስሜት ተቃራኒ የሆነው ጉጉት የምንለው ነገር አለ:: አሁንም እነዚህ ስሜቶች ማለትም ጉጉትና ፍርሃት እና ጉጉትና ጭንቀት አንድ አይነት ስሜት ናቸው ነገር ግን በተለያየ መንገድ ነው የተቀመጡት:: ለምሳሌ ወፍራም ሰው ብትሆኑ ስፖርት ለመሥራት ወደ ጂም እየሄዳችሁ ሁለት አይነት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል:: አንደኛው ከፍርሃት የተነሳ ምቾት የሚሰጣችሁ ስሜት ውስጣችሁ አይፈጠርም:: እያንዳንዱ ቀን ለናንተ አስጨናቂ እየሆነባችሁ ይሄዳል:: በተቃራኒው ደግሞ ጉጉት ሊሰማችሁ ይችላል:: ሰውነቴን ከቀየርኩት በኋላ እንዲ አይነት ሰው ልሆን እችላለው ብላችሁ ተነስታችሁ ስፖርት ቤት ልትሄዱ ትችላላችሁ:: አንድ አይነት ሥራ ነው ምንም የተለያየ ነገር የለም:: ነገር ግን በአንድ በኩል ስትመለከቱ ፍርሃት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጉጉትን በውስጣችሁ ይኖራል::

ጭንቀት ማለት ምን ማለት ነው? ጭንቀት ማለት ወደፊት የሚፈጠሩ አሉታዊ ነገሮችን ገና ካሁኑ ማሰብ ነው:: ለምሳሌ ፍቅረኛ የመያዝ ሀሳብ ካላችሁ ደሞ ፍቅር ከያዘኝ ጥላኝ ብትሄድስ/ቢሄድስ ወይም ሌላ ቢደርብብኝ/ብትደርብብኝ ትችላለች/ይችላል የሚሉ ነገሮች ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ:: ስለዚህ አሜግዱላ የተባለው የአዕምሯችን ክፍል እናንተን ከነዚህ ሀሳቦች ለመጠበቅ እናንተ ወጥታችሁ ሰው እንዳትተዋወቁ ሊደርጋችሁ ይችላል:: አዲስ ሰው ብታገኙ ምንም አይነት ሀሳብ አይኖራችሁም ማለት ነው:: ከዛ ሰው መራቅ ብቻ ነው የምትፈልጉት::

በሌላ መልኩ ደግሞ ጉጉትን እናገኘዋለን:: ጉጉት የሚባለው ወደፊት በሚፈጠር በጎ ነገሮችን አሁን ላይ ሆኖ የመመልከት ችሎታ ነው:: እዚህ ስሜት ላይ መቆየት ከቻላችሁ ተነሳሽነታችሁ መቼም የሚጠፋ አይደለም:: ሁሌም ውስጣችሁ ተነቃቅቶ መንቀሳቀስ ትችላላችሁ:: የምታደርጉትም ነገር በፍቅር መሥራት ትችላላችሁ ማለት ነው::

ታድያ መፍትሄዎቹ ምንድናቸው ብላችሁ ካሰባችሁ በአንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ የፎቶግራፍ አስተማሪ ብዙ ተማሪዎች ነበሩት፤ ተማሪዎቹን ለሁለት ቡድን ይከፍላቸዋል:: አንደኛውን ቡድን ብዛት ላይ ትኩረት አድርገው ፎቶ እንዲያነሱ ብቻ ይነግራቸዋል:: ሁለተኛውን ቡድን ደግሞ ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው ፎቶ እንዲነሱ ያዛቸዋል:: ሁለቱም ቡድኖች በታዘዙት መንገድ ፎቶ አንስተው ማምጣት ይጠበቅባቸዋል:: ውጤትም የሚሰጣቸው በነዚህ ሁለት ነገር ላይ ነው:: በዚህም የመጀመሪያው ቡድን መቶ ፎቶግራፍ በማንሳት ለመምህሩ ያስረክባሉ:: እንዳመጡት ፎቶፍራፍ ብዛትም ውጤት ይሰጣቸዋል:: ሌላኛው ቡድን ግን ምንም ያክል ፎቶ ቢያነሱ ችግር የለውም ነገር ግን ምርጥ ሚሉትን ፎቶግራፍ ይዘው ሲመጡ ማርክ ይሰጣቸዋል:: ታድያ በሴሚስተሩ መጨረሻ የትኛው ቡድን ምርጥ ሊባል ይችላል?

በሴሚስተሩ መጨረሻ ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ጥራት ላይ የሰሩት ሳይሆን ብዛት ላይ ያተኮሩት ናቸው:: ጥራት ላይ ያተኮሩት ቡድኖች ብዙ ጫና ነበረባቸው:: የሚያስረክቡት አንድ ፎቶ በጣም የተዋጣለት መሆን ስላለበት ነው:: ፎቶ ከተነሳበት አንግል እና የጥራት ደረጃ ታይቶ ነበር ማርክ የተሰጠው:: የመጀመሪያው ቡድን ግን ምንም አይነት ጫና አልነበረባቸውም:: የፎቶግራፍ ተማሪዎች እንደመሆናቸው ፎቶ ማንሳት እንደሚወዱ ግልፅ ነው:: ስለዚህ ብዙ ፎቶ አንስታችሁ ነው አምጡ የተባሉት የዛ ፎቶ ጥራት የማይመረመር ከሆነ ምን ያክል አስደሳችና አዝናኝ እንደሆነ አስቡት:: ያንን ሁሉ ሴሚስተር ሲዝናኑ ነበር የከረሙት ታድያ ሥራቸው ሲገመገም አሪፍ የተባለ ፎቶ የተገኘው በብዛት ካነሱት ውስጥ ነው::

ጥራት ብዙ ጊዜ የሚገኘው ከብዛት ውስጥ ሊሆን ይችላል:: አንድ ነገር ብዙ ጊዜ እየተደጋገመ ሲመጣ ጥራቱም እያደገ ምርጥ የሚባል ደረጀ ላይ ሊደርስ ይችላል:: ይህ ነገሮችን ከማራዘም ጋር በምን ይገናኛል ካላችሁ አንድን ነገር ለመጀመር ካሰባችሁ ፍጹም ለመሆን አትሞክሩ ወይም ደግሞ ጥራቱ ላይ አታተኩሩ:: መሥራት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጉ ያነገር ምንም አይነት ጥሩ ነገር ሆኖ እናንተን ብቻ የሚያስደስት ብቻ ይሁን:: በብዛት እያደረጋችሁ ብቻ እለፉ ከዛም በኋላ የምትፈልጉት ጥራት እየመጣ ወይም እያሻሻላችሁ ትመጣላችሁ:: ጅማሪያችሁ ላይ ፍጹም መሆን አይገባችሁም::

ነገሮችን እራሳችሁ ላይ እያከበዳችሁ በመጣችሁ ቁጥር ያንን ነገር ለመጀመር እድላችሁ የበለጠ እየጠበበ ነው የሚመጣው ምክንቱም ይሄንን ነገር እስካመጣ ቆይ ትንሽ ልጠብቅ ትላላችሁ:: ለዚህ ነው የሰው ልጅ ሥራዎችን ለነገ የማስቀመጥ ልማድ ያዳበረው:: ለምሳሌ ቲክቶክ ለመጀመር የሚፈልግ ሰው ውድ የሚባል ካሜራና ላፕቶፕ መግዛትን ይፈልጋል:: ይሄ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚቻል አይደለም:: ሁሉም ሰው ባለው ጀምሮ ከዛ እያሻሻለ ይሄዳል:: እረጅም ርቀት ለመጓዝና ከስንፍና ለመላቀቅ ከበስተጀርባ ያለውን ምክንያት ማወቅ ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ተብሎ የሚጠቀሰው ፍርሃት ነው:: ፍርሃትን በማስወገድ ነገሮችን ማስተካከል ይቻላል::

ነገሮችን ለመቀየር ቅድሚያ ቀላል የሚባሉ ግቦችን ማስቀመጥ ይገባል:: በአጀማመር ላይ ከፍተኛ ግብ ማስቀመጥ መዳከምን ሊፈጥር ስለሚችል ሥራው ይቅርብኝ ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል:: ስለዚህ ሥራዎችን ቀላል አድርጎ መጀመር እንደመፍትሄ ይቀመጣል ማለት ነው:: ሌላው ደግሞ ማድረግ የማትፈልጉትን ነገር ለሁለት ደቂቃ ብቻ ላድርገው ብላችሁ ለራሳችሁ ንገሩት ከዛም ከሁለት ደቂቃ በኋላ ነገርየውን አቁሙት:: ለምሳሌ ዛሬ እስቲ መኝታ ክፍሌን ላፅዳ ብላችሁ ተነስታችሁ አይ ይቅርብኝ ከምትሉ ኤርፎን አንስታችሁ አንድ ዘፈን ክፈቱ ሙዚቃው እስኪያልቅ ክፍላችሁን ማፅዳት ጀምሩ::

ሙዚቃው ካለቀ በኋላ ማፅዳቱን አቁሙ፤ በጣም በሚገርም ሁኔታ ሌላ ሙዚቃ ከፍታችሁ ክፍላችሁን ማፅዳታችን ትቀጥላላችሁ:: ይሄ ደግሞ ለማሳካት ያስቀመጣችሁት ግብ ትንሽ በመሆኑ ይሳካል ማለት ነው:: አንድ ነገር መሥራት ስትጀምሩ በዛው ትቀጥላላችሁ:: በዚህ መንገድ ስንፍናችሁንና ነገሮችን የማራዘም ልማዳችሁን ማስቀረት ትችላላችሁ ማለት ነው::

በመርድ ክፍሉ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You