
የዛሬው ወቅታዊ እንግዳችን የውሃ መሃንዲሱ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ናቸው:: በውሃ ምሕንድስና አማካሪነት በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ28 ዓመታት አገልግለዋል:: በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል በመሆን ሰርተዋል:: “የመግባባት ዴሞክራሲ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመዋል:: ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ምክር ቤት አባላት መካከልም አንዱ ናቸው:: ከፕሮፌሰሩ ጋር ባደረግነው ቆይታ በመስከረም ወር የሚመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለፈባቸውን አጠቃላይ ሁኔታዎች እና ሀገራዊ ምክክርን የተመለከቱ ጉዳዮችን ዳስሰናል::
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ተሳትፎ እንዴት ይገልጹታል ?
ፕ/ር አድማሱ፡– ይሄ ግድብ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግድብ ነው:: እንደዚህ አይነት ግድብ ላይ የሃይድሮ ፖለቲክስ እና የዲፕሎማሲ ጉዳይ እንቅፋት ሊሆን ወይም ደግሞ በተገላቢጦሹ ነገሮች የተሳኩ ሊሆኑ ይችላል:: ግብጽና ሱዳን ግድቡ እንዲሠራ አልፈለጉም:: በእኛ በኩል ደግሞ ቁርጠኝነቱ ነበረ:: ይሄን ቁርጠኝነት ደግሞ ከመንግሥት አልፎ ጉዳዩ በሕዝብ እጅ ገብቶ ሕዝቡ የሚችለውን ያህል ተረባርቦ እዚህ ደርሷል::
ትላልቅ ግድቦች በየትም ሀገር፣ ሀብታም በሚባሉትም ጭምር የሚሠሩት በብድር ነው:: ምክንያቱም አንድን ትልቅ ግድብ ሊሠራ የሚችል ገንዘብ በእጁ ያለው መንግሥት አይገኝም:: ግድቡ እስከ ሁለት መቶ ዓመታት ሊደርስ የሚችል የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አለው:: ለብዙ ትውልዶች የሚያገለግል ነው:: ለትውልዶች የሚያገለግልን ግድብ በጥቂት የምርጫ ዓመታት የሚኖር መንግሥት ሠርቶ አያጠናቅቀውም:: ስለዚህ በሀገር ስም ተበድረው በረጅም ጊዜ በሚከፈል ብድር ነው የሚገነቡት:: እኛ እንዲህ ያለ የብድር አገልግሎት ለማግኘትም አልቻልንም:: ምክንያቱም እባካችሁ አታበድሩብን እኛን ይጎዳናል እያሉ በሚወተውቱት ግብጾች ምክንያት ብድር ማግኘት ሳንችል ቀርተናል:: ይሄ ሁኔታ ባለበት ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተረባርቦ ግድቡን የገነባው:: በእውነት በኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ኮርቻለሁ::
አዲስ ዘመን፡- እንደ ውሃ ምሕንድስና ምሁር በግድቡ ግንባታ ሂደት እንዴት ያለ ልምድ ተገኝቷል ?
ፕ/ር አድማሱ፡- ግድቡ በዓለማችን ውስጥ ካሉት በጣም ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው:: በአፍሪካ ደረጃም ሆነ በመሰል ሀገሮች በሕዳሴ ግድብ ደረጃ ያለ ፕሮጀክት ተሠርቶ አያውቅም:: ተሳትፎ አድርገው እዚህ ያደረሱንን ሁሉ በጣም ላመሰግን እወዳለሁ:: ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ርብርብ አደንቃለሁ::
ግድቡ በቴክኒክ ረገድ በጣም ከባድ የሚባል ውስብስብ ፕሮጀክት ነው:: በግንባታ ሂደቱ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች ተሳትፈውበታል:: በግንባታው ሂደት ከተገኙት ትልቁና አንደኛው ጥቅም ኢትዮጵያውያን መሰል ግድቦችን በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበትን እውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ያካተተ ልምድ ማካበታችን ነው:: ስለዚህም በሂደቱ ሌላ ተመሳሳይ ፕሮጀክት ለማጥናት፣ ለመገንባትና ለማስተዳደር የሚችል የሰው ኃይል ተፈጥሯል:: ይህ ልምድ ተጨማሪ ግድቦችን ከመገንባት ባለፈ ግድቡ በሚገባ እንዲያዝና አገልግሎቱ የሚጠበቀውን ያህል እንዲሆን የሚያግዝ የሰው ኃይል አልምቷል:: እነዚህ ሁሉ በጣም ጠቃሚ ውጤቶች ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቀቀ ማለት በጨለማው ውስጥ የሚኖረው ሕዝባችን በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያገኛል ማለት አይደለም ሲባል ይሰማል:: ምን ማለት ነው?
ፕ/ር አድማሱ፡- ግድቡ እንዳለቀ ሁሉም አካባቢ የሚፈልገውን የኃይል መጠን በአንድ ጊዜ ማግኘት አይችልም:: ከግድቡ የሚገኘው ኃይል መሰራጨትና ወደ ተጠቃሚው መቅረብ መቻል አለበት:: ይሄን ለማድረግ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታዎችና በየቦታው የሚያስፈልጉ ጣቢያዎች መደራጀት አለባቸው:: በዚህ ረገድ ጠንክረን በመሥራት እስካሁን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ያላገኙ ወገኖች ሁሉ እንዲደርሳቸው ማድረግ ይጠበቅብናል:: ዋናው ነገር ግን ግድቡ እውን በመሆኑ ምክንያት የኃይል አቅርቦትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ተችሏል:: ይሄን ኃይል በአራቱም የሀገራችን አቅጣጫዎች፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በሚፈለገው ቦታ ሁሉ ለማዳረስ ርብርቡ መቀጠል አለበት::
በሀገር ውስጥ እንዳለ ሆኖ ለአጎራባች ሀገሮች ለሶማሌ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ ሊቀርብ የሚችልና ያንንም ሰበብ አድርጎ ሀገራቱ በኢኮኖሚው መስክ ተሳስረው በጋራ የተሻለ ውጤት እንዲፈጥሩ የሚያደርግ ነው:: በአጠቃላይ ግድቡ ለበርካታ ችግሮቻችን መፍትሔ የሚሆን ትልቅ ቅመም ነው::
አዲስ ዘመን፡- በውሃ ዲፕሎማሲ እንደ ሀገር ያለን ልምድ ምን ይመስላል ?
ፕ/ር አድማሱ፡- ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ከውሃ ጋር የተያያዘ ጠንካራ ዲፕሎማሲ አላት ብዬ አላምንም:: ነገር ግን ይኼንን ሥራዬ ብሎ ማጎልበት ይቻላል:: የውሃ ሀብትን የተመለከተ ዲፕሎማሲው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ የታቀፉ ሹሞችን ብቻ የሚመለከት አይደለም:: እያንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ታጥቆ መነሳት አለበት:: ሕዝባዊ መልክ መያዝ ይኖርበታል::
ዲፕሎማሲው ደካማ ነው ስል በአንድ መንግሥት መሥሪያ ቤት የሚደረገውን ጥረት ማለቴ አይደለም:: እኔ ትኩረት የምሰጠውና ድክመት አለብን የምለው በሕዝባዊው እንቅስቃሴ ረገድ ነው:: ያ ማለት ዝም ብሎ መጯጯሁ አይደለም:: ሰዎች ተጨባጭ መረጃዎችን ይዘው በውሃው መስክ አዋጭ የሆኑ የመከራከሪያ፣ የመወያያ እና ማሳመኛ ጉዳዮችን ሁሉ ለይተው፣ ያላቸውን ግንኙነት በመጠቀም በበጎም ሆነ በመጥፎ መንገድ ተጽዕኖ ማሳደር ለሚችሉ ወገኖች የሀገራቸውን እውነታ ለማስረዳት መንቀሳቀስ አለባቸው:: ይህን የመሰለው ጥረት እንኳን እምብዛም በሌለበት ነው ግድቡን ከጫፍ ማድረስ የቻልነው::
ዓለም አቀፋዊ ወንዞችን በተመለከተ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በዚህ ብቻ የሚቋጭ አይደለም:: በሌሎች ተፋሰሶችም በራሱ በዓባይ ወንዝም ገና ወደፊት ልናደርጋቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ:: እነዚያን ሁሉ እውን ለማድረግ ትልቁ ነገር ሥርዓት ባለው መንገድ ተጨባጭ እውነታን የያዘ መልዕክት በመለዋወጥ ዲፕሎማሲያዊ ትግልን ማፋፋም ነው::
እንደ ግብጾች ዝም ብሎ ያልተጨበጠና ያልተያያዘ ወይም ተገቢ ያልሆነ አካሄድን መምረጥ የለብንም:: ለምሳሌ ግብጾች ከሚከተሉት ተገቢ ያልሆነ መንገድ አንዱ እ.አ.አ. በ1959 ሱዳንና ግብጽ ስምምነት ብለው ያሰፈሩትን ኢፍትሃዊ ውል በወቅቱ ባልተሳተፈችው ዋነኛዋ የተፋሰሱ ሀገር ኢትዮጵያ ላይ በግድ ለመጫን የሚያደርጉት ጥረት ነው:: ግብጽና ሱዳን ይህን የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ደጋግመው የሚጠቅሱት ኢትዮጵያ ደከም ካለች ተጠቃሚ እንሆናለን ከበረታችም ደግሞ እንግዲህ እኛ ሞክረናል በሚል እምነት እንጂ ነገሩ ያዋጣናል ብለው አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ 12 ጊዜ የግድቡን ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ወስዳ ነበር:: ኢትዮጵያ ያደረገችውን ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ እንዴት ይገልጹታል?
ፕ/ር አድማሱ፡- ሁሉም ሀገር ለራሱ ጥቅም ሲል ትክክለኛ ያልሆነ መረጃና ማስረጃ በማቅረብ ጭምር ይታገላል:: አንዳንዱ ሀቅ ላይ የተመሰረተ ሌላው ደግሞ ፈጠራ ሊሆን ይችላል:: አንዳንድ ሀገሮች ደግሞ የውስጣቸውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በሚፈልጉት መንገድ ለመግፋት የግድ የውጭ ጠላት መፍጠር አለባቸው:: ስለዚህ መጣብህ እንዲህ ያለ አደጋ ተደቀነብህ በማለት የእነሱን የተነቃነቀ የሥልጣን ኮርቻ አስተማማኝ ለማድረግ የሚታገሉ አሉ:: ይህ በብዙ ሀገርም የሚደረግ ነው:: በውስጥ ጣጣ ሲበረክት ጠላት መፍጠር የተለመደ ነው:: ግብጾች ይህን ማድረጋቸውን መደረግ የሌለበት ነው ልል አልችልም፤ በተለያዩ ሀገራት ለተለያየ ነገር ሲደረግ የኖረ ነው:: ሰው ሀገር ሁሉ ሄደው ጦርነት የሚለኩሱ ሃያላን ሀገሮች አሉ::
ወደ ሃያላን ሀገራት እና ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት ሄደው አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በቁርጠኝነት ጉዳዩን ስለያዙት የትም ሊደርሱ አልቻሉም:: ውሃው ተይዟል፤ ግድቡም ተጠናቋል:: ይህን ማሳካት የቻልነው በጠብመንጃ ኃይል ወይም ሌላ አትንኳቸው የሚል ወገን አግኝተን አይደለም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በግድቡ ጉዳይ አንድ ላይ በመቆሙ ነው:: አንድ ላይ የቆመ ሕዝብ ይፈራል፤ ይከበራል::
እኔ እስከማውቀው ድረስ በሙያዊ አስተያየት ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራትን ለመጉዳትና ጥቅማቸውን ለማጉደል ብላ የሠራችው ሥራ የለም:: ማንሳት ያለብን ጥያቄ እኛ ምን እያደረግን ነው የሚል መሆን አለበት:: እንደ እነሱ ተልካሻ ነገር እየፈጠርን ሌሎች ሀገራትን ማሳሳትና ጊዜ መግዛት አይደለም ያለብን:: እኛ ሀቅ አለን:: ተጨባጭ ነገር አለን:: ያን ጥሩ መሳሪያ በጨዋነት በሚያስፈልገው መንገድ ሁሉ መጠቀም አለብን:: ልክ እንደማያገባን ሆነን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም:: ጊዜያችንንም ጉልበታችንንም የማሰብ አቅማችንንም የእነሱ አሉታዊ እንቅስቃሴ ሊሰርቀው አይገባም:: መደረግ ያለበት ላይ አቅማችንን አሰባስበን እንዝመት ነው የምለው::
አዲስ ዘመን፡- የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ወንዙን በፍትሃዊነት ለመጠቀም አሻፈረኝ የሚሉት ሀገራት ላይ ጫና ያሳድራል ?
ፕ/ር አድማሱ፡- በባሕላችን የወንዜ ልጅ የሚባል ትልቅ አባባል አለ:: ወገኔ፣ አጋዤ ፣ ወዳጄ የሚል ትርጓሜ አለው:: ሀረጉን ብዙ ጊዜ እጠቀምበታለሁ:: እንዲያውም ለዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ በጣም ጠቃሚ የሆነ አባባል ነው:: ወደድንም ጠላንም የአንድ ተፋሰስ ሀገሮች ተፋሰሱን በፈጠረው ወንዝ መጠቀም ተፈጥሯዊ መብታቸው ነው:: በሌላ አባባል ዓባይ ወይም ባጠቃላይ የናይል ወንዝ የሚባለው የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ሀብት ነው:: ይህን ሀብት በመነታረክ እና በመቋሰል አይደለም መጠቀም የሚቻለው:: ተቀራርቦ የጋራ የሆነውን ነገር እንዴት እንጠቀምበት የሚል አስተሳሰብ ላይ መሰረት በማድረግ በተናጠል ከመሯሯጥ እና የአንዱ መጠቀም የሌላው ጥፋት ነው ከሚል አስተሳሰብ ወጥተን በጋራ ብንሠራ ሁላችንም የተሻለ ጥቅም እናገኛለን:: ተፋሰሱ ውስጥ ያሉት ሀገራት በሙሉ የተፈጥሮ ሀብቱ ባለቤቶች ስለሆኑ ማንንም አያገባህም ማለት አይቻልም:: የብቻዬ የሚል ካለም ነውረኛ ነው፤ አይቻልምም::
ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለይም የተፋሰሱ ሀገሮች ከኢትዮጵያ የሚማሩት መደረግ ያለበት ነገር ላይ ሀቅን ይዞ መሥራት የሚቻለውን ሁሉ ጨክነው ከሕዝባቸው ጋር ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ነው:: ኢትዮጵያ ይህን ትምህርት ለተቀሩት በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ሀገራት አስተላልፋለች:: በታሪክም የሚሰፍር ጉዳይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ያለፉበት የተራዘመ የድርድር ሂደት ላይ ያልዎት ግምገማ ምንድን ነው ?
ፕ/ር አድማሱ፡- ድርድሩን በአግባቡ ለመቋጨት ብዙ ትግል ተደርጓል:: በርካታ ስብሰባዎች ተካሂደዋል:: ብዙዎቹን በቅርብ ተከታትያቸዋለሁ:: ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በብዙ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ነበር:: በበርካታ ቴክኒካል ጉዳዮች ላይም እንደሚግባቡ አምናለሁ:: ቴክኒካዊ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩ የሶስቱ ሀገራት መሃንዲሶች አንድ ላይ ቢቀመጡ ለኢትዮጵያም ለሱዳንም ለግብጽም ያላደላ ይልቁንም ሶሥቱም ሀገራት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ነገር ለማወቅ የሚያዳግታቸው አይደሉም:: ነገር ግን ቴክኒካል ጉዳዮቹ ወለል ብለው ቢታዩም ፖለቲካዊ ወይም ሌላ ፍላጎቶች ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ያደርጉታል:: ግብጽም ሆነች ሱዳን የግድቡን ደህነነት ተመልክተው ይሄ ስህተት ነው ይስተካከል በሚል ያቀረቡት ነገር የለም::
ከመነሻው ጀምሮ በሦስቱ ሀገራት መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች አሉ:: እነዚያ ሁሉ ጤነኛና ተገቢ ናቸው:: በሙያ ዐይን ካየነው ግድቡን በተመለከተ የሶሥቱም ሀገራት ሰዎች የተለየ እይታ ሊኖረን አይችልም:: አለመስማማቱ በሙያ እይታ የነበረ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም እኔም ተሳትፌበታለሁ:: የኢትዮጵያ የቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ አባል ነበርኩ:: የቴክኒክ ኮሚቴ ማለት ምህንድስናዊ እይታ ያለው ነው:: ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ይሰበስበው በነበረው የኢትዮጵያ ቴክኒካል ኮሚቴ ሙያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ የሚመክር ነበር:: የመከረባቸውን ጉዳዮችም ስለሺ (ዶ/ር) በኩል ለመንግሥት ያቀርብ ነበር:: በሕግም በዲፕሎማሲውም እንደዚሁ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ነበሩ::
ፕሬዚደንት ትራምፕ የመሩት ሂደት አጼ በጉልበቱ አይነት እንጂ አግባብነት ያለው የማደራደር ስልት ተጠቅሞ የተደረገና ቴክኒካዊ የነበረ አልነበረም:: ኢትዮጵያ በሂደቱ የተሳተፈችው ፕሬዚዳንቱ ፕሮጀክቱን በበጎ ማገዝ ባይችሉ በመጥፎ መልኩ እንዳይጎዱት በሚል ነው:: የተደረገው ውሃን በትብብር በማልማት ሂደት ውስጥ አጋዥነት የሌለው ተግባር ነው::
አዲስ ዘመን፡- ግብጾች የአረቡን ዓለም ሚዲያ ተቆጣጥረውት ስለሚገኙ የኢትዮጵያን ስም በፈለጉበት መንገድ ሲያነሱ ኖረዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ሚዲያዎች ብቅ እያሉ የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዱ ሀገር ወዳዶችን ተመልክተናል:: በቀጣይ በዚህ ረገድ ምን መሠራት አለበት ይላሉ ?
ፕ/ር አድማሱ፡– ከቋንቋ አጠቃቀም ልጀምር:: ቋንቋ መሳሪያ ነው ለሕይወታችን:: የጎረቤትህን ቋንቋ እንደማወቅ የበለጠ ጥቅም የሚያስገኝ ነገር የለም:: ምክንያቱም በመነጋገር መልዕክትን በተለያየ መልኩ በማስተላለፍ መጥፎ ሊሆን የሚችለውን ነገር ማርገብና ወደ ወዳጅነት ማዞር ይቻላል:: አረብኛን ዋና ቋንቋ አድርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ መጠቀም በጣም ወሳኝ ነው:: የቅርቦቹም ሆኑ የሩቆቹ ጎረቤቶቻችን በሙሉ አረቦችም ባይሆኑ አረብኛ የሚሰሙ ናቸው:: ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት ወዳጅነት በማጠንከር እንዲሁም አለመግባባቶች ሲፈጠሩም በመቀልበስ የምንፈልገውን አብሮነት ማስፈን እንችላለን::
ከሁሉም በላይ ግን በሀሰተኛ መረጃ እንዳይጋርዳቸው ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ መቻል አለበት:: ይሄን በመንግሥት ደረጃ የሚሠራው እንዳለ ሆኖ በግለሰብ ደረጃ እንደ አንድ የሕዝብ ዲፕሎማሲ አባል ሁሉም ሰው መመኮር ያለበት ነገር ነው:: ከመሞከሪያ መንገዶቹ አንዱ አረብኛ ነው:: ሌሎችም ይጠቅማሉ:: እንግሊዝኛ በብዙ ሀገር የሚናገረውና የሚያዳምጠው አለ:: ፈረንሳይኛ፣ ቻይንኛ፣ ራሺያኛ ወይም ሕንድኛ ሊሆን ይችላል ሁሉንም ቋንቋዎች በመጠቀም ኢትዮጵያን እውነታ ለመላው ዓለም ማድረስ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አማካሪ ኮሚቴ አባላት አንዱ እንደመሆንዎ እያለፍንበት ስላለነው የምክክር ሂደት ምን ይላሉ ?
ፕ/ር አድማሱ፡-በየጊዜው ምክክሮች ይደረጋሉ:: በየዘመኑ መመካከርና መወያይት ስላለብን ይህ አይነቱ ውይይት በየጊዜው የሚቀጥል ነው:: የሚቀጥሉትም ትውልዶች እንደዚሁ በየወቅቱ እየተነጋገሩ ችግራቸውን እንዲፈቱ ለማድረግ የፖለቲካ ሥልጣንንም ሆነ ሌሎች ጉዳዮቻችንን በኃይል ላይ እንዳይመሰረቱ ማድረግ የምንችለው እየተከተለን የመጣውን ሰንሰለት መበጠስ ስንችል ነው:: በተለየ ሁኔታ ግን በዚህ ትውልድ ላይ ከሌላ ወገን ያልሆነ ከራሱ የመነጨ ኃላፊነት ተጥሎበታል::
ፖለቲካው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ከሆኑት ከሌሎች ጉዳዮቻችን የተለየ አይደለም:: ፖለቲካንም ቢሆን ጉልበትን ከመሃሉ አውጥተን ተነጋግረን ተወያይተን እንዴት እንሂድበት የሚለው ሂደት ላይ መስማማት አለብን:: አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ወገን ሀገራዊ ምክክርን ዋነኛ መንገድ ነው ብሎ አምኖበት አዋጅ አው|ጥቶ ማንኛውም ወገን እንዲሳተፍ ማድረጉ በእኔ በኩል የማደንቀው ነገር ነው:: ነገር ግን ይሄን ኃላፊነት መወጣት በአንድ ሰው ወይም ኮሚሽኑ ላይ ብቻ የተጣለ አይደለም:: ኮሚሽኑ አጀንዳው ዳር እንዲደርስ የሚያስተባብር አካል ነው:: እስካሁን በምክክር ሂደቱ የመሳተፍ ዕድል የገጠማቸው ኢትዮጵያውያንም ጠንክረው ተሳትፈው አጀንዳ ማሰባሰብ ደረጃ ተደርሷል፤ ይህ በጣም የሚደነቅ ነው:: ጊዜው የረዘመ ቢመስልም ሂደቱን ወጥነን ልናቆመው አይገባም፤ ዳር ማድረስ አለብን:: በመንግሥት፣ በሕዝብ እና ለኢትዮጵያ በሚቆረቆሩ ወገኖች ሁሉ የተደገፈ ሂደት ነው::
መላው ሕዝባችን በአንድ አዳራሽ ተገናኝቶ ሊነጋገር የሚችልበት ዕድል የለም::ነገር ግን ደረጃ በደረጃ ከወረዳ ተጀምሮ እያደገ እየተሰባሰበ እየተጠቃለለ ከየአቅጣጫው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉበት እየተደረገ ነው:: የሚወከሉ ወገኖች የራሳቸውን ሳይሆን የሚወክሉትን ማኀበረሰብ እያሰቡ መወያየትና መነጋገር አለባቸው:: እያንዳንዱ ወገን የራሱን ሃሳብ አቅርቦ የሚኮሰኩሰውም ቢሆን የሌሎችን ሀሳብ አድምጦ ሁሉን ነገር የሀገር ጉዳይ አድርጎ በማየት ለሀገር የሚበጅ ነገር ማምጣት ሀገራችን የተረጋጋችና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ መወጣት አለበት::
በኢትዮጵ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር እና ለመመካከር ዕድል ሲገኝ ከወዲሁ ስለሚመጣው ውጤት መደምደሚያ ላይ ደርሶ ዳኝነት ማሳረፍ አይቻልም:: እኛ ባሳለፍናቸው የፖለቲካ ሂደቶች ሲታይ መጪውን ነገር መጠራጠር መጥፎ ነው ብዬ አላምንም:: ነገር ግን ሀገራዊ ምክክር ከበፊት ጀምሮ ለብዙ ዓመታት ሲጮህለት የኖረ አጀንዳ ነው:: የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ወይም ሌሎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚሉ ሁሉ በአስተሳሰብ ደረጃ ምክክርን መሸሽ አይደለም የጎሪጥ የሚያዩት አይመስለኝም::
አሁን እየተነሳ ያለው ጥያቄ ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ ታሪካችን አንጻር በእጃችን ያለው መልካም አጀንዳ እንደ ድሮ በማይሆን መንገድ ላለመቋጨቱ ምን ዋስትና አለ የሚል ነው:: ለዚህ ዋስትና መስጠት ቢያስቸግርም እስካሁን በመጣነው ሂደት ግን አካሄዱ በጣም ግልጽ ነው:: በሂደቱ ለመሳተፍም ሲጀምር ከነበረው በተለየ ሁኔታ መመዘን የሚያስችል ሂደት አለ:: ጥርጣሬው ለምን ኖረ አይባልም ነገር ግን ሂደቱን በመገምገም እምነት እያሳደርን መሄድ ይኖርብናል:: ምክክሩ እስካሁን ባለፈባቸው ሂደቶች ከትናንት ዛሬ ከግጭትና ጦርነት ይልቅ ምክክር እንደሚሻል ይበልጥ እያሳመነ መጥቷል ብዬ አምናለሁ::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ ?
ፕ/ር አድማሱ፡- የማስተላልፈው መልዕክት ከልቤ የማምነውና አጠንክሬ የምናገረው ነው:: እኛ እንደ ኢትዮጵያውያን ንፋስ የማናስገባ አንድ ላይ የምንቆም መሆን አለብን:: ብንጨቃጨቅም፤ ብንነታረክም፤ ቅሬታ ቢኖረንም በራችንን ዘግተን ማንም ጤነኛ ቤተሰብ እንደሚያደርገው ነው ማድረግ ያለብን:: ራሳችንን አንክሰስ:: እንዲህ አይነቱ መካሰስ የፈለገ ጥረት ብናደርግ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያሻሽለው አይችልም፤ እንዲያውም ያበላሸዋል:: በር እየከፈትን ለሚጎዳን ወገን አንጋለጥ ነው የምለው::
አዲስ ዘመን፡- ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን ዝርዝር ምላሽ ስለሰጡን በዝግጅት ክፍላችን ስም አመሰግናለሁ!
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– እኔም አመሰግናለሁ!
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም