ኢትዮጵያ በዓለምና በአህጉር አቀፍ የአትሌቲክስ መድረክ በታሪክና በውጤት ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ አገሮች መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። በየዘመኑ የሚፈጠሩ አትሌቶቿም በታሪክ ከከፍታው ላይ እንድትቀመጥ ያደረጓት ባለውለታዎቿ ናቸው። ጀግኖቿ በየዘመኑ የሚያስመዘግቡት ውጤት ኢትዮጵያ እና አትሌቲክስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ተደርገው እንዲቆጠሩ አስችሏል።ይህ ስምና ዝና ምሉዕ ያልሆነ፤ የተገኙት ድሎችና የወለዱት ክብርና ዝና ግን ርቀት የገደባቸው ናቸው የሚሉ በርካቶች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ከረዥም ርቀትና ከማራቶን ውጪ በአጭርና በመካከለኛ ርቀት ውጤታማ አለመሆናቸውን በአመክንዮዋቸው ውስጥ ይገልጻሉ፡፡ በኦሎምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና እና በመሳሰሉት ውድድሮች የተገኙት ድሎች በሙሉ በረዥም ርቀት ነው። አጭር ርቀትን፤ ብሎም የሜዳ ተግባራትን ያማከለ አይደለም። ከአትሌቲክሱ ጋር ያለውን ታሪካዊና ጥብቅ ቁርኝት በርቀት የተገደቡ ለማለት ያስደፈረውም ይህ ምክንያት ነበር።
በረጅም ርቀት የተገኘውን ድልና ውጤታማነት በተመሳሳይ በአጭር ርቀትና በሜዳ ተግባራት መድገም የሚቻል ቢሆንም፤ ባለመሠራቱ ግን ግንጥል ጌጥ የሆነ ታሪክ ተሸክመን ለመጓዝ ተገደናል ሲሉ ይሞግታሉ። የአጭር፣ የመካከለኛ፤ የእርምጃና የሜዳ ተግባራት መሥራት ቢቻል የሚመጣውን ውጤት ጎረቤት አገር ኬንያን እንደማነጻጸሪያነት በማንሳት ሀሳቡን ማጠናከር ይቻላል። ሞጋቾቹም የኢትዮጵያን የምንጊዜም የረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር ብርቱ ተፎካካሪ የሆነችውን ኬንያን እንደማሳያ ያነሳሉ።
ኬንያ በኦሎምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና … ወዘተ. የመሳሰሉ ትልልቅ የውድድር መድረኮች ላይ በረጅም ርቀት ውጤታማ ናት። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ፤ በአጭር ርቀት ላይም ጥሩ ጅምር በማሳየት ላይ ትገኛለች። የኬንያ ጅምር በተለይ ባለፉት የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና የአጭርና የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ ብቃቷን አሳይታለች። ይህ ጥረቷ በአጭርና በመካከለኛ ርቀቶች ብቻ ሳይገደብ በሜዳ ተግባሩም ሜዳሊያ ማግኘት ጀመራለች። ታዲያ እዚህ ላይ ኢትዮጵያና አትሌቲክስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች የሚለው አባባል ለኬንያም ይሠራል። ግንጥል ጌጥነቱ ግን ለኬንያ የሚሠራ አይሆንም።
የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በረጅም ርቀት በሚመዘገበውን ውጤት መወሰን ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ ተንቀሳቅሷል። ይህም የተስፋ ብልጭታዎች ማሳየት ያስቻለም ጭምር ነው። ይህ የሆነውም ርቀት ሳይከልለው መጓዝ በመቻሉ ነው። በኬንያ ውጤት እያሳየ ያለውን የአጭር፣ የመካከለኛ እንዲሁም በሌሎች የሜዳ ተግባራት በኢትዮጵያም ማምጣት እንደሚቻል በርካታ ባለሙያዎች ያምናሉ። ሰሞኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲዮም በክለቦች መካከል ሲያከናውን በሰነበተው የአጭር፣ መካከለኛ፣ ዕርምጃና የሜዳ ተግባራት ውድድር ተሳታፊ ከነበሩት በዲስከስ ውርወራ ሲዳማ ቡናን በመወከል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ለማ ከተማ ይህንን ሀሳብ ይጋራል።
አትሌት ለማ ኢትዮጵያ በየውድድር አይነቶቹ ላይ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመፎካከር የሚያስችል አቅም እንዳላት ይስማማል። ይሁን እንጂ፤ «በአገሪቱ ያለውን እምቅ አቅም መሰረት ያደረገ የሥልጠናም ሆነ ሌሎች መሰረታዊ ተግባራት አልተከናወኑም። በመሆኑም መገኘት ያለበት ውጤት መምጣት አልቻለም» ሲል መሥራት ቢቻል ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ሀሳቡን ያስቀምጣል። አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በአጭር፣ በመካከለኛና ተመሳሳይ በሆኑ የውድድር አይነቶች ላይ የሰጠውን ትኩረት ካጠናከረ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያምናል።
እንደ አትሌት ለማ ሁሉ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት በረጅም ርቀት ብቻ ሳይገደብ ቢሠራ አመርቂ ምላሽ ማግኘት እንደሚቻል የበርካቶች እምነት ነው። ለዚህም እንደማሳያ እኤአ በ2017 በአልጄሪያ የተካሄደውን የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠቃሽ ነው። በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በ38 ሜዳሊያዎች ቀዳሚ ሆና ፈጽማለች። ሜዳሊያዎቹ የተገኙት ደግሞ በተለመዱት የመካከለኛና የረጅም ርቀት ሩጫዎች ብቻ አልነበረም። ይልቁንም በአጭር ርቀትና ከሩጫ ውጪ ባሉ የአትሌቲክስ ውድድሮች ጭምር ነበር።
ከነዚህም መካከል፤ በወንዶች 4በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ወርቅ፣ በወንዶች 5000 ሜትር ወርቅና ብር፣ በሴቶች 3000 ሜትር ወርቅና ብር፣ በሴቶች 10,000 ሜትር እርምጃ ወርቅና ብር እንዲሁም በሴቶች 4በ400 ሜትር ወርቅ አግኝታለች፡፡ በሴቶች ስሉስ ዝላይ የብር ሜዳሊያ ማግኘት ተችሏል። አዎን ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ ከተሠራ እንደ ረጅም ርቀቶቹ ሁሉ በመካከለኛ፣ በአጭርም ሆነ በሌሎች የውድድር አይነቶች ታሪክ መሥራት እንደሚቻል ያመላከተ ነበር። በዚህ ውስጥ መመልከት የሚቻለውም በርቀቶቹ መሥራት ከተቻለ በርቀት የተገደበውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የድል ታሪክ ጉዞ በነዚህ የውድድር ዓይነቶችም ማስቀጠል እንደሚቻል ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አስተያየታቸውን የሰጡት ስፖርተኞች በርካቶች ሲሆኑ፤ እነርሱም፤ በአሠለጣጠን፣ በልምምድና በቴክኒክ ሥራዎች ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል በተለየ መልኩ ትኩረት ቢሰጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያመላክታሉ።
በዓመታዊው ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ በሴቶች የርዝመት ዝላይ አሸናፊ የሆነችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አራያት ዲቦ አስተያየ ታቸውን ከሰጡት መካከል ትገኛለች። አትሌቷ እንደገለጸችው፤ ለስፖርቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ አለመሟላት እንደሳንካ የሚታይ መሆኑን ትገልጻለች። ለውድድርና ለልምምድ የሚያስፈልጉ የስፖርት ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ አይሟሉም፤ አልተሟሉምም። ኢትዮጵያ ለውድድር ዓይነቶቹ የሚሆን ተክለ ሰውነት፤ ጉልበትና ጥሩ አቅም ያላቸው አትሌቶች እንዳሉ ትናገራለች። ይህን አቅምና እምቅ ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ ሥልጠና ማገዝ ቢቻል ፍሬያማ መሆን ይቻላልም ትላለች። በአገራችን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። በተክለ ሰውነትና በጉልበት ጥሩ አቅም ያላቸው ስፖርተኞች ቢኖሩም፤ የቴክኒክ ችግር ይስተዋልባ ቸዋል። ምክንያቱም ሳይንሳዊ በሆነ ሥልጠና እየታገዙ አይደለም። ስለዚህ በስፖርተኞቹ ላይ የሚስተዋለውን የቴክኒክ ችግር በሳይንሳዊ ሥልጠና መቅረፍና አቅማቸውን መሙላት ያስፈልጋል ባይ ነች።
የአሠልጣኞችንና የተወዳዳሪዎችን አቅም የሚያጎለብቱ ተከታታይ ሥልጠናዎች አለመስጠት የውድድር ዓይነቶቹ እንዳያድጉ ማድረጉን ነው ያመለከቱት የምትለዋ አትሌት፤ ሌሎች ጎረቤት አገሮች በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በሜዳ ተግባራትና በእርምጃ ውድድር ችሎታ ያላቸውን አትሌቶች ብቃታቸውን ለማሳደግ ወደ ውጭ ሀገር ሁሉ ልከው ያሠለጥናሉ። በአገራችን ግን ይህ ነገር አይታይም። በመሆኑም አገራችንን በአጭርና በመካከለኛ ርቀቶች ውጤታማ ለማድረግ እነዚህን ክፍተቶች በሚገባ መሙላት ያስፈልጋል ስትል ሀሳቧን ቋጭታለች።
የመከላከያ ስፖርት ክለብ የዝላይ አሠልጣኝ ሻምበል ኡጉላ ኡባንግ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በውድድር አይነቶቹ ላይ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመፎካከር የሚያስችል አቅም የሌለን ለውድድሮች ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው ሲሉ እንደምክንያት ያነሳሉ። ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ፣ አትሌቱ፣ አሰልጣኙም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አጠንክረው የሚሠሩት በረጅም ርቀት ላይ ነው። የውድድር መርሀ ግብሮችም ይህንኑ መንገድ ይዘው የሚፈሱ ናቸው። እንዲህ አይነቱ አሰራር ደግሞ፤ በቂ ውድድሮች በሌሉበት ሁኔታ አትሌቶች ራሳቸውን የሚፈትሹበትና የሚያዘጋጁበት እድል የሚያሳጣቸው ነው። በዓመት ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ከሚገባው በታች አነስተኛ መሆናቸውን እንደ ሌላ ችግር ያነሱት አሠልጣኙ፤ በነዚህ ዘርፎች ላይ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራ ኢትዮጵያ ውጤታማ የማትሆንበት ምክንያት አይኖርም ባይ ናቸው። ሰሞኑን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከናወን የሰነበተው ውድድርም ያሉበትን ችግሮች በሚገባ በማጤንና በማሳደግ፤ በተጨማሪም ሌሎች የውድድር መድረኮችን በመፍጠር በአጭር ርቀት እንደ ረጅም ርቀት ስኬታማ መሆን ያስችላል ሲሉ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ ሻምፒዮናው ለአጭር፣ ለመካከለኛ፣ ለሜዳ ተግባራትና ለእርምጃ ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ሻምፒዮናው በውድድር ዓይነቶቹ ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን የሚፈትሹበት የአቋም መለኪያ ውድድር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ጭምር ነው። በውድድር አይነቶቹ ኢትዮጵያ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች። የሚመዘገበው ውጤት ግን ከሌሎች አገሮች አኳያ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የቤት ሥራን ሰጥቶ አልፏል። ከአንድ ዓመት በፊት ናይጄሪያ አሳባ ከተማ የተካሄደውን 21ኛው የአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስታወሱት አቶ ቢልልኝ ፤ ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች ከ100 ሜትር ጀምሮ ተሳትፊ ነበረች። በሻምፒዮናው የተገኘው ውጤት መሰረታዊ ችግሮች እንዲለዩ አጋጣሚ የፈጠረ ነበር ።
በውድድር አይነቶቹ ውጤታማ ለመሆን በአሠለጣጠን፣ በልምምድና ቴክኒክ ሥራዎች በመለወጥ ጊዜው በፈቀደውና ዓለም በደረሰበት ልክ መሥራት እንደሚያስፈልግ እርሳቸውም እንደሚያምኑ ይናገራሉ። በአሠለጣጠን በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በጋና፣ በኩባ፤ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገሮች ከሚገኙ አሠልጣኞች ጋር በመነጋገር ወደኢትዮጵያ መጥተው እንዲያሠለጥኑ ጥረት መደረጉን ያነሳሉ። ነገር ግን አሠልጣኞቹ ያላቸው አቅም ያን ያህል አመርቂ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ከውጭ የሚመጡት አሠልጣኞች ከኢትዮጵያውያኖቹ መሻል አለባቸው። ከዚህ አኳያ ያለውን ጥረት ከመቀጠል ወደኋላ እንዳልተባለ ያመለክታሉ።
በብሔራዊ ፌዴሬሽን በኩል በመቀጠል በአገራችን ውስጥ የተሻሉ አሠልጣኞች እስኪገኙ ድረስ የአገር ውስጥ አሠልጣኞች አቅማቸውን ማጎልበት የሚችሉበት ተከታታይ ሥልጠና ለመስጠት በእቅድ እንደተያዘ ይናገራሉ።«አሠልጣኞቹንም ወደ ውጭ አገር በመላክ ልምድ እንዲቀስሙ የማድረግና ታዋቂ አሠልጣኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ይደረጋል። የውድድር አማራጮችን ማስፋት፣ የስፖርት ቁሳቁስን ማሟላትና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። በመጨረሻም፤ በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በእርምጃና በሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ውድድሮች እድገት ክለቦች፣ አሠልጣኞችና ተወዳዳሪዎች የየበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በአጠቃላይ በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በእርምጃና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ኢትዮጵያ በዓለምም ሆነ በአህጉር አቀፍ መድረክ ከተወሰኑ አጋጣሚዎች ውጪ ውጤታማ አይደለችም። በውድድሮቹ ወቅት በተወዳዳሪዎች ላይ በአሠለጣጠን፣ በልምምድና ቴክኒክ ሥራዎች ላይ ጉድለት እንዳለ የተመላከተና በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተስተውሏል። በአሁኑ ወቅት በእነዚህ የውድድር ዓይነቶች ብቁ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራትና ውጤታማ ለመሆን እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ አትሌቱና ሀብቱ መኖሩ እሙን ነው ። በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ፤ ይሄንን ወደ ውጤት ለመቀየር ደግሞ ባለድርሻ አካላት ከሚመለከታቸው ጋር ተግባብተው በቅንነት ከሠሩ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ ብዙም አያዳግትም እንላለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2011
ዳንኤል ዘነበ