እንደተለመደው በሥራ መውጫ ሰዓት ሰርቪስ ለመያዝ ተሰልፈናል። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ወደእኛ ሰፈር የሚሄደው መኪና ሁሌም በተሳፋሪዎች ይጨናነቃል። ብዙዎች የሾፌሩ ፍጥነትና የመንገድ ቆረጣ ስለሚመቻቸው ምርጫቸውን ለይተዋል። የባስ ካፒቴኑ ፈጣንና ቀልጣፋ ነው። መንገድ መርጦ መጓዝ ያውቅበታል።
ከረጅሙ ሰልፍ መሀል ወንበር ለማግኘት የታደልነው ጎን ለጎን ተቀምጠን ጨዋታ ይዘናል። ተራው ያልደረሳቸው ደግሞ ከውጭ ወደውስጥ እያንጋጠጡ ነው። እንደእውነቱ ከሆነ ራቅ ያለ መንገድ ቆሞ መሄድ ከባድ ነው። እንደታክሲ ሦስት ሆኖ መቀመጥ ደግሞ አይሞከርም። እናም ከደጅ ያሉት ተንጠራርተው ቢያንጋጥጡ አይፈረድም።
መቼም የመንገድ ላይ ወግ አይነቱ ብዙ ነው። አንዳንዴ ስለቤት ጣጣ ይወራል። አንዳንዴ ደግሞ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳይ ሰፊ ሽፋን ያገኛል። ብዙ ጊዜ ግን አስራሁለት ሰዓት ላይ የሚደመጠውን ዜና መነሻ አድርጎ የሚከተለው አስተያየት ይበረክታል። ጥግ ይዘው የሚያንጎላጁት መንገደኞችም ከዕንቅልፋቸው በባነኑ ጊዜ የሚጨዋወቱት አያጡም።
እሰይ! አሁን መንገዱን ገፋ አድርገነዋል። ፈጣኑ ካፒቴን እንደተለመደው በአጭር ጊዜ ረጅሙን ጎዳና አጋምሶታል። ሜክሲኮ አደባባይን ከመሻገራችን መጨናነቅ መጀመሩ ግን እንዳያስመሸን እየሰጋን ነው። ከኋላችን ደርሶ «እሪ» የሚለው አምቡላንስ ማለፊያ በማጣቱ ጨኸቱ ቀጥሏል። አንዳንድ መኪኖች ችግሩን ተረድተው ሊያሳልፉት እየሞከሩ ነው። ይህ መሆኑ ብቻ ግን እምብዛም መፍትሄ አልሆነም።
የአምቡላንሱን ጨኸት ተከትሎ አዲስ ጨዋታ ተነሳ። አንደኛው የሚናገረው ከሌሎች በተለየ ነው። እርሱ አካባቢውን ስላወከው ድምጽ እምብዛም የተጨነቀ አይመስልም። መኪናው የታመመ ሰው ይዟል የሚለው እውነታም አልተዋጠለትም። እንደውም በስፍራው እንደተገኘ ሆኖ አሳማኝ የሚመስሉ ማሳያዎችን መምዘዝ ይዟል። የእርሱን ሀሳብ ተከትሎም ብዙዎች የራሳቸውን ግምት ማከል ጀምረዋል። በየወንበሩ ጨዋታው ደርቷል። አስተያየትና የግምት ሀሳብም እንዲሁ፤
የእኔን ጆሮ የሳበው ግን ይህ አይነቱ ክርክር አልነበረም። ከጎኔ የተቀመጠችው ወይዘሮ በስልኳ በያዘችው ፎቶግራፍና ተያያዥ ታሪክ ልቤ ተማርኳል። ጉዳዩን በጥልቀት ስሰማው ደግሞ አእምሮዬ ርቆ ተጓዘ። በዚህ መሀል የብዘዎችን የተሳሳተ ግምት አሰብኩ። ራሴንም ገመገምኩ። እውነት ግን ስንቶቻችን በተሳሳተ እሳቤ እንመራለን? ስንቶቻችንስ ይህን በጎ ያልሆነ አመለካከት እንደያዝን እንገኛለን?
ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ ማለዳ ወደቤ ተክርስቲያን የሄዱት አባወራ ጸሎታቸውን አድርሰው ዞር ከማለታቸው ከአንድ ጎስቋላ አዛውንት ጋር ዓይን ለዓይን ይጋጫሉ። ሰውዬው ጥሩ ቁመና ቢኖራቸውም ኑሮ እንደጎዳቸው ያስታውቃል። ከላይ የደረቡት ልብስ አርጅቷል። ጫማቸው አልቋል። ችግር ያንገላታው መልካቸው ድካም ተጭኖታል።
ከእርሳቸው አለፍ ብሎ ከተቀመጡት ባልንጀራቸው ጋር በልመና የሚያገኙትን ቁራሽ ይካፈላሉ። ለነፍስ ብሎ ሳንቲም የሚጥል ሲገኝም የተሰጣቸውን ተቀብለው ለሌላ ምጽዋዕት እጃቸውን ይዘረጋሉ። ልመና ለአዛውንቶቹ መተዳደሪያ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከሁለቱ ግን የአንደኛው ታሪክ ይለያል። ባገራቸው ቤት ንብረት አላጡም። ጥማድ በሬና የሚታረስ መሬትም አላቸው። እንደዋዛ አዲስ አበባን የለመደው እግራቸው ግን በቀላሉ አልመለሳቸውም። የልጆቻቸው ከተማ መዝለቅ ምክንያት ሆኗቸው ዋል አደር ማለት ለመዱ። ልጆችና እርሳቸው በአንድ ቤት አይኖሩም። ገሚሶቹ በቀን ሥራ ራሳቸውን ይደጉማሉ። የተቀሩትም በተመሳሳይ ሙያ ተሰማርተው ገንዘብ ያገኛሉ።
አሁን አባትና ልጆች በአንድ ቤት ስለማይኖሩ አዋዋላቸውም ለየቅል ሆኗል። አባት በልመና ከሚያገኙት ገንዘብ የራሳቸውን ቤት ኪራይ ይከፍላሉ። ባገኟት ቁራሽ ሆዳቸውን ይችላሉ። በልመና ውሎ ህይወታቸውን ይመራሉ። ከማለዳ እስከምሽት በሚዘልቁበት አጸድ ብርድና ፀሐይ ብርቃቸው ሆኖ አያውቅም። ሁሉንም እንደአመጣጡ ተቀብለው የሰው ፊት ማየትን ከተለማመዱት ቆይተዋል።
በቅርበት ሆነው ሁኔታቸውን ሲያስተውሉ የቆዩት አባወራ በአዛውንቱ ጉስቁልና ልባቸው በኀዘን ተነክቷል። ይህ ስሜት ብቻ ግን የበቃቸው አይመስልም። እርሳቸውን እያሰቡ ከቤት የተቀመጡትን ልብሶች ያስታውሳሉ። ካስታወሷቸው መሀልም ለእርሳቸው የሚበጀውን ይለያሉ። ይህን ሀሳባቸውንም ለአዛውንቱ ሲነግሯቸው ምስኪኑ ሰውየ ከልብ ተደሰቱ። እንዲህ አይነት ቅን አሳቢ ስላገኙም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ።
አዛውንቱና አባወራው ወደቤት ከመሄዳቸው በፊት ጉዳዩን የሰሙት ባልንጀራቸው ጥያቄ አነሱ። እርሳቸውም እንደጓደኛቸው ቢለብሱ እንደሚወዱ ተናገሩ። አባወራው በጥያቄአቸው አልተከፉም። ሁለቱንም ሊያለብሷቸው ቃል ገብተው እንዲከተሏ ቸው አደረጉ።
እኔና ወይዘሮዋ ጨዋታችንን ቀጥለናል። በግሌ የሰዎቹ ታሪክና የአባወራው ቅንነት እያስገረመኝ ነው። እግረመንገዴን በርካቶችን አሰብኳቸው። ቤት ንበረታቸውን ትተው፤ የሞቀ ትዳራቸውን ፈትተው ለልመና የተዳረጉ ቁጥር አልባ ወገኖች ትውስ አሉኝ ። ቤት ይቁጠራቸው እንጂ ብዙዎቹ ተመሳሳይ ህይወት ይጋራሉ። እያላቸው የሌላቸው ሳያጡ ያጡ ጎስቋሎች ጥቂት አይደሉም።
ሦስቱ ሰዎች ጀሞ አንድ ከሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአንደኛው ተገኝተዋል። አባወራው ከፊት ቀድመው ሁለቱ እየተከተሉ ነው። በቁምሳጥኑ ከተሰደሩት ሙሉ ልብሶች መሀል ያሰቧቸውን አውርደው ለአዛውንቶቹ መስጠት የጀመሩት ሰው ምስጋና እየደረሳቸው ነው። እነርሱም የተራበን ያበላ፣ የታረዘን ያለበሰ በሚለው ቃል መሰረት ቅን ላደረጉት አባወራ ምርቃት እያወረዱ ነው።
አሁን ሁሉም ተጠናቅቆ ተሰነባብተዋል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ዳግም ለመገናኘት ቀነ ቀጠሮ ወስደዋል። ከቀናት በኋላ አባወራው በቤታቸው የሚያደርጉትን ጠበል ጠዲቅ ምክንያት አድርገው እንዲመጡ ጠርተዋቸዋል። ሁለቱም ተጋባዞች ዕለቱን አልዘነጉም። እንዲህ አይነቱ ጥሪ ለእነሱ ከስንት አንድ ነው። አክብረው የሚጠሯቸውና እንደሌሎች በእኩል የሚጋብዟችውም ጥቂቶች ናቸው።
ቀናት ተቆጥረዋል። በአባወራው መኖሪያ ለጠበል ጸዲቁ የሚሆነው ዝግጅት ተጀምሯል። የሚጠሩ ሰዎች ተለይተው የጎደለው ሁሉ ተሟልቷል። ሁሌም ዕለቱን አስበው የሚዘክሩት ባልና ሚስት በጥሪው የሚገኙ እንግዶች እንዳይረሱ ያስባሉ።
አሁን ቀኑ ደርሷል። እንደተለመደው መላው ቤተሰብ በመስተንግዶው ተዋክቧል። እንግዶች ይገባሉ፣ ይወጣሉ። አባወራውና ወይዘሮዋ ቆመው ያስተናግዳሉ፤ ሰዎችን ይቀበላሉ፣ ይሸኛሉ። ከተጠሩት መሀል ቀኑን ያልዘነጉት አዛውንት በሰዓቱ ተገኝተዋል። እርሳቸው ከሌሎች ቀደም ብለው ቢገኙም እንደአመጣጣቸው ፈጥነው መውጣት አልፈለጉም። ወጪ ገቢውን እያስተዋሉ በዝምታ ተቀምጠዋል።
ቀኑ ተጋምሶ ምሽቱ እንደተቃረበ የተጠሩት እንግዶች ቁጥርም ጋብ ማለት ጀመረ። ጥቂት ቆይቶም ቤቱ ጭር አለ። ይህኔ አዛውንቱ እንግዳ ከመቀመጫቸው ተነሱ። ተነስተውም መላው ቤተሰብ ወደ እርሳቸው እንዲመጣ ጠየቁ። ይህን የሰሙ ሁሉ ቃላቸውን አክብረው በአንድ ተሰባሰቡ። ቀኑ እየመሸ በመሆኑ አባወራውና ባለቤታቸው ማሰብ ጀምረዋል። የእርሳቸው ቤት ከአካባቢው የራቀ በመሆኑ እያስጨነቃቸው ነው ። እርሳቸው ግን ይህ ሁሉ ስሜት ምናቸውም አልነበረም።
ንግግራቸውን በተለየ ምስጋና የጀመሩት እንግዳ እንባ እየተናነቃቸው እጃቸውን ወደጉያቸው ሰደዱ። ወዲያው ዳጎስ ያለ እስር በጣቶቻቸው መሀል ታየ። አዛውንቱ ያወጡትን ከማስረከባቸው በፊት ስለሆነው ሁሉ ተናገሩ። የዛን ዕለት አባራው ስለእርሳቸው አዝነው ሙሉውን ልብስ በሰጧቸው ጊዜ ቤታቸው ገብተው ልብሱን ሲለኩት በኮቱ የውስጠኛው ኪስ የታሰረ የብር ኖት ያገኛሉ።
ብሩ ከለመዱት መጠን የበዛ በመሆኑ በድንጋጤ ክው ብለው ይቆያሉ። አዎን! አባወራው በተለገሳቸው ሙሉ ልብስ ውስጥ አስር ሺ ብር እንደታሰረ ተቀምጧል። ይህን ሲመለከቱ አዕምሯቸው ክፋት አላሰበም። ቅን አስቦ መልካም ላደረገ ማንነት ውለታው በበጎነት መመለስ እንደሚኖርበት ወስነው ብሩን እንደነበረ አስቀመጡት። ይህን እውነት ያጫወተችኝ ወይዘሮ ይህ ታሪክ በባለቤቷና በመኖሪያ ቤቷ ስለመፈጸሙ ሳውቅ ግርምታዬ ላቀ ።
ሰውዬው ያስረከቡትን የአስር ሺ ብር ጥቅል ባለቤቷ ቆጥረው ሲረከቡም በፎቶግራፍ የቀረውን ምስል ተመልክቼ አረጋገጥኩ። ወዳጆቼ! እውነት እንነጋገር ከተባለ ምን ያህሎቻችን እንሆን ይህን መሰሉን ታሪክ የምንጋራው? ማንኛችንስ ነን ሰውን በልቡ ሳይሆን በልብሱ ብቻ የማንመዝነው? እኚህ ገንዘብና እንጀራ ናፋቂ አዛውንት ግን ይህን እውነት ፈጽመዋል። ሰዎችን በልብስ ብቻ ሳይሆን በንጹህ ልቦና ብቻ እንድንመዝንም አስተምረውናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2011
መልካምስራ አፈወርቅ