ሰው የተሰጠውን መልካም እድል በራሱ ያመክናል? የኛ ነገር እንደዚያ እየመሰለኝ ተቸገርኩ፡፡ ትላንት ብዙ ሆነን ዛሬ የተገኘው ለውጥ ላይ ደረስን፡፡ ምን ዋጋ አለው ለውጥ ፈላጊ እንጂ መለወጥ አንፈልግምና መደናቀፋችን በዛ፤ ባለፈ ተረት መወቃቀስ ፈቅደን ባልፈጠርነው መቧደን ተግባራችን ሆነ፡፡ በቃ እጣ ፋንታህ ሆነና አሁን የተገኘህበት ያለህበት ቦታ ያንተ መገኛና መታያ ሆነ፡፡ ማንም ማመልከቻ አስገብቶ ከዚህኛው ብሔርና ማህበረሰብ እዚህ ቦታ ላይ መወለድ እፈልጋለሁ ብሎ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል አመልክቶ አልተፈጠረም፡፡ አዎን! አሁን ላይ የተገኘነው እሱ ሀያሉ አምላክ በወደደውና በፈቀደው ቦታ ነው፡፡ የእኛ አስተዋጽዖ ምንም የለም፡፡ አንተን ከተገኘህበት ማህበረሰብ ውስጥ ሊያስገኝህ ፈልጎ ነበር፤ አደረገው፡፡ ውደደው ወይም ጥላው በቃ አንተ ማለት አንተ ነህ፡፡ የአንተን ከፍታ ልክ የምታሰምረው አንተው ራሳህ ነህ፡፡ ላንተ አድልቶ የሰጠህ ወይም ያሳነሰብህ ነገርም የለም፡፡ ምክንያት ስላለው በዚህ መልክ አስገኘህ፡፡ ሰው ሆነህ እራቁትህ ምድርን ሳትፈልግ ተቀላቀልክ፡፡ ንጹህ የሆነ ልብና አይን ተላብሰህ ተገኘህ፡፡
እናም መልካም ያልሆኑ ሰዎች ቀረቡህና ንጽህናህን አነተቡት፡፡ ባልተገባ መልኩ እንድትሻክር አድርገው ሞረዱህ፡፡ “እኛ ምርጥ ዘር ነን እነእንትና ደግሞ ምራጭ” አሉህ ፡፡ እኛ ተመርጠን የተገኘን ነን ብለው ያልተመረጡ ናቸው ያሉትን ሌሎችን እያሳዩህ፤ ቤተሰብህን ወደህ የከበቡህን ጎረቤቶች የጎሪጥ ማየት ጀመርክ፡፡ ምልከታህን አስፍተህ የሌላን በጎነት ከማየት ይልቅ ያጠለቁልህ የጥላቻ መነጽር በጎነትን በክፋት የሚቀይር ነውና የሌሎች መልካም ስራ እንደ ሴራ ታየህ፡፡ ሲፈጠር ብሩህ ነገር እንዲያሳይህ የተፈጠረልህን አይንህን ጋርደውት አጠበቡብህ፡፡ ፍቅር ሞልቶ የተፈጠረውን ልብህን ጥላቻና ምቀኝነት ሰፍረውበት በጎነትን፤ አብሮነትንና ህብረትን አልቀበል አለህ፡፡
የህዝቡን ስሜትና አንዳንዴ መንጋነት እየተከተላችሁ በየለቱ አቋማችሁን የምትቀያይሩ ፖለቲከኞቻችን ፖለቲካችሁ እንጨት እንጨት ብሎናል። ምናችሁም አይጥምም እስቲ ንትርካችሁን ቆም ጋብ አድርጉትና ስለ ሰላም ብቻ ስበኩ፤ ስለፍቅርና ስለአንድነት አውሩ። ተሸናንፋችሁ ስልጣን ላይ ብትወጡም (እዚህ ሀገር ላይ እስካሁን ማሸነፍ ስለሌለ ነው) እንኳን ህዝብ ከሌለ ማንን ልትመሩ ነው? በፍቅር ካልሆነ በምን ልታስተዳድሩን ነው? አዎ የሰለቸንን የፖለቲካ ንትርካችሁን አቁሙና ሰው ላይ ስሩ። መልካም አመለካከት ያለው ሰው በመፍጠር ላይ አተኩሩ፡፡
“ኢትዮጵያዊያን ጨዋዎች ነን፣ ሀገራችን ቅድስት ናት፣ ህዝባችን ብሩክ ነው፣ወዘተ” እየተባልን እንሰበካለን፤ ተደጋግሞም ይነገረናል። ግን ደግሞ የማይካድ ሀቅ የኛ የምንላቸውን አውሬዎችም ታቅፈናል። አዎ ስለዚህም በሚያስተምር መልኩ ይወራ፡፡ እያየነው ያለውን ጉድ የሚያሳዩን የኛው ጉዶች አይደሉ እንዴ? ከየትም አልመጡም ከኛው የበቀሉ አረሞች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የተባረከች ምድር ስለሆነች ከርስዋ የተፈጠሩ አይደሉም ብሎ የሚክድ የለም። እነዚህን ሰው በላ አውሬዎች ለማስቆም ሁሉም የቤት ስራ ይጠበቅበታል። መሰል መሰሪዎች እንዳይፈጠሩ ቤተሰብ ስለልጆቹ መልካም ሆኖ ማደግ መጨነቅ ይኖርበታል። አካባቢ ስለራሱ ስለትውልዱ ሊመክር ይገባል። የሃይማኖት አባቶች ክፋቱን ለማራቅ ፈጣሪን መማፀን ይገባቸዋል። ለወንጀለኞች መበራከትና እንዳሻቸው መፈንጨት መደላደልን የፈጠረው መንግሥት ስራውን ለመስራት በመርፌ ተወግቶ እስኪቀሰቀስ ድረስ ማንቀላፋቱን ማቆም ይገባዋል።
ሚዲያው የወቅቶችንና ሁነቶችን ዋይታ ብቻ ሳይሆን እውነት እንዲወጣ፤ ፍትህ እንዲሰፍን፤ ፍቅር እንዲነግስ መስበክ ይገባዋል። ባለሙያዎች ትውልድ እንዲገራ፤ ሀገር እንዲደረጅ መጣር ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም የሚኖረው፤ መገኘትም የሚችለው በጎ የሆነውን የቤት ስራ ሲሰራ ነውና! ዛሬ ላይ እርስ በርስ መጠላለፉን አቁመን፤ መወነጃጀሉን ጋብ አድርገን ጥሩም መጥፎም የምናስተናግድባትን ሀገራችንን እናድን፤ ሀገር ከሌለ ድነትም ሽረትም፤ ከፍታም ዝቅታም የለም። ከጥፋትና ከሲቃ ውጪ፤ ከእሳትና ሞት ውጪ ሀገርና ሰላም ከሌለ መልካም ነገር የለም። እናም ሀገሬ ክብሬ የምንላት ሀገር እንገንባ፤ አፍራሹን እናንፅ፤
ትውልድ እንደህንፃ አይደለም፡፡ ህንፃ ሲሰራ ከተጣመመ ብሎኬት ነውና ፈርሶ መልሶ ይታነፃል፡፡ የሰው ልጅ ባህሪው ካልተገራ እንደ ብሎኬቱ አይፈርስ ነገር ሰው ነው። ይህን የተጣመመውን ትውልድ ማቅኛው አንድ ነገር ብቻ ነው። ፍቅር፤ በፍቅር የማይናድ ጥላቻ፤ የማይረጥብ ድንጋይ ልብ የለም። ሳናቋርጥ ፍቅርን እንስበክ፤ እንተግብር፡፡ በፍቅር ጥላ ስር ተቻችሎ በማደር፤ ተባብሮ በማደግ ደስታና ሀሴት ለሁሉም ይዳረሳል። በመሀላችን እየገባ የሚያናጨን ክፉ ሀሳብ ማርከሻው ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው።
እዚህ ላይ ግን መልካምነትን አንድነትን በመናፈቅ ፍቅርን የሚሰብኩትን፤ ለሰው ልጆች ሰላም ውሎ ማደርና አብሮ መኖር የሚታትሩትን ልሂቃን ልፋት ገደል መክተቴ አይደለም፡፡ ሁሌም መልካም መንገድ ለማመላከትና ይህችን ሀገር ለማቅናት የሚለፉ ብዙ አሉ፡፡ ለነርሱ ለነዚህ የሰላም አምባሳደሮች የፍቅር ጀግኖች ክብር ይገባቸዋል፡፡
በአንጻሩ፤ በጥላቻ ተሞልተው ህዝብን ከህዝብ የሚያናክሱ የክፋት መልዕክተኞችን እውቅና ባንሰጣቸው፤ እነዚህ ጎጠኛ ምሁር ተብዬዎች ለህዝብ ክብር እንደሌላቸው በደንብ ማሳያ ሰዓታቸው ነውና ምንም ቢሉ ምንም አለማለት የሚሻል ይመስለኛል። እናንተ በዘረኝነት ናላችሁ የዞረ ቆሻሻ ነገር ሙጭጭ ያላችሁ ትንንሾች ሆይ! ተግባርና ሀሳባችሁ የመዝቀጣችሁ ማመላከቻ ነው። እንዴት እምነት አለን ብላችሁ በፍቅር ጥላቻ ለመቀየር ትደክማላችሁ፣ በዘረኝነት ሰውን ከሰው ለማናከስ ታሴራላችሁ?
በቃ እኛም ከእነርሱ መልካም ነገር መጠበቅ እናቁም! ተግተን ቤታችንን ካፀዳን ዝንቦች መች ይኖሩበትና፤ ንቀን እንተዋቸው! ደግሞ ባገኘነው አጋጣሚ ተግባራቸው መልካም አለመሆኑን እንንገራቸው፤ እንገስፃቸው፤ እናውግዛቸው፡፡ ግን አደራ ህዝብና ግለሰቦችን እየለየን! ህዝብን መተቸት ፈፅሞ ከኛ አይጠበቅም። መስፋት፤ ህዝብን ማክበር፤ ሁሉም ወገን መሆኑን ተገንዝቦ ሳይሰስቱ ፍቅርን መግለፅ የዘወትር ምግባራችን ይሁን! እነዚያን ማፈሪያዎች ግን እውቅና ባንሰጣቸው መልካም ነው። ከሰሜን እስከደቡብ፤ ከምስራቅ እስከምዕራብ ያለው የሀገሬ ምድር፤ የኢትዮጵያ አየር ሰላም ውሎ ይደር!
መቼም የተንሸዋረረ እይታ ያለው ካልሆነ በስተቀር ሀገር ምድሩ ስለ ፍቅር ሲዘምር ስለ አንድነት ሲሰብክ ማን ይከፋዋል። ለመደመር መመርመር ይቅደም፤ ሁሉም ከዘረኝነት፣ ከጥላቻና ከምቀኝነት ደዌ መፅዳቱን ያረጋግጥ፤ እነዚህ ሃጢያቶች በውስጡ ያሉበት መጥቶ ድምቀታችንን ከሚያደበዝዝ እዚያው ይቆይ፤ ባይሆን ይታከም፤ ይህ እውነት ከገባን ከፍቅር በላይ መድሃኒት፤ ከአንድነት በላይ ፈውስ የለም። ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የላቀ ክብር ይገባል። በሰውነት መበላለጥና ማነስ የለም፡፡ ሁሉም በሰውነቱ እኩል ነው። በጎ የሰራ፤ ፍቅርን የሰበከ፤ መዋደድን ያፀና ለሰው ልጆች በጎ የዋለ ሰው ያልበደለ ርቱኡ ግን በምግባሩ ከሌላው ላቅ ይላል።
ወዳጆቼ ስለፍቅር ብሎ ሁሉን ከመተው በላይ አሸናፊነት የት አለ? ይቅር ተባብሎ ከመደመር በላይ ከፍታ የት ላይ ነው? በፍቅር መፈወስ ያቃተው፤ የውስጡን ጭለማ ወደ ብርሃን መለወጥ የተሳነው በተለይ ብዙ ነው። ቢሞክሩት በፍቅር ማደር ምንኛ ልዩ ጣዕም እንዳለው ባወቀው፤
አዎን! አንድ ነን እና አንድ አይነት ነን ይለያያል። በልዩነታችን ተከባብረን ግን ደግሞ አንድ ሆነን ለማደር ይህቺ ውብ ሀገር አትጠበንም። እናም ሀገሬን የምትል ሆይ ስማኝ! ሰውን ያለ ገደብ አፍቅር፤ ጥላቻን በፍቅር አሸንፍ፤ ፍቅር ጥላቻን ማጥፋት ይችላልና!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111
ተገኝ ብሩ